text stringlengths 4 267 |
|---|
ደግሞም እነዚህ ሰዎች ራሳቸው ተስፋ እንደሚያደርጉት ጻድቃንም ሆኑ ዓመፀኞች ከሞት እንደሚነሱ በአምላክ ተስፋ አደርጋለሁ። |
በዚህ የተነሳ በአምላክም ሆነ በሰው ፊት ንጹሕ ሕሊና ይዤ ለመኖር ሁልጊዜ ጥረት አደርጋለሁ። |
ከብዙ ዓመታት በኋላም ለወገኖቼ ምጽዋት ለመስጠትና ለአምላክ መባ ለማቅረብ መጣሁ። |
በቤተ መቅደሱ ውስጥ ያገኙኝ የመንጻት ሥርዓት ፈጽሜ ይህንኑ ሳደርግ እንጂ ከብዙ ሕዝብ ጋር ሆኜ ሁከት ሳነሳሳ አልነበረም። ሆኖም ከእስያ አውራጃ የመጡ አንዳንድ አይሁዳውያን ነበሩ፤ |
እነሱ እኔን የሚከሱበት ነገር ካላቸው እዚህ ፊትህ ተገኝተው ሊከሱኝ ይገባ ነበር። |
ወይም እዚህ ያሉት ሰዎች በሳንሄድሪን ሸንጎ ፊት በቀረብኩበት ጊዜ ያገኙብኝ ጥፋት ካለ እነሱ ራሳቸው ይናገሩ፤ |
በመካከላቸው ቆሜ በነበረበት ጊዜ ድምፄን ከፍ አድርጌ ‘ዛሬ በፊታችሁ ለፍርድ የቀረብኩት በሙታን ትንሣኤ በማመኔ ነው!’ ብዬ ከመናገር በቀር ያደረግኩት ነገር የለም።” |
ይሁን እንጂ ፊሊክስ ስለ ጌታ መንገድ በሚገባ ያውቅ ስለነበረ “የሠራዊቱ ሻለቃ ሉስዮስ ሲመጣ ለጉዳያችሁ ውሳኔ እሰጣለሁ” በማለት ያቀረቡትን ክስ ለሌላ ጊዜ አስተላለፈው። |
ከዚያም ጳውሎስ በቁጥጥር ሥር እንዲቆይ፣ ይሁንና መጠነኛ ነፃነት እንዲሰጠው መኮንኑን አዘዘው፤ ደግሞም ወዳጆቹ የሚያስፈልገውን ነገር ለማድረግ ሲመጡ እንዲፈቅድላቸው መመሪያ ሰጠው። |
ከተወሰኑ ቀናት በኋላ ፊሊክስ አይሁዳዊት ከሆነችው ሚስቱ ከድሩሲላ ጋር መጣ፤ ጳውሎስንም አስጠርቶ በክርስቶስ ኢየሱስ ስለ ማመን ሲናገር አዳመጠው። |
ጳውሎስ ስለ ጽድቅ፣ ራስን ስለ መግዛትና ስለሚመጣው ፍርድ ሲናገር ግን ፊሊክስ ፈርቶ “ለአሁኑ ይበቃል፤ አጋጣሚ ሳገኝ ግን እንደገና አስጠራሃለሁ” አለው። |
በዚሁ አጋጣሚ ጳውሎስ ጉቦ ይሰጠኛል ብሎ ተስፋ ያደርግ ስለነበር ብዙ ጊዜ እያስጠራ ያነጋግረው ነበር። |
ይሁንና ሁለት ዓመት ካለፈ በኋላ ፊሊክስ በጶርቅዮስ ፊስጦስ ተተካ፤ በዚህ ጊዜ ፊሊክስ በአይሁዳውያን ዘንድ ተወዳጅነት ማትረፍ ስለፈለገ ጳውሎስን እንደታሰረ ተወው። |
እኛም በመርከብ ወደ ጣሊያን እንድንሄድ ስለተወሰነ ጳውሎስንና የተወሰኑ እስረኞችን የአውግስጦስ ክፍለ ጦር አባል ለሆነ ዩልዮስ ለሚባል አንድ የጦር መኮንን አስረከቧቸው። |
ከአድራሚጢስ ተነስቶ በእስያ አውራጃ የባሕር ዳርቻ ላይ ወደሚገኙት ወደቦች ሊሄድ በተዘጋጀ መርከብ ተሳፍረን ጉዞ ጀመርን፤ በተሰሎንቄ የሚኖረው የመቄዶንያው አርስጥሮኮስም አብሮን ነበር። |
በማግስቱ ሲዶና ደረስን፤ ዩልዮስም ለጳውሎስ ደግነት በማሳየት ወደ ወዳጆቹ እንዲሄድና እንክብካቤ እንዲያደርጉለት ፈቀደለት። |
ከዚያም ተነስተን በባሕር ላይ ጉዟችንን ቀጠልን፤ ነፋሱ ከፊት ለፊታችን ይነፍስ ስለነበር ቆጵሮስን ተገን አድርገን አለፍን። |
ከዚያም በኪልቅያና በጵንፍልያ ዳርቻ በኩል ያለውን ባሕር አቋርጠን በሊቂያ ወደሚገኘው የሚራ ወደብ ደረስን። |
በዚያም መኮንኑ ወደ ጣሊያን የሚሄድ ከእስክንድርያ የመጣ መርከብ አግኝቶ አሳፈረን። |
ከዚያም ለብዙ ቀናት በዝግታ ተጉዘን በስንት ችግር ቀኒዶስ ደረስን። ነፋሱ እንደ ልብ እንድንጓዝ ስላልፈቀደልን በስልሞና በኩል ቀርጤስን ተገን አድርገን አለፍን። |
የባሕሩን ዳርቻ ይዘን በብዙ ችግር በመጓዝ በላሲያ ከተማ አቅራቢያ ወዳለው “መልካም ወደብ” ወደተባለ ስፍራ ደረስን። |
ረጅም ጊዜ በመቆየታችንና የስርየት ቀን ጾም እንኳ ሳይቀር በማለፉ፣ ወቅቱ በባሕር ላይ ለመጓዝ አደገኛ ነበር፤ በመሆኑም ጳውሎስ አንድ ሐሳብ አቀረበ፤ |
እንዲህም አላቸው፦ “እናንተ ሰዎች፣ ይህ ጉዞ በጭነቱና በመርከቡ ላይ ብቻ ሳይሆን በሕይወታችንም ላይ እንኳ ሳይቀር ከፍተኛ ጉዳትና ጥፋት ሊያስከትል እንደሚችል ይታየኛል።” |
ይሁን እንጂ መኮንኑ ጳውሎስ የተናገረውን ከመቀበል ይልቅ የመርከቡ መሪና የመርከቡ ባለቤት የተናገሩትን ሰማ። |
ወደቡ የክረምቱን ጊዜ በዚያ ለማሳለፍ አመቺ ስላልነበረ አብዛኞቹ ከዚያ ተነስተው ጉዟቸውን በመቀጠል እንደ ምንም ፊንቄ ወደተባለው የቀርጤስ ወደብ ደርሰው ክረምቱን እዚያ ለማሳለፍ ሐሳብ አቀረቡ፤ ይህ ወደብ ወደ ሰሜን ምሥራቅም ሆነ ወደ ደቡብ ምሥራቅ ለመሄድ የሚያስችል ነበር። |
የደቡብ ነፋስ በቀስታ እየነፈሰ እንዳለ ባዩ ጊዜ እንዳሰቡት የሆነላቸው መስሏቸው መልሕቁን ነቅለው የቀርጤስን የባሕር ዳርቻ ይዘው መጓዝ ጀመሩ። |
ይሁንና ብዙም ሳይቆይ አውራቂስ የሚባል ኃይለኛ አውሎ ነፋስ ከደሴቲቱ ቁልቁል ነፈሰ። |
መርከቡ እንቅስቃሴው ስለተገታና ነፋሱን ሰንጥቆ መሄድ ስላልቻለ ዝም ብለን በነፋሱ እየተነዳን ሄድን። |
ከዚያም ቄዳ የተባለችውን ትንሽ ደሴት ተገን አድርገን በፍጥነት ተጓዝን፤ ሆኖም በመርከቡ ኋለኛ ክፍል የነበረችውን ትንሿን ጀልባ መቆጣጠር የቻልነው በብዙ ችግር ነበር። |
ጀልባዋ ወደ ላይ ተጎትታ ከተጫነች በኋላ መርከቡን ዙሪያውን በማሰር አጠናከሩት፤ ከስርቲስ አሸዋማ ደለል ጋር እንዳይላተሙ ስለፈሩም የሸራውን ገመዶች በመፍታት ሸራውን ዝቅ ካደረጉ በኋላ በነፋስ እየተነዱ ሄዱ። |
አውሎ ነፋሱ ክፉኛ እያንገላታን ስለነበር በማግስቱ የመርከቡን ጭነት ያቃልሉ ጀመር። |
በሦስተኛውም ቀን ለመርከቡ የሚያገለግሉትን ቁሳቁሶች በገዛ እጃቸው ወደ ባሕሩ ወረወሩ። |
ለብዙ ቀናት ፀሐይንም ሆነ ከዋክብትን ማየት ስላልቻልንና ውሽንፍሩ ስለበረታብን በመጨረሻ በሕይወት የመትረፍ ተስፋችን እየተሟጠጠ ሄደ። |
ሰዎቹ እህል ሳይቀምሱ ብዙ ቀን ከቆዩ በኋላ ጳውሎስ በመካከላቸው ቆሞ እንዲህ አለ፦ “እናንተ ሰዎች፣ ምክሬን ሰምታችሁ ቢሆን ኖሮ ከቀርጤስ ባልተነሳችሁና ይህ ጉዳትና ኪሳራ ባልደረሰ ነበር። |
አሁንም ቢሆን አይዟችሁ! ምክንያቱም መርከቡ ብቻ እንጂ ከእናንተ አንድም ሰው አይጠፋም። |
ቅዱስ አገልግሎት የማቀርብለትና ንብረቱ የሆንኩለት አምላክ የላከው መልአክ ትናንት ሌሊት አጠገቤ ቆሞ |
‘ጳውሎስ ሆይ፣ አትፍራ። ቄሳር ፊት መቅረብ ይገባሃል፤ አምላክ ለአንተ ሲል ከአንተ ጋር የሚጓዙት ሰዎች ሁሉ እንዲተርፉ ያደርጋል’ ብሎኛል። |
ስለዚህ እናንተ ሰዎች፣ አይዟችሁ! ምክንያቱም ይህ የተነገረኝ ነገር በትክክል እንደሚፈጸም በአምላክ ላይ እምነት አለኝ። |
ይሁን እንጂ ከአንዲት ደሴት ዳርቻ ጋር መላተማችን የግድ ነው።” |
በ14ኛው ሌሊት በአድርያ ባሕር ላይ ወዲያና ወዲህ እየተንገላታን ሳለ እኩለ ሌሊት ላይ መርከበኞቹ ወደ አንድ የብስ የተቃረቡ መሰላቸው። |
ጥልቀቱንም ሲለኩ 36 ሜትር ገደማ ሆኖ አገኙት፤ ጥቂት ርቀት ከተጓዙም በኋላ በድጋሚ ሲለኩ 27 ሜትር ገደማ ሆኖ አገኙት። |
ከዓለት ጋር እንላተማለን ብለው ስለፈሩ ከመርከቡ የኋለኛ ክፍል አራት መልሕቆች ጥለው የሚነጋበትን ጊዜ በጉጉት መጠባበቅ ጀመሩ። |
ሆኖም መርከበኞቹ ከመርከቡ የፊተኛ ክፍል መልሕቅ የሚጥሉ አስመስለው ትንሿን ጀልባ ወደ ባሕር በማውረድ ከመርከቡ ለማምለጥ ሲሞክሩ |
ጳውሎስ መኮንኑንና ወታደሮቹን “እነዚህ ሰዎች መርከቡን ጥለው ከሄዱ ልትድኑ አትችሉም” አላቸው። |
በዚህ ጊዜ ወታደሮቹ የትንሿን ጀልባ ገመዶች ቆርጠው ብቻዋን ተንሳፋ እንድትቀር አደረጓት። |
ሊነጋ ሲል ጳውሎስ እንዲህ በማለት ምግብ እንዲቀምሱ ሁሉንም አበረታታቸው፦ “እህል የሚባል ነገር ሳትቀምሱ እንዲሁ ልባችሁ ተንጠልጥሎ ስትጠባበቁ ይኸው ዛሬ 14ኛ ቀናችሁ ነው። |
ስለዚህ ለራሳችሁ ደህንነት ስለሚበጅ እህል እንድትቀምሱ እለምናችኋለሁ፤ ምክንያቱም ከእናንተ መካከል ከራስ ፀጉሩ አንድ እንኳ የሚጠፋበት የለም።” |
ይህን ካለ በኋላ ዳቦ ወስዶ በሁሉ ፊት አምላክን አመሰገነ፤ ቆርሶም ይበላ ጀመር። |
በዚህ ጊዜ ሁሉም ተበረታተው ምግብ እየወሰዱ ይበሉ ጀመር። |
መርከቡ ላይ በአጠቃላይ 276 ሰዎች ነበርን። |
በልተው ከጠገቡ በኋላ ስንዴውን ወደ ባሕሩ በመጣል የመርከቡን ጭነት አቃለሉ። |
ሲነጋም የደረሱበትን አገር ለይተው ማወቅ አልቻሉም፤ ሆኖም አሸዋማ የሆነ የባሕር ወሽመጥ ተመለከቱ፤ ስለዚህ እንደ ምንም ብለው መርከቡን ወደ ባሕሩ ዳርቻ ለማድረስ ወሰኑ። |
በመሆኑም መልሕቆቹን ቆርጠው ባሕሩ ውስጥ ጣሉ፤ በዚያው ጊዜም የመቅዘፊያዎቹን ገመዶች ፈቱ፤ የፊተኛውንም ሸራ ነፋስ እንዲያገኘው ከፍ ካደረጉ በኋላ ወደ ባሕሩ ዳርቻ አመሩ። |
ሆኖም ድንገት በባሕር ውስጥ ካለ የአሸዋ ቁልል ጋር ተላተሙ፤ በዚህ ጊዜ መርከቡ መሬት ስለነካ የፊተኛው ክፍሉ ሊንቀሳቀስ በማይችል ሁኔታ አሸዋው ውስጥ ተቀረቀረ፤ የመርከቡ የኋለኛ ክፍል ግን በማዕበል እየተመታ ይሰባበር ጀመር። |
በዚህ ጊዜ ወታደሮቹ ከእስረኞቹ አንዳቸውም እንኳ ዋኝተው እንዳያመልጡ ሊገድሏቸው ወሰኑ። |
መኮንኑ ግን ጳውሎስን ለማዳን ቆርጦ ስለነበር ያሰቡትን እንዳይፈጽሙ ከለከላቸው። ከዚያም መዋኘት የሚችሉ ወደ ባሕሩ እየዘለሉ እንዲገቡና ቀድመው ወደ የብስ እንዲደርሱ አዘዘ፤ |
የቀሩትም ሰዎች አንዳንዶቹ በሳንቃዎች፣ ሌሎቹ ደግሞ በመርከቡ ስብርባሪዎች ላይ እየተንጠላጠሉ እንዲወጡ አዘዘ። በዚህ መንገድ ሁሉም በደህና ወደ የብስ ደረሱ። |
በጴንጤቆስጤ በዓል ቀን ሁሉም በአንድ ቦታ ተሰብስበው ነበር። |
ድንገትም እንደ ኃይለኛ ነፋስ ያለ ድምፅ ከሰማይ መጣ፤ ተቀምጠውበት የነበረውንም ቤት ሞላው። |
የእሳት ምላሶች የሚመስሉም ታዩአቸው፤ ተከፋፍለውም በእያንዳንዳቸው ላይ አረፉ፤ |
ሁሉም በመንፈስ ቅዱስ ተሞሉ፤ መንፈስም እንዲናገሩ ባስቻላቸው መሠረት በተለያዩ ቋንቋዎች ይናገሩ ጀመር። |
በዚያን ጊዜ በምድር ዙሪያ ካለ አገር ሁሉ የመጡ ለአምላክ ያደሩ አይሁዳውያን በኢየሩሳሌም ነበሩ። |
ስለዚህ ይህ ድምፅ በተሰማ ጊዜ ብዙ ሕዝብ ተሰበሰበ፤ እያንዳንዱም ሰው ደቀ መዛሙርቱ በገዛ ቋንቋው ሲናገሩ በመስማቱ ግራ ተጋባ። |
ደግሞም ሕዝቡ እጅግ ተደንቀው እንዲህ አሉ፦ “እንዴ፣ እነዚህ እየተናገሩ ያሉት የገሊላ ሰዎች አይደሉም? |
ታዲያ እያንዳንዳችን በአገራችን ቋንቋ ሲናገሩ የምንሰማው እንዴት ነው? |
እኛ ከጳርቴና፣ ከሜዶን፣ ከኤላም፣ ከሜሶጶጣሚያ፣ ከይሁዳ፣ ከቀጰዶቅያ፣ ከጳንጦስ፣ ከእስያ አውራጃ፣ |
ከፍርግያ፣ ከጵንፍልያ፣ ከግብፅ፣ በቀሬና አቅራቢያ ካሉት የሊቢያ አውራጃዎችና ከሮም የመጣን አይሁዶችና ወደ ይሁዲነት የተለወጥን ሰዎች፣ |
የቀርጤስና የዓረብ ሰዎች ሁላችን ስለ አምላክ ታላቅ ሥራ በየቋንቋችን ሲናገሩ እየሰማናቸው ነው።” |
ስለዚህ ሁሉም ተገርመውና ግራ ተጋብተው እርስ በርሳቸው “ይህ ነገር ምን ይሆን?” ይባባሉ ነበር። |
ይሁን እንጂ ሌሎች “ያልፈላ የወይን ጠጅ ተግተው ነው” በማለት አፌዙባቸው። |
ጴጥሮስ ግን ከአሥራ አንዱ ጋር ተነስቶ በመቆም ድምፁን ከፍ አድርጎ እንዲህ ሲል ለሕዝቡ ተናገረ፦ “እናንተ የይሁዳ ሰዎችና የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ሁሉ፣ አንድ ማወቅ ያለባችሁ ነገር ስላለ ንግግሬን በጥሞና አዳምጡ። |
ጊዜው ገና ከጠዋቱ ሦስት ሰዓት ስለሆነ እነዚህ ሰዎች እናንተ እንዳሰባችሁት አልሰከሩም። |
ከዚህ ይልቅ ይህ የሆነው በነቢዩ ኢዩኤል በኩል እንዲህ ተብሎ በተነገረው መሠረት ነው፦ |
‘አምላክ እንዲህ ይላል፦ “በመጨረሻው ቀን በሥጋ ለባሽ ሁሉ ላይ ከመንፈሴ አፈሳለሁ፤ ወንዶች ልጆቻችሁና ሴቶች ልጆቻችሁም ትንቢት ይናገራሉ፤ ወጣቶቻችሁ ራእዮችን ያያሉ፤ ሽማግሌዎቻችሁም ሕልም ያልማሉ፤ |
በዚያ ቀን በወንዶች ባሪያዎቼና በሴቶች ባሪያዎቼ ላይ ሳይቀር ከመንፈሴ አፈሳለሁ፤ እነሱም ትንቢት ይናገራሉ። |
በላይ በሰማይ ድንቅ ነገሮች፣ በታች በምድር ደግሞ ተአምራዊ ምልክቶች አሳያለሁ፤ ደም፣ እሳትና የጭስ ደመናም ይታያል። |
ታላቁና ክብራማው የይሖዋ ቀን ከመምጣቱ በፊት ፀሐይ ወደ ጨለማ፣ ጨረቃም ወደ ደም ይለወጣሉ። |
የይሖዋን ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናል።”’ |
“የእስራኤል ሰዎች ሆይ፣ ይህን ቃል ስሙ፦ እናንተ ራሳችሁ እንደምታውቁት፣ አምላክ በኢየሱስ አማካኝነት በመካከላችሁ የፈጸማቸው ተአምራት፣ ድንቅ ነገሮችና ምልክቶች የናዝሬቱ ኢየሱስ በአምላክ የተላከ ሰው እንደሆነ የሚያሳዩ ማስረጃዎች ናቸው። |
ይህ ሰው ለሞት አልፎ ተሰጠ። ይህም አምላክ አስቀድሞ የወሰነው ፈቃዱና የሚያውቀው ነገር ነበር። እናንተም በክፉ ሰዎች እጅ በእንጨት ላይ ሰቅላችሁ ገደላችሁት። |
አምላክ ግን ከሞት ጣር አላቆ አስነሳው፤ ምክንያቱም ሞት ይዞ ሊያስቀረው አልቻለም። |
ዳዊትም ስለ እሱ እንዲህ ይላል፦ ‘ይሖዋን ሁልጊዜ በፊቴ አደርገዋለሁ፤ እሱ በቀኜ ስለሆነ ፈጽሞ አልናወጥም። |
ስለዚህ ልቤ ደስ አለው፤ አንደበቴም ሐሴት አደረገ። እኔም በተስፋ እኖራለሁ፤ |
ምክንያቱም በመቃብር አትተወኝም፤ ታማኝ አገልጋይህም መበስበስን እንዲያይ አትፈቅድም። |
የሕይወትን መንገድ አሳውቀኸኛል፤ በፊትህ በታላቅ ደስታ እንድሞላ ታደርገኛለህ።’ |
“ወንድሞች፣ ከቀድሞ አባቶች አንዱ የሆነው ዳዊት እንደሞተና እንደተቀበረ እንዲሁም መቃብሩ እስከ ዛሬ ድረስ በእኛ ዘንድ እንደሚገኝ ለእናንተ በግልጽ እንድናገር ፍቀዱልኝ። |
እሱ ነቢይ ስለነበረና አምላክ ከዘሮቹ አንዱን በዙፋኑ ላይ እንደሚያስቀምጥ በመሐላ ቃል እንደገባለት ስላወቀ |
አምላክ ክርስቶስን በመቃብር እንደማይተወውና ሥጋውም እንደማይበሰብስ አስቀድሞ ተረድቶ ስለ ትንሣኤው ተናገረ። |
ይህን ኢየሱስን አምላክ ከሞት አስነሳው፤ እኛ ሁላችንም ለዚህ ነገር ምሥክሮች ነን። |
ስለዚህ ወደ አምላክ ቀኝ ከፍ ከፍ ስለተደረገና ቃል የተገባውን ቅዱስ መንፈስ ከአብ ስለተቀበለ ይህን የምታዩትንና የምትሰሙትን አፈሰሰው። |
ዳዊት ወደ ሰማያት አልወጣምና፤ ሆኖም እሱ ራሱ እንዲህ ሲል ተናግሯል፦ ‘ይሖዋ ጌታዬን እንዲህ ብሎታል፦ “በቀኜ ተቀመጥ፤ |
ጠላቶችህን ለእግርህ መርገጫ እስከማደርግልህ ድረስ በቀኜ ሁን።”’ |
ስለዚህ ይህን እናንተ በእንጨት ላይ የሰቀላችሁትን ኢየሱስን አምላክ ጌታም ክርስቶስም እንዳደረገው የእስራኤል ቤት ሁሉ በእርግጥ ይወቅ።” |
ሰዎቹም ይህን በሰሙ ጊዜ ልባቸው እጅግ ተነክቶ ጴጥሮስንና የቀሩትን ሐዋርያት “ወንድሞች፣ ታዲያ ምን ብናደርግ ይሻላል?” አሏቸው። |
ጴጥሮስም እንዲህ አላቸው፦ “ንስሐ ግቡ፤ እያንዳንዳችሁም ለኃጢአታችሁ ይቅርታ እንድታገኙ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ፤ የመንፈስ ቅዱስንም ነፃ ስጦታ ትቀበላላችሁ። |
ምክንያቱም የተስፋው ቃል ለእናንተና ለልጆቻችሁ እንዲሁም ይሖዋ አምላካችን ወደ ራሱ ለሚጠራቸው በሩቅ ላሉ ሁሉ ነው።” |
በሌላ ብዙ ቃልም በሚገባ መሠከረላቸው፤ “ከዚህ ጠማማ ትውልድ ዳኑ” እያለም አጥብቆ አሳሰባቸው። |
ስለዚህ ቃሉን በደስታ የተቀበሉ ተጠመቁ፤ በዚያም ቀን 3,000 ገደማ የሚሆኑ ሰዎች ተጨመሩ። |
የሐዋርያቱንም ትምህርት በትኩረት መከታተላቸውን ቀጠሉ፤ አንድ ላይ ይሰበሰቡ፣ ምግባቸውንም አብረው ይበሉ እንዲሁም በጸሎት ይተጉ ነበር። |
ሰው ሁሉ ፍርሃት አደረበት፤ ሐዋርያቱም ብዙ ድንቅ ነገሮችና ተአምራዊ ምልክቶች ያደርጉ ጀመር። |
Subsets and Splits
No community queries yet
The top public SQL queries from the community will appear here once available.