text stringlengths 4 267 |
|---|
ሆኖም ኢየሱስ ወደ እሱ ጠርቶ እንዲህ አላቸው፦ “የዚህ ዓለም ገዢዎች በሕዝባቸው ላይ ሥልጣናቸውን እንደሚያሳዩ፣ ታላላቅ ሰዎችም በኃይል እንደሚገዟቸው ታውቃላችሁ። |
በእናንተ መካከል ግን እንዲህ መሆን የለበትም፤ ከመካከላችሁ ታላቅ መሆን የሚፈልግ ሁሉ አገልጋያችሁ ሊሆን ይገባል፤ |
እንዲሁም ከመካከላችሁ ፊተኛ መሆን የሚፈልግ ሁሉ ባሪያችሁ ሊሆን ይገባል። |
የሰው ልጅም የመጣው ለማገልገልና በብዙ ሰዎች ምትክ ሕይወቱን ቤዛ አድርጎ ለመስጠት እንጂ እንዲገለገል አይደለም።” |
ከኢያሪኮ ወጥተው እየሄዱ ሳሉ እጅግ ብዙ ሕዝብ ተከተለው። |
በዚህ ጊዜ መንገድ ዳር የተቀመጡ ሁለት ዓይነ ስውሮች ኢየሱስ በዚያ እያለፈ መሆኑን ሲሰሙ “ጌታ ሆይ፣ የዳዊት ልጅ፣ ምሕረት አድርግልን!” እያሉ ጮኹ። |
ሆኖም ሕዝቡ ዝም እንዲሉ ገሠጿቸው፤ እነሱ ግን “ጌታ ሆይ፣ የዳዊት ልጅ፣ ምሕረት አድርግልን!” እያሉ ይበልጥ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ጮኹ። |
ኢየሱስም ቆም ብሎ ጠራቸውና “ምን እንዳደርግላችሁ ትፈልጋላችሁ?” አላቸው። |
እነሱም “ጌታ ሆይ፣ ዓይናችንን አብራልን” አሉት። |
ኢየሱስም በጣም አዘነላቸውና ዓይኖቻቸውን ዳሰሰ፤ ወዲያውኑም ማየት ቻሉ፤ ከዚያም ተከተሉት። |
በዚያን ጊዜ ኢየሱስ በሰንበት ቀን በእህል እርሻ መካከል አለፈ። ደቀ መዛሙርቱም ተርበው ስለነበር እሸት እየቀጠፉ መብላት ጀመሩ። |
ፈሪሳውያን ይህን ባዩ ጊዜ “ተመልከት! ደቀ መዛሙርትህ በሰንበት ቀን በሕግ የተከለከለ ነገር እያደረጉ ነው” አሉት። |
እሱም እንዲህ አላቸው፦ “ዳዊት እሱና ከእሱ ጋር የነበሩት ሰዎች በተራቡ ጊዜ ምን እንዳደረገ አላነበባችሁም? |
ወደ አምላክ ቤት ገብቶ ከካህናት በስተቀር እሱም ሆነ ከእሱ ጋር የነበሩት ሰዎች እንዲበሉ ያልተፈቀደውን በአምላክ ፊት የቀረበ ኅብስት አልበሉም? |
ደግሞስ ካህናት የሰንበትን ሕግ እንደሚተላለፉና ይህም እንደ በደል እንደማይቆጠርባቸው በሕጉ ላይ አላነበባችሁም? |
እኔ ግን እላችኋለሁ፣ ከቤተ መቅደሱ የሚበልጥ እዚህ አለ። |
ይሁንና ‘እኔ የምፈልገው ምሕረትን እንጂ መሥዋዕትን አይደለም’ የሚለውን ቃል ትርጉም ተረድታችሁ ቢሆን ኖሮ ምንም በደል ባልሠሩት ላይ ባልፈረዳችሁ ነበር። |
የሰው ልጅ የሰንበት ጌታ ነውና።” |
ከዚያ ስፍራ ከሄደ በኋላ ወደ ምኩራባቸው ገባ፤ |
በዚያም እጁ የሰለለ አንድ ሰው ነበር። እነሱም ኢየሱስን መክሰስ ፈልገው “በሰንበት መፈወስ በሕግ ተፈቅዷል?” ሲሉ ጠየቁት። |
እሱም እንዲህ አላቸው፦ “ከእናንተ መካከል አንድ በግ ያለው ሰው ቢኖርና በሰንበት ቀን ጉድጓድ ውስጥ ቢገባበት በጉን ጎትቶ የማያወጣው ይኖራል? |
ታዲያ ሰው ከበግ እጅግ አይበልጥም? ስለዚህ በሰንበት መልካም ነገር ማድረግ ተፈቅዷል።” |
ከዚያም ሰውየውን “እጅህን ዘርጋ” አለው። ሰውየውም እጁን ዘረጋ፤ እጁም እንደ ሌላኛው እጁ ደህና ሆነለት። |
ፈሪሳውያኑ ግን ወጥተው እሱን ለመግደል አሴሩ። |
ኢየሱስም ይህን ሲያውቅ አካባቢውን ለቆ ሄደ። ብዙ ሰዎችም ተከትለውት ሄዱ፤ እሱም የታመሙትን ሁሉ ፈወሳቸው፤ |
ሆኖም የእሱን ማንነት ለሌሎች እንዳይገልጹ በጥብቅ አዘዛቸው፤ |
ይህን ያደረገው በነቢዩ ኢሳይያስ እንዲህ ተብሎ የተነገረው ይፈጸም ዘንድ ነው፦ |
“እነሆ፣ የምወደውና ደስ የምሰኝበት የመረጥኩት አገልጋዬ! መንፈሴን በእሱ ላይ አደርጋለሁ፤ ፍትሕ ምን ማለት እንደሆነም ለብሔራት ያሳውቃል። |
አይጨቃጨቅም ወይም አይጮኽም፤ በአውራ ጎዳናዎችም ላይ ድምፁን የሚሰማ አይኖርም። |
ፍትሕን በአስተማማኝ ሁኔታ እስኪያሰፍን ድረስ፣ የተቀጠቀጠን ሸምበቆ አይሰብርም፤ የሚጨስንም የጧፍ ክር አያጠፋም። |
በእርግጥም ብሔራት በስሙ ተስፋ ያደርጋሉ።” |
ከጊዜ በኋላም፣ ጋኔን የያዘው ዓይነ ስውርና ዱዳ ሰው ወደ እሱ አመጡ፤ እሱም ፈወሰው፤ ዱዳውም መናገርና ማየት ቻለ። |
ሕዝቡም ሁሉ በጣም ተደንቀው “ይህ የዳዊት ልጅ ይሆን እንዴ?” ይሉ ጀመር። |
ፈሪሳውያን ይህን ሲሰሙ “ይህ ሰው በአጋንንት አለቃ በብዔልዜቡል ካልሆነ በስተቀር አጋንንትን ሊያስወጣ አይችልም” አሉ። |
ኢየሱስም ሐሳባቸውን አውቆ እንዲህ አላቸው፦ “እርስ በርሱ የሚከፋፈል መንግሥት ሁሉ ይጠፋል፤ እንዲሁም እርስ በርሱ የሚከፋፈል ከተማ ወይም ቤት ሁሉ ጸንቶ አይቆምም። |
በተመሳሳይም ሰይጣን ሰይጣንን የሚያስወጣ ከሆነ እርስ በርሱ ተከፋፍሏል ማለት ነው፤ ይህ ከሆነ ታዲያ መንግሥቱ እንዴት ጸንቶ ሊቆም ይችላል? |
በተጨማሪም እኔ አጋንንትን የማስወጣው በብዔልዜቡል ከሆነ፣ ልጆቻችሁ የሚያስወጧቸው ታዲያ በማን ነው? ልጆቻችሁ ፈራጆች የሚሆኑባችሁ ለዚህ ነው። |
ሆኖም አጋንንትን የማስወጣው በአምላክ መንፈስ ከሆነ የአምላክ መንግሥት ሳታስቡት ደርሶባችኋል ማለት ነው። |
ደግሞስ አንድ ሰው በቅድሚያ ሰውየውን ሳያስር ወደ አንድ ብርቱ ሰው ቤት ገብቶ እንዴት ንብረቱን ሊወስድ ይችላል? ቤቱን መዝረፍ የሚችለው እንዲህ ካደረገ ብቻ ነው። |
ከእኔ ጎን ያልቆመ ሁሉ ይቃወመኛል፤ ከእኔ ጋር የማይሰበስብም ሁሉ ይበትናል። |
“ስለሆነም እላችኋለሁ፣ ሰዎች የሚሠሩት ኃጢአትና የሚሳደቡት ስድብ ሁሉ ይቅር ይባልላቸዋል፤ መንፈስ ቅዱስን የሰደበ ግን ይቅር አይባልለትም። |
ለምሳሌ በሰው ልጅ ላይ ክፉ ቃል የሚናገር ሁሉ ይቅርታ ይደረግለታል፤ በመንፈስ ቅዱስ ላይ ክፉ ቃል የሚናገር ሁሉ ግን በዚህም ሆነ በሚመጣው ሥርዓት ይቅርታ አይደረግለትም። |
“መልካም ዛፍ ካላችሁ መልካም ፍሬ ያፈራል፤ የበሰበሰ ዛፍ ካላችሁ ደግሞ የበሰበሰ ፍሬ ያፈራል፤ ዛፍ የሚታወቀው በፍሬው ነውና። |
እናንተ የእፉኝት ልጆች፣ ክፉዎች ሆናችሁ ሳለ እንዴት መልካም ነገር ልትናገሩ ትችላላችሁ? አንደበት የሚናገረው በልብ ውስጥ የሞላውን ነውና። |
ጥሩ ሰው በልቡ ካከማቸው መልካም ነገር ጥሩ ነገር ያወጣል፤ ክፉ ሰው ደግሞ በልቡ ካከማቸው መጥፎ ነገር ክፉ ነገር ያወጣል። |
ነገር ግን እላችኋለሁ፣ ሰዎች ለሚናገሩት ከንቱ ቃል ሁሉ በፍርድ ቀን ይጠየቁበታል፤ |
ከቃልህ የተነሳ ጻድቅ ትባላለህና፤ ከቃልህም የተነሳ ትኮነናለህ።” |
ከዚያም ከጸሐፍትና ከፈሪሳውያን አንዳንዶቹ “መምህር፣ ምልክት እንድታሳየን እንፈልጋለን” አሉት። |
እሱም መልሶ እንዲህ አላቸው፦ “ክፉና አመንዝራ ትውልድ ሁልጊዜ ምልክት ማየት ይፈልጋል፤ ሆኖም ከነቢዩ ዮናስ ምልክት በስተቀር ምንም ምልክት አይሰጠውም። |
ዮናስ በትልቅ ዓሣ ሆድ ውስጥ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት እንደነበረ ሁሉ የሰው ልጅም በምድር ልብ ውስጥ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት ይቆያል። |
የነነዌ ሰዎች የዮናስን ስብከት ሰምተው ንስሐ ስለገቡ በፍርድ ወቅት ከዚህ ትውልድ ጋር ተነስተው ይኮንኑታል። ነገር ግን ከዮናስ የሚበልጥ እዚህ አለ። |
የደቡብ ንግሥት የሰለሞንን ጥበብ ለመስማት ከምድር ዳርቻ ስለመጣች በፍርድ ወቅት ከዚህ ትውልድ ጋር ተነስታ ትኮንነዋለች። ነገር ግን ከሰለሞን የሚበልጥ እዚህ አለ። |
“ርኩስ መንፈስ ከሰው ሲወጣ የሚያርፍበት ቦታ ፍለጋ ውኃ በሌለበት ስፍራ ይንከራተታል፤ ሆኖም የሚያርፍበት ቦታ አያገኝም። |
ከዚያም ‘ወደለቀቅኩት ቤቴ ተመልሼ እሄዳለሁ’ ይላል፤ ሲመለስም ቤቱ ባዶ ሆኖ፣ ጸድቶና አጊጦ ያገኘዋል። |
ከዚያም ሄዶ ከእሱ የከፉ ሌሎች ሰባት መናፍስት ይዞ ይመጣል፤ ገብተውም ይኖሩበታል፤ የዚያም ሰው የኋለኛው ሁኔታ ከቀድሞው የከፋ ይሆንበታል። ይህ ክፉ ትውልድም ተመሳሳይ ነገር ይደርስበታል።” |
ኢየሱስ ለሕዝቡ እየተናገረ ሳለ እናቱና ወንድሞቹ ሊያነጋግሩት ፈልገው ውጭ ቆመው ነበር። |
ስለሆነም አንድ ሰው “እነሆ፣ እናትህና ወንድሞችህ ሊያነጋግሩህ ፈልገው ውጭ ቆመዋል” አለው። |
ኢየሱስም መልሶ ሰውየውን “እናቴ ማን ናት? ወንድሞቼስ እነማን ናቸው?” አለው። |
እጁንም ወደ ደቀ መዛሙርቱ ዘርግቶ እንዲህ አለ፦ “እናቴና ወንድሞቼ እነዚህ ናቸው! |
በሰማይ ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ ሁሉ ለእኔ ወንድሜ፣ እህቴና እናቴ ነውና።” |
በዚያን ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ወደ ኢየሱስ ቀርበው “በመንግሥተ ሰማያት ከሁሉ የሚበልጠው ማን ነው?” አሉት። |
ኢየሱስም አንድ ትንሽ ልጅ ጠርቶ በመካከላቸው በማቆም |
እንዲህ አለ፦ “እውነት እላችኋለሁ፣ ካልተመለሳችሁና እንደ ልጆች ካልሆናችሁ በምንም ዓይነት ወደ መንግሥተ ሰማያት አትገቡም። |
ስለዚህ በመንግሥተ ሰማያት ከሁሉ የሚበልጠው እንደዚህ ትንሽ ልጅ ራሱን ዝቅ የሚያደርግ ነው፤ |
እንዲሁም እንደዚህ ያለውን ትንሽ ልጅ በስሜ የሚቀበል ሁሉ እኔንም ይቀበላል። |
ሆኖም በእኔ ከሚያምኑት ከእነዚህ ከትናንሾቹ አንዱን የሚያሰናክል ሁሉ የወፍጮ ድንጋይ በአንገቱ ታስሮ ጥልቅ ባሕር ውስጥ ቢሰጥም ይሻለዋል። |
“ይህ ዓለም ሰዎችን የሚያሰናክል ነገር ስለሚያስቀምጥ ወዮለት! እርግጥ ማሰናከያ መምጣቱ የማይቀር ነው፤ ነገር ግን በእሱ ጠንቅ ሌሎች እንዲሰናከሉ ለሚያደርግ ሰው ወዮለት! |
እንግዲያው እጅህ ወይም እግርህ ቢያሰናክልህ ቆርጠህ ጣለው። ሁለት እጅ ወይም ሁለት እግር ኖሮህ ወደ ዘላለማዊ እሳት ከምትወረወር ጉንድሽ ወይም አንካሳ ሆነህ ሕይወት ብታገኝ ይሻልሃል። |
እንዲሁም ዓይንህ ቢያሰናክልህ አውጥተህ ጣለው። ሁለት ዓይን ኖሮህ ወደ እሳታማ ገሃነም ከምትወረወር አንድ ዓይን ኖሮህ ሕይወት ብታገኝ ይሻልሃል። |
በሰማይ ያሉት መልአኮቻቸው በሰማይ ባለው አባቴ ፊት ዘወትር ስለሚቀርቡ ከእነዚህ ከትናንሾቹ መካከል አንዱንም እንዳትንቁ ተጠንቀቁ። |
“ምን ይመስላችኋል? አንድ ሰው 100 በጎች ቢኖሩትና ከእነሱ አንዷ ብትጠፋ 99ኙን በተራራ ላይ ትቶ የጠፋችውን ለመፈለግ አይሄድም? |
እውነት እላችኋለሁ፣ የጠፋችውን በግ ካገኛት፣ ካልጠፉት ከ99ኙ ይልቅ በእሷ ይበልጥ ይደሰታል። |
በተመሳሳይም በሰማይ ያለው አባቴ ከእነዚህ ከትናንሾቹ መካከል አንዱም እንኳ እንዲጠፋ አይፈልግም። |
“በተጨማሪም ወንድምህ ቢበድልህ አንተና እሱ ብቻችሁን ሆናችሁ ጥፋቱን በግልጽ ንገረው። ከሰማህ ወንድምህን ታተርፋለህ። |
የማይሰማህ ከሆነ ግን ማንኛውም ጉዳይ ሁለት ወይም ሦስት ምሥክሮች በሚሰጡት የምሥክርነት ቃል ስለሚጸና አንድ ወይም ሁለት ሰው ይዘህ ሂድ። |
እነሱንም ካልሰማ ለጉባኤ ተናገር። ጉባኤውንም እንኳ የማይሰማ ከሆነ እንደ አሕዛብና እንደ ቀረጥ ሰብሳቢ አድርገህ ቁጠረው። |
“እውነት እላችኋለሁ፣ በምድር የምታስሩት ነገር ሁሉ ቀድሞውኑ በሰማያት የታሰረ ይሆናል፤ እንዲሁም በምድር የምትፈቱት ነገር ሁሉ ቀድሞውኑ በሰማያት የተፈታ ይሆናል። |
ደግሞም እውነት እላችኋለሁ፣ በምድር ላይ ከእናንተ መካከል ሁለታችሁ አንድ አስፈላጊ የሆነ ነገር ለመለመን ብትስማሙ በሰማይ ያለው አባቴ ያደርግላችኋል። |
ሁለት ወይም ሦስት ሆነው በስሜ በሚሰበሰቡበት በዚያ በመካከላቸው እገኛለሁና።” |
ከዚያም ጴጥሮስ ወደ ኢየሱስ ቀርቦ “ጌታ ሆይ፣ ወንድሜ ቢበድለኝ ስንት ጊዜ ይቅር ልበለው? እስከ ሰባት ጊዜ ይቅር ልበለው?” አለው። |
ኢየሱስም እንዲህ አለው፦ “እስከ 77 ጊዜ እንጂ እስከ ሰባት ጊዜ ብቻ አልልህም። |
“ስለዚህ መንግሥተ ሰማያት ከባሪያዎቹ ጋር ሒሳብ መተሳሰብ ከፈለገ አንድ ንጉሥ ጋር ይመሳሰላል። |
ሒሳቡን መተሳሰብ በጀመረ ጊዜም 10,000 ታላንት ዕዳ ያለበትን አንድ ሰው አቀረቡለት። |
ሆኖም ሰውየው ዕዳውን የሚከፍልበት ምንም መንገድ ስላልነበረው ጌታው እሱም ሆነ ሚስቱ እንዲሁም ልጆቹና ያለው ንብረት ሁሉ ተሸጠው ዕዳው እንዲከፈል አዘዘ። |
ባሪያውም ወድቆ በመስገድ ‘ጌታዬ ሆይ፣ እባክህ ታገሠኝ፤ ያለብኝን ዕዳ ሁሉ እከፍልሃለሁ’ ሲል ለመነው። |
ጌታውም እጅግ አዘነለትና ለቀቀው፤ ዕዳውንም ሰረዘለት። |
ሆኖም ይህ ባሪያ ወጥቶ ከሄደ በኋላ 100 ዲናር ያበደረውን እንደ እሱ ያለ ባሪያ አግኝቶ ያዘውና አንገቱን አንቆ ‘ያለብህን ዕዳ ክፈለኝ’ አለው። |
ባልንጀራው የሆነው ያ ባሪያም እግሩ ላይ ወድቆ ‘ወንድሜ ሆይ፣ እባክህ ታገሠኝ፤ እከፍልሃለሁ’ ብሎ ይለምነው ጀመር። |
እሱ ግን ፈቃደኛ አልሆነም፤ ከዚህ ይልቅ ሄዶ ያለበትን ዕዳ እስኪከፍል ድረስ ወህኒ ቤት አሳሰረው። |
ባልንጀሮቹ የሆኑ ባሪያዎች የሆነውን ነገር ባዩ ጊዜ እጅግ አዘኑ፤ ሄደውም የሆነውን ነገር ሁሉ ለጌታቸው ነገሩት። |
በዚህ ጊዜ ጌታው አስጠራውና እንዲህ አለው፦ ‘አንተ ክፉ ባሪያ፣ ስለተማጸንከኝ ያን ሁሉ ዕዳ ተውኩልህ። |
ታዲያ እኔ ምሕረት እንዳደረግኩልህ ሁሉ አንተስ ባልንጀራህ ለሆነው ባሪያ ምሕረት ልታደርግለት አይገባም ነበር?’ |
ጌታውም በዚህ እጅግ ተቆጥቶ ያለበትን ዕዳ ሁሉ እስኪከፍል ድረስ ለወህኒ ቤት ጠባቂዎቹ አሳልፎ ሰጠው። |
እናንተም እያንዳንዳችሁ ወንድማችሁን ከልባችሁ ይቅር ካላላችሁ በሰማይ ያለው አባቴ እንደዚሁ ያደርግባችኋል።” |
ከዚያም ኢየሱስ ሕዝቡንና ደቀ መዛሙርቱን እንዲህ አላቸው፦ |
“ጸሐፍትና ፈሪሳውያን በገዛ ሥልጣናቸው የሙሴን ቦታ ወስደዋል። |
ስለዚህ የሚነግሯችሁን ነገር ሁሉ አድርጉ፤ ጠብቁትም፤ ሆኖም የሚናገሩትን በተግባር ስለማያውሉ እነሱ የሚያደርጉትን አታድርጉ። |
ከባድ ሸክም አስረው በሰዎች ትከሻ ላይ ይጭናሉ፤ እነሱ ግን በጣታቸው እንኳ ለመንካት ፈቃደኞች አይደሉም። |
ማንኛውንም ነገር የሚያደርጉት በሰዎች ለመታየት ብለው ነው፤ ለምሳሌ ትልቅ ክታብ ያስራሉ፤ የልብሳቸውንም ዘርፍ ያስረዝማሉ። |
በራት ግብዣ ላይ የክብር ቦታ ማግኘት፣ በምኩራብ ደግሞ ከፊት መቀመጥ ይወዳሉ፤ |
Subsets and Splits
No community queries yet
The top public SQL queries from the community will appear here once available.