text
stringlengths
4
267
እኔ ግን እላችኋለሁ፣ ክፉን ሰው አትቃወሙት፤ ከዚህ ይልቅ ቀኝ ጉንጭህን በጥፊ ለሚመታህ ሌላኛውን ደግሞ አዙርለት።
አንድ ሰው ፍርድ ቤት ሊያቀርብህና እጀ ጠባብህን ሊወስድ ቢፈልግ መደረቢያህንም ጨምረህ ስጠው፤
እንዲሁም አንድ ባለሥልጣን አንድ ኪሎ ሜትር እንድትሄድ ቢያስገድድህ ሁለት ኪሎ ሜትር አብረኸው ሂድ።
ለሚለምንህ ስጥ፤ ሊበደርህ የሚፈልገውንም ሰው ፊት አትንሳው።
“‘ባልንጀራህን ውደድ፤ ጠላትህን ጥላ’ እንደተባለ ሰምታችኋል።
እኔ ግን እላችኋለሁ፦ ጠላቶቻችሁን ውደዱ እንዲሁም ስደት ለሚያደርሱባችሁ ጸልዩ፤
ይህን ብታደርጉ በሰማያት ላለው አባታችሁ ልጆች ትሆናላችሁ፤ እሱ በክፉዎችም ሆነ በጥሩ ሰዎች ላይ ፀሐዩን ያወጣልና፤ በጻድቃንም ሆነ ጻድቃን ባልሆኑ ሰዎች ላይ ዝናብ ያዘንባል።
የሚወዷችሁን ብቻ ብትወዱ ምን ብድራት ታገኛላችሁ? ቀረጥ ሰብሳቢዎችስ የሚያደርጉት ይህንኑ አይደለም?
ደግሞስ ወንድሞቻችሁን ብቻ ሰላም ብትሉ ምን የተለየ ነገር ታደርጋላችሁ? አሕዛብስ የሚያደርጉት ይህንኑ አይደለም?
በሰማይ ያለው አባታችሁ ፍጹም እንደሆነ እናንተም ፍጹማን ሁኑ።
በዚያን ጊዜ የአውራጃ ገዢ የነበረው ሄሮድስ ስለ ኢየሱስ ሲሰማ
አገልጋዮቹን “ይህ መጥምቁ ዮሐንስ ነው። ከሞት ተነስቷል ማለት ነው፤ እነዚህን ተአምራት መፈጸም የቻለውም ለዚህ ነው” አላቸው።
ሄሮድስ የወንድሙ የፊልጶስ ሚስት በሆነችው በሄሮድያዳ ምክንያት ዮሐንስን ይዞ በሰንሰለት በማሰር ወህኒ አስገብቶት ነበር።
ዮሐንስ ሄሮድስን “እሷን እንድታገባ ሕግ አይፈቅድልህም” ይለው ነበር።
ሄሮድስ ሊገድለው ይፈልግ የነበረ ቢሆንም ሕዝቡ እንደ ነቢይ ይመለከተው ስለነበር ሕዝቡን ፈራ።
ሆኖም የሄሮድስ ልደት በተከበረበት ዕለት የሄሮድያዳ ልጅ በግብዣው ላይ በመጨፈር ሄሮድስን እጅግ ደስ አሰኘችው፤
በመሆኑም የጠየቀችውን ሁሉ ሊሰጣት በመሐላ ቃል ገባላት።
ከዚያም እናቷ በሰጠቻት ምክር መሠረት “የመጥምቁ ዮሐንስን ራስ በዚህ ሳህን ስጠኝ” አለችው።
ንጉሡ ቢያዝንም ስለ መሐላውና አብረውት ይበሉ ስለነበሩት ሲል የዮሐንስ ራስ እንዲሰጣት አዘዘ።
ሰው ልኮም የዮሐንስን ራስ በወህኒ ቤት አስቆረጠ።
ራሱን በሳህን አምጥተው ለልጅቷ ሰጧት፤ እሷም ለእናቷ ሰጠቻት።
በኋላም የዮሐንስ ደቀ መዛሙርት መጡና አስከሬኑን ወስደው ቀበሩት፤ ከዚያም መጥተው ለኢየሱስ ነገሩት።
ኢየሱስ ይህን ሲሰማ ብቻውን ለመሆን በጀልባ ተሳፍሮ ገለል ወዳለ ስፍራ ሄደ። ሕዝቡ ግን መሄዱን ሰምተው ከየከተማው እየወጡ በእግር ተከተሉት።
ኢየሱስ ወደ ባሕሩ ዳርቻ ሲመጣ እጅግ ብዙ ሕዝብ ተመለከተና በጣም አዘነላቸው፤ በመካከላቸው የነበሩትንም ሕመምተኞች ፈወሰ።
በመሸ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ወደ እሱ ቀርበው “ቦታው ገለል ያለ ነው፤ ሰዓቱ ደግሞ ገፍቷል፤ ስለዚህ ሕዝቡ ወደ መንደሮቹ ሄደው ምግብ እንዲገዙ አሰናብታቸው” አሉት።
ይሁን እንጂ ኢየሱስ “መሄድ አያስፈልጋቸውም፤ እናንተ የሚበሉት ነገር ስጧቸው” አላቸው።
እነሱም “ከአምስት ዳቦና ከሁለት ዓሣ በስተቀር እዚህ ምንም ነገር የለንም” አሉት።
እሱም “ያለውን ወደ እኔ አምጡት” አላቸው።
ሕዝቡንም ሣሩ ላይ እንዲቀመጡ አዘዘ። ከዚያም አምስቱን ዳቦና ሁለቱን ዓሣ ይዞ ወደ ሰማይ ቀና በማለት ባረከ፤ ዳቦውን ከቆረሰ በኋላም ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠ፤ እነሱ ደግሞ ለሕዝቡ ሰጡ።
ሁሉም በልተው ጠገቡ፤ ከዚያም የተረፈውን ቁርስራሽ ሰበሰቡ፤ ቁርስራሹም 12 ቅርጫት ሙሉ ሆነ።
የበሉትም ከሴቶችና ከትናንሽ ልጆች ሌላ 5,000 ወንዶች ነበሩ።
ወዲያውም፣ እሱ ሕዝቡን እያሰናበተ ሳለ ደቀ መዛሙርቱን ጀልባ ተሳፍረው ቀድመውት ወደ ማዶ እንዲሻገሩ ነገራቸው።
ሕዝቡን ካሰናበተ በኋላ ለመጸለይ ብቻውን ወደ ተራራ ወጣ። በመሸም ጊዜ በዚያ ብቻውን ነበር።
በዚህ ጊዜ ጀልባው በመቶዎች የሚቆጠሩ ሜትሮች ከየብስ ርቆ የነበረ ሲሆን ነፋሱ ወደ እነሱ ይነፍስ ስለነበር ማዕበሉ በጣም አስቸገራቸው።
ሆኖም ኢየሱስ በአራተኛው ክፍለ ሌሊት በባሕሩ ላይ እየተራመደ ወደ እነሱ መጣ።
ደቀ መዛሙርቱ በባሕሩ ላይ ሲራመድ ባዩት ጊዜ ደንግጠው “ምትሃት ነው!” አሉ። በፍርሃት ተውጠውም ጮኹ።
ሆኖም ኢየሱስ ወዲያውኑ “አይዟችሁ! እኔ ነኝ፤ አትፍሩ” አላቸው።
ጴጥሮስም መልሶ “ጌታ ሆይ፣ አንተ ከሆንክ በውኃው ላይ እየተራመድኩ ወደ አንተ እንድመጣ እዘዘኝ” አለው።
እሱም “ና!” አለው። በዚህ ጊዜ ጴጥሮስ ከጀልባው ላይ ወርዶ በውኃው ላይ እየተራመደ ወደ ኢየሱስ አመራ።
ሆኖም አውሎ ነፋሱን ሲያይ ፈራ። መስጠም ሲጀምርም “ጌታ ሆይ፣ አድነኝ!” ብሎ ጮኸ።
ወዲያው ኢየሱስ እጁን ዘርግቶ ያዘውና “አንተ እምነት የጎደለህ! ለምን ተጠራጠርክ?” አለው።
ጀልባው ላይ ከወጡ በኋላ አውሎ ነፋሱ ጸጥ አለ።
ከዚያም በጀልባው ውስጥ ያሉት “አንተ በእርግጥ የአምላክ ልጅ ነህ” ብለው ሰገዱለት።
ባሕሩንም ተሻግረው ጌንሴሬጥ ወደተባለ ቦታ ደረሱ።
በዚያ የሚኖሩ ሰዎች ኢየሱስ መሆኑን ሲያውቁ በዙሪያው ወዳለው አካባቢ ሁሉ መልእክት ላኩ፤ ሰዎችም የታመሙትን ሁሉ ወደ እሱ አመጡ።
የልብሱን ዘርፍ ብቻ እንኳ ለመንካት ይማጸኑት ነበር፤ የነኩትም ሁሉ ሙሉ በሙሉ ተፈወሱ።
ከሰንበት ቀን በኋላ በሳምንቱ የመጀመሪያ ቀን ጎህ ሲቀድ መግደላዊቷ ማርያምና ሌላዋ ማርያም መቃብሩን ለማየት መጡ።
እነሆም የይሖዋ መልአክ ከሰማይ ስለወረደ ታላቅ የምድር መናወጥ ተከሰተ፤ መልአኩም መጥቶ ድንጋዩን አንከባለለውና በላዩ ተቀመጠ።
መልኩ እንደ መብረቅ ያበራ ነበር፤ ልብሱም እንደ በረዶ ነጭ ነበር።
ጠባቂዎቹ እሱን ከመፍራታቸው የተነሳ ተንቀጠቀጡ፤ እንደ በድንም ሆኑ።
ሆኖም መልአኩ ሴቶቹን እንዲህ አላቸው፦ “አትፍሩ፤ በእንጨት ላይ የተሰቀለውን ኢየሱስን እየፈለጋችሁ እንደሆነ አውቃለሁ።
አስቀድሞ እንደተናገረው ከሞት ስለተነሳ እዚህ የለም። ኑና አስከሬኑ አርፎበት የነበረውን ስፍራ እዩ።
ስለሆነም ፈጥናችሁ ሂዱና ለደቀ መዛሙርቱ ከሞት እንደተነሳ ንገሯቸው፤ ‘እነሆ፣ ቀድሟችሁ ወደ ገሊላ ይሄዳል። እዚያም ታዩታላችሁ’ በሏቸው። እነሆ ነግሬአችኋለሁ።”
ስለዚህ ሴቶቹ በፍርሃትና በታላቅ ደስታ ተውጠው ከመታሰቢያ መቃብሩ በፍጥነት በመውጣት ወሬውን ለደቀ መዛሙርቱ ለመንገር እየሮጡ ሄዱ።
ወዲያውም ኢየሱስ አገኛቸውና “ሰላም ለእናንተ ይሁን!” አላቸው። እነሱም ወደ እሱ ቀረቡና እግሩን ይዘው ሰገዱለት።
ከዚያም ኢየሱስ “አትፍሩ! ሂዱና ወደ ገሊላ እንዲሄዱ ለወንድሞቼ ንገሯቸው፤ እዚያም ያዩኛል” አላቸው።
ሴቶቹ በመንገድ ላይ ሳሉ ከጠባቂዎቹ አንዳንዶቹ ወደ ከተማ ሄደው የሆነውን ነገር ሁሉ ለካህናት አለቆቹ ነገሯቸው።
የካህናት አለቆቹም ከሽማግሌዎቹ ጋር ተሰብስበው ከተማከሩ በኋላ ለወታደሮቹ በርከት ያሉ የብር ሳንቲሞች በመስጠት
እንዲህ አሏቸው፦ “‘ሌሊት ተኝተን ሳለ ደቀ መዛሙርቱ መጥተው አስከሬኑን ሰረቁት’ በሉ።
አትጨነቁ፤ ወሬው ወደ አገረ ገዢው ጆሮ ከደረሰ ሁኔታውን እናስረዳዋለን።”
እነሱም የብር ሳንቲሞቹን ተቀብለው እንደታዘዙት አደረጉ፤ ይህም ታሪክ እስከ ዛሬ ድረስ በአይሁዳውያን ዘንድ በስፋት ይወራል።
ይሁንና የኢየሱስ 11 ደቀ መዛሙርት ከእሱ ጋር ለመገናኘት በገሊላ ወደሚገኘው፣ እሱ ወደነገራቸው ተራራ ሄዱ።
ባዩትም ጊዜ ሰገዱለት፤ አንዳንዶች ግን ተጠራጠሩ።
ኢየሱስም ቀረበና እንዲህ አላቸው፦ “ሥልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር ተሰጥቶኛል።
ስለዚህ ሂዱና ከሁሉም ብሔራት ሰዎችን ደቀ መዛሙርት አድርጉ፤ በአብ፣ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፣
ያዘዝኳችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው። እነሆም እኔ እስከ ሥርዓቱ መደምደሚያ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ።”
በተጨማሪም ኢየሱስ እንዲህ ሲል በምሳሌ ነገራቸው፦
“መንግሥተ ሰማያት ለልጁ ሠርግ ከደገሰ ንጉሥ ጋር ሊመሳሰል ይችላል።
ንጉሡም ወደ ሠርጉ የተጋበዙትን እንዲጠሩ ባሪያዎቹን ላከ፤ ተጋባዦቹ ግን ለመምጣት ፈቃደኛ አልሆኑም።
በድጋሚ ሌሎች ባሪያዎች ልኮ ‘ተጋባዦቹን “የምሳ ግብዣ አዘጋጅቻለሁ፤ ሰንጋዎቼና የሰቡት ፍሪዳዎቼ ታርደዋል፤ ሁሉም ነገር ዝግጁ ነው። ወደ ሠርጉ ኑ” በሏቸው’ አለ።
እነሱ ግን ግብዣውን ችላ በማለት አንዱ ወደ እርሻው፣ ሌላው ወደ ንግዱ ሄደ፤
ሌሎቹ ደግሞ ባሪያዎቹን ይዘው ካንገላቷቸው በኋላ ገደሏቸው።
“ንጉሡም እጅግ ተቆጣ፤ ወታደሮቹንም ልኮ እነዚያን ነፍሰ ገዳዮች ገደለ እንዲሁም ከተማቸውን አቃጠለ።
ከዚያም ባሪያዎቹን እንዲህ አላቸው፦ ‘ሠርጉ ተደግሷል፤ የተጋበዙት ግን የሚገባቸው ሆነው አልተገኙም።
ስለዚህ በየአውራ ጎዳናው ሂዱና ያገኛችሁትን ሰው ሁሉ ወደ ሠርጉ ጥሩ።’
በዚህ መሠረት ባሪያዎቹ ወደ አውራ ጎዳናዎች ሄደው ክፉውንም ጥሩውንም፣ ያገኙትን ሰው ሁሉ ሰበሰቡ፤ የሠርጉ አዳራሽም በተጋባዦች ተሞላ።
“ንጉሡ እንግዶቹን ለማየት ሲገባ የሠርግ ልብስ ያልለበሰ አንድ ሰው አየ።
በዚህ ጊዜ ‘ወዳጄ ሆይ፣ የሠርግ ልብስ ሳትለብስ እንዴት እዚህ ልትገባ ቻልክ?’ አለው። ሰውየውም የሚለው ጠፋው።
ከዚያም ንጉሡ አገልጋዮቹን ‘እጁንና እግሩን አስራችሁ በውጭ ወዳለው ጨለማ ጣሉት። እዚያም ሆኖ ያለቅሳል፤ ጥርሱንም ያፋጫል’ አላቸው።
“የተጠሩት ብዙዎች፣ የተመረጡት ግን ጥቂቶች ናቸውና።”
ከዚያም ፈሪሳውያን ሄደው በንግግሩ ሊያጠምዱት ሴራ ጠነሰሱ።
ስለዚህ ደቀ መዝሙሮቻቸውን ከሄሮድስ ሥርወ መንግሥት ደጋፊዎች ጋር ወደ እሱ በመላክ እንዲህ አሉት፦ “መምህር፣ አንተ እውነተኛ እንደሆንክና የአምላክን መንገድ በትክክል እንደምታስተምር እንዲሁም ለመወደድ ብለህ ምንም ነገር እንደማታደርግ፣ የሰውንም ውጫዊ ማንነት አይተህ እንደማትፈርድ እናውቃለን።
እስቲ ንገረን፣ ምን ይመስልሃል? ለመሆኑ ለቄሳር ግብር መክፈል ይገባል ወይስ አይገባም?”
ኢየሱስ ግን ክፋታቸውን አውቆ እንዲህ አላቸው፦ “እናንተ ግብዞች፣ ለምን ትፈትኑኛላችሁ?
እስቲ ለግብር የሚከፈለውን ሳንቲም አሳዩኝ።” እነሱም አንድ ዲናር አመጡለት።
እሱም “ይህ ምስልና የተቀረጸው ጽሑፍ የማን ነው?” አላቸው።
እነሱም “የቄሳር” አሉ። እሱም “እንግዲያው የቄሳር የሆነውን ለቄሳር፣ የአምላክ የሆነውን ደግሞ ለአምላክ ስጡ” አላቸው።
ይህን ሲሰሙ ተደነቁ፤ ከዚያም ትተውት ሄዱ።
በዚያኑ ዕለት፣ በትንሣኤ የማያምኑት ሰዱቃውያን መጥተው እንዲህ ሲሉ ጠየቁት፦
“መምህር፣ ሙሴ ‘አንድ ሰው ልጅ ሳይወልድ ቢሞት ወንድሙ የሟቹን ሚስት ማግባትና ለወንድሙ ዘር መተካት አለበት’ ብሏል።
በእኛ ዘንድ ሰባት ወንድማማቾች ነበሩ። የመጀመሪያው ሚስት አግብቶ ልጅ ሳይወልድ በመሞቱ ወንድሙ የሟቹን ሚስት አገባ።
ሁለተኛውም ሆነ ሦስተኛው እስከ ሰባተኛው ድረስ ልጅ ሳይወልዱ ሞቱ።
በመጨረሻም ሴትየዋ ሞተች።
እንግዲህ ሁሉም ስላገቧት በትንሣኤ ከሰባቱ ለየትኛው ሚስት ትሆናለች?”
ኢየሱስ እንዲህ ብሎ መለሰላቸው፦ “እናንተ ቅዱሳን መጻሕፍትንም ሆነ የአምላክን ኃይል ስለማታውቁ ተሳስታችኋል፤
ምክንያቱም በትንሣኤ ጊዜ ወንዶችም አያገቡም ሴቶችም አይዳሩም፤ ከዚህ ይልቅ በሰማይ እንዳሉ መላእክት ይሆናሉ።
የሙታንን ትንሣኤ በተመለከተ አምላክ እንዲህ ሲል ለእናንተ የተናገረውን አላነበባችሁም?
‘እኔ የአብርሃም አምላክ፣ የይስሐቅ አምላክና የያዕቆብ አምላክ ነኝ’ ብሏል። እሱ የሕያዋን እንጂ የሙታን አምላክ አይደለም።”
ሕዝቡ ይህን ሲሰሙ በትምህርቱ ተደነቁ።
ፈሪሳውያን፣ ኢየሱስ ሰዱቃውያንን ዝም እንዳሰኛቸው ሲሰሙ ተሰብስበው መጡ።