text
stringlengths
4
267
ወርቅ ወይም ብር አሊያም መዳብ በመቀነታችሁ አትያዙ፤
ወይም ለጉዞ የምግብ ከረጢት ወይም ሁለት ልብስ ወይም ትርፍ ጫማ ወይም በትር አትያዙ፤ ለሠራተኛ ምግቡ ይገባዋልና።
“በምትገቡበት ማንኛውም ከተማ ወይም መንደር መልእክቱን መስማት የሚገባውን ሰው ፈልጉ፤ እስክትወጡም ድረስ እዚያው ቆዩ።
ወደ ቤትም ስትገቡ ቤተሰቡን ሰላም በሉ።
ቤቱ የሚገባው ሆኖ ከተገኘ ሰላማችሁ ይድረሰው፤ የማይገባው ከሆነ ግን ሰላማችሁ ወደ እናንተ ይመለስ።
የሚቀበላችሁ ወይም ቃላችሁን የሚሰማ ሰው ካጣችሁ ከዚያ ቤት ወይም ከተማ ስትወጡ፣ የእግራችሁን አቧራ አራግፉ።
እውነት እላችኋለሁ፣ በፍርድ ቀን ከዚያች ከተማ ይልቅ ለሰዶምና ለገሞራ ይቀልላቸዋል።
“እነሆ፣ በተኩላዎች መካከል እንዳሉ በጎች እልካችኋለሁ፤ ስለዚህ እንደ እባብ ጠንቃቆች፣ እንደ ርግብ የዋሆች ሁኑ።
ሰዎች ለፍርድ ሸንጎ አሳልፈው ይሰጧችኋል፤ በምኩራቦቻቸውም ይገርፏችኋል፤ ስለዚህ ራሳችሁን ከእነሱ ጠብቁ።
ደግሞም በእኔ ምክንያት በገዢዎችና በነገሥታት ፊት ያቀርቧችኋል፤ በዚያ ጊዜ ለእነሱም ሆነ ለአሕዛብ መመሥከር ትችላላችሁ።
ይሁን እንጂ አሳልፈው ሲሰጧችሁ እንዴት ወይም ምን ብለን እንመልሳለን? ብላችሁ አትጨነቁ፤ የምትናገሩት ነገር በዚያኑ ሰዓት ይሰጣችኋልና፤
በምትናገሩበት ጊዜ ብቻችሁን አይደላችሁም፤ ይልቁንም በእናንተ የሚናገረው የአባታችሁ መንፈስ ነው።
በተጨማሪም ወንድም ወንድሙን፣ አባትም ልጁን ለሞት አሳልፎ ይሰጣል፤ ልጆችም በወላጆቻቸው ላይ ይነሳሉ፤ ደግሞም ያስገድሏቸዋል።
በስሜ የተነሳም ሰዎች ሁሉ ይጠሏችኋል፤ እስከ መጨረሻው የጸና ግን ይድናል።
በአንድ ከተማ ስደት ሲያደርሱባችሁ ወደ ሌላ ከተማ ሽሹ፤ እውነት እላችኋለሁ፣ የሰው ልጅ እስከሚመጣ ድረስ የእስራኤልን ከተሞችና መንደሮች ፈጽሞ አታዳርሱም።
“ተማሪ ከአስተማሪው፣ ባሪያም ከጌታው አይበልጥም።
ተማሪ እንደ አስተማሪው፣ ባሪያም እንደ ጌታው ከሆነ በቂ ነው። ሰዎች የቤቱን ጌታ ብዔልዜቡል ካሉት ቤተሰቦቹንማ እንዴት ከዚህ የከፋ አይሏቸው!
ስለዚህ አትፍሯቸው፤ የተሸፈነ ሁሉ መገለጡ፣ ሚስጥር የሆነም ሁሉ መታወቁ አይቀርም።
በጨለማ የነገርኳችሁን በብርሃን ተናገሩ፤ በሹክሹክታ የሰማችሁትንም በይፋ ስበኩ።
ሥጋን የሚገድሉትን ነፍስን ግን መግደል የማይችሉትን አትፍሩ፤ ከዚህ ይልቅ ነፍስንም ሆነ ሥጋን በገሃነም ሊያጠፋ የሚችለውን ፍሩ።
ሁለት ድንቢጦች የሚሸጡት አነስተኛ ዋጋ ባላት ሳንቲም አይደለም? ሆኖም ከእነሱ አንዷም እንኳ አባታችሁ ሳያውቅ መሬት ላይ አትወድቅም።
የራሳችሁ ፀጉር እንኳ አንድ ሳይቀር ተቆጥሯል።
ስለዚህ አትፍሩ፤ እናንተ ከብዙ ድንቢጦች የላቀ ዋጋ አላችሁ።
“እንግዲያው በሰዎች ፊት ለሚመሠክርልኝ ሁሉ እኔም በሰማያት ባለው አባቴ ፊት እመሠክርለታለሁ።
በሰዎች ፊት የሚክደኝን ሁሉ ግን እኔም በሰማያት ባለው አባቴ ፊት እክደዋለሁ።
በምድር ላይ ሰላም ለማስፈን የመጣሁ አይምሰላችሁ፤ የመጣሁት ሰይፍን እንጂ ሰላምን ለማምጣት አይደለም።
እኔ የመጣሁት ወንድ ልጅን ከአባቱ፣ ሴት ልጅን ከእናቷ እንዲሁም ምራትን ከአማቷ ለመለያየት ነው።
በእርግጥም የሰው ጠላቶቹ የገዛ ቤተሰቦቹ ይሆናሉ።
ከእኔ ይልቅ አባቱን ወይም እናቱን የሚወድ ሁሉ ለእኔ ሊሆን አይገባም፤ ከእኔ ይልቅ ወንድ ልጁን ወይም ሴት ልጁን የሚወድ ሁሉ ለእኔ ሊሆን አይገባም።
የመከራውን እንጨት የማይቀበልና የማይከተለኝ ሁሉ ለእኔ ሊሆን አይገባውም።
ነፍሱን ለማዳን የሚሞክር ሁሉ ያጣታል፤ ነፍሱን ስለ እኔ አሳልፎ የሚሰጥ ሁሉ ግን ያገኛታል።
“እናንተን የሚቀበል ሁሉ እኔን ይቀበላል፤ እኔን የሚቀበል ሁሉ ደግሞ የላከኝን ይቀበላል።
ነቢይን ስለ ነቢይነቱ የሚቀበል ሁሉ የነቢይን ዋጋ ያገኛል፤ ጻድቅን ስለ ጻድቅነቱ የሚቀበል ሁሉ የጻድቅን ዋጋ ያገኛል።
እውነት እላችኋለሁ፣ የእኔ ደቀ መዝሙር በመሆኑ ምክንያት ከእነዚህ ከትናንሾቹ ለአንዱ አንድ ብርጭቆ ቀዝቃዛ ውኃ የሚሰጥ ሁሉ በምንም ዓይነት ዋጋውን አያጣም።”
ከዚያም ፈሪሳውያንና ሰዱቃውያን ወደ እሱ መጡ፤ ሊፈትኑትም ፈልገው ከሰማይ ምልክት እንዲያሳያቸው ጠየቁት።
እሱም መልሶ እንዲህ አላቸው፦ “ሲመሽ ‘ሰማዩ ስለ ቀላ ብራ ይሆናል’ ትላላችሁ፤
ጠዋት ላይ ደግሞ ‘ሰማዩ ቢቀላም ደመና ስለሆነ ዛሬ ብርድ ይሆናል፣ ዝናብም ይዘንባል’ ትላላችሁ። የሰማዩን መልክ በማየት መተርጎም ትችላላችሁ፤ የዘመኑን ምልክት ግን መተርጎም አትችሉም።
ክፉና አመንዝራ ትውልድ ሁልጊዜ ምልክት ማየት ይፈልጋል፤ ሆኖም ከዮናስ ምልክት በስተቀር ምንም ምልክት አይሰጠውም።” ይህን ከተናገረ በኋላ ትቷቸው ሄደ።
ደቀ መዛሙርቱ ወደ ባሕሩ ማዶ ተሻገሩ፤ በዚህ ጊዜ ዳቦ መያዝ ረስተው ነበር።
ኢየሱስ “ተጠንቀቁ፣ ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን እርሾ ተጠበቁ” አላቸው።
እነሱም እርስ በርሳቸው “ዳቦ ስላልያዝን ይሆናል” ይባባሉ ጀመር።
ኢየሱስም ይህን አውቆ እንዲህ አላቸው፦ “እናንተ እምነት የጎደላችሁ! ዳቦ ስላልያዝን ነው ብላችሁ ለምን እርስ በርሳችሁ ትነጋገራላችሁ?
አሁንም ነጥቡ አልገባችሁም? ወይስ አምስቱ ዳቦ ለ5,000ዎቹ ሰዎች በቅቶ ከዚያ የተረፈውን ምን ያህል ቅርጫት እንደሰበሰባችሁ አታስታውሱም?
ወይስ ሰባቱ ዳቦ ለ4,000ዎቹ ሰዎች በቅቶ ከዚያ የተረፈውን በትላልቅ ቅርጫት ምን ያህል እንደሰበሰባችሁ ትዝ አይላችሁም?
ታዲያ የነገርኳችሁ ስለ ዳቦ እንዳልሆነ እንዴት አታስተውሉም? እንግዲህ ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን እርሾ ተጠንቀቁ።”
በዚህ ጊዜ ተጠንቀቁ ያላቸው ከዳቦ እርሾ ሳይሆን ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን ትምህርት እንደሆነ ገባቸው።
ኢየሱስ ወደ ቂሳርያ ፊልጵስዩስ አካባቢ በመጣ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱን “ሰዎች፣ የሰውን ልጅ ማን ነው ይሉታል?” ሲል ጠየቃቸው።
እነሱም “አንዳንዶች መጥምቁ ዮሐንስ፣ ሌሎች ኤልያስ፣ ሌሎች ደግሞ ኤርምያስ ወይም ከነቢያት አንዱ ነው ይላሉ” አሉት።
እሱም “እናንተስ ስለ እኔ ማንነት ምን ትላላችሁ?” አላቸው።
ስምዖን ጴጥሮስም “አንተ ክርስቶስ፣ የሕያው አምላክ ልጅ ነህ” ብሎ መለሰለት።
ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለው፦ “የዮናስ ልጅ ስምዖን፣ ይህን የገለጠልህ ሥጋና ደም ሳይሆን በሰማያት ያለው አባቴ ስለሆነ ደስ ይበልህ።
ደግሞም እልሃለሁ፦ አንተ ጴጥሮስ ነህ፤ በዚህች ዓለት ላይ ጉባኤዬን እገነባለሁ፤ የመቃብር በሮችም አያሸንፏትም።
የመንግሥተ ሰማያትን ቁልፎች እሰጥሃለሁ፤ በምድር የምታስረው ሁሉ ቀድሞውኑ በሰማያት የታሰረ ይሆናል፤ እንዲሁም በምድር የምትፈታው ሁሉ ቀድሞውኑ በሰማያት የተፈታ ይሆናል።”
ከዚያም ደቀ መዛሙርቱን እሱ ክርስቶስ መሆኑን ለማንም እንዳይናገሩ አጥብቆ አዘዛቸው።
ከዚያን ጊዜ አንስቶ፣ ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም መሄድ እንዳለበት እንዲሁም በሽማግሌዎች፣ በካህናት አለቆችና በጸሐፍት እጅ ከባድ መከራ ይቀበልና ይገደል ዘንድ እንደሚገባው ብሎም በሦስተኛው ቀን እንደሚነሳ ለደቀ መዛሙርቱ ይገልጽላቸው ጀመር።
በዚህ ጊዜ ጴጥሮስ ኢየሱስን ለብቻው በመውሰድ “ጌታ ሆይ፣ በራስህ ላይ እንዲህ አትጨክን፤ በምንም ዓይነት እንዲህ ያለ ነገር አይደርስብህም” እያለ ይገሥጸው ጀመር።
እሱ ግን ጀርባውን በመስጠት ጴጥሮስን “ወደ ኋላዬ ሂድ፣ ሰይጣን! የሰውን እንጂ የአምላክን ሐሳብ ስለማታስብ እንቅፋት ሆነህብኛል” አለው።
ከዚያም ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን እንዲህ አላቸው፦ “ሊከተለኝ የሚፈልግ ማንም ቢኖር ራሱን ይካድ፤ የራሱን የመከራ እንጨት ይሸከም፤ ያለማቋረጥም ይከተለኝ።
ሕይወቱን ማዳን የሚፈልግ ሁሉ ያጣታልና፤ ለእኔ ሲል ሕይወቱን የሚያጣ ሁሉ ግን ያገኛታል።
ደግሞስ አንድ ሰው ዓለምን ሁሉ የራሱ ቢያደርግ፣ ሕይወቱን ግን ቢያጣ ምን ይጠቅመዋል? ወይስ ሰው ለሕይወቱ ምትክ የሚሆን ምን ነገር ሊሰጥ ይችላል?
የሰው ልጅ ከመላእክቱ ጋር በአባቱ ክብር ይመጣልና፤ ከዚያም ለእያንዳንዱ እንደ ምግባሩ ይከፍለዋል።
እውነት እላችኋለሁ፣ እዚህ ከቆሙት መካከል አንዳንዶች የሰው ልጅ በመንግሥቱ ሲመጣ እስኪያዩ ድረስ ፈጽሞ ሞትን አይቀምሱም።”
ሕዝቡንም ባየ ጊዜ ወደ ተራራ ወጣ፤ በዚያ ከተቀመጠ በኋላም ደቀ መዛሙርቱ ወደ እሱ መጡ።
ከዚያም ኢየሱስ መናገር ጀመረ፤ እንዲህም ሲል አስተማራቸው፦
“መንፈሳዊ ነገሮችን የተጠሙ ደስተኞች ናቸው፤ መንግሥተ ሰማያት የእነሱ ነውና።
“የሚያዝኑ ደስተኞች ናቸው፤ መጽናኛ ያገኛሉና።
“ገሮች ደስተኞች ናቸው፤ ምድርን ይወርሳሉና።
“ጽድቅን የሚራቡና የሚጠሙ ደስተኞች ናቸው፤ ይጠግባሉና።
“መሐሪዎች ደስተኞች ናቸው፤ ምሕረት ይደረግላቸዋልና።
“ልባቸው ንጹሕ የሆነ ደስተኞች ናቸው፤ አምላክን ያያሉና።
“ሰላም ፈጣሪዎች ደስተኞች ናቸው፤ የአምላክ ልጆች ይባላሉና።
“ለጽድቅ ሲሉ ስደት የሚደርስባቸው ደስተኞች ናቸው፤ መንግሥተ ሰማያት የእነሱ ነውና።
“በእኔ ምክንያት ሰዎች ሲነቅፏችሁ፣ ስደት ሲያደርሱባችሁና ክፉውን ሁሉ በውሸት ሲያስወሩባችሁ ደስተኞች ናችሁ።
በሰማያት የሚጠብቃችሁ ሽልማት ታላቅ ስለሆነ ሐሴት አድርጉ፤ በደስታም ፈንጥዙ፤ ከእናንተ በፊት የነበሩትን ነቢያት እንደዚሁ ስደት አድርሰውባቸው ነበርና።
“እናንተ የምድር ጨው ናችሁ፤ ሆኖም ጨው የጨውነት ጣዕሙን ቢያጣ ጨውነቱን እንዴት መልሶ ሊያገኝ ይችላል? ከዚህ በኋላ ወደ ውጭ ተጥሎ በሰው ከመረገጥ በቀር ለምንም ነገር አያገለግልም።
“እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ። በተራራ ላይ ያለች ከተማ ልትሰወር አትችልም።
ሰዎች መብራት አብርተው እንቅብ አይደፉበትም፤ ከዚህ ይልቅ በመቅረዝ ላይ ያስቀምጡታል፤ በቤት ውስጥ ላሉትም ሁሉ ያበራል።
በተመሳሳይም ሰዎች መልካም ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ በሰው ፊት ይብራ።
“ሕጉን ወይም የነቢያትን ቃል ልሽር እንደመጣሁ አድርጋችሁ አታስቡ። ልፈጽም እንጂ ልሽር አልመጣሁም።
እውነት እላችኋለሁ፣ ሰማይና ምድር ቢያልፉ እንኳ እነዚህ ሁሉ ነገሮች እስኪከናወኑ ድረስ ከሕጉ አነስተኛዋ ፊደል ወይም የአንዷ ፊደል ጭረት ሳትፈጸም አትቀርም።
በመሆኑም አነስተኛ ከሆኑት ከእነዚህ ትእዛዛት አንዷን የሚጥስና ሌሎች ሰዎችም እንዲህ እንዲያደርጉ የሚያስተምር ሰው ሁሉ በመንግሥተ ሰማያት ታናሽ ይባላል። እነዚህን ትእዛዛት የሚያከብርና የሚያስተምር ሰው ግን በመንግሥተ ሰማያት ታላቅ ይባላል።
ጽድቃችሁ ከጸሐፍትና ከፈሪሳውያን ጽድቅ ካልበለጠ በምንም ዓይነት ወደ መንግሥተ ሰማያት እንደማትገቡ ልነግራችሁ እወዳለሁ።
“በጥንት ዘመን ለነበሩት ‘አትግደል፤ ሰው የገደለ ሁሉ ግን በፍርድ ቤት ይጠየቃል’ እንደተባለ ሰምታችኋል።
እኔ ግን እላችኋለሁ፣ በወንድሙ ላይ ተቆጥቶ ቁጣው የማይበርድለት ሁሉ በፍርድ ቤት ይጠየቃል፤ ወንድሙንም ጸያፍ በሆነ ቃል የሚያጥላላ ሁሉ በከፍተኛ ፍርድ ቤት ይጠየቃል፤ ‘አንተ የማትረባ ጅል’ የሚለው ደግሞ ለእሳታማ ገሃነም ሊዳረግ ይችላል።
“እንግዲያው መባህን ወደ መሠዊያው ባመጣህ ጊዜ ወንድምህ በአንተ ቅር የተሰኘበት ነገር እንዳለ ትዝ ካለህ
መባህን በመሠዊያው ፊት ትተህ ሂድ። በመጀመሪያ ከወንድምህ ጋር ታረቅ፤ ከዚያም ተመልሰህ መባህን አቅርብ።
“ክስ ከመሠረተብህ ባላጋራ ጋር ወደ ፍርድ ቤት እየሄዳችሁ ሳለ ፈጥነህ ታረቅ፤ አለዚያ ባላጋራህ ለዳኛው፣ ዳኛው ደግሞ ለፍርድ ቤቱ ዘብ አሳልፎ ይሰጥህና እስር ቤት ልትገባ ትችላለህ።
እውነት እልሃለሁ፣ የመጨረሻዋን ሳንቲምህን ከፍለህ እስክትጨርስ ድረስ ፈጽሞ ከዚያ አትወጣም።
“‘አታመንዝር’ እንደተባለ ሰምታችኋል።
እኔ ግን እላችኋለሁ፣ አንዲትን ሴት በፍትወት ስሜት የሚመለከት ሁሉ በዚያን ጊዜ በልቡ ከእሷ ጋር አመንዝሯል።
ስለዚህ ቀኝ ዓይንህ ቢያሰናክልህ አውጥተህ ጣለው። መላ ሰውነትህ ወደ ገሃነም ከሚወረወር ከሰውነትህ ክፍሎች አንዱን ብታጣ ይሻልሃል።
እንዲሁም ቀኝ እጅህ ቢያሰናክልህ ቆርጠህ ጣለው። መላ ሰውነትህ ወደ ገሃነም ከሚጣል ከሰውነትህ ክፍሎች አንዱን ብታጣ ይሻልሃል።
“በተጨማሪም ‘ሚስቱን የሚፈታ ሁሉ የፍቺ የምሥክር ወረቀት ይስጣት’ ተብሏል።
እኔ ግን እላችኋለሁ፣ በፆታ ብልግና ምክንያት ካልሆነ በስተቀር ሚስቱን የሚፈታ ሁሉ ምንዝር ለመፈጸም እንድትጋለጥ ያደርጋታል፤ እንዲሁም በዚህ መንገድ የተፈታችን ሴት የሚያገባ ሁሉ ያመነዝራል።
“ከዚህም ሌላ በጥንት ዘመን ለነበሩት ‘በከንቱ አትማል፤ ይልቁንም ለይሖዋ የተሳልከውን ፈጽም’ እንደተባለ ሰምታችኋል።
እኔ ግን እላችኋለሁ፣ ፈጽሞ አትማሉ። በሰማይም ቢሆን አትማሉ፤ የአምላክ ዙፋን ነውና፤
በምድርም ቢሆን አትማሉ፤ የእግሩ ማሳረፊያ ነችና፤ በኢየሩሳሌምም ቢሆን አትማሉ፤ የታላቁ ንጉሥ ከተማ ነችና።
በራስህም ቢሆን አትማል፤ ከፀጉርህ አንዷን እንኳ ነጭ ወይም ጥቁር ማድረግ አትችልምና።
ቃላችሁ ‘አዎ’ ከሆነ አዎ ይሁን፤ ‘አይደለም’ ከሆነ አይደለም ይሁን፤ ከዚህ ውጭ የሆነ ግን ከክፉው ነው።
“‘ዓይን ስለ ዓይን፣ ጥርስ ስለ ጥርስ’ እንደተባለ ሰምታችኋል።