text stringlengths 4 267 |
|---|
ደግሞም ከመጀመሪያው አንስቶ የዓይን ምሥክሮች የነበሩ ሰዎችና መልእክቱን የሚያውጁ አገልጋዮች እነዚህን መረጃዎች ለእኛ አስተላልፈዋል። |
ክቡር ቴዎፍሎስ ሆይ፣ እኔም በበኩሌ ሁሉንም ነገር ከመጀመሪያው አንስቶ በጥንቃቄ ስለመረመርኩ ታሪኩን በቅደም ተከተል ልጽፍልህ ወሰንኩ። |
ይህን ያደረግኩት በቃል የተማርካቸው ነገሮች እርግጠኛ መሆናቸውን በሚገባ እንድታውቅ ነው። |
በይሁዳ ንጉሥ በሄሮድስ ዘመን፣ በአቢያህ የክህነት ምድብ ውስጥ የሚያገለግል ዘካርያስ የሚባል አንድ ካህን ነበር። ሚስቱ የአሮን ዘር ስትሆን ስሟም ኤልሳቤጥ ነበር። |
ሁለቱም በአምላክ ፊት ጻድቃን ነበሩ፤ የይሖዋን ትእዛዛትና ሕግጋት ሁሉ እየጠበቁ ያለነቀፋ ይኖሩ ነበር። |
ይሁን እንጂ ኤልሳቤጥ መሃን በመሆኗ ልጅ አልነበራቸውም፤ እንዲሁም ሁለቱም በዕድሜ የገፉ ነበሩ። |
አንድ ቀን ዘካርያስ እሱ ያለበት ምድብ ተራው ደርሶ በአምላክ ፊት በክህነት እያገለገለ ሳለ |
በክህነት ሥርዓቱ መሠረት ወደ ይሖዋ ቤተ መቅደስ ገብቶ ዕጣን የሚያጥንበት ተራ ደረሰው። |
ዕጣን በሚቀርብበትም ሰዓት ሕዝቡ ሁሉ በውጭ ሆነው ይጸልዩ ነበር። |
የይሖዋም መልአክ ከዕጣን መሠዊያው በስተ ቀኝ ቆሞ ታየው። |
ዘካርያስም መልአኩን ባየው ጊዜ ደነገጠ፤ በፍርሃትም ተዋጠ። |
መልአኩ ግን እንዲህ አለው፦ “ዘካርያስ፣ አትፍራ፤ ምክንያቱም አምላክ ያቀረብከውን ምልጃ ሰምቷል፤ ሚስትህ ኤልሳቤጥም ወንድ ልጅ ትወልድልሃለች፤ ስሙንም ዮሐንስ ትለዋለህ። |
አንተም ደስ ይልሃል፤ ሐሴትም ታደርጋለህ፤ ብዙዎችም በእሱ መወለድ ደስ ይላቸዋል፤ |
በይሖዋ ፊት ታላቅ ይሆናልና። ይሁንና የወይን ጠጅም ሆነ ሌላ የሚያሰክር መጠጥ ፈጽሞ መጠጣት የለበትም፤ ከመወለዱ በፊት እንኳ በመንፈስ ቅዱስ ይሞላል፤ |
ከእስራኤል ልጆች መካከልም ብዙዎቹን ወደ አምላካቸው ወደ ይሖዋ ይመልሳል። |
በተጨማሪም ሰዎችን ለይሖዋ ያዘጋጅ ዘንድ የአባቶችን ልብ እንደ ልጆች ልብ ለማድረግ፣ የማይታዘዙትንም ሰዎች ወደ ጻድቃን ጥበብ ለመመለስ በኤልያስ መንፈስና ኃይል በአምላክ ፊት ይሄዳል።” |
ዘካርያስ መልአኩን “ይህ እንደሚሆን እንዴት እርግጠኛ መሆን እችላለሁ? እኔ እንደሆነ አርጅቻለሁ፤ ሚስቴም ዕድሜዋ ገፍቷል” አለው። |
መልአኩም መልሶ እንዲህ አለው፦ “እኔ በአምላክ አጠገብ በፊቱ የምቆመው ገብርኤል ነኝ፤ አንተን እንዳነጋግርህና ይህን ምሥራች እንዳበስርህ ተልኬአለሁ። |
ሆኖም የተወሰነለትን ጊዜ ጠብቆ የሚፈጸመውን ቃሌን ስላላመንክ ይህ ነገር እስኪፈጸም ድረስ ዱዳ ትሆናለህ! መናገርም አትችልም።” |
ይህ በእንዲህ እንዳለ ሕዝቡ ዘካርያስን በመጠባበቅ ላይ ነበሩ፤ ቤተ መቅደሱ ውስጥ ብዙ በመቆየቱም ግራ ተጋቡ። |
በወጣ ጊዜም ሊያናግራቸው አልቻለም፤ እነሱም በቤተ መቅደሱ ውስጥ አንድ ራእይ እንዳየ ተገነዘቡ። ከዚያ በኋላ ዱዳ ስለሆነ በምልክት ብቻ ያናግራቸው ነበር። |
በቤተ መቅደሱ ውስጥ ቅዱስ አገልግሎት የሚያቀርብባቸው ቀናት ሲያበቁ ወደ ቤቱ ሄደ። |
ከተወሰኑ ቀናት በኋላ ሚስቱ ኤልሳቤጥ ፀነሰች፤ ለአምስት ወርም ከቤት ሳትወጣ ቆየች፤ እንዲህም አለች፦ |
“ይሖዋ በዚህ ወቅት ይህን አደረገልኝ። በሰዎች መካከል ይደርስብኝ የነበረውን ነቀፋ ለማስወገድ ፊቱን ወደ እኔ መለሰ።” |
ኤልሳቤጥ በፀነሰች በስድስተኛ ወሯ አምላክ መልአኩ ገብርኤልን በገሊላ ወደምትገኝ ናዝሬት ወደተባለች ከተማ ላከው፤ |
የተላከውም ከዳዊት ቤት ለሆነ ዮሴፍ ለሚባል ሰው ወደታጨች አንዲት ድንግል ሲሆን የድንግሊቱም ስም ማርያም ነበር። |
መልአኩም ገብቶ “እጅግ የተባረክሽ ሆይ፣ ሰላም ለአንቺ ይሁን፤ ይሖዋ ከአንቺ ጋር ነው” አላት። |
እሷ ግን በንግግሩ በጣም ደንግጣ ይህ ሰላምታ ምን ትርጉም እንዳለው ለመረዳት በውስጧ ታስብ ጀመር። |
ስለዚህ መልአኩ እንዲህ አላት፦ “ማርያም ሆይ፣ በአምላክ ፊት ሞገስ ስላገኘሽ አትፍሪ። |
እነሆም፣ ትፀንሻለሽ፤ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ፤ ስሙንም ኢየሱስ ትዪዋለሽ። |
እሱም ታላቅ ይሆናል፤ የልዑሉም አምላክ ልጅ ይባላል፤ ይሖዋ አምላክም የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል፤ |
በያዕቆብ ቤትም ላይ ለዘላለም ንጉሥ ሆኖ ይገዛል፤ ለመንግሥቱም መጨረሻ የለውም።” |
ማርያም ግን መልአኩን “እኔ ከወንድ ጋር ግንኙነት ፈጽሜ ስለማላውቅ ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል?” አለችው። |
መልአኩም መልሶ እንዲህ አላት፦ “መንፈስ ቅዱስ በአንቺ ላይ ይመጣል፤ የልዑሉም ኃይል በአንቺ ላይ ያርፋል። ስለሆነም የሚወለደው ልጅ ቅዱስና የአምላክ ልጅ ይባላል። |
እነሆ፣ ዘመድሽ ኤልሳቤጥም በስተርጅናዋ ወንድ ልጅ ፀንሳለች፤ መሃን ትባል የነበረ ቢሆንም ይኸው ስድስተኛ ወሯን ይዛለች፤ |
አምላክ የተናገረው ቃል ሳይፈጸም አይቀርምና።” |
በዚህ ጊዜ ማርያም “እነሆ፣ እኔ የይሖዋ ባሪያ ነኝ! እንደ ቃልህ ይሁንልኝ” አለች። ከዚያም መልአኩ ተለይቷት ሄደ። |
ማርያምም በዚያው ሰሞን ተነስታ በተራራማው አገር ወደምትገኝ አንዲት የይሁዳ ከተማ በፍጥነት ሄደች፤ |
ወደ ዘካርያስ ቤት ገብታም ኤልሳቤጥን ሰላም አለቻት። |
ኤልሳቤጥ የማርያምን ሰላምታ በሰማች ጊዜ በማህፀኗ ውስጥ ያለው ፅንስ ዘለለ፤ ኤልሳቤጥም በመንፈስ ቅዱስ ተሞላች፤ |
ድምፅዋንም ከፍ አድርጋ እንዲህ አለች፦ “አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ፤ የማህፀንሽም ፍሬ የተባረከ ነው! |
የጌታዬ እናት ወደ እኔ መምጣቷ ለእኔ እንዴት ያለ ታላቅ ክብር ነው! |
እነሆ፣ የሰላምታሽን ድምፅ እንደሰማሁ በማህፀኔ ያለው ፅንስ በደስታ ዘሏልና። |
ይሖዋ የነገራት ነገር ሙሉ በሙሉ የሚፈጸም በመሆኑ ይህን ያመነች ደስተኛ ነች።” |
ማርያምም እንዲህ አለች፦ “ነፍሴ ይሖዋን ከፍ ከፍ ታደርገዋለች፤ |
መንፈሴም አዳኜ በሆነው አምላክ እጅግ ደስ ይሰኛል፤ |
ምክንያቱም የባሪያውን መዋረድ ተመልክቷል። እነሆ፣ ከአሁን ጀምሮ ትውልድ ሁሉ ደስተኛ ይሉኛል፤ |
ምክንያቱም ኃያል የሆነው አምላክ ታላላቅ ነገሮች አድርጎልኛል፤ ስሙም ቅዱስ ነው፤ |
ምሕረቱም በሚፈሩት ሁሉ ላይ ከትውልድ እስከ ትውልድ ይኖራል። |
በክንዱም ታላላቅ ሥራዎች አከናውኗል፤ በልባቸው ሐሳብ ትዕቢተኛ የሆኑትንም በትኗቸዋል። |
ኃያላን ሰዎችን ከዙፋናቸው አውርዷል፤ ዝቅ ያሉትንም ከፍ አድርጓል፤ |
የተራቡትን በመልካም ነገሮች አጥግቧል፤ ሀብታሞችንም ባዶ እጃቸውን ሰዷቸዋል። |
ምሕረቱን በማስታወስ አገልጋዩን እስራኤልን ረድቷል፤ |
ይህን ያደረገው ለአባቶቻችን በገባው ቃል መሠረት ለአብርሃምና ለዘሩ ለዘላለም ምሕረት ለማሳየት ነው።” |
ማርያምም ከኤልሳቤጥ ጋር ሦስት ወር ያህል ከቆየች በኋላ ወደ ቤቷ ተመለሰች። |
ኤልሳቤጥ የመውለጃዋ ጊዜ ደረሰና ወንድ ልጅ ወለደች። |
ጎረቤቶቿና ዘመዶቿም ይሖዋ ታላቅ ምሕረት እንዳደረገላት ሰምተው የደስታዋ ተካፋዮች ሆኑ። |
በስምንተኛው ቀን ሕፃኑን ሊገርዙት መጡ፤ በአባቱም ስም ዘካርያስ ብለው ሊጠሩት ፈልገው ነበር። |
እናትየው ግን መልሳ “አይሆንም! ዮሐንስ ይባል” አለች። |
በዚህ ጊዜ “ከዘመዶችሽ መካከል በዚህ ስም የተጠራ ማንም የለም” አሏት። |
ከዚያም አባቱን ማን ተብሎ እንዲጠራ እንደሚፈልግ በምልክት ጠየቁት። |
እሱም የእንጨት ጽላት እንዲያመጡለት ጠየቀና “ስሙ ዮሐንስ ነው” ብሎ ጻፈ። በዚህ ጊዜ ሁሉም ተደነቁ። |
ወዲያውም አፉ ተከፈተ፤ ምላሱም ተፈቶ መናገር ጀመረ፤ አምላክንም አወደሰ። |
ጎረቤቶቻቸውም ሁሉ በፍርሃት ተዋጡ፤ የሆነውም ነገር ሁሉ በተራራማው የይሁዳ አገር በሙሉ ይወራ ጀመር። |
ይህን የሰሙም ሁሉ “የዚህ ሕፃን መጨረሻ ምን ይሆን?” በማለት ነገሩን በልባቸው ያዙ። የይሖዋ እጅ ከእሱ ጋር እንደሆነ በግልጽ ይታይ ነበርና። |
ከዚያም አባቱ ዘካርያስ በመንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ እንዲህ ሲል ትንቢት ተናገረ፦ |
“የእስራኤል አምላክ ይሖዋ ፊቱን ወደ ሕዝቡ ስለመለሰና ሕዝቡን ስላዳነ ውዳሴ ይድረሰው። |
ደግሞም በአገልጋዩ በዳዊት ቤት የመዳን ቀንድ አስነስቶልናል፤ |
ይህም ከጥንት ዘመን ጀምሮ በነበሩት ቅዱሳን ነቢያቱ አፍ በተናገረው መሠረት ነው። |
ከባላጋራዎቻችንና ከሚጠሉን ሰዎች ሁሉ እጅ እንደሚያድነን ቃል ገብቷል። |
ለአባቶቻችን በሰጠው ተስፋ መሠረት ምሕረት ያሳየናል፤ ቅዱስ ቃል ኪዳኑንም ያስታውሳል። |
ይህም ቃል ኪዳን ለአባታችን ለአብርሃም የማለው መሐላ ነው፤ |
በመሐላው መሠረትም ከጠላቶቻችን እጅ ነፃ ካወጣን በኋላ ለእሱ ያለፍርሃት ቅዱስ አገልግሎት የማቅረብ መብት ይሰጠናል፤ |
ይህም ታማኝ እንድንሆንና በሕይወት ዘመናችን ሁሉ ጽድቅ የሆነውን ነገር እንድናደርግ ነው። |
ደግሞም አንተ ሕፃን፣ መንገዱን ለማዘጋጀት ቀድመህ በይሖዋ ፊት ስለምትሄድ የልዑሉ ነቢይ ትባላለህ፤ |
ለሕዝቡም ኃጢአታቸው ይቅር ተብሎላቸው መዳን እንዲያገኙ የሚያስችላቸውን እውቀት ትሰጣቸዋለህ፤ |
ይህም የሆነው አምላካችን ከአንጀት ስለራራልን ነው። ከዚህ ርኅራኄም የተነሳ እንደ ንጋት ፀሐይ የሚያበራ ብርሃን ከላይ ይወጣልናል፤ |
ይኸውም በጨለማና በሞት ጥላ ውስጥ ለተቀመጡት ብርሃን ለመስጠት እንዲሁም እግሮቻችንን በሰላም መንገድ ለመምራት ነው።” |
ሕፃኑም አደገ፤ በመንፈስም ጠነከረ፤ ለእስራኤልም በይፋ እስከታየበት ቀን ድረስ በበረሃ ኖረ። |
ኢየሱስ ለሕዝቡ ተናግሮ ከጨረሰ በኋላ ወደ ቅፍርናሆም ገባ። |
በዚያም አንድ የጦር መኮንን ነበር፤ በጣም የሚወደው ባሪያውም በጠና ታሞ ሊሞት ተቃርቦ ነበር። |
እሱም ስለ ኢየሱስ ሲሰማ መጥቶ ባሪያውን እንዲፈውስለት ይለምኑለት ዘንድ የተወሰኑ አይሁዳውያን ሽማግሌዎችን ላከ። |
እነሱም ወደ ኢየሱስ መጥተው እንዲህ በማለት ተማጸኑት፦ “ይህን ሰው ልትረዳው ይገባል፤ |
ምክንያቱም ሕዝባችንን ይወዳል፤ ምኩራባችንንም ያሠራልን እሱ ነው።” |
ስለዚህ ኢየሱስ አብሯቸው ሄደ። ሆኖም ወደ ቤቱ በተቃረበ ጊዜ መኮንኑ ወዳጆቹን እንዲህ ሲል ወደ ኢየሱስ ላከ፦ “ጌታዬ፣ በቤቴ ጣሪያ ሥር ልትገባ የሚገባኝ ሰው ስላልሆንኩ አትድከም። |
ከዚህም የተነሳ አንተ ፊት መቅረብ የሚገባኝ ሰው እንደሆንኩ አልተሰማኝም። ስለዚህ አንተ አንድ ቃል ተናገርና አገልጋዬ ይፈወስ። |
እኔ ራሴ የምታዘዛቸው የበላይ አዛዦች አሉ፤ ለእኔም የሚታዘዙ የበታች ወታደሮች አሉኝ፤ አንዱን ‘ሂድ!’ ስለው ይሄዳል፤ ሌላውንም ‘ና!’ ስለው ይመጣል፤ ባሪያዬንም ‘ይህን አድርግ!’ ስለው ያደርጋል።” |
ኢየሱስ ይህን በሰማ ጊዜ በሰውየው በጣም ተደንቆ ይከተለው ወደነበረው ሕዝብ ዞር በማለት “እላችኋለሁ፣ በእስራኤል ውስጥ እንኳ እንዲህ ዓይነት ታላቅ እምነት አላገኘሁም” አለ። |
የተላኩትም ሰዎች ወደ ቤት ሲመለሱ ባሪያው ድኖ አገኙት። |
ከዚህ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ናይን ወደምትባል ከተማ ተጓዘ፤ ደቀ መዛሙርቱና ሌሎች ብዙ ሰዎችም አብረውት ይጓዙ ነበር። |
ወደ ከተማዋ መግቢያ ሲቃረብ ሰዎች የአንድ ሰው አስከሬን ተሸክመው በመውጣት ላይ ነበሩ፤ ሟቹ ለእናቱ አንድ ልጇ ነበር። በተጨማሪም እናቱ መበለት ነበረች። ብዙ የከተማዋ ሕዝብም ከእሷ ጋር ነበር። |
ጌታ ባያት ጊዜ በጣም አዘነላትና “በቃ፣ አታልቅሺ” አላት። |
ከዚያም ቀረብ ብሎ ቃሬዛውን ነካ፤ የተሸከሙት ሰዎችም ባሉበት ቆሙ፤ ኢየሱስም “አንተ ወጣት፣ ተነስ እልሃለሁ!” አለ። |
የሞተውም ሰው ቀና ብሎ ተቀመጠና መናገር ጀመረ፤ ኢየሱስም ለእናቱ ሰጣት። |
በዚህ ጊዜ ሁሉም በፍርሃት ተውጠው “ታላቅ ነቢይ በመካከላችን ተነስቷል፤” እንዲሁም “አምላክ ሕዝቡን አሰበ” እያሉ አምላክን ያወድሱ ጀመር። |
ኢየሱስ ያከናወነውም ነገር በይሁዳ ሁሉና በአካባቢው ባለ አገር ሁሉ ተሰማ። |
በዚህ ጊዜ የዮሐንስ ደቀ መዛሙርት ይህን ሁሉ አወሩለት። |
ዮሐንስም ከደቀ መዛሙርቱ መካከል ሁለቱን ጠርቶ “ይመጣል የተባልከው አንተ ነህ ወይስ ሌላ እንጠብቅ?” ብለው እንዲጠይቁት ወደ ጌታ ላካቸው። |
ሰዎቹም ወደ ኢየሱስ መጥተው “መጥምቁ ዮሐንስ፣ ‘ይመጣል የተባልከው አንተ ነህ ወይስ ሌላ እንጠብቅ?’ ብለን እንድንጠይቅህ ወደ አንተ ልኮናል” አሉት። |
ኢየሱስ በዚያኑ ሰዓት ብዙዎችን ከሕመምና ከከባድ በሽታ ፈወሳቸው፤ እንዲሁም ያደሩባቸውን ክፉ መናፍስት አወጣ፤ የብዙ ዓይነ ስውራንንም ዓይን አበራ። |
Subsets and Splits
No community queries yet
The top public SQL queries from the community will appear here once available.