text
stringlengths
4
267
ከእኔ ጋር የነበሩት ሰዎች ብርሃኑን አይተዋል፤ ሆኖም እሱ ሲያነጋግረኝ ድምፁን አልሰሙም።
በዚህ ጊዜ ‘ጌታ ሆይ፣ ምን ባደርግ ይሻላል?’ አልኩት። ጌታም ‘ተነስተህ ወደ ደማስቆ ሂድ፤ እዚያም ልታደርገው የሚገባህ ነገር ሁሉ ይነገርሃል’ አለኝ።
ይሁንና ከብርሃኑ ድምቀት የተነሳ ዓይኔ ማየት ስለተሳነው አብረውኝ የነበሩት ሰዎች እጄን ይዘው እየመሩ ደማስቆ አደረሱኝ።
“ከዚያም ሕጉን በሚገባ በመጠበቅ ለአምላክ ያደረ እንዲሁም እዚያ በሚኖሩት አይሁዳውያን ሁሉ የተመሠከረለት ሐናንያ የሚባል አንድ ሰው
ወደ እኔ መጣ። አጠገቤም ቆሞ ‘ወንድሜ ሳኦል፣ ዓይኖችህ ይብሩልህ!’ አለኝ። እኔም በዚያው ቅጽበት ቀና ብዬ አየሁት።
እሱም እንዲህ አለኝ፦ ‘የአባቶቻችን አምላክ ፈቃዱን እንድታውቅ፣ ጻድቁን እንድታይና ድምፁን እንድትሰማ መርጦሃል፤
ይህን ያደረገው ስላየኸውና ስለሰማኸው ነገር በሰው ሁሉ ፊት ለእሱ ምሥክር እንድትሆን ነው።
ታዲያ አሁን ምን ትጠብቃለህ? ተነስና ተጠመቅ፤ ስሙንም እየጠራህ ኃጢአትህን ታጠብ።’
“ሆኖም ወደ ኢየሩሳሌም ከተመለስኩ በኋላ በቤተ መቅደሱ ውስጥ እየጸለይኩ ሳለ ሰመመን ውስጥ ገባሁ፤
ጌታም ‘ስለ እኔ የምትሰጠውን ምሥክርነት ስለማይቀበሉ ፍጠን፤ ከኢየሩሳሌም ቶሎ ብለህ ውጣ’ ሲለኝ አየሁት።
እኔም እንዲህ አልኩት፦ ‘ጌታ ሆይ፣ በየምኩራቡ እየዞርኩ በአንተ የሚያምኑትን አስርና እገርፍ እንደነበረ እነሱ ራሳቸው በሚገባ ያውቃሉ፤
ደግሞም የአንተ ምሥክር የነበረው የእስጢፋኖስ ደም ሲፈስ እኔ በድርጊቱ በመስማማት እዚያ ቆሜ የገዳዮቹን ልብስ ስጠብቅ ነበር።’
እሱ ግን ‘በሩቅ ወዳሉ አሕዛብ ስለምልክህ ተነስተህ ሂድ’ አለኝ።”
ሕዝቡ ይህን እስኪናገር ድረስ ጸጥ ብለው ሲያዳምጡት ቆዩ። ከዚያም “ይህ ሰው መኖር የማይገባው ስለሆነ ከምድር ገጽ ይወገድ!” ብለው ጮኹ።
ደግሞም እየጮኹ መደረቢያቸውን ይወረውሩና አፈር ወደ ላይ ይበትኑ ስለነበር
የሠራዊቱ ሻለቃ ጳውሎስን ወደ ጦር ሰፈሩ እንዲያስገቡት ትእዛዝ ሰጠ፤ ደግሞም በጳውሎስ ላይ እንዲህ የሚጮኹት ለምን እንደሆነ በትክክል ማወቅ ስለፈለገ እየተገረፈ እንዲመረመር አዘዘ።
ሆኖም ሊገርፉት ወጥረው ባሰሩት ጊዜ ጳውሎስ አጠገቡ የቆመውን መኮንን “አንድን ሮማዊ ሳይፈረድበት ለመግረፍ ሕግ ይፈቅድላችኋል?” አለው።
መኮንኑ ይህን ሲሰማ ወደ ሠራዊቱ ሻለቃ ሄዶ “ምን ለማድረግ ነው ያሰብከው? ይህ ሰው እኮ ሮማዊ ነው” አለው።
ሻለቃውም ወደ ጳውሎስ ቀርቦ “ሮማዊ ነህ እንዴ?” አለው። እሱም “አዎ” አለው።
ሻለቃውም መልሶ “እኔ ይህን የዜግነት መብት የገዛሁት ብዙ ገንዘብ አውጥቼ ነው” አለው። ጳውሎስ ደግሞ “እኔ ግን በመወለድ አገኘሁት” አለ።
ስለዚህ እያሠቃዩ ሊመረምሩት የነበሩት ሰዎች ወዲያውኑ ከእሱ ራቁ፤ የሠራዊቱ ሻለቃም በሰንሰለት አስሮት ስለነበር ሮማዊ መሆኑን ሲገነዘብ ፈራ።
በመሆኑም በማግስቱ አይሁዳውያን የከሰሱት ለምን እንደሆነ በትክክል ማወቅ ስለፈለገ ፈታውና የካህናት አለቆቹ እንዲሁም መላው የሳንሄድሪን ሸንጎ እንዲሰበሰቡ አዘዘ። ከዚያም ጳውሎስን አውርዶ በመካከላቸው አቆመው።
አንዳንድ ሰዎች ከይሁዳ ወደ አንጾኪያ ወርደው “በሙሴ ሥርዓት መሠረት ካልተገረዛችሁ በቀር ልትድኑ አትችሉም” እያሉ ወንድሞችን ያስተምሩ ጀመር።
በዚህ የተነሳ ጳውሎስና በርናባስ ከሰዎቹ ጋር የጦፈ ክርክርና ጭቅጭቅ ውስጥ ገቡ። በመሆኑም ጳውሎስና በርናባስ እንዲሁም አንዳንድ ወንድሞች ወደ ኢየሩሳሌም ወጥተው ጉዳዩን በዚያ ለሚገኙት ሐዋርያትና ሽማግሌዎች እንዲያቀርቡ ተወሰነ።
በዚህም መሠረት ጉባኤው የተወሰነ መንገድ ከሸኛቸው በኋላ በፊንቄና በሰማርያ በኩል በማለፍ ከአሕዛብ ወገን የሆኑ ሰዎች ተለውጠው አምላክን ማምለክ እንደጀመሩ በዝርዝር ተናገሩ፤ ወንድሞችንም ሁሉ እጅግ ደስ አሰኟቸው።
ኢየሩሳሌም ሲደርሱም በዚያ የሚገኘው ጉባኤ እንዲሁም ሐዋርያትና ሽማግሌዎች ጥሩ አቀባበል አደረጉላቸው፤ የተላኩትም ወንድሞች አምላክ በእነሱ አማካኝነት ያከናወናቸውን በርካታ ነገሮች ተረኩላቸው።
ይሁንና ከፈሪሳውያን ሃይማኖታዊ ቡድን መካከል አማኞች የሆኑ አንዳንድ ሰዎች ከመቀመጫቸው ተነስተው “እነዚህን ሰዎች መግረዝና የሙሴን ሕግ እንዲጠብቁ ማዘዝ አስፈላጊ ነው” ሲሉ ተናገሩ።
ሐዋርያትና ሽማግሌዎችም ይህን ጉዳይ ለመመርመር ተሰበሰቡ።
ከብዙ ክርክር በኋላ ጴጥሮስ ተነስቶ እንዲህ አላቸው፦ “ወንድሞች፣ አሕዛብ የምሥራቹን ቃል ከእኔ አፍ ሰምተው እንዲያምኑ አምላክ ገና ከመጀመሪያው ከእናንተ መካከል እኔን እንደመረጠኝ በሚገባ ታውቃላችሁ።
ልብን የሚያውቀው አምላክ ለእኛ እንዳደረገው ሁሉ ለእነሱም መንፈስ ቅዱስን በመስጠት መሠከረላቸው።
ደግሞም በእኛና በእነሱ መካከል ምንም ልዩነት አላደረገም፤ ከዚህ ይልቅ በእምነታቸው የተነሳ ልባቸውን አነጻ።
ታዲያ አባቶቻችንም ሆኑ እኛ ልንሸከመው ያልቻልነውን ቀንበር በደቀ መዛሙርቱ ጫንቃ ላይ በመጫን አሁን አምላክን ለምን ትፈታተናላችሁ?
በአንጻሩ ግን እኛ የምንድነው በጌታ ኢየሱስ ጸጋ አማካኝነት እንደሆነ እናምናለን፤ እነሱም ቢሆኑ ይህንኑ ያምናሉ።”
በዚህ ጊዜ የተሰበሰበው ሰው ሁሉ ጸጥ አለ፤ በርናባስና ጳውሎስ፣ አምላክ በእነሱ አማካኝነት በአሕዛብ መካከል ያከናወናቸውን በርካታ ተአምራዊ ምልክቶችና ድንቅ ነገሮች ሲናገሩም ያዳምጥ ጀመር።
እነሱ ተናግረው ካበቁ በኋላ ያዕቆብ እንዲህ ሲል መለሰ፦ “ወንድሞች፣ ስሙኝ።
አምላክ ከአሕዛብ መካከል ለስሙ የሚሆኑ ሰዎችን ለመውሰድ ለመጀመሪያ ጊዜ እንዴት ለእነሱ ትኩረት እንደሰጠ ሲምዖን በሚገባ ተርኳል።
እንዲህ ተብሎ የተጻፈው የነቢያት ቃልም ከዚህ ጋር ይስማማል፦
‘ከዚህ በኋላ ተመልሼ የፈረሰውን የዳዊትን ድንኳን ዳግመኛ አቆማለሁ፤ ፍርስራሹንም አድሼ ዳግም እገነባዋለሁ፤
ይህን የማደርገው የቀሩት ሰዎች፣ ከብሔራት ከመጡት በስሜ የተጠሩ ሰዎች ጋር አንድ ላይ ሆነው ይሖዋን ከልብ እንዲፈልጉ ነው በማለት እነዚህን ነገሮች የሚያደርገው ይሖዋ ተናግሯል፤
እነዚህም ነገሮች ከጥንት ዘመን ጀምሮ ይታወቃሉ።’
ስለዚህ እንደ እኔ ሐሳብ ከሆነ፣ ተለውጠው አምላክን ማምለክ የጀመሩትን አሕዛብ ባናስቸግራቸው ይሻላል፤
ከዚህ ይልቅ በጣዖት ከረከሱ ነገሮች፣ ከፆታ ብልግና፣ ታንቆ ከሞተ እንስሳ ሥጋ እንዲሁም ከደም እንዲርቁ እንጻፍላቸው።
ምክንያቱም ከጥንት ዘመን ጀምሮ በየከተማው በሰንበት ቀናት ሁሉ በምኩራቦች ውስጥ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ከሙሴ መጻሕፍት በማንበብ በውስጡ የሰፈረውን ቃል የሚሰብኩ ሰዎች ነበሩ።”
ከዚያም ሐዋርያትና ሽማግሌዎች ከመላው ጉባኤ ጋር ሆነው ከመካከላቸው የተመረጡ ሰዎችን ከጳውሎስና ከበርናባስ ጋር ወደ አንጾኪያ ለመላክ ወሰኑ፤ በወንድሞች መካከል ግንባር ቀደም የሆኑትን በርስያን የሚባለውን ይሁዳንና ሲላስን ላኩ።
ደግሞም የሚከተለውን ደብዳቤ ጽፈው በእነሱ እጅ ላኩላቸው፦ “ከወንድሞቻችሁ ከሐዋርያትና ከሽማግሌዎች፣ በአንጾኪያ፣ በሶርያና በኪልቅያ ለምትኖሩ ከአሕዛብ ወገን ለሆናችሁ ወንድሞች፤ ሰላምታችን ይድረሳችሁ!
ከእኛ መካከል አንዳንዶች ወጥተው እኛ ምንም ሳናዛቸው በሚናገሩት ነገር እንዳስቸገሯችሁና ሊያውኳችሁ እንደሞከሩ ስለሰማን
ሰዎች መርጠን ከተወደዱት ወንድሞቻችን ከበርናባስና ከጳውሎስ ጋር ወደ እናንተ ለመላክ በአንድ ልብ ወሰንን፤
በርናባስና ጳውሎስ ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ ስም ሕይወታቸውን አሳልፈው የሰጡ ናቸው።
ስለዚህ ይህንኑ ነገር በቃልም እንዲነግሯችሁ ይሁዳንና ሲላስን ልከናል።
ከሚከተሉት አስፈላጊ ነገሮች በስተቀር፣ ሌላ ተጨማሪ ሸክም እንዳንጭንባችሁ መንፈስ ቅዱስና እኛ ወስነናል፦
ለጣዖት ከተሠዉ ነገሮች፣ ከደም፣ ታንቆ ከሞተ እንስሳ ሥጋና ከፆታ ብልግና ራቁ። ከእነዚህ ነገሮች ሙሉ በሙሉ ከራቃችሁ መልካም ይሆንላችኋል። ጤና ይስጣችሁ!”
የተላኩትም ሰዎች ከተሰናበቱ በኋላ ወደ አንጾኪያ ወረዱ፤ እዚያ የሚገኙትንም ደቀ መዛሙርት በአንድነት ሰብስበው ደብዳቤውን ሰጧቸው።
እነሱም ካነበቡት በኋላ ባገኙት ማበረታቻ እጅግ ተደሰቱ።
ይሁዳና ሲላስም ራሳቸው ነቢያት ስለነበሩ ብዙ ቃል በመናገር ወንድሞችን አበረታቷቸው፤ እንዲሁም አጠናከሯቸው።
በዚያም የተወሰነ ጊዜ ከቆዩ በኋላ ወደላኳቸው ሰዎች እንዲመለሱ ወንድሞች በሰላም አሰናበቷቸው።
ይሁን እንጂ ጳውሎስና በርናባስ እያስተማሩና ከሌሎች ብዙ ሰዎች ጋር ሆነው ምሥራቹን ይኸውም የይሖዋን ቃል እየሰበኩ በአንጾኪያ ቆዩ።
ከተወሰኑ ቀናት በኋላ ጳውሎስ በርናባስን “የይሖዋን ቃል ባወጅንባቸው ከተሞች ሁሉ ያሉት ወንድሞች በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ለማወቅ ተመልሰን እንጠይቃቸው” አለው።
በርናባስ፣ ማርቆስ ተብሎ የሚጠራው ዮሐንስ አብሯቸው እንዲሄድ ወስኖ ነበር።
ጳውሎስ ግን ማርቆስ በጵንፍልያ ተለይቷቸው ስለነበረና ያከናውኑት ወደነበረው ሥራ ከእነሱ ጋር ስላልሄደ አሁን አብሯቸው እንዲሄድ አልፈለገም።
በዚህ ምክንያት በመካከላቸው ኃይለኛ ጭቅጭቅ ስለተፈጠረ ተለያዩ፤ ስለዚህ በርናባስ ማርቆስን ይዞ በመርከብ ወደ ቆጵሮስ ሄደ።
ጳውሎስ ደግሞ ሲላስን መረጠ፤ ወንድሞችም ለይሖዋ ጸጋ በአደራ ከሰጡት በኋላ ከዚያ ተነስቶ ሄደ።
ጉባኤዎችንም እያበረታታ በሶርያና በኪልቅያ በኩል አለፈ።
ጴጥሮስና ዮሐንስ ለሕዝቡ እየተናገሩ ሳሉ ካህናቱ፣ የቤተ መቅደሱ ሹምና ሰዱቃውያን ድንገት ወደ እነሱ መጡ።
እነሱም ሐዋርያቱ ሕዝቡን እያስተማሩና ኢየሱስ ከሞት እንደተነሳ በግልጽ እየተናገሩ ስለነበር እጅግ ተቆጡ።
በመሆኑም ያዟቸው፤ መሽቶም ስለነበር እስከ ማግስቱ ድረስ እስር ቤት አቆዩአቸው።
ይሁን እንጂ ንግግሩን ሰምተው ከነበሩት መካከል ብዙዎቹ አመኑ፤ የወንዶቹም ቁጥር 5,000 ገደማ ሆነ።
በማግስቱም የሕዝቡ ገዢዎች፣ ሽማግሌዎችና ጸሐፍት በኢየሩሳሌም ተሰበሰቡ፤
የካህናት አለቃው ሐና፣ ቀያፋ፣ ዮሐንስ፣ እስክንድርና የካህናት አለቃው ዘመዶችም ሁሉ ከእነሱ ጋር ነበሩ።
ጴጥሮስንና ዮሐንስን በመካከላቸው አቁመው “ይህን ያደረጋችሁት በምን ሥልጣን ወይም በማን ስም ነው?” ብለው ጠየቋቸው።
በዚህ ጊዜ ጴጥሮስ በመንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ እንዲህ አላቸው፦ “እናንተ የሕዝቡ ገዢዎችና ሽማግሌዎች፣
ዛሬ በእኛ ላይ ምርመራ እየተካሄደ ያለው ለአንድ ሽባ ሰው በተደረገ መልካም ሥራ የተነሳ ከሆነና ይህን ሰው ያዳነው ማን እንደሆነ ማወቅ የምትፈልጉ ከሆነ፣
ይህ ሰው ጤናማ ሆኖ እዚህ ፊታችሁ የቆመው፣ እናንተ በእንጨት ላይ በሰቀላችሁት ሆኖም አምላክ ከሞት ባስነሳው በናዝሬቱ ኢየሱስ ክርስቶስ ስም፣ ይኸውም በኢየሱስ አማካኝነት እንደሆነ እናንተም ሆናችሁ መላው የእስራኤል ሕዝብ ይወቅ።
‘እናንተ ግንበኞች የናቃችሁት፣ የማዕዘን ራስ የሆነው ድንጋይ’ እሱ ነው።
ደግሞም መዳን በሌላ በማንም አይገኝም፤ ምክንያቱም ልንድንበት የምንችል ከሰማይ በታች ለሰዎች የተሰጠ ሌላ ስም የለም።”
ሰዎቹ ጴጥሮስና ዮሐንስ በድፍረት ሲናገሩ ባዩአቸው ጊዜ ያልተማሩና ተራ ሰዎች መሆናቸውን ተረድተው ተደነቁ። ከኢየሱስ ጋር እንደነበሩም ተገነዘቡ።
የተፈወሰውንም ሰው ከእነሱ ጋር ቆሞ ሲያዩት ምንም መልስ መስጠት አልቻሉም።
ስለዚህ ከሳንሄድሪን ሸንጎ አዳራሽ እንዲወጡ አዘዟቸው፤ ከዚያም እርስ በርሳቸው ይማከሩ ጀመር፤
እንዲህም ተባባሉ፦ “እነዚህን ሰዎች ምን ብናደርጋቸው ይሻላል? ምክንያቱም በኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ሁሉ ዘንድ የታወቀ አስደናቂ ነገር እንደፈጸሙ የማይታበል ሐቅ ነው፤ ይህን ደግሞ ልንክድ አንችልም።
ይሁንና ይህ ነገር በሕዝቡ መካከል ይበልጥ እንዳይስፋፋ ከዚህ በኋላ በዚህ ስም ለማንም ሰው እንዳይናገሩ በማሳሰብ እናስፈራራቸው።”
ከዚያም ጠርተዋቸው በኢየሱስ ስም ፈጽሞ እንዳይናገሩ ወይም እንዳያስተምሩ አዘዟቸው።
ጴጥሮስና ዮሐንስ ግን መልሰው እንዲህ አሏቸው፦ “አምላክን ከመስማት ይልቅ እናንተን መስማት በአምላክ ፊት ተገቢ እንደሆነና እንዳልሆነ እስቲ እናንተው ፍረዱ።
እኛ ግን ስላየነውና ስለሰማነው ነገር ከመናገር ወደኋላ ማለት አንችልም።”
በመሆኑም እንደገና ካስፈራሯቸው በኋላ ለቀቋቸው፤ ይህን ያደረጉት እነሱን ለመቅጣት የሚያስችል ምንም ተጨባጭ ነገር ስላላገኙና ሕዝቡን ስለፈሩ ነው፤ ምክንያቱም ሕዝቡ ሁሉ በተፈጸመው ሁኔታ አምላክን እያከበረ ነበር።
በዚህ ተአምር የተፈወሰውም ሰው ዕድሜው ከ40 ዓመት በላይ ነበር።
ከተለቀቁ በኋላ ወደ ወንድሞቻቸው ሄደው የካህናት አለቆቹና ሽማግሌዎቹ ያሏቸውን ሁሉ ነገሯቸው።
እነሱም ይህን በሰሙ ጊዜ በአንድ ልብ ሆነው ድምፃቸውን ከፍ በማድረግ እንዲህ ሲሉ ወደ አምላክ ጸለዩ፦ “ሉዓላዊው ጌታ ሆይ፣ ሰማይን፣ ምድርን፣ ባሕርንና በውስጣቸው ያሉትን ነገሮች ሁሉ የፈጠርክ አንተ ነህ፤
በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት በአገልጋይህ በአባታችን በዳዊት አፍ እንዲህ ብለሃል፦ ‘ብሔራት ለምን ታወኩ? ሕዝቦችስ ለምን ከንቱ ነገር ያውጠነጥናሉ?
የምድር ነገሥታት ተሰለፉ፤ ገዢዎችም በአንድነት ተሰብስበው በይሖዋና እሱ በቀባው ላይ ተነሱ።’
በእርግጥም ሄሮድስና ጳንጥዮስ ጲላጦስ ከአሕዛብና ከእስራኤል ሕዝብ ጋር በዚህች ከተማ ተሰብስበው አንተ በቀባኸው በቅዱስ አገልጋይህ በኢየሱስ ላይ ተነሱ፤
ይህም የሆነው እጅህና ፈቃድህ አስቀድመው የወሰኑት እንዲፈጸም ነው።
አሁንም ይሖዋ ሆይ፣ ዛቻቸውን ተመልከት፤ ባሪያዎችህም ቃልህን በፍጹም ድፍረት መናገራቸውን እንዲቀጥሉ እርዳቸው፤
ለመፈወስም የዘረጋኸውን እጅህን አትጠፍ፤ በቅዱስ አገልጋይህ በኢየሱስ ስም ተአምራዊ ምልክቶችና ድንቅ ነገሮች ማድረግህንም ቀጥል።”
ምልጃ ካቀረቡም በኋላ ተሰብስበውበት የነበረው ቦታ ተናወጠ፤ ሁሉም በመንፈስ ቅዱስ ተሞልተው የአምላክን ቃል በድፍረት መናገር ጀመሩ።
በተጨማሪም ከፍተኛ ቁጥር የነበራቸው ያመኑት ሰዎች አንድ ልብና ነፍስ ነበራቸው፤ አንዳቸውም ቢሆኑ ያላቸው ማንኛውም ንብረት የግላቸው እንደሆነ አድርገው አይቆጥሩም ነበር፤ ከዚህ ይልቅ ያላቸው ነገር ሁሉ የጋራ ነበር።
ደግሞም ሐዋርያቱ ስለ ጌታ ኢየሱስ ትንሣኤ በታላቅ ኃይል መመሥከራቸውን ቀጠሉ፤ ሁሉም የአምላክን ታላቅ ጸጋ አግኝተው ነበር።
ከመካከላቸውም አንድም ችግረኛ አልነበረም፤ ምክንያቱም መሬት ወይም ቤት የነበራቸው ሁሉ እየሸጡ ገንዘቡን በማምጣት
ለሐዋርያት ያስረክቡ ነበር። ከዚያም ለእያንዳንዱ ሰው በሚያስፈልገው መጠን ይከፋፈል ነበር።
የቆጵሮስ ተወላጅ የሆነ ዮሴፍ የሚባል አንድ ሌዋዊ ነበር፤ ሐዋርያት በርናባስ ብለውም ይጠሩት የነበረ ሲሆን ትርጉሙም “የመጽናናት ልጅ” ማለት ነው፤
እሱም መሬት ስለነበረው መሬቱን ሸጦ ገንዘቡን በማምጣት ለሐዋርያት አስረከበ።
ሁከቱ ሲበርድ ጳውሎስ ደቀ መዛሙርቱን አስጠራቸው፤ ካበረታታቸውና ከተሰናበታቸው በኋላ ወደ መቄዶንያ ጉዞ ጀመረ።