text
stringlengths
4
267
ድንግል የሆኑትን በተመለከተ ከጌታ የተቀበልኩት ትእዛዝ የለኝም፤ ይሁን እንጂ ጌታ ካሳየኝ ምሕረት የተነሳ እንደ ታማኝ ሰው የራሴን ሐሳብ እሰጣለሁ።
ስለዚህ አሁን ካለው ችግር አንጻር አንድ ሰው ባለበት ሁኔታ ቢቀጥል የተሻለ ይመስለኛል።
በሚስት ታስረሃል? ከሆነ መፈታትን አትሻ። ሚስት የሌለህ ነህ? ከሆነ ሚስት ለማግባት አትፈልግ።
ይሁንና ብታገባም ኃጢአት ይሆንብሃል ማለት አይደለም። እንዲሁም ድንግል የሆነ ሰው ቢያገባ ኃጢአት ይሆንበታል ማለት አይደለም። ይሁን እንጂ የሚያገቡ ሰዎች በሥጋቸው ላይ መከራ ይደርስባቸዋል። ነገር ግን የእኔ ምኞት ከዚህ እንድትድኑ ነው።
ከዚህም በላይ ወንድሞች፣ የቀረው ጊዜ አጭር መሆኑን ልነግራችሁ እወዳለሁ። ከእንግዲህ ወዲህ ሚስት ያላቸው እንደሌላቸው ይሁኑ፤
የሚያለቅሱም እንደማያለቅሱ፣ የሚደሰቱም እንደማይደሰቱ፣ የሚገዙም ምንም እንደሌላቸው
እንዲሁም በዓለም የሚጠቀሙ ሰዎች ሙሉ በሙሉ እንደማይጠቀሙበት ይሁኑ፤ የዚህ ዓለም ትእይንት እየተለዋወጠ ነውና።
በመሆኑም ከጭንቀት ነፃ እንድትሆኑ እፈልጋለሁ። ያላገባ ሰው ጌታን እንዴት ደስ ማሰኘት እንደሚችል በማሰብ ስለ ጌታ ነገር ይጨነቃል።
ያገባ ሰው ግን ሚስቱን እንዴት ደስ ማሰኘት እንደሚችል በማሰብ ስለ ዓለም ነገር ይጨነቃል፤
በመሆኑም ሐሳቡ ተከፋፍሏል። በተጨማሪም ያላገባች ሴትም ሆነች ድንግል በአካሏም ሆነ በመንፈሷ ቅዱስ መሆን ትችል ዘንድ ስለ ጌታ ነገር ትጨነቃለች። ይሁን እንጂ ያገባች ሴት ባሏን እንዴት ደስ ማሰኘት እንደምትችል በማሰብ ስለ ዓለም ነገር ትጨነቃለች።
ይህን የምለው ግን ለእናንተው ጥቅም ብዬ ነው እንጂ ነፃነት ላሳጣችሁ ብዬ አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ ተስማሚ የሆነውን ነገር እንድታደርጉና ሐሳባችሁ ሳይከፋፈል ዘወትር ለጌታ ያደራችሁ እንድትሆኑ ላነሳሳችሁ ብዬ ነው።
ይሁንና አንድ ሰው ሳያገባ ቀርቶ ራሱን መቆጣጠር እንደተሳነው ከተሰማው፣ በተለይ ደግሞ አፍላ የጉርምስና ዕድሜን ያለፈ ከሆነና ማግባቱ የሚመረጥ ከሆነ የፈለገውን ያድርግ፤ ኃጢአት አይሆንበትም። እንዲህ ያሉ ሰዎች ያግቡ።
ሆኖም አንድ ሰው ልቡ ከቆረጠና ይህን ማድረግ እንደማያስፈልገው ከተሰማው፣ ደግሞም ራሱን መግዛት የሚችል ከሆነና ሳያገባ ለመኖር በልቡ ከወሰነ መልካም ያደርጋል።
ስለዚህ የሚያገባ ሁሉ መልካም ያደርጋል፤ ሳያገባ የሚኖር ሁሉ ደግሞ የተሻለ ያደርጋል።
አንዲት ሚስት ባሏ በሕይወት ባለበት ዘመን ሁሉ የታሰረች ናት። ባሏ በሞት ካንቀላፋ ግን በጌታ ብቻ ይሁን እንጂ ከፈለገችው ሰው ጋር ለመጋባት ነፃ ናት።
እንደ እኔ ከሆነ ግን እንዳለች ብትቀጥል ይበልጥ ደስተኛ ትሆናለች፤ እኔ ደግሞ የአምላክ መንፈስ እንዳለኝ እርግጠኛ ነኝ።
በሰዎችና በመላእክት ልሳን ብናገር ፍቅር ግን ከሌለኝ በኃይል እንደሚጮኽ ደወል ወይም ሲምባል ሆኛለሁ።
የመተንበይ ስጦታ ቢኖረኝ፣ ቅዱስ ሚስጥርን ሁሉና እውቀትን ሁሉ ባውቅ እንዲሁም ተራራን ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ማንቀሳቀስ የሚያስችል እምነት ቢኖረኝ፣ ፍቅር ግን ከሌለኝ ከንቱ ነኝ።
ሌሎችን ለመመገብ ያለኝን ሁሉ ብሰጥ እንዲሁም እኩራራ ዘንድ ሰውነቴን አሳልፌ ብሰጥ ፍቅር ግን ከሌለኝ ምንም የማገኘው ጥቅም የለም።
ፍቅር ታጋሽና ደግ ነው። ፍቅር አይቀናም። ጉራ አይነዛም፣ አይታበይም፣
ጨዋነት የጎደለው ምግባር አያሳይም፣ የራሱን ፍላጎት አያስቀድምም፣ በቀላሉ አይበሳጭም። ፍቅር የበደል መዝገብ የለውም።
ፍቅር በዓመፅ አይደሰትም፤ ከዚህ ይልቅ ከእውነት ጋር ደስ ይለዋል።
ሁሉን ችሎ ያልፋል፣ ሁሉን ያምናል፣ ሁሉን ተስፋ ያደርጋል፣ ሁሉን ነገር በጽናት ይቋቋማል።
ፍቅር ለዘላለም ይኖራል። ሆኖም የመተንበይ፣ በልሳን የመናገርም ሆነ የእውቀት ስጦታ ይቀራል።
እውቀታችን ከፊል ነውና፤ ትንቢት የምንናገረውም በከፊል ነው፤
የተሟላው ሲመጣ ግን ከፊል የሆነው ይቀራል።
ልጅ በነበርኩበት ጊዜ እንደ ልጅ እናገር፣ እንደ ልጅ አስብ እንዲሁም እንደ ልጅ አመዛዝን ነበር፤ አሁን ሙሉ ሰው ከሆንኩ በኋላ ግን የልጅነትን ጠባይ ትቻለሁ።
አሁን በብረት መስተዋት ብዥ ያለ ምስል ይታየናል፤ በዚያን ጊዜ ግን ፊት ለፊት የማየት ያህል በግልጽ ይታየናል። አሁን ስለ አምላክ የማውቀው በከፊል ነው፤ በዚያን ጊዜ ግን እሱ እኔን በትክክል የሚያውቀኝን ያህል የተሟላ እውቀት ይኖረኛል።
ይሁን እንጂ እምነት፣ ተስፋ፣ ፍቅር፣ እነዚህ ሦስቱ ይቀጥላሉ፤ ከእነዚህ መካከል የሚበልጠው ግን ፍቅር ነው።
በመሆኑም ወንድሞች፣ ከክርስቶስ ጋር በተያያዘ ገና ሕፃናት እንደሆኑ እንደ ሥጋውያን ሰዎች እንጂ እንደ መንፈሳውያን ሰዎች ላነጋግራችሁ አልቻልኩም።
ጠንካራ ስላልነበራችሁ ወተት እንጂ ጠንካራ ምግብ አልመገብኳችሁም። አሁንም ቢሆን ገና አልጠነከራችሁም፤
ደግሞም ገና ሥጋውያን ናችሁ። ቅናትና ጠብ በመካከላችሁ ስላለ ሥጋውያን መሆናችሁ፣ ደግሞም በዓለም እንዳሉ ሰዎች መመላለሳችሁ አይደለም?
አንዱ “እኔ የጳውሎስ ነኝ፣” ሌላው ደግሞ “እኔ የአጵሎስ ነኝ” ሲል እንደ ማንኛውም ሰው መሆናችሁ አይደለም?
ለመሆኑ አጵሎስ ምንድን ነው? ጳውሎስስ ምንድን ነው? ጌታ የሰጣቸውን ሥራ የሚያከናውኑ አገልጋዮች ናቸው፤ እናንተም አማኞች የሆናችሁት በእነሱ አማካኝነት ነው።
እኔ ተከልኩ፤ አጵሎስ አጠጣ፤ ያሳደገው ግን አምላክ ነው፤
ስለዚህ ምስጋና የሚገባው የሚያሳድገው አምላክ እንጂ የሚተክለውም ሆነ የሚያጠጣው አይደለም።
የሚተክለውም ሆነ የሚያጠጣው በኅብረት የሚሠሩ ናቸው፤ ሆኖም እያንዳንዱ ሰው እንደ ሥራው መጠን የራሱን ወሮታ ይቀበላል።
እኛ ከአምላክ ጋር አብረን የምንሠራ ነንና። እናንተ በመልማት ላይ ያለ የአምላክ እርሻ ናችሁ፤ የአምላክ ሕንፃ ናችሁ።
በተሰጠኝ የአምላክ ጸጋ መሠረት በሙያው እንደተካነ ግንበኛ እኔ መሠረት ጣልኩ፤ ሌላው ደግሞ በዚያ ላይ ይገነባል። ሆኖም እያንዳንዱ በዚያ ላይ እንዴት እንደሚገነባ በጥንቃቄ ሊያስብ ይገባል።
ማንም ሰው ከተጣለው መሠረት ሌላ አዲስ መሠረት መጣል አይችልምና፤ ይህም መሠረት ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።
ማንም በዚህ መሠረት ላይ በወርቅ፣ በብር፣ በከበሩ ድንጋዮች፣ በእንጨት፣ በሣር ወይም በአገዳ ቢገነባ
የፈተናው ቀን ሲመጣ የእያንዳንዱ ሥራ ይገለጣል፤ እሳቱ ሁሉንም ነገር ይገልጣልና፤ እንዲሁም እያንዳንዱ ሰው ምን ዓይነት ግንባታ እንዳከናወነ እሳቱ ራሱ ፈትኖ ያሳያል።
ማንም በመሠረቱ ላይ የገነባው ነገር ቢጸናለት ወሮታ ያገኛል፤
ይሁንና ማንም ሰው የሠራው ሥራ ቢቃጠል ኪሳራ ይደርስበታል፤ እሱ ግን ይተርፋል፤ ሆኖም በእሳት ውስጥ አልፎ የመትረፍ ያህል ይሆናል።
እናንተ ራሳችሁ የአምላክ ቤተ መቅደስ እንደሆናችሁና የአምላክ መንፈስ በእናንተ ውስጥ እንደሚያድር አታውቁም?
ማንም የአምላክን ቤተ መቅደስ ቢያፈርስ አምላክ ያፈርሰዋል፤ የአምላክ ቤተ መቅደስ ቅዱስ ነውና፤ ቤተ መቅደሱም እናንተ ናችሁ።
ማንም ራሱን አያታል፤ ከእናንተ መካከል ማንም በዚህ ሥርዓት ጥበበኛ እንደሆነ ቢያስብ፣ ጥበበኛ መሆን ይችል ዘንድ ሞኝ ይሁን።
ምክንያቱም የዚህ ዓለም ጥበብ በአምላክ ፊት ሞኝነት ነው፤ “ጥበበኞችን በራሳቸው ተንኮል ይይዛቸዋል” ተብሎ ተጽፏልና።
ደግሞም “ይሖዋ የጥበበኞች ሐሳብ ከንቱ እንደሆነ ያውቃል” ተብሏል።
በመሆኑም ማንም በሰዎች አይኩራራ፤ ሁሉም ነገር የእናንተ ነውና፤
ጳውሎስም ቢሆን አጵሎስም ቢሆን ኬፋም ቢሆን ዓለምም ቢሆን ሕይወትም ቢሆን ሞትም ቢሆን አሁን ያሉት ነገሮችም ቢሆኑ የሚመጡትም ነገሮች ቢሆኑ ሁሉም ነገር የእናንተ ነው፤
እናንተም የክርስቶስ ናችሁ፤ ክርስቶስ ደግሞ የአምላክ ነው።
እኔ ነፃ ሰው አይደለሁም? ሐዋርያስ አይደለሁም? ደግሞስ ጌታችንን ኢየሱስን አላየሁትም? እናንተ በጌታ የሥራዬ ውጤት አይደላችሁም?
ለሌሎች ሐዋርያ ባልሆን እንኳ ለእናንተ ሐዋርያ እንደሆንኩ የተረጋገጠ ነው! እናንተ የጌታ ሐዋርያ መሆኔን የሚያረጋግጥ ማኅተም ናችሁና።
ለሚመረምሩኝ የማቀርበው የመከላከያ መልስ ይህ ነው፦
እኛ የመብላትና የመጠጣት መብት የለንም እንዴ?
እንደ ሌሎቹ ሐዋርያትና እንደ ጌታ ወንድሞች እንዲሁም እንደ ኬፋ አማኝ የሆነች ሚስት ይዘን የመዞር መብት የለንም?
ወይስ ሰብዓዊ ሥራ የመተው መብት የሌለን እኔና በርናባስ ብቻ ነን?
ለመሆኑ በራሱ ወጪ ወታደር ሆኖ የሚያገለግል ማን ነው? ወይን ተክሎ ፍሬውን የማይበላ ማን ነው? ወይስ መንጋ እየጠበቀ ከመንጋው ወተት የተወሰነ ድርሻ የማያገኝ ማን ነው?
ይህን የምለው ከሰብዓዊ አመለካከት አንጻር ነው? ሕጉስ ቢሆን እንዲህ አይልም?
በሙሴ ሕግ “እህል እያበራየ ያለውን በሬ አፉን አትሰር” ተብሎ ተጽፏልና። አምላክ ይህን የተናገረው ስለ በሬዎች ተጨንቆ ነው?
እንዲህ ያለው ስለ እኛ በማሰብ አይደለም? እንዲህ ተብሎ የተጻፈው በእርግጥ ስለ እኛ ነው፤ ምክንያቱም አራሹም ሆነ የሚያበራየው ሰው ሥራቸውን የሚያከናውኑት ከምርቱ ድርሻ እንደሚኖራቸው ተስፋ በማድረግ ነው።
እኛ በእናንተ መካከል መንፈሳዊ ነገሮች ከዘራን ከእናንተ ሥጋዊ ነገሮች ብናጭድ ትልቅ ነገር መሆኑ ነው?
ሌሎች የእናንተን ድጋፍ የማግኘት መብት ካላቸው እኛ ከእነሱ የበለጠ መብት የለንም? ይሁንና እኛ በዚህ መብት አልተጠቀምንም፤ ከዚህ ይልቅ ስለ ክርስቶስ የሚሰበከውን ምሥራች የሚያደናቅፍ ምንም ነገር ላለመፍጠር ሁሉን ችለን እንኖራለን።
ቅዱስ አገልግሎት የሚያከናውኑት ሰዎች ከቤተ መቅደስ የሚያገኙትን ምግብ እንደሚመገቡ እንዲሁም ዘወትር በመሠዊያው የሚያገለግሉ ከመሠዊያው የራሳቸውን ድርሻ እንደሚያገኙ አታውቁም?
በተመሳሳይም ምሥራቹን የሚያውጁ ሰዎች በምሥራቹ አማካኝነት በሚያገኙት ነገር እንዲኖሩ ጌታ አዟል።
ይሁን እንጂ እኔ ከእነዚህ ዝግጅቶች በአንዱም አልተጠቀምኩም። እርግጥ ይህን የጻፍኩት እንዲህ ሊደረግልኝ ይገባል ለማለት አይደለም፤ ማንም ሰው የምኮራበትን ነገር ከሚያሳጣኝ ብሞት ይሻለኛልና!
አሁን ምሥራቹን እየሰበክሁ ብሆንም ለመኩራራት ምክንያት አይሆነኝም፤ እንዲህ የማድረግ ግዴታ ተጥሎብኛልና። እንዲያውም ምሥራቹን ባልሰብክ ወዮልኝ!
ይህን በፈቃደኝነት ካከናወንኩ ሽልማት አለኝ፤ ይሁንና ሳልወድ ባደርገውም እንኳ የመጋቢነት አደራ ተጥሎብኛል።
ታዲያ ሽልማቴ ምንድን ነው? ከምሥራቹ ጋር በተያያዘ ሥልጣኔን አላግባብ እንዳልጠቀምበት ምሥራቹን በምሰብክበት ጊዜ ምሥራቹን ያለክፍያ ማቅረብ ነው።
እኔ ከሰው ሁሉ ነፃ ነኝ፤ ሆኖም በተቻለ መጠን ብዙዎችን እማርክ ዘንድ ራሴን ለሁሉ ባሪያ አደረግኩ።
አይሁዳውያንን እማርክ ዘንድ ለአይሁዳውያን እንደ አይሁዳዊ ሆንኩ፤ እኔ ራሴ በሕግ ሥር ባልሆንም እንኳ በሕግ ሥር ያሉትን እማርክ ዘንድ በሕግ ሥር ላሉት በሕግ ሥር እንዳለሁ ሆንኩ።
በአምላክ ፊት ከሕግ ነፃ ያልሆንኩና በክርስቶስ ፊት በሕግ ሥር ያለሁ ብሆንም እንኳ ሕግ የሌላቸውን እማርክ ዘንድ ሕግ ለሌላቸው ሕግ እንደሌለው ሰው ሆንኩ።
ደካሞችን እማርክ ዘንድ ለደካሞች ደካማ ሆንኩ። በተቻለ መጠን የተወሰኑ ሰዎችን አድን ዘንድ ለሁሉም ዓይነት ሰዎች ሁሉንም ነገር ሆንኩ።
ምሥራቹን ለሌሎች አካፍል ዘንድ ለምሥራቹ ስል ሁሉን ነገር አደርጋለሁ።
በሩጫ ውድድር ሁሉም እንደሚሮጡ፣ ሽልማቱን የሚያገኘው ግን አንዱ ብቻ እንደሆነ አታውቁም? እናንተም ሽልማቱን እንድታገኙ በዚሁ ሁኔታ ሩጡ።
በውድድር የሚሳተፍ ማንኛውም ሰው በሁሉም ነገር ራሱን ይገዛል። እነሱ ይህን የሚያደርጉት የሚጠፋውን አክሊል ለማግኘት ሲሆን እኛ ግን የማይጠፋውን አክሊል ለማግኘት ነው።
ስለዚህ እኔ ያለግብ አልሮጥም፤ ቡጢ የምሰነዝረውም አየር ለመምታት አይደለም፤
ከዚህ ይልቅ ለሌሎች ከሰበክሁ በኋላ እኔ ራሴ በሆነ መንገድ ተቀባይነት እንዳላጣ ሰውነቴን እየጎሰምኩ እንደ ባሪያ እንዲገዛልኝ አደርገዋለሁ።
ስለዚህ ወንድሞች፣ የአምላክን ቅዱስ ሚስጥር ለእናንተ ለመግለጽ በመጣሁ ጊዜ በንግግር ችሎታ ወይም በጥበብ እናንተን ለማስደመም አልሞከርኩም።
ከእናንተ ጋር በነበርኩ ጊዜ ትኩረቴን በኢየሱስ ክርስቶስና በእሱ መሰቀል ላይ ብቻ ለማድረግ ወስኜ ነበርና።
ወደ እናንተም የመጣሁት ደካማ ሆኜ እንዲሁም በፍርሃትና እጅግ በመንቀጥቀጥ ነበር፤
ንግግሬም ሆነ የሰበክሁላችሁ መልእክት የሚያባብል የጥበብ ቃል አልነበረም፤ ከዚህ ይልቅ የአምላክን መንፈስና ኃይል የሚያሳይ ነበር፤
ይኸውም እምነታችሁ በአምላክ ኃይል ላይ እንጂ በሰው ጥበብ ላይ የተመሠረተ እንዳይሆን ነው።
በመሆኑም በጎለመሱት መካከል ስለ ጥበብ እንናገራለን፤ ሆኖም የምንናገረው የዚህን ሥርዓት ጥበብ ወይም የሚጠፉትን የዚህን ሥርዓት ገዢዎች ጥበብ አይደለም።
ከዚህ ይልቅ የምንናገረው በቅዱስ ሚስጥር የተገለጠውን የአምላክ ጥበብ ይኸውም አምላክ ለእኛ ክብር ከዘመናት በፊት አስቀድሞ የወሰነውን የተሰወረ ጥበብ ነው።
ይህን ጥበብ ከዚህ ሥርዓት ገዢዎች መካከል አንዳቸውም አላወቁትም፤ ቢያውቁትማ ኖሮ ታላቅ ክብር ያለውን ጌታ ባልሰቀሉት ነበር።
ይሁንና “አምላክ ለሚወዱት ያዘጋጃቸውን ነገሮች ዓይን አላየም፣ ጆሮም አልሰማም፣ የሰውም ልብ አላሰበም” ተብሎ እንደተጻፈው ነው።
አምላክ እነዚህን ነገሮች በመንፈሱ አማካኝነት የገለጠው ለእኛ ነውና፤ ምክንያቱም መንፈስ ሁሉንም ነገሮች አልፎ ተርፎም የአምላክን ጥልቅ ነገሮች ይመረምራል።
ከሰዎች መካከል በአንድ ሰው ውስጥ ያለውን ነገር በውስጡ ካለው የሰውየው መንፈስ በቀር ማን ሊያውቅ ይችላል? በተመሳሳይም በአምላክ ውስጥ ያለውን ነገር ከአምላክ መንፈስ በቀር ማንም አያውቅም።
እኛ አምላክ በደግነት የሰጠንን ነገሮች ማወቅ እንድንችል ከአምላክ የሆነውን መንፈስ ተቀበልን እንጂ የዓለምን መንፈስ አልተቀበልንም።
ደግሞም እነዚህን ነገሮች እንናገራለን፤ የምንናገረው ግን ከሰው ጥበብ በተማርነው ቃል አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ መንፈሳዊ ጉዳዮችን በመንፈሳዊ ቃል ስናብራራ ከመንፈስ በተማርነው ቃል እንናገራለን።
ዓለማዊ ሰው ግን ከአምላክ መንፈስ የሆኑትን ነገሮች አይቀበልም፤ እንዲህ ያሉት ነገሮች ለእሱ ሞኝነት ናቸውና፤ በመንፈስ የሚመረመሩ ስለሆኑም ሊረዳቸው አይችልም።
ይሁን እንጂ መንፈሳዊ ሰው ሁሉንም ነገር ይመረምራል፤ እሱ ራሱ ግን በማንም ሰው አይመረመርም።
“ያስተምረው ዘንድ የይሖዋን አስተሳሰብ ያወቀ ማን ነው?” ተብሏልና፤ እኛ ግን የክርስቶስ አስተሳሰብ አለን።
እንግዲህ ወንድሞች፣ አባቶቻችን ሁሉ ከደመና በታች እንደነበሩና ሁሉም በባሕር መካከል እንዳለፉ ታውቁ ዘንድ እወዳለሁ፤
ሁሉም ከሙሴ ጋር በመተባበር በደመናውና በባሕሩ ተጠመቁ፤
ደግሞም ሁሉም አንድ ዓይነት መንፈሳዊ ምግብ ተመገቡ፤
በተጨማሪም ሁሉም አንድ ዓይነት መንፈሳዊ መጠጥ ጠጡ። ይከተላቸው ከነበረው መንፈሳዊ ዓለት ይጠጡ ነበርና፤ ይህም ዓለት ክርስቶስን ያመለክታል።
ይሁንና አምላክ በአብዛኞቹ ስላልተደሰተ በምድረ በዳ ወድቀው ቀርተዋል።