text
stringlengths
4
267
ይሁንና የዚህ ሥርዓት ጭንቀትና ሀብት ያለው የማታለል ኃይል እንዲሁም የሌሎች ነገሮች ሁሉ ምኞት ወደ ልባቸው ሰርጎ በመግባት ቃሉን ያንቀዋል፤ የማያፈራም ይሆናል።
በመጨረሻም፣ ጥሩ አፈር ላይ እንደተዘሩት ዘሮች የሆኑት ቃሉን የሚሰሙና በደስታ የሚቀበሉ እንዲሁም 30፣ 60 እና 100 እጥፍ የሚያፈሩ ናቸው።”
ደግሞም እንዲህ አላቸው፦ “መብራት አምጥቶ እንቅብ የሚደፋበት ወይም አልጋ ሥር የሚያስቀምጠው ይኖራል? የሚቀመጠው በመቅረዝ ላይ አይደለም?
ስለዚህ የተሸሸገ መገለጡ፣ የተሰወረም ይፋ መውጣቱ አይቀርም።
የሚሰማ ጆሮ ያለው ሁሉ ይስማ።”
አክሎም እንዲህ አላቸው፦ “የምትሰሙትን ነገር ልብ በሉ። በምትሰፍሩበት መስፈሪያ ይሰፈርላችኋል፤ እንዲያውም ከዚያ የበለጠ ይጨመርላችኋል።
ላለው ይጨመርለታልና፤ የሌለው ግን ያው ያለው እንኳ ይወሰድበታል።”
ከዚያም እንዲህ አለ፦ “የአምላክ መንግሥት መሬት ላይ ዘር የሚዘራን ሰው ይመስላል።
ሰውየው ሌሊት ይተኛል፤ ማለዳም ይነሳል፤ እንዴት እንደሆነም ሳያውቅ ዘሩ ይበቅልና ያድጋል።
መሬቱም ራሱ ቀስ በቀስ ፍሬ ያፈራል፤ በመጀመሪያ ቡቃያውን፣ ከዚያም ዛላውን በመጨረሻም በዛላው ላይ የጎመራ ፍሬ ይሰጣል።
ሰብሉ እንደደረሰ ግን የመከር ወቅት በመሆኑ ሰውየው ማጭዱን ይዞ ያጭዳል።”
ደግሞም እንዲህ አለ፦ “የአምላክን መንግሥት ከምን ጋር ልናነጻጽረው እንችላለን? ወይስ በምን ምሳሌ ልንገልጸው እንችላለን?
መሬት ላይ በተዘራች ጊዜ በምድር ላይ ካሉ ዘሮች ሁሉ እጅግ የምታንስን የሰናፍጭ ዘር ይመስላል።
ከተዘራች በኋላ ግን አድጋ ከሌሎች ተክሎች ሁሉ የምትበልጥ ትሆናለች፤ ትላልቅ ቅርንጫፎችም ታወጣለች፤ በመሆኑም የሰማይ ወፎች በጥላዋ ሥር መስፈሪያ ያገኛሉ።”
ኢየሱስ እንዲህ የመሳሰሉ በርካታ ምሳሌዎችን ተጠቅሞ መረዳት በሚችሉት መጠን ቃሉን ይነግራቸው ነበር።
እንዲያውም ያለምሳሌ አይነግራቸውም ነበር፤ ብቻቸውን በሚሆኑበት ጊዜ ግን ለደቀ መዛሙርቱ ሁሉንም ነገር ያብራራላቸው ነበር።
በዚያ ቀን፣ ምሽት ላይ “ወደ ባሕሩ ማዶ እንሻገር” አላቸው።
በመሆኑም ሕዝቡን ካሰናበቱ በኋላ እዚያው ጀልባዋ ውስጥ እንዳለ ይዘውት ሄዱ፤ ሌሎች ጀልባዎችም አብረውት ነበሩ።
በዚህ ጊዜ እጅግ ኃይለኛ አውሎ ነፋስ ተነሳ፤ ማዕበሉም ከጀልባዋ ጋር እየተላተመ ወደ ውስጥ ይገባ ጀመር፤ ከዚህም የተነሳ ጀልባዋ በውኃ ልትሞላ ተቃረበች።
ኢየሱስ ግን በጀልባዋ የኋለኛ ክፍል ትራስ ተንተርሶ ተኝቶ ነበር። ስለዚህ ቀስቅሰውት “መምህር፣ ስናልቅ ዝም ብለህ ታያለህ?” አሉት።
በዚህ ጊዜ ተነስቶ ነፋሱን ገሠጸው፤ ባሕሩንም “ጸጥ በል! ረጭ በል!” አለው። ነፋሱ ቆመ፤ ታላቅ ጸጥታም ሰፈነ።
ከዚያም “ለምን ትሸበራላችሁ? አሁንም እምነት የላችሁም?” አላቸው።
እነሱ ግን በታላቅ ፍርሃት ተውጠው እርስ በርሳቸው “ለመሆኑ ይህ ማን ነው? ነፋስና ባሕር እንኳ ይታዘዙለታል” ተባባሉ።
ከዚያም ምሳሌ በመጠቀም እንዲህ አላቸው፦ “አንድ ሰው የወይን እርሻ አለማ፤ ዙሪያውንም አጠረው፤ ጉድጓድ ቆፍሮም የወይን መጭመቂያ አዘጋጀ፤ ማማም ሠራለት፤ ከዚያም ለገበሬዎች አከራይቶ ወደ ሌላ አገር ሄደ።
ወቅቱ ሲደርስ ከወይኑ ፍሬ ድርሻውን ከገበሬዎቹ እንዲያመጣለት አንድ ባሪያ ወደ እነሱ ላከ።
እነሱ ግን ይዘው ደበደቡት፤ ባዶ እጁንም ሰደዱት።
በድጋሚ ሌላ ባሪያ ወደ እነሱ ላከ፤ እሱንም ራሱን ፈነከቱት፤ ደግሞም አዋረዱት።
ሌላም ባሪያ ላከ፤ እሱን ደግሞ ገደሉት፤ ሌሎች ብዙዎችንም ላከ፤ አንዳንዶቹን ደበደቡ፤ አንዳንዶቹን ደግሞ ገደሉ።
አሁን የቀረው የሚወደው ልጁ ነበር። ‘መቼም ልጄን ያከብሩታል’ በማለት በመጨረሻ እሱን ላከው።
እነዚያ ገበሬዎች ግን እርስ በርሳቸው ‘ወራሹ ይሄ ነው። ኑ እንግደለው፤ ርስቱም የእኛ ይሆናል’ ተባባሉ።
ስለዚህ ይዘው ገደሉት፤ ከወይን እርሻውም አውጥተው ጣሉት።
እንግዲህ የወይኑ እርሻ ባለቤት ምን የሚያደርግ ይመስላችኋል? ይመጣና ገበሬዎቹን ይገድላል፤ የወይን እርሻውንም ለሌሎች ይሰጣል።
እንዲህ የሚለውን የቅዱሳን መጻሕፍት ቃል አላነበባችሁም? ‘ግንበኞች የናቁት ድንጋይ፣ የማዕዘን ራስ ድንጋይ ሆነ።
ይህ የይሖዋ ሥራ ነው፤ ለዓይናችንም ድንቅ ነው።’”
በዚህ ጊዜ ምሳሌውን የተናገረው እነሱን አስቦ እንደሆነ ስለተረዱ ሊይዙት ፈለጉ። ሆኖም ሕዝቡን ስለፈሩ ትተውት ሄዱ።
ከዚያም በንግግሩ ሊያጠምዱት ፈልገው አንዳንድ ፈሪሳውያንን እና የሄሮድስ ሥርወ መንግሥት ደጋፊዎችን ወደ እሱ ላኩ።
እነሱም መጥተው እንዲህ አሉት፦ “መምህር፣ አንተ እውነተኛ እንደሆንክና ለመወደድ ብለህ ምንም ነገር እንደማታደርግ፣ የሰውንም ውጫዊ ማንነት አይተህ እንደማትፈርድ፣ ከዚህ ይልቅ የአምላክን መንገድ በእውነት እንደምታስተምር እናውቃለን። ለመሆኑ ለቄሳር ግብር መክፈል ይገባል ወይስ አይገባም?
እንክፈል ወይስ አንክፈል?” እሱም ግብዝነታቸውን ተረድቶ “ለምን ትፈትኑኛላችሁ? እስቲ አንድ ዲናር አምጡና አሳዩኝ” አላቸው።
እነሱም አመጡለት፤ እሱም “ይህ ምስልና የተቀረጸው ጽሑፍ የማን ነው?” አላቸው። እነሱም “የቄሳር” አሉት።
ከዚያም ኢየሱስ “የቄሳር የሆነውን ለቄሳር፣ የአምላክ የሆነውን ደግሞ ለአምላክ ስጡ” አላቸው። እነሱም በእሱ ተደነቁ።
በትንሣኤ የማያምኑት ሰዱቃውያን ደግሞ መጥተው እንዲህ ሲሉ ጠየቁት፦
“መምህር፣ ሙሴ አንድ ሰው ልጅ ሳይወልድ ከሚስቱ በሞት ቢለይ ወንድሙ ሚስትየዋን አግብቶ ለወንድሙ ዘር መተካት እንዳለበት ጽፎልናል።
ሰባት ወንድማማቾች ነበሩ። የመጀመሪያው ሚስት አገባና ዘር ሳይተካ ሞተ።
ከዚያም ሁለተኛው አገባት፤ ሆኖም ዘር ሳይተካ ሞተ፤ ሦስተኛውም እንዲሁ፤
ሰባቱም ዘር አልተኩም። በመጨረሻም ሴትየዋ ሞተች።
እንግዲህ ሰባቱም ስላገቧት በትንሣኤ ለየትኛው ሚስት ትሆናለች?”
ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፦ “እናንተ የምትሳሳቱት ቅዱሳን መጻሕፍትንም ሆነ የአምላክን ኃይል ባለማወቃችሁ አይደለም?
ከሞት በሚነሱበት ጊዜ ወንዶችም አያገቡም ሴቶችም አይዳሩም፤ ከዚህ ይልቅ በሰማያት እንዳሉ መላእክት ይሆናሉ።
ስለ ሙታን መነሳት ግን በሙሴ መጽሐፍ፣ ስለ ቁጥቋጦው በሚገልጸው ታሪክ ላይ አምላክ ሙሴን ‘እኔ የአብርሃም አምላክ፣ የይስሐቅ አምላክና የያዕቆብ አምላክ ነኝ’ እንዳለው አላነበባችሁም?
እሱ የሕያዋን እንጂ የሙታን አምላክ አይደለም። እናንተ እጅግ ተሳስታችኋል።”
ከጸሐፍት ወገን የሆነ አንድ ሰው መጥቶ ሲከራከሩ ይሰማ ነበር፤ ኢየሱስ ጥሩ አድርጎ እንደመለሰላቸው አስተውሎ “ከትእዛዛት ሁሉ የመጀመሪያው የትኛው ነው?” ሲል ጠየቀው።
ኢየሱስ እንዲህ ሲል መለሰ፦ “የመጀመሪያው ይህ ነው፦ ‘እስራኤል ሆይ ስማ፤ ይሖዋ አምላካችን አንድ ይሖዋ ነው፤
አንተም አምላክህን ይሖዋን በሙሉ ልብህ፣ በሙሉ ነፍስህ፣ በሙሉ አእምሮህና በሙሉ ኃይልህ ውደድ።’
ሁለተኛው ደግሞ ‘ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ’ የሚል ነው። ከእነዚህ የሚበልጥ ሌላ ትእዛዝ የለም።”
ጸሐፊውም እንዲህ አለው፦ “መምህር፣ የተናገርከው እውነት ነው፤ ‘እሱ አንድ ነው፤ ከእሱ ሌላ አምላክ የለም’፤
እሱን በሙሉ ልብ፣ በሙሉ አእምሮና በሙሉ ኃይል መውደድ እንዲሁም ባልንጀራን እንደ ራስ መውደድ፣ ሙሉ በሙሉ ከሚቃጠል መባና ከመሥዋዕት ሁሉ እጅግ ይበልጣል።”
በዚህ ጊዜ ኢየሱስ በማስተዋል እንደመለሰ ተረድቶ “አንተ ከአምላክ መንግሥት የራቅክ አይደለህም” አለው። ከዚህ በኋላ ግን ሊጠይቀው የደፈረ አልነበረም።
ይሁን እንጂ ኢየሱስ ቤተ መቅደሱ ውስጥ እያስተማረ ሳለ እንዲህ አለ፦ “ጸሐፍት ክርስቶስ የዳዊት ልጅ ነው እንዴት ይላሉ?
ዳዊት ራሱ በመንፈስ ቅዱስ ሲናገር ‘ይሖዋ ጌታዬን “ጠላቶችህን ከእግርህ በታች እስካደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ” አለው’ ብሏል።
ዳዊት ራሱ ጌታ ብሎ ከጠራው እንዴት ልጁ ይሆናል?” ሕዝቡም በደስታ ያዳምጠው ነበር።
ማስተማሩንም በመቀጠል እንዲህ አለ፦ “ከጸሐፍት ተጠንቀቁ፤ ዘርፋፋ ልብስ ለብሰው መዞር ይወዳሉ፤ በገበያ ቦታም ሰዎች እጅ እንዲነሷቸው ይፈልጋሉ፤
በምኩራብ ከፊት መቀመጥ፣ በራት ግብዣ ላይም የክብር ቦታ ይፈልጋሉ።
የመበለቶችን ቤት ያራቁታሉ፤ ለታይታ ብለውም ጸሎታቸውን ያስረዝማሉ። እነዚህ የከፋ ፍርድ ይጠብቃቸዋል።”
ኢየሱስ በመዋጮ ሣጥኖቹ ትይዩ ተቀምጦ ሕዝቡ በመዋጮ ሣጥኖቹ ውስጥ ገንዘብ እንዴት እንደሚከቱ ይመለከት ጀመር፤ ብዙ ሀብታሞችም ብዙ ሳንቲሞች ይከቱ ነበር።
በዚህ ጊዜ አንዲት ድሃ መበለት መጥታ በጣም አነስተኛ ዋጋ ያላቸው ሁለት ትናንሽ ሳንቲሞች ከተተች።
ኢየሱስም ደቀ መዛሙርቱን ጠርቶ እንዲህ አላቸው፦ “እውነት እላችኋለሁ፣ በመዋጮ ሣጥኖቹ ውስጥ ገንዘብ ከጨመሩት ሁሉ የበለጠ የሰጠችው ይህች ድሃ መበለት ነች።
ሁሉም የሰጡት ከትርፋቸው ነውና፤ እሷ ግን በድሃ አቅሟ ያላትን ሁሉ፣ መተዳደሪያዋን በጠቅላላ ሰጥታለች።”
ከዚያ ተነስቶ ወደ ትውልድ አገሩ መጣ፤ ደቀ መዛሙርቱም ተከተሉት።
እሱም በሰንበት ቀን በምኩራብ ማስተማር ጀመረ፤ የሰሙትም አብዛኞቹ ሰዎች በመገረም እንዲህ አሉ፦ “ይህ ሰው እነዚህን ነገሮች የተማረው ከየት ነው? ይህን ጥበብ ያገኘውስ እንዴት ነው? ደግሞስ እንዲህ ያሉ ተአምራትን ማከናወን የቻለው እንዴት ነው?
ይህ አናጺው የማርያም ልጅ እንዲሁም የያዕቆብ፣ የዮሴፍ፣ የይሁዳና የስምዖን ወንድም አይደለም? እህቶቹስ የሚኖሩት ከእኛው ጋር አይደለም?” ከዚህም የተነሳ ተሰናከሉበት።
ኢየሱስ ግን “ነቢይ በገዛ አገሩ፣ በዘመዶቹ ዘንድና በገዛ ቤቱ ካልሆነ በስተቀር በሌላ ቦታ ሁሉ ይከበራል” አላቸው።
ስለሆነም ጥቂት ሕመምተኞች ላይ እጁን በመጫን ከመፈወስ በቀር በዚያ ሌላ ተአምር መፈጸም አልቻለም።
እንዲያውም ባለማመናቸው እጅግ ተደነቀ። ከዚህ በኋላ በዙሪያው ባሉት መንደሮች እየተዘዋወረ አስተማረ።
አሥራ ሁለቱን ከጠራ በኋላ ሁለት ሁለት አድርጎ ላካቸው፤ ርኩሳን መናፍስትን እንዲያዝዙም ሥልጣን ሰጣቸው።
ደግሞም ከበትር በስተቀር ለጉዟቸው ዳቦም ሆነ የምግብ ከረጢት እንዲሁም በመቀነታቸው ገንዘብ እንዳይዙ አዘዛቸው፤
በተጨማሪም ሁለት ልብስ እንዳይዙ፣ ጫማ ግን እንዲያደርጉ ነገራቸው።
አክሎም እንዲህ አላቸው፦ “ወደ አንድ ቤት ስትገቡ አካባቢውን ለቃችሁ እስክትሄዱ ድረስ እዚያው ቆዩ።
ነገር ግን የሚቀበላችሁ ወይም የሚሰማችሁ ካጣችሁ ከዚያ ቦታ ስትወጡ ምሥክር እንዲሆንባቸው የእግራችሁን አቧራ አራግፉ።”
እነሱም ከዚያ ወጥተው ሰዎች ንስሐ ይገቡ ዘንድ ሰበኩ፤
ብዙ አጋንንትም አስወጡ፤ እንዲሁም ብዙ ሕመምተኞችን ዘይት እየቀቡ ፈወሱ።
የኢየሱስ ስም በሰፊው ታውቆ ስለነበር ንጉሥ ሄሮድስ ይህን ሰማ፤ ሰዎችም “አጥማቂው ዮሐንስ ከሞት ተነስቷል፤ እንዲህ ያሉ ተአምራት መፈጸም የቻለውም ለዚህ ነው” ይሉ ነበር።
ሌሎች ግን “ኤልያስ ነው” ይሉ ነበር። ሌሎች ደግሞ “እንደቀድሞዎቹ ነቢያት ያለ ነቢይ ነው” ይሉ ነበር።
ሄሮድስ ግን ይህን በሰማ ጊዜ “እኔ ራሱን የቆረጥኩት ዮሐንስ ከሞት ተነስቷል” አለ።
ሄሮድስ የወንድሙ የፊልጶስ ሚስት በሆነችው በሄሮድያዳ ምክንያት ሰዎች ልኮ ዮሐንስን በማስያዝ በሰንሰለት አስሮ ወህኒ አስገብቶት ነበር፤ ይህም የሆነው ሄሮድስ እሷን አግብቶ ስለነበር ነው።
ዮሐንስ ሄሮድስን “የወንድምህን ሚስት እንድታገባ ሕግ አይፈቅድልህም” ይለው ነበር።
በመሆኑም ሄሮድያዳ በእሱ ላይ ቂም ይዛ ልትገድለው ትፈልግ ነበር፤ ሆኖም ይህን ማድረግ አልቻለችም።
ሄሮድስ፣ ዮሐንስ ጻድቅና ቅዱስ ሰው መሆኑን ስለሚያውቅ ይፈራውና ጉዳት እንዳያገኘው ይጠብቀው ነበር። ዮሐንስ የሚናገረውን ሲሰማ ምን እንደሚያደርገው ግራ ይገባው የነበረ ቢሆንም በደስታ ያዳምጠው ነበር።
ይሁንና ሄሮድስ በልደት ቀኑ ከፍተኛ ባለሥልጣናቱን፣ የጦር አዛዦቹንና በገሊላ ያሉ ታላላቅ ሰዎችን ራት በጋበዘ ጊዜ ሄሮድያዳ ምቹ አጋጣሚ ተፈጠረላት።
የሄሮድያዳ ልጅ ገብታ በመጨፈር ሄሮድስንና ከእሱ ጋር እየበሉ የነበሩትን አስደሰተቻቸው። ንጉሡም ልጅቷን “የፈለግሽውን ሁሉ ጠይቂኝ፣ እሰጥሻለሁ” አላት።
ደግሞም “እስከ መንግሥቴ እኩሌታ እንኳ ቢሆን የምትጠይቂኝን ሁሉ እሰጥሻለሁ” ሲል ማለላት።
እሷም ወደ እናቷ ሄዳ “ምን ብጠይቀው ይሻላል?” አለቻት። እናቷም “የአጥማቂው ዮሐንስን ራስ ጠይቂው” አለቻት።
ወዲያውም ወደ ንጉሡ ፈጥና በመግባት “የመጥምቁ ዮሐንስን ራስ አሁኑኑ በሳህን እንድትሰጠኝ እፈልጋለሁ” ስትል ጠየቀችው።
ንጉሡ በዚህ እጅግ ቢያዝንም ስለገባው መሐላና ስለ እንግዶቹ ሲል እንቢ ሊላት አልፈለገም።
ከዚያም ንጉሡ ጠባቂውን ወዲያው ልኮ የዮሐንስን ራስ እንዲያመጣ አዘዘው። ጠባቂውም ሄዶ ወህኒ ቤት ውስጥ ራሱን ቆረጠው፤
ራሱንም በሳህን ይዞ መጣ። ከዚያም ለልጅቷ ሰጣት፤ ልጅቷም ለእናቷ ሰጠቻት።
ደቀ መዛሙርቱም ይህን በሰሙ ጊዜ መጥተው አስከሬኑን በመውሰድ በመቃብር አኖሩት።
ሐዋርያቱ በኢየሱስ ዙሪያ ተሰብስበው ያደረጉትንና ያስተማሩትን ነገር ሁሉ ነገሩት።
እሱም “ለብቻችን ወደ አንድ ገለል ያለ ስፍራ እንሂድና በዚያ ትንሽ አረፍ በሉ” አላቸው። ብዙዎች ይመጡና ይሄዱ ስለነበር ምግብ ለመብላት እንኳ ፋታ አላገኙም።
ስለዚህ ብቻቸውን ለመሆን በጀልባ ተሳፍረው ገለል ወዳለ ስፍራ ሄዱ።
ይሁንና ሰዎች ሲሄዱ አዩአቸው፤ ብዙዎችም መሄዳቸውን አወቁ፤ ስለሆነም ከከተሞች ሁሉ አንድ ላይ በእግር በመሮጥ ቀድመዋቸው ደረሱ።