text
stringlengths
4
267
በይሁዳ ካሉት የማያምኑ ሰዎች እጅ እንድድንና በኢየሩሳሌም ለሚገኙት ቅዱሳን የማቀርበው አገልግሎት በእነሱ ዘንድ ተቀባይነት እንዲያገኝ ጸልዩልኝ፤
ይኸውም አምላክ ከፈቀደ ወደ እናንተ በደስታ እንድመጣና ከእናንተ ጋር በመሆን መንፈሴ እንዲታደስ ነው።
ሰላም የሚሰጠው አምላክ ከሁላችሁ ጋር ይሁን። አሜን።
እንዲህ ከሆነ ታዲያ በሥጋ አባታችን የሆነው አብርሃም ምን አገኘ እንላለን?
ለምሳሌ አብርሃም ጻድቅ የተባለው በሥራ ቢሆን ኖሮ የሚመካበት ነገር በኖረው ነበር፤ ሆኖም በአምላክ ፊት ሊመካ አይችልም።
የቅዱስ መጽሐፉስ ቃል ምን ይላል? “አብርሃም በይሖዋ አመነ፤ ይህም ጽድቅ ሆኖ ተቆጠረለት።”
ይሁንና ለሚሠራ ሰው ደሞዙ እንደ ሥራው ዋጋ እንጂ እንደ ጸጋ ስጦታ ተደርጎ አይቆጠርለትም።
በሌላ በኩል ግን በራሱ ሥራ ከመመካት ይልቅ ኃጢአተኛውን ጻድቅ ነህ ብሎ በሚጠራው አምላክ የሚያምን እምነቱ እንደ ጽድቅ ይቆጠርለታል።
ይህም ዳዊት፣ አምላክ ያለሥራ እንደ ጻድቅ አድርጎ የሚቆጥረው ሰው ስለሚያገኘው ደስታ እንዲህ ብሎ እንደተናገረው ነው፦
“የዓመፅ ሥራቸው ይቅር የተባለላቸው፣ ኃጢአታቸውም የተሸፈነላቸው ደስተኞች ናቸው፤
ይሖዋ ኃጢአቱን የማይቆጥርበት ሰው ደስተኛ ነው።”
ታዲያ ይህን ደስታ የሚያገኙት የተገረዙ ሰዎች ብቻ ናቸው ወይስ ያልተገረዙትም ጭምር? ምክንያቱም “አብርሃም እምነቱ ጽድቅ ሆኖ ተቆጠረለት” ብለናል።
ታዲያ እምነቱ እንደ ጽድቅ የተቆጠረው በምን ዓይነት ሁኔታ እያለ ነው? ተገርዞ እያለ ነው ወይስ ከመገረዙ በፊት? ተገርዞ እያለ ሳይሆን ከመገረዙ በፊት ነው።
ገና ከመገረዙ በፊት በነበረው እምነት ላገኘው ጽድቅ ምልክት ሆኖ የሚያገለግለውን ግርዘትን እንደ ማኅተም ተቀበለ፤ ስለዚህ ባይገረዙም እንኳ በእምነታቸው የተነሳ እንደ ጻድቃን ለተቆጠሩት ሁሉ አባት ሆኗል፤
ለተገረዙት ዘሮቹም አባት ነው፤ ይሁንና ግርዘትን አጥብቀው ለሚከተሉት ብቻ ሳይሆን አባታችን አብርሃም ከመገረዙ በፊት የነበረውን እምነት ተከትለው በሥርዓት ለሚመላለሱ ሰዎችም ሁሉ አባት ነው።
ምክንያቱም አብርሃም ወይም ዘሩ የዓለም ወራሽ እንደሚሆን ተስፋ የተሰጠው በሕግ አማካኝነት ሳይሆን በእምነት በሚገኘው ጽድቅ ነው።
ወራሾች የሚሆኑት ሕጉን በጥብቅ የሚከተሉ ቢሆኑ ኖሮ እምነት ከንቱ በሆነ ነበርና፤ የተስፋውም ቃል ባከተመ ነበር።
እንደ እውነቱ ከሆነ ሕጉ ቁጣ ያስከትላል፤ ሆኖም ሕግ ከሌለ ሕግን መተላለፍ የሚባል ነገር አይኖርም።
በመሆኑም ተስፋው በእምነት የተገኘ ነው፤ ይህም የሆነው ተስፋው በጸጋ ላይ የተመሠረተ እንዲሆንና ለዘሩ ሁሉ ይኸውም ሕጉን በጥብቅ ለሚከተል ብቻ ሳይሆን የሁላችንም አባት የሆነውን የአብርሃምን እምነት በጥብቅ ለሚከተል ጭምር የተረጋገጠ እንዲሆን ነው።
(ይህም “ለብዙ ብሔራት አባት አድርጌሃለሁ” ተብሎ እንደተጻፈው ነው።) ይህ የሆነው እሱ ባመነበት ማለትም ሙታንን ሕያው በሚያደርገውና የሌለውን እንዳለ አድርጎ በሚጠራው አምላክ ፊት ነው።
ተስፋ ለማድረግ የሚያበቃ ምንም መሠረት ባይኖርም እንኳ “የአንተም ዘር እጅግ ይበዛል” ተብሎ በተነገረው መሠረት የብዙ ብሔራት አባት እንደሚሆን በተሰጠው ተስፋ አምኗል።
እምነቱ ባይዳከምም እንኳ 100 ዓመት ገደማ ሆኖት ስለነበር የሞተ ያህል ስለሆነው የገዛ ራሱ አካል እንዲሁም ሙት ስለሆነው የሣራ ማህፀን አሰበ።
ሆኖም አምላክ ከሰጠው የተስፋ ቃል የተነሳ ለአምላክ ክብር በመስጠት በእምነት በረታ እንጂ እምነት በማጣት አልወላወለም፤
ደግሞም አምላክ የሰጠውን ተስፋ መፈጸም እንደሚችል ሙሉ በሙሉ እርግጠኛ ነበር።
በመሆኑም “ጽድቅ ሆኖ ተቆጠረለት።”
ሆኖም “ተቆጠረለት” ተብሎ የተጻፈው ስለ እሱ ብቻ አይደለም፤
ከዚህ ይልቅ እንደ ጻድቃን ስለምንቆጠረው ስለ እኛም ጭምር ነው፤ ምክንያቱም ጌታችንን ኢየሱስን ከሞት ባስነሳው በእሱ እናምናለን።
ኢየሱስ ስለ በደላችን ለሞት አልፎ ተሰጠ፤ አምላክ ጻድቃን ናችሁ ብሎ እንዲያስታውቅልንም ከሞት ተነሳ።
እንግዲህ ወንድሞች፣ ሰውነታችሁን ሕያው፣ ቅዱስና በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያለው መሥዋዕት አድርጋችሁ እንድታቀርቡ በአምላክ ርኅራኄ እለምናችኋለሁ፤ ይህም የማሰብ ችሎታችሁን ተጠቅማችሁ የምታቀርቡት ቅዱስ አገልግሎት ነው።
በተጨማሪም ይህ ሥርዓት እንዲቀርጻችሁ አትፍቀዱ፤ ከዚህ ይልቅ ጥሩ የሆነውን፣ ተቀባይነት ያለውንና ፍጹም የሆነውን የአምላክ ፈቃድ መርምራችሁ ማረጋገጥ ትችሉ ዘንድ አእምሯችሁን በማደስ ተለወጡ።
እያንዳንዱ ሰው ከሚገባው በላይ ስለ ራሱ በማሰብ ራሱን ከፍ አድርጎ አይመልከት፤ ከዚህ ይልቅ አምላክ ለእያንዳንዱ በሰጠው እምነት መሠረት ጤናማ አስተሳሰብ እንዳለው በሚያሳይ መንገድ እንዲያስብ፣ በመካከላችሁ ያለውን እያንዳንዱን ሰው በተሰጠኝ ጸጋ እመክራለሁ።
በአንድ አካል ላይ ብዙ የአካል ክፍሎች አሉን፤ ደግሞም ሁሉም የአካል ክፍሎች አንድ ዓይነት ተግባር አያከናውኑም፤
ልክ እንደዚሁ እኛም ብዙ ብንሆንም እንኳ ከክርስቶስ ጋር ባለን አንድነት አንድ አካል ነን፤ ደግሞም አንዳችን የሌላው የአካል ክፍል ነን።
በመሆኑም በተሰጠን ጸጋ መሠረት የተለያዩ ስጦታዎች ስላሉን ስጦታችን ትንቢት መናገር ከሆነ በተሰጠን እምነት መሠረት ትንቢት እንናገር፤
ማገልገል ከሆነ ማገልገላችንን እንቀጥል፤ የሚያስተምርም ቢሆን ማስተማሩን ይቀጥል፤
የሚያበረታታም ቢሆን ማበረታቻ መስጠቱን ይቀጥል፤ የሚሰጥ በልግስና ይስጥ፤ የሚያስተዳድር በትጋት ያስተዳድር፤ የሚምር በደስታ ይማር።
ፍቅራችሁ ግብዝነት የሌለበት ይሁን። ክፉ የሆነውን ተጸየፉ፤ ጥሩ የሆነውን አጥብቃችሁ ያዙ።
በወንድማማች ፍቅር እርስ በርሳችሁ ከልብ ተዋደዱ። አንዳችሁ ሌላውን ለማክበር ቀዳሚ ሁኑ።
ታታሪዎች ሁኑ እንጂ አትስነፉ። በመንፈስ የምትቃጠሉ ሁኑ። ይሖዋን እንደ ባሪያ አገልግሉ።
በተስፋው ደስ ይበላችሁ። መከራን በጽናት ተቋቋሙ። ሳትታክቱ ጸልዩ።
ለቅዱሳን እንደየችግራቸው ያላችሁን አካፍሉ። የእንግዳ ተቀባይነትን ባሕል አዳብሩ።
ስደት የሚያደርሱባችሁን መርቁ፤ መርቁ እንጂ አትርገሙ።
ደስ ከሚላቸው ጋር ደስ ይበላችሁ፤ ከሚያለቅሱ ጋር አልቅሱ።
ለራሳችሁ ያላችሁ ዓይነት አመለካከት ለሌሎችም ይኑራችሁ፤ የትዕቢት ዝንባሌ እንዳያድርባችሁ ተጠንቀቁ፤ ትሕትና የሚንጸባረቅበት አስተሳሰብ ይኑራችሁ። ጥበበኞች እንደሆናችሁ አድርጋችሁ አታስቡ።
ለማንም በክፉ ፋንታ ክፉ አትመልሱ። በሰው ሁሉ ፊት መልካም የሆነውን ነገር ለማድረግ ጥረት አድርጉ።
ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ለመኖር በእናንተ በኩል የተቻላችሁን ሁሉ አድርጉ።
የተወደዳችሁ ወንድሞች፣ ራሳችሁ አትበቀሉ፤ ከዚህ ይልቅ “‘በቀል የእኔ ነው፤ እኔ ብድራትን እመልሳለሁ’ ይላል ይሖዋ” ተብሎ ስለተጻፈ ለቁጣው ዕድል ስጡ።
ነገር ግን “ጠላትህ ቢራብ አብላው፤ ቢጠማ አጠጣው፤ ይህን በማድረግ በራሱ ላይ ፍም ትከምራለህ።”
በክፉ አትሸነፍ፤ ከዚህ ይልቅ ምንጊዜም ክፉውን በመልካም አሸንፍ።
እንግዲህ ምን እንበል? ጸጋ እንዲበዛ ኃጢአት መሥራታችንን እንቀጥል?
በፍጹም! እኛ ለኃጢአት የሞትን ሆነን ሳለን ከእንግዲህ እንዴት በኃጢአት ውስጥ መኖራችንን እንቀጥላለን?
ወይስ ክርስቶስ ኢየሱስ ውስጥ የተጠመቅን ሁላችን እሱ ሞት ውስጥ እንደተጠመቅን አታውቁም?
ስለዚህ ክርስቶስ በአብ ክብር ከሞት እንደተነሳ ሁሉ እኛም አዲስ ሕይወት እንድንኖር እሱ ሞት ውስጥ በመጠመቅ ከእሱ ጋር ተቀብረናል።
ሞቱን በሚመስል ሞት ከእሱ ጋር አንድ ከሆንን ትንሣኤውን በሚመስል ትንሣኤ ደግሞ ከእሱ ጋር አንድ እንደምንሆን ጥርጥር የለውም።
ምክንያቱም ኃጢአተኛው ሰውነታችን በእኛ ላይ ምንም ኃይል እንዳይኖረውና ከእንግዲህ የኃጢአት ባሪያዎች ሆነን እንዳንኖር አሮጌው ስብዕናችን ከእሱ ጋር በእንጨት ላይ እንደተቸነከረ እናውቃለን።
የሞተ ከኃጢአቱ ነፃ ወጥቷልና።
በተጨማሪም ከክርስቶስ ጋር ከሞትን ከእሱ ጋር እንደምንኖር እናምናለን።
ክርስቶስ አሁን ከሞት እንደተነሳና ዳግመኛ እንደማይሞት እናውቃለን፤ ከእንግዲህ ሞት በእሱ ላይ እንደ ጌታ ሊሠለጥን አይችልም።
ምክንያቱም እሱ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለኃጢአት ሞቷል፤ ሆኖም አሁን እየኖረ ያለውን ሕይወት የሚኖረው ለአምላክ ነው።
በተመሳሳይም እናንተ ለኃጢአት እንደሞታችሁ ሆኖም በክርስቶስ ኢየሱስ ለአምላክ እንደምትኖሩ አድርጋችሁ አስቡ።
በመሆኑም ኃጢአት ለሰውነታችሁ ምኞት ተገዢ እንድትሆኑ በማድረግ ሟች በሆነው ሰውነታችሁ ላይ መንገሡን እንዲቀጥል አትፍቀዱ።
በተጨማሪም ሰውነታችሁን የክፋት መሣሪያ አድርጋችሁ ለኃጢአት አታቅርቡ፤ ከዚህ ይልቅ ከሞት ወደ ሕይወት እንደተሻገሩ ሰዎች አድርጋችሁ ራሳችሁን ለአምላክ አቅርቡ፤ ሰውነታችሁንም የጽድቅ መሣሪያ አድርጋችሁ ለአምላክ አቅርቡ።
ምክንያቱም በጸጋ ሥር እንጂ በሕግ ሥር ስላልሆናችሁ ኃጢአት በእናንተ ላይ ጌታ ሊሆን አይገባም።
እንግዲህ ከዚህ በመነሳት ምን ማለት እንችላለን? በጸጋ ሥር እንጂ በሕግ ሥር ስላልሆንን ኃጢአት እንሥራ ማለት ነው? በፍጹም!
ለማንም ቢሆን ታዛዥ ባሪያዎች ሆናችሁ ራሳችሁን ካቀረባችሁ ለዚያ ለምትታዘዙለት ባሪያዎች እንደሆናችሁ አታውቁም? በመሆኑም ሞት ለሚያስከትለው ለኃጢአት አለዚያም ጽድቅ ለሚያስገኘው ለታዛዥነት ባሪያዎች ናችሁ።
ሆኖም እናንተ በአንድ ወቅት የኃጢአት ባሪያዎች የነበራችሁ ቢሆንም እንድትከተሉት ለተሰጣችሁ ለእንዲህ ዓይነቱ ትምህርት ከልብ ስለታዘዛችሁ አምላክ የተመሰገነ ይሁን።
አዎ፣ ከኃጢአት ነፃ ስለወጣችሁ የጽድቅ ባሪያዎች ሆናችኋል።
እኔ ሰዎች በሚረዱት ቋንቋ የምናገረው በሥጋችሁ ድክመት የተነሳ ነው፤ የአካል ክፍሎቻችሁን ክፉ ድርጊት ለመፈጸም ለርኩሰትና ለክፋት ባሪያዎች አድርጋችሁ አቅርባችሁ እንደነበረ ሁሉ አሁን ደግሞ የአካል ክፍሎቻችሁን ቅዱስ ሥራ ለመሥራት የጽድቅ ባሪያዎች አድርጋችሁ አቅርቡ።
የኃጢአት ባሪያዎች በነበራችሁበት ጊዜ በጽድቅ ሥር አልነበራችሁምና።
ታዲያ በዚያን ጊዜ ታፈሯቸው የነበሩት ፍሬዎች ምን ዓይነት ነበሩ? አሁን የምታፍሩባቸው ነገሮች ናቸው። የእነዚህ ነገሮች መጨረሻ ሞት ነውና።
ይሁን እንጂ አሁን ከኃጢአት ነፃ ወጥታችሁ የአምላክ ባሪያዎች ስለሆናችሁ በቅድስና ጎዳና ፍሬ እያፈራችሁ ነው፤ የዚህም መጨረሻ የዘላለም ሕይወት ነው።
የኃጢአት ደሞዝ ሞት ነውና፤ አምላክ የሚሰጠው ስጦታ ግን በጌታችን በክርስቶስ ኢየሱስ የዘላለም ሕይወት ነው።
ስለዚህ ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር አንድነት ያላቸው ኩነኔ የለባቸውም።
ምክንያቱም ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር አንድነት ላላቸው ሰዎች ሕይወት የሚያስገኘው መንፈስ ሕግ፣ ከኃጢአትና ከሞት ሕግ ነፃ አውጥቷችኋል።
ሕጉ ከሰብዓዊ አለፍጽምና የተነሳ ደካማ በመሆኑ ሊፈጽመው ያልቻለውን ነገር አምላክ ኃጢአትን ለማስወገድ የገዛ ራሱን ልጅ ኃጢአተኛ በሆኑ ሰዎች አምሳል በመላክ ፈጽሞታል። እንዲህ በማድረግም የሥጋን ኃጢአት ኮንኗል፤
ይህም የሆነው የሕጉ የጽድቅ መሥፈርት እንደ ሥጋ ፈቃድ ሳይሆን እንደ መንፈስ ፈቃድ በምንመላለሰው በእኛ እንዲፈጸም ነው።
እንደ ሥጋ ፈቃድ የሚኖሩ አእምሯቸው በሥጋዊ ነገሮች ላይ ያተኮረ ነው፤ እንደ መንፈስ ፈቃድ የሚኖሩ ግን አእምሯቸው በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ ያተኮረ ነው።
በሥጋዊ ነገሮች ላይ ማተኮር ሞት ያስከትላልና፤ በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ ማተኮር ግን ሕይወትና ሰላም ያስገኛል፤
ሥጋ ለአምላክ ሕግ ስለማይገዛና ደግሞም ሊገዛ ስለማይችል በሥጋዊ ነገሮች ላይ ማተኮር የአምላክ ጠላት ያደርጋል።
ስለሆነም እንደ ሥጋ ፈቃድ የሚመላለሱ አምላክን ማስደሰት አይችሉም።
ይሁን እንጂ የአምላክ መንፈስ በእርግጥ በውስጣችሁ የሚኖር ከሆነ ከሥጋ ጋር ሳይሆን ከመንፈስ ጋር ስምም ናችሁ። ሆኖም አንድ ሰው የክርስቶስ መንፈስ ከሌለው ይህ ሰው የክርስቶስ አይደለም።
ይሁንና ክርስቶስ ከእናንተ ጋር አንድነት ካለው፣ ሰውነታችሁ በኃጢአት ምክንያት የሞተ ቢሆንም እንኳ መንፈስ ከጽድቅ የተነሳ ሕይወት ያስገኛል።
እንግዲህ ኢየሱስን ከሞት ያስነሳው የአምላክ መንፈስ በእናንተ ውስጥ የሚኖር ከሆነ ክርስቶስ ኢየሱስን ከሞት ያስነሳው እሱ በእናንተ ውስጥ በሚኖረው መንፈሱ አማካኝነት ሟች ሰውነታችሁንም ሕያው ያደርገዋል።
ስለዚህ ወንድሞች ግዴታ አለብን፤ ይሁንና ግዴታችን እንደ ሥጋ ፈቃድ መኖር አይደለም፤
እንደ ሥጋ ፈቃድ የምትኖሩ ከሆነ መሞታችሁ የማይቀር ነውና፤ ይሁን እንጂ ሰውነታችሁ የሚፈጽመውን ሥራ በመንፈስ ብትገድሉ በሕይወት ትኖራላችሁ።
በአምላክ መንፈስ የሚመሩ ሁሉ በእርግጥ የአምላክ ልጆች ናቸውና።
ዳግመኛ ለፍርሃት የሚዳርጋችሁን የባርነት መንፈስ አልተቀበላችሁም፤ ከዚህ ይልቅ አምላክ ልጆቹ አድርጎ እንዲወስዳችሁ የሚያስችል መንፈስ አግኝታችኋል፤ ይህም መንፈስ “አባ፣ አባት!” ብለን እንድንጣራ ይገፋፋናል።
የአምላክ ልጆች መሆናችንን ይህ መንፈስ ራሱ ከመንፈሳችን ጋር ሆኖ ይመሠክራል።
እንግዲህ ልጆች ከሆን ወራሾች ነን፤ ይኸውም ከአምላክ ውርሻ እንቀበላለን፤ ይሁንና የምንወርሰው ከክርስቶስ ጋር ነው፤ አሁን አብረነው መከራ ከተቀበልን፣ በኋላ ደግሞ አብረነው ክብር እንጎናጸፋለን።
በአሁኑ ጊዜ የሚደርስብን መከራ በእኛ ላይ ከሚገለጠው ክብር ጋር ሲነጻጸር ከምንም ሊቆጠር እንደማይችል አምናለሁ።
ፍጥረት የአምላክን ልጆች መገለጥ በከፍተኛ ጉጉት እየተጠባበቀ ነው።
ፍጥረት ለከንቱነት ተገዝቷልና፤ የተገዛው ግን በገዛ ፈቃዱ ሳይሆን በተስፋ እንዲገዛ ባደረገው በእሱ አማካኝነት ነው፤
ተስፋውም ፍጥረት ራሱ ደግሞ ከመበስበስ ባርነት ነፃ ወጥቶ የአምላክ ልጆች የሚያገኙት ዓይነት ክብራማ ነፃነት ማግኘት ነው።
ፍጥረት ሁሉ እስካሁን ድረስ አብሮ በመቃተትና በመሠቃየት ላይ እንደሚገኝ እናውቃለን።
ይህም ብቻ ሳይሆን የውርሻችንን በኩራት ይኸውም መንፈስን ያገኘን እኛ ራሳችንም በቤዛው አማካኝነት ከሥጋዊ አካላችን ነፃ በመውጣት አምላክ ልጆቹ አድርጎ እንዲወስደን በጉጉት እየተጠባበቅን በውስጣችን እንቃትታለን።
በዚህ ተስፋ ድነናል፤ ነገር ግን ተስፋ የሚደረገው ነገር የሚታይ ከሆነ ተስፋ መሆኑ ይቀራል፤ ደግሞስ አንድ ሰው የሚያየውን ነገር ተስፋ ያደርጋል?
የማናየውን ነገር ተስፋ የምናደርግ ከሆነ ግን ጸንተን በጉጉት እንጠባበቀዋለን።
በተመሳሳይም መንፈስ በድካማችን ይረዳናል። ምን ብለን መጸለይ እንዳለብን ግራ የምንጋባበት ጊዜ ሊኖር ይችላል። እንዲህ ያለ ሁኔታ ሲያጋጥመንና ስሜታችንን በቃላት መግለጽ ተስኖን ስንቃትት መንፈስ ራሱ ስለ እኛ ይማልዳል።
ይሁንና ልብን የሚመረምረው አምላክ የመንፈስን ዓላማ ያውቃል፤ ምክንያቱም መንፈስ ለቅዱሳን የሚማልደው ከአምላክ ፈቃድ ጋር በሚስማማ መንገድ ነው።
አምላክ ለሚወዱት ይኸውም ከእሱ ዓላማ ጋር በሚስማማ መንገድ ለተጠሩት ሥራውን ሁሉ አቀናጅቶ ለበጎ እንዲሆንላቸው እንደሚያደርግ እናውቃለን፤