text
stringlengths
4
267
በገበያ ቦታም ሰዎች እጅ እንዲነሷቸው ይፈልጋሉ እንዲሁም ረቢ ተብለው መጠራት ይሻሉ።
እናንተ ግን መምህራችሁ አንድ ስለሆነ ረቢ ተብላችሁ አትጠሩ፤ እናንተ ሁላችሁም ወንድማማቾች ናችሁ።
በተጨማሪም አባታችሁ አንድ እሱም በሰማይ ያለው ብቻ ስለሆነ በምድር ላይ ማንንም አባት ብላችሁ አትጥሩ።
እንዲሁም መሪያችሁ አንድ እሱም ክርስቶስ ስለሆነ መሪ ተብላችሁ አትጠሩ።
ይልቁንም ከመካከላችሁ ታላቅ የሆነው የእናንተ አገልጋይ መሆን ይገባዋል።
ራሱን ከፍ ከፍ የሚያደርግ ሁሉ ዝቅ ይደረጋል፤ ራሱን ዝቅ የሚያደርግ ሁሉ ደግሞ ከፍ ይደረጋል።
“እናንተ ግብዞች ጸሐፍትና ፈሪሳውያን፣ ሰዎች ወደ መንግሥተ ሰማያት እንዳይገቡ በሩን ስለምትዘጉ ወዮላችሁ! እናንተ ራሳችሁ አትገቡም፤ ለመግባት የሚመጡትንም እንዳይገቡ ትከለክላላችሁ።
“እናንተ ግብዞች ጸሐፍትና ፈሪሳውያን፣ አንድን ሰው ወደ ይሁዲነት ለመለወጥ በባሕርና በየብስ ስለምትጓዙና ሰውየው በተለወጠ ጊዜ ከእናንተ ይባስ ሁለት እጥፍ ለገሃነም የተገባ እንዲሆን ስለምታደርጉት ወዮላችሁ!
“‘አንድ ሰው በቤተ መቅደሱ ቢምል ምንም አይደለም፤ በቤተ መቅደሱ ውስጥ ባለው ወርቅ ቢምል ግን መሐላውን የመጠበቅ ግዴታ አለበት’ የምትሉ እናንተ ዕውር መሪዎች ወዮላችሁ!
እናንተ ሞኞችና ዕውሮች! ለመሆኑ ከወርቁና ወርቁ እንዲቀደስ ካደረገው ቤተ መቅደስ የትኛው ይበልጣል?
ደግሞም ‘አንድ ሰው በመሠዊያው ቢምል ምንም አይደለም፤ በመሠዊያው ላይ ባለው መባ ቢምል ግን መሐላውን የመጠበቅ ግዴታ አለበት’ ትላላችሁ።
እናንተ ዕውሮች! ለመሆኑ ከመባውና መባው እንዲቀደስ ካደረገው መሠዊያ የትኛው ይበልጣል?
ስለዚህ በመሠዊያው የሚምል ሁሉ በመሠዊያውና በላዩ ላይ ባለው ነገር ሁሉ ይምላል፤
እንዲሁም በቤተ መቅደሱ የሚምል ሁሉ በቤተ መቅደሱና በዚያ በሚኖረው ይምላል፤
በሰማይ የሚምል ሁሉ ደግሞ በአምላክ ዙፋንና በዙፋኑ ላይ በተቀመጠው ይምላል።
“እናንተ ግብዞች ጸሐፍትና ፈሪሳውያን ወዮላችሁ! ከኮሰረት፣ ከእንስላልና ከከሙን አሥራት ትሰጣላችሁ፤ ነገር ግን በሕጉ ውስጥ የሚገኙትን እንደ ፍትሕ፣ ምሕረትና ታማኝነት ያሉ ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑ ነገሮች ችላ ትላላችሁ። እነዚያን ችላ ማለት ባይኖርባችሁም እነዚህን ነገሮች ማድረጋችሁ አስፈላጊ ነው።
እናንተ ዕውር መሪዎች! ትንኝን አጥልላችሁ ታወጣላችሁ፤ ግመልን ግን ትውጣላችሁ!
“እናንተ ግብዞች ጸሐፍትና ፈሪሳውያን ወዮላችሁ! ጽዋውንና ሳህኑን ከውጭ በኩል ታጸዳላችሁ፤ ውስጡ ግን ስግብግብነትና ራስ ወዳድነት የሞላበት ነው።
አንተ ዕውር ፈሪሳዊ፣ በመጀመሪያ ጽዋውንና ሳህኑን ከውስጥ በኩል አጽዳ፤ ከዚያ በኋላ ከውጭ በኩልም ንጹሕ ይሆናል።
“እናንተ ግብዞች ጸሐፍትና ፈሪሳውያን፣ ከውጭ አምረው የሚታዩ ከውስጥ ግን በሙታን አፅምና በብዙ ዓይነት ርኩሰት የተሞሉ በኖራ የተቀቡ መቃብሮችን ስለምትመስሉ ወዮላችሁ!
እናንተም ከውጭ ስትታዩ ጻድቅ ትመስላላችሁ፤ ውስጣችሁ ግን በግብዝነትና በዓመፅ የተሞላ ነው።
“እናንተ ግብዞች ጸሐፍትና ፈሪሳውያን፣ የነቢያትን መቃብር ስለምትገነቡና የጻድቃንን መቃብር ስለምታስጌጡ ወዮላችሁ!
ደግሞም ‘በአባቶቻችን ዘመን ኖረን ቢሆን ኖሮ የነቢያትን ደም በማፍሰስ አንተባበራቸውም ነበር’ ትላላችሁ።
በመሆኑም የነቢያት ገዳዮች ልጆች እንደሆናችሁ በራሳችሁ ላይ ትመሠክራላችሁ።
እንግዲያው አባቶቻችሁ የጀመሩትን ተግባር ዳር አድርሱ።
“እናንተ እባቦች፣ የእፉኝት ልጆች፣ ከገሃነም ፍርድ እንዴት ታመልጣላችሁ?
ስለዚህ ነቢያትን፣ ጥበበኞችንና የሕዝብ አስተማሪዎችን ወደ እናንተ እልካለሁ። ከእነሱም መካከል አንዳንዶቹን ትገድላላችሁ እንዲሁም በእንጨት ላይ ትሰቅላላችሁ፤ አንዳንዶቹን ደግሞ በምኩራቦቻችሁ ትገርፋላችሁ፤ ከከተማ ወደ ከተማም ታሳድዷቸዋላችሁ፤
በዚህም ምክንያት ከጻድቁ ከአቤል ደም ጀምሮ በመቅደሱና በመሠዊያው መካከል እስከገደላችሁት እስከ በራክዩ ልጅ እስከ ዘካርያስ ደም ድረስ በምድር ላይ ለፈሰሰው የጻድቃን ደም ሁሉ ተጠያቂ ትሆናላችሁ።
እውነት እላችኋለሁ፣ እነዚህ ነገሮች ሁሉ በዚህ ትውልድ ላይ ይደርሳሉ።
“ኢየሩሳሌም፣ ኢየሩሳሌም፣ ነቢያትን የምትገድል! ወደ እሷ የተላኩትንም በድንጋይ የምትወግር! ዶሮ ጫጩቶቿን በክንፎቿ ሥር እንደምትሰበስብ እኔም ልጆችሽን ለመሰብሰብ ስንት ጊዜ ፈለግኩ! እናንተ ግን አልፈለጋችሁም።
እነሆ፣ ቤታችሁ ለእናንተ የተተወ ይሆናል።
ስለዚህ እላችኋለሁ፣ ‘በይሖዋ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው!’ እስክትሉ ድረስ ከእንግዲህ ወዲህ ፈጽሞ አታዩኝም።”
“ሰዎች እንዲያዩላችሁ ብላችሁ የጽድቅ ሥራችሁን በእነሱ ፊት እንዳታደርጉ ተጠንቀቁ፤ አለዚያ በሰማያት ካለው አባታችሁ ምንም ብድራት አታገኙም።
በመሆኑም ምጽዋት በምትሰጡበት ጊዜ በሰዎች ዘንድ ለመከበር ብለው በምኩራቦችና በጎዳናዎች ላይ አስቀድመው መለከት እንደሚያስነፉ ግብዞች አትሁኑ። እውነት እላችኋለሁ፣ እነሱ ሙሉ ብድራታቸውን ተቀብለዋል።
አንተ ግን ምጽዋት ስትሰጥ ቀኝ እጅህ የሚያደርገውን ግራ እጅህ አይወቅ፤
ይህም ምጽዋትህ በስውር እንዲሆን ያስችላል። በስውር የሚያይ አባትህም መልሶ ይከፍልሃል።
“በተጨማሪም በምትጸልዩበት ጊዜ እንደ ግብዞች አትሁኑ፤ እነሱ ሰዎች እንዲያዩአቸው በምኩራቦችና በየአውራ ጎዳናው ማዕዘኖች ላይ ቆመው መጸለይ ይወዳሉና። እውነት እላችኋለሁ፣ እነሱ ሙሉ ብድራታቸውን ተቀብለዋል።
አንተ ግን ስትጸልይ ወደ ክፍልህ ግባ፤ በርህንም ዘግተህ በስውር ወዳለው አባትህ ጸልይ። በስውር የሚያይ አባትህም መልሶ ይከፍልሃል።
በምትጸልዩበት ጊዜ አሕዛብ እንደሚያደርጉት አንድ ዓይነት ነገር ደጋግማችሁ አታነብንቡ፤ እነሱ ቃላት በማብዛት ጸሎታቸው የሚሰማላቸው ይመስላቸዋል።
ስለዚህ እንደ እነሱ አትሁኑ፤ አባታችሁ ገና ሳትለምኑት ምን እንደሚያስፈልጋችሁ ያውቃልና።
“እንግዲያው እናንተ በዚህ መንገድ ጸልዩ፦ “‘በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ፣ ስምህ ይቀደስ።
መንግሥትህ ይምጣ። ፈቃድህ በሰማይ እየተፈጸመ እንዳለ ሁሉ በምድርም ላይ ይፈጸም።
የዕለቱን ምግባችንን ዛሬ ስጠን፤
የበደሉንን ይቅር እንዳልን በደላችንን ይቅር በለን።
ከክፉው አድነን እንጂ ወደ ፈተና አታግባን።’
“የበደሏችሁን ሰዎች ይቅር ካላችሁ በሰማይ ያለው አባታችሁ ይቅር ይላችኋል፤
እናንተ ግን የበደሏችሁን ሰዎች ይቅር ካላላችሁ አባታችሁም በደላችሁን ይቅር አይላችሁም።
“በምትጾሙበት ጊዜ እንደ ግብዞች ፊታችሁን አታጠውልጉ፤ እነሱ መጾማቸው በሰው ዘንድ እንዲታወቅላቸው ፊታቸውን ያጠወልጋሉ። እውነት እላችኋለሁ፣ እነሱ ሙሉ ብድራታቸውን ተቀብለዋል።
አንተ ግን ስትጾም ራስህን ተቀባ፤ ፊትህንም ታጠብ፤
እንዲህ ካደረግክ የምትጾመው በሰው ለመታየት ሳይሆን በስውር ላለው አባትህ ስትል ብቻ ይሆናል። በስውር የሚያይ አባትህም መልሶ ይከፍልሃል።
“ብል ሊበላው፣ ዝገት ሊያበላሸውና ሌባ ገብቶ ሊሰርቀው በሚችልበት በምድር ላይ ለራሳችሁ ሀብት አታከማቹ።
ከዚህ ይልቅ ብል ሊበላው፣ ዝገት ሊያበላሸውና ሌባ ገብቶ ሊሰርቀው በማይችልበት በሰማይ ለራሳችሁ ሀብት አከማቹ።
ሀብትህ ባለበት ልብህም በዚያ ይሆናልና።
“የሰውነት መብራት ዓይን ነው። ስለሆነም ዓይንህ በአንድ ነገር ላይ ያተኮረ ከሆነ መላ ሰውነትህ ብሩህ ይሆናል።
ይሁን እንጂ ዓይንህ ምቀኛ ከሆነ መላ ሰውነትህ ጨለማ ይሆናል። እንግዲህ በአንተ ውስጥ ያለው ብርሃን በእርግጥ ጨለማ ከሆነ ጨለማው እንዴት ድቅድቅ ይሆን!
“ለሁለት ጌቶች ባሪያ ሆኖ መገዛት የሚችል ማንም የለም፤ አንዱን ጠልቶ ሌላውን ይወዳል ወይም አንዱን ደግፎ ሌላውን ይንቃል። ለአምላክም ለሀብትም በአንድነት መገዛት አትችሉም።
“ስለዚህ እላችኋለሁ፦ ስለ ሕይወታችሁ ምን እንበላለን፣ ምንስ እንጠጣለን ወይም ደግሞ ስለ ሰውነታችሁ ምን እንለብሳለን ብላችሁ አትጨነቁ። ሕይወት ከምግብ፣ ሰውነትስ ከልብስ አይበልጥም?
የሰማይ ወፎችን ልብ ብላችሁ ተመልከቱ፤ እነሱ አይዘሩም፣ አያጭዱም ወይም በጎተራ አያከማቹም፤ ይሁንና በሰማይ ያለው አባታችሁ ይመግባቸዋል። ታዲያ እናንተ ከእነሱ አትበልጡም?
ከእናንተ መካከል ተጨንቆ በዕድሜው ርዝማኔ ላይ አንድ ክንድ መጨመር የሚችል ይኖራል?
ስለ ልብስስ ቢሆን ለምን ትጨነቃላችሁ? እስቲ የሜዳ አበቦች እንዴት እንደሚያድጉ ልብ ብላችሁ ተመልከቱ፤ አይለፉም ወይም አይፈትሉም፤
እኔ ግን እላችኋለሁ፣ ያን ያህል ክብር የነበረው ሰለሞን እንኳ ከእነዚህ አበቦች እንደ አንዷ አላጌጠም።
አምላክ ዛሬ ታይቶ ነገ ወደ ምድጃ የሚጣለውን የሜዳ ተክል እንዲህ የሚያለብሰው ከሆነ እናንተ እምነት የጎደላችሁ፣ እናንተንማ እንዴት አብልጦ አያለብሳችሁም?
ስለዚህ ‘ምን እንበላለን?’ ወይም ‘ምን እንጠጣለን?’ አሊያም ‘ምን እንለብሳለን?’ ብላችሁ ፈጽሞ አትጨነቁ።
እነዚህ ነገሮች ሁሉ አሕዛብ አጥብቀው የሚፈልጓቸው ናቸው። በሰማይ የሚኖረው አባታችሁ እነዚህ ሁሉ እንደሚያስፈልጓችሁ ያውቃል።
“እንግዲያው ከሁሉ አስቀድማችሁ የአምላክን መንግሥትና ጽድቅ ፈልጉ፤ እነዚህም ነገሮች ሁሉ ይሰጧችኋል።
ስለዚህ ስለ ነገ ፈጽሞ አትጨነቁ፤ ምክንያቱም ነገ የራሱ የሆኑ የሚያስጨንቁ ነገሮች አሉት። እያንዳንዱ ቀን የራሱ የሆነ በቂ ችግር አለው።
ከተራራው ከወረደ በኋላ እጅግ ብዙ ሕዝብ ተከተለው።
በዚህ ጊዜ በሥጋ ደዌ የተያዘ አንድ ሰው ወደ እሱ መጥቶ በመስገድ “ጌታ ሆይ፣ ብትፈልግ እኮ ልታነጻኝ ትችላለህ” አለው።
ኢየሱስም እጁን ዘርግቶ ዳሰሰውና “እፈልጋለሁ! ንጻ” አለው። ወዲያውኑ ከሥጋ ደዌው ነጻ።
ከዚያም ኢየሱስ “ለማንም እንዳትናገር ተጠንቀቅ፤ ነገር ግን ሄደህ ራስህን ለካህን አሳይ፤ ሙሴ ያዘዘውንም መባ አቅርብ። ካህናቱም ማስረጃውን ይመለከታሉ” አለው።
ኢየሱስ ወደ ቅፍርናሆም በገባ ጊዜ አንድ የጦር መኮንን ወደ እሱ ቀርቦ እንዲህ ሲል ተማጸነው፦
“ጌታዬ፣ አገልጋዬ ሽባ ሆኖ ቤት ተኝቷል፤ በጣም እየተሠቃየ ነው።”
እሱም “መጥቼ እፈውሰዋለሁ” አለው።
መኮንኑም እንዲህ ሲል መለሰ፦ “ጌታዬ፣ አንተ ወደ ቤቴ ትገባ ዘንድ የሚገባኝ ሰው አይደለሁም፤ ነገር ግን እዚሁ ሆነህ አንድ ቃል ተናገር፣ አገልጋዬም ይፈወሳል።
እኔ ራሴ የምታዘዛቸው የበላይ አዛዦች አሉ፤ ለእኔም የሚታዘዙ የበታች ወታደሮች አሉኝ፤ አንዱን ‘ሂድ!’ ስለው ይሄዳል፤ ሌላውንም ‘ና!’ ስለው ይመጣል፤ ባሪያዬንም ‘ይህን አድርግ!’ ስለው ያደርጋል።”
ኢየሱስ ይህን ሲሰማ በጣም ተገርሞ ይከተሉት ለነበሩት እንዲህ አላቸው፦ “እውነት እላችኋለሁ፣ በእስራኤል ውስጥ እንዲህ ዓይነት ታላቅ እምነት ያለው አንድም ሰው አላገኘሁም።
ነገር ግን እላችኋለሁ፣ ብዙዎች ከምሥራቅና ከምዕራብ ይመጣሉ፤ በመንግሥተ ሰማያትም ከአብርሃም፣ ከይስሐቅና ከያዕቆብ ጋር በማዕድ ይቀመጣሉ።
የመንግሥተ ሰማያት ልጆች ግን ውጭ ወዳለው ጨለማ ይጣላሉ። በዚያም ያለቅሳሉ፤ ጥርሳቸውንም ያፋጫሉ።”
ከዚያም ኢየሱስ መኮንኑን “ሂድ። እንደ እምነትህ ይሁንልህ” አለው። አገልጋዩም በዚያች ቅጽበት ተፈወሰ።
ኢየሱስ ወደ ጴጥሮስ ቤት ሲመጣ የጴጥሮስ አማት ትኩሳት ይዟት ተኝታ አገኛት።
እጇንም ሲዳስሳት ትኩሳቱ ለቀቃት፤ ተነስታም ታገለግለው ጀመር።
ከመሸ በኋላ ሰዎች አጋንንት ያደሩባቸውን ብዙ ሰዎች ወደ እሱ አመጡ፤ መናፍስቱንም በአንድ ቃል አስወጣ፤ እየተሠቃዩ የነበሩትንም ሁሉ ፈወሰ፤
ይህም የሆነው በነቢዩ ኢሳይያስ “እሱ ሕመማችንን ተቀበለ፤ ደዌያችንንም ተሸከመ” ተብሎ የተነገረው እንዲፈጸም ነው።
ኢየሱስ በዙሪያው ብዙ ሰዎች እንደተሰበሰቡ ባየ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱን ወደ ባሕሩ ማዶ እንዲሻገሩ አዘዛቸው።
ከጸሐፍትም አንዱ መጥቶ “መምህር፣ ወደምትሄድበት ሁሉ እከተልሃለሁ” አለው።
ኢየሱስ ግን “ቀበሮዎች ጉድጓድ፣ የሰማይ ወፎችም ጎጆ አላቸው፤ የሰው ልጅ ግን ራሱን እንኳ የሚያሳርፍበት ቦታ የለውም” አለው።
ከዚያም ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ “ጌታ ሆይ፣ በመጀመሪያ ሄጄ አባቴን እንድቀብር ፍቀድልኝ” አለው።
ኢየሱስም “አንተ እኔን መከተልህን ቀጥል፤ ሙታን ሙታናቸውን እንዲቀብሩ ተዋቸው” አለው።
ከዚያም ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ጀልባ ላይ ተሳፈሩ።
እነሆ፣ በጉዞ ላይ ሳሉ በባሕሩ ላይ ኃይለኛ ማዕበል ስለተነሳ ጀልባዋ በውኃ ተሞልታ ልትሰጥም ተቃረበች፤ ኢየሱስ ግን ተኝቶ ነበር።
እነሱም ወደ እሱ ቀርበው ቀሰቀሱትና “ጌታ ሆይ፣ ማለቃችን እኮ ነው፤ አድነን!” አሉት።
እሱ ግን “እናንተ እምነት የጎደላችሁ! ለምን ትሸበራላችሁ?” አላቸው። ከዚያም ተነስቶ ነፋሱንና ባሕሩን ገሠጸ፤ ታላቅ ጸጥታም ሰፈነ።
ሰዎቹም ተደንቀው “ይህ እንዴት ያለ ሰው ነው? ነፋስና ባሕር እንኳ ይታዘዙለታል” አሉ።
ባሕሩን ተሻግሮ ገዳሬኖስ ወደተባለው ክልል በደረሰ ጊዜ አጋንንት ያደሩባቸው ሁለት ሰዎች ከመቃብር ቦታ ወጥተው ከእሱ ጋር ተገናኙ። ሰዎቹ በጣም ኃይለኛ ከመሆናቸው የተነሳ ማንም ሰው በዚያ ለማለፍ አይደፍርም ነበር።
እነሱም “የአምላክ ልጅ ሆይ፣ እኛ ከአንተ ጋር ምን ጉዳይ አለን? የመጣኸው ጊዜው ሳይደርስ ልታሠቃየን ነው?” ብለው ጮኹ።
ከእነሱ ራቅ ብሎ ብዙ የአሳማ መንጋ ተሰማርቶ ነበር።
አጋንንቱም “የምታስወጣን ከሆነ ወደ አሳማው መንጋ ስደደን” ብለው ይማጸኑት ጀመር።
እሱም “ሂዱ!” አላቸው። እነሱም ወጥተው ወደ አሳማዎቹ ሄዱ፤ የአሳማውም መንጋ በሙሉ ከገደሉ አፋፍ እየተንደረደረ በመውረድ ባሕሩ ውስጥ ሰጥሞ አለቀ።
እረኞቹ ግን ሸሽተው ወደ ከተማው በመሄድ አጋንንት ባደሩባቸው ሰዎች ላይ የተፈጸመውን ጨምሮ የሆነውን ነገር ሁሉ አወሩ።
ከተማው ሁሉ ኢየሱስን ለማግኘት ወጣ፤ ሰዎቹም ባዩት ጊዜ አካባቢያቸውን ለቆ እንዲሄድ ለመኑት።