text
stringlengths
4
267
ከፊቱ የእሳት ጅረት ይፈልቅና ይፈስ ነበር። ሺህ ጊዜ ሺዎች ያገለግሉት ነበር፤ እልፍ ጊዜ እልፍም በፊቱ ቆመው ነበር። ችሎቱ ተሰየመ፤ መጻሕፍትም ተከፈቱ።
“በዚህ ጊዜ ቀንዱ ከሚናገረው የእብሪት ቃል የተነሳ መመልከቴን ቀጠልኩ፤ እኔም እየተመለከትኩ ሳለ አውሬው ተገደለ፤ አካሉም ወደሚንበለበል እሳት ተጥሎ እንዲጠፋ ተደረገ።
የቀሩት አራዊት ግን የገዢነት ሥልጣናቸውን ተቀሙ፤ ሆኖም ለተወሰነ ጊዜና ወቅት ዕድሜያቸው ተራዘመ።
“በሌሊት የተገለጡልኝን ራእዮች ማየቴን ቀጠልኩ፤ እነሆ የሰው ልጅ የሚመስል ከሰማያት ደመና ጋር መጣ፤ ከዘመናት በፊት ወደነበረውም እንዲገባ ተፈቀደለት፤ ወደ ፊቱም አቀረቡት።
ከተለያዩ ብሔራትና ቋንቋዎች የተውጣጡ ሕዝቦች ሁሉ እንዲያገለግሉት የገዢነት ሥልጣን፣ ክብርና መንግሥት ተሰጠው። የገዢነት ሥልጣኑ የማያልፍና ዘላለማዊ፣ መንግሥቱም የማይጠፋ ነው።
“እኔ ዳንኤል ያየኋቸው ራእዮች ፍርሃት ስላሳደሩብኝ በውስጤ መንፈሴ ታወከ።
ከቆሙት መካከል ወደ አንዱ ቀርቤ የዚህ ሁሉ ትክክለኛ ትርጉም ምን እንደሆነ ጠየቅኩት። እሱም መለሰልኝ፤ ደግሞም የእነዚህን ነገሮች ትርጉም ገለጸልኝ።
“‘እነዚህ አራት ግዙፍ አራዊት ከምድር የሚነሱ አራት ነገሥታት ናቸው።
ይሁንና ከሁሉ የላቀው አምላክ ቅዱሳን፣ መንግሥቱን ይቀበላሉ፤ መንግሥቱን ለዘላለም፣ አዎ ለዘላለም ዓለም ይወርሳሉ።’
“ከዚያም ከሌሎቹ ሁሉ የተለየ ስለሆነው ስለ አራተኛው አውሬ ይበልጥ ማወቅ ፈለግኩ፤ የብረት ጥርሶችና የመዳብ ጥፍሮች ያሉት እጅግ አስፈሪ አውሬ ነበር፤ ይበላና ያደቅ እንዲሁም የቀረውን በእግሩ ይረጋግጥ ነበር፤
ደግሞም በራሱ ላይ ስለነበሩት አሥር ቀንዶች እንዲሁም በኋላ ስለወጣውና ሦስቱ በፊቱ እንዲወድቁ ስላደረገው ስለ ሌላኛው ቀንድ ይኸውም ዓይኖችና በእብሪት የሚናገር አፍ ስላሉት እንዲሁም ከሌሎቹ ስለበለጠው ቀንድ ማወቅ ፈለግኩ።
“እየተመለከትኩ ሳለ ይህ ቀንድ በቅዱሳኑ ላይ ጦርነት ከፈተ፤ በእነሱም ላይ አየለባቸው፤
ይህም የሆነው ከዘመናት በፊት የነበረው እስኪመጣና ከሁሉ የላቀው አምላክ ቅዱሳን አገልጋዮች እስኪፈረድላቸው ድረስ ነበር፤ ቅዱሳኑም መንግሥቱን የሚወርሱበት የተወሰነው ዘመን መጣ።
“እሱም እንዲህ አለ፦ ‘አራተኛው አውሬ በምድር ላይ የሚነሳ አራተኛ መንግሥት ነው። ከሌሎቹ መንግሥታት ሁሉ የተለየ ይሆናል፤ መላዋን ምድር ያወድማል፣ ይረግጣል እንዲሁም ያደቃል።
አሥሩ ቀንዶች ከዚህ መንግሥት የሚነሱ አሥር ነገሥታት ናቸው፤ ከእነሱም በኋላ ሌላ ይነሳል፤ እሱም ከመጀመሪያዎቹ የተለየ ይሆናል፤ ሦስት ነገሥታትንም ያዋርዳል።
በልዑሉ አምላክ ላይ የተቃውሞ ቃል ይናገራል፤ ከሁሉ በላቀው አምላክ ቅዱሳንም ላይ ያለማቋረጥ ችግር ያደርስባቸዋል። ዘመናትንና ሕግን ለመለወጥ ያስባል፤ እነሱም ለዘመን፣ ለዘመናትና ለዘመን እኩሌታ በእጁ አልፈው ይሰጣሉ።
ይሁንና ችሎቱ ተሰየመ፤ የገዢነት ሥልጣኑንም ቀሙት፤ ከዚያም አስወገዱት፤ ፈጽሞም አጠፉት።
“‘ከሰማያት በታች ያለ መንግሥት፣ የገዢነት ሥልጣንና የመንግሥታት ግርማ በሙሉ ከሁሉ የላቀው አምላክ ቅዱሳን ለሆኑት ሰዎች ተሰጠ። መንግሥታቸው ዘላለማዊ መንግሥት ነው፤ መንግሥታትም ሁሉ ያገለግሏቸዋል፤ ደግሞም ይታዘዟቸዋል።’
“የነገሩ ፍጻሜ ይህ ነው። እኔም ዳንኤል ሳስበው የነበረው ነገር በጣም አስፈራኝ፤ ፊቴም ገረጣ፤ ነገሩን ግን በልቤ ያዝኩት።”
ንጉሥ ናቡከደነጾር ቁመቱ 60 ክንድ፣ ወርዱ 6 ክንድ የሆነ የወርቅ ምስል ሠራ። ምስሉን በባቢሎን አውራጃ በዱራ ሜዳ አቆመው።
ከዚያም ንጉሥ ናቡከደነጾር የአውራጃ ገዢዎቹ፣ አስተዳዳሪዎቹ፣ አገረ ገዢዎቹ፣ አማካሪዎቹ፣ የግምጃ ቤት ኃላፊዎቹ፣ ዳኞቹ፣ ሕግ አስከባሪዎቹና የየአውራጃዎቹ አስተዳዳሪዎች በሙሉ ንጉሥ ናቡከደነጾር ላቆመው ምስል የምረቃ ሥነ ሥርዓት እንዲሰበሰቡ ጥሪ አስተላለፈ።
በመሆኑም የአውራጃ ገዢዎቹ፣ አስተዳዳሪዎቹ፣ አገረ ገዢዎቹ፣ አማካሪዎቹ፣ የግምጃ ቤት ኃላፊዎቹ፣ ዳኞቹ፣ ሕግ አስከባሪዎቹና የየአውራጃዎቹ አስተዳዳሪዎች በሙሉ ንጉሥ ናቡከደነጾር ላቆመው ምስል የምረቃ ሥነ ሥርዓት ተሰበሰቡ። ናቡከደነጾር ባቆመውም ምስል ፊት ቆሙ።
አዋጅ ነጋሪው ከፍ ባለ ድምፅ እንዲህ አለ፦ “እናንተ ከተለያዩ ብሔራትና ቋንቋዎች የተውጣጣችሁ ሕዝቦች ሆይ፣ እንዲህ እንድታደርጉ ታዛችኋል፦
የቀንደ መለከት፣ የእምቢልታ፣ የተለያዩ ባለ አውታር መሣሪያዎች፣ የባለ ሦስት ማዕዘን በገና፣ የባለ ከረጢት ዋሽንትና የሌሎቹን የሙዚቃ መሣሪያዎች ሁሉ ድምፅ ስትሰሙ በግንባራችሁ ተደፍታችሁ ንጉሥ ናቡከደነጾር ላቆመው የወርቅ ምስል ስገዱ።
ተደፍቶ የማይሰግድ ማንኛውም ሰው ወዲያውኑ ወደሚንበለበለው የእቶን እሳት ይጣላል።”
ስለዚህ ከተለያዩ ብሔራትና ቋንቋዎች የተውጣጡት ሕዝቦች በሙሉ የቀንደ መለከት፣ የእምቢልታ፣ የተለያዩ ባለ አውታር መሣሪያዎች፣ የባለ ሦስት ማዕዘን በገናና የሌሎቹን የሙዚቃ መሣሪያዎች ሁሉ ድምፅ ሲሰሙ ተደፍተው ንጉሥ ናቡከደነጾር ላቆመው የወርቅ ምስል ሰገዱ።
በዚህ ጊዜ አንዳንድ ከለዳውያን ወደ ፊት ቀርበው አይሁዳውያንን ከሰሱ።
ንጉሥ ናቡከደነጾርን እንዲህ አሉት፦ “ንጉሥ ሆይ፣ ለዘላለም ኑር።
ንጉሥ ሆይ፣ ማንኛውም ሰው የቀንደ መለከት፣ የእምቢልታ፣ የተለያዩ ባለ አውታር መሣሪያዎች፣ የባለ ሦስት ማዕዘን በገና፣ የባለ ከረጢት ዋሽንትና የሌሎቹን የሙዚቃ መሣሪያዎች ሁሉ ድምፅ ሲሰማ ተደፍቶ ለወርቁ ምስል እንዲሰግድ ትእዛዝ አስተላልፈሃል፤
ተደፍቶ የማይሰግድ ሁሉ ወደሚንበለበለው የእቶን እሳት እንደሚጣል ተናግረሃል።
ሆኖም በባቢሎን አውራጃ አስተዳዳሪዎች አድርገህ የሾምካቸው ሲድራቅ፣ ሚሳቅና አብደናጎ የሚባሉ አይሁዳውያን አሉ። ንጉሥ ሆይ፣ እነዚህ ሰዎች ለአንተ አክብሮት የላቸውም። አማልክትህን አያገለግሉም እንዲሁም ላቆምከው የወርቅ ምስል ለመስገድ እንቢተኞች ሆነዋል።”
በዚህ ጊዜ ናቡከደነጾር እጅግ ተቆጥቶ ሲድራቅን፣ ሚሳቅንና አብደናጎን እንዲያመጧቸው አዘዘ። እነሱንም በንጉሡ ፊት አቀረቧቸው።
ናቡከደነጾርም እንዲህ አላቸው፦ “ሲድራቅ፣ ሚሳቅና አብደናጎ፣ አማልክቴን አለማገልገላችሁና ላቆምኩት የወርቅ ምስል አንሰግድም ማለታችሁ እውነት ነው?
አሁንም የቀንደ መለከት፣ የእምቢልታ፣ የተለያዩ ባለ አውታር መሣሪያዎች፣ የባለ ሦስት ማዕዘን በገና፣ የባለ ከረጢት ዋሽንትና የሌሎቹን የሙዚቃ መሣሪያዎች ሁሉ ድምፅ ስትሰሙ ለሠራሁት ምስል ተደፍታችሁ ለመስገድ ፈቃደኞች ከሆናችሁ፣ መልካም! የማትሰግዱ ከሆነ ግን ወዲያውኑ ወደሚንበለበለው የእቶን እሳት ትጣላላችሁ። ለመሆኑ ከእጄ ሊያስጥላችሁ የሚችል አምላክ ማን ነው?”
ሲድራቅ፣ ሚሳቅና አብደናጎ ለንጉሡ መልሰው እንዲህ አሉ፦ “ናቡከደነጾር ሆይ፣ በዚህ ጉዳይ ለአንተ መልስ መስጠት አያስፈልገንም።
ወደ እሳቱ የምንጣል ከሆነ የምናገለግለው አምላካችን ከሚንበለበለው የእቶን እሳት ሊያስጥለን ይችላል፤ ንጉሥ ሆይ፣ ከእጅህም ያስጥለናል።
ሆኖም እሱ ባያስጥለንም እንኳ ንጉሥ ሆይ፣ የአንተን አማልክት እንደማናገለግልና ላቆምከው የወርቅ ምስል እንደማንሰግድ እወቅ።”
በዚህ ጊዜ ናቡከደነጾር በሲድራቅ፣ በሚሳቅና በአብደናጎ እጅግ ተቆጣ፤ የፊቱም ገጽታ ተለወጠባቸው፤ የእቶኑም እሳት ከወትሮው ይበልጥ ሰባት እጥፍ እንዲነድ አዘዘ።
ከዚያም በሠራዊቱ መካከል ያሉ ኃያላን ሰዎች ሲድራቅን፣ ሚሳቅንና አብደናጎን አስረው ወደሚንበለበለው የእቶን እሳት እንዲጥሏቸው አዘዘ።
በመሆኑም እነዚህ ሰዎች ልብሳቸውን እንደለበሱ ማለትም መጎናጸፊያቸውን፣ ከውስጥም ሆነ ከላይ ያደረጉትን ልብስና ጥምጥማቸውን በሙሉ እንደለበሱ ታስረው ወደሚንበለበለው የእቶን እሳት ተጣሉ።
የንጉሡ ትእዛዝ እጅግ ጥብቅ ስለነበረና የእቶኑ እሳት በኃይል ስለተቀጣጠለ ሲድራቅን፣ ሚሳቅንና አብደናጎን የወሰዷቸው ሰዎች በእሳቱ ወላፈን ተቃጥለው ሞቱ።
ይሁንና ሦስቱ ሰዎች ይኸውም ሲድራቅ፣ ሚሳቅና አብደናጎ እንደታሰሩ በሚንበለበለው የእቶን እሳት ውስጥ ወደቁ።
ከዚያም ንጉሥ ናቡከደነጾር በድንጋጤ ከተቀመጠበት ዘሎ ተነሳ፤ ከፍተኛ ባለሥልጣናቱንም “አስረን እሳት ውስጥ የጣልናቸው ሦስት ሰዎች አልነበሩም እንዴ?” ሲል ጠየቃቸው፤ እነሱም “አዎ፣ ንጉሥ ሆይ” ብለው መለሱ።
እሱም እንዲህ አላቸው፦ “እነሆ፣ ያልታሰሩ አራት ሰዎች በእሳቱ መካከል ሲመላለሱ አያለሁ፤ ጉዳትም አልደረሰባቸውም፤ አራተኛውም የአማልክትን ልጅ ይመስላል።”
ናቡከደነጾር የሚንበለበል እሳት ወዳለበት እቶን በር ቀርቦ “እናንተ የልዑል አምላክ አገልጋዮች፣ ሲድራቅ፣ ሚሳቅና አብደናጎ ወጥታችሁ ወደዚህ ኑ!” አለ። ሲድራቅ፣ ሚሳቅና አብደናጎም ከእሳቱ ውስጥ ወጡ።
በዚያ ተሰብስበው የነበሩት የአውራጃ ገዢዎቹ፣ አስተዳዳሪዎቹ፣ አገረ ገዢዎቹና የንጉሡ ከፍተኛ ባለሥልጣናት፣ እሳቱ ሰውነታቸውን እንዳልጎዳው፣ ከራሳቸው ፀጉር አንዲቷ እንኳ እንዳልተቃጠለች፣ መጎናጸፊያቸው መልኩ እንዳልተለወጠና የእሳቱ ሽታ በላያቸው እንዳልነበረ ተመለከቱ።
ከዚያም ናቡከደነጾር እንዲህ አለ፦ “መልአኩን ልኮ አገልጋዮቹን የታደገው የሲድራቅ፣ የሚሳቅና የአብደናጎ አምላክ የተመሰገነ ይሁን። እነሱ በእሱ በመታመን የንጉሡን ትእዛዝ ለመቀበል ፈቃደኞች አልሆኑም፤ የራሳቸውን አምላክ ትተው ሌላ አምላክ ከማገልገል ወይም ከማምለክ ይልቅ ሞትን መርጠዋል።
ስለዚህ በሲድራቅ፣ በሚሳቅና በአብደናጎ አምላክ ላይ ማንኛውንም መጥፎ ነገር የሚናገር ከየትኛውም ብሔርና ቋንቋ የሆነ ሕዝብ ሁሉ እንዲቆራረጥ፣ ቤቱም የሕዝብ መጸዳጃ እንዲሆን አዝዣለሁ፤ እንደ እሱ ማዳን የሚችል ሌላ አምላክ የለምና።”
ከዚያም ንጉሡ ሲድራቅ፣ ሚሳቅና አብደናጎ በባቢሎን አውራጃ ውስጥ የደረጃ እድገት እንዲያገኙ አደረገ።
በከለዳውያን መንግሥት ላይ ንጉሥ ሆኖ የተሾመውና የሜዶናውያን ተወላጅ የሆነው የአሐሽዌሮስ ልጅ ዳርዮስ በነገሠ በመጀመሪያው ዓመት፣
አዎ፣ በዘመነ መንግሥቱ የመጀመሪያ ዓመት እኔ ዳንኤል ለነቢዩ ኤርምያስ በተነገረው የይሖዋ ቃል ላይ በተጠቀሰው መሠረት ኢየሩሳሌም ፈራርሳ የምትቆየው ለ70 ዓመት እንደሆነ ከመጻሕፍቱ አስተዋልኩ።
በመሆኑም ወደ እውነተኛው አምላክ ወደ ይሖዋ ፊቴን አዞርኩ፤ ማቅ ለብሼና በራሴ ላይ አመድ ነስንሼ በጸሎትና በጾም ተማጸንኩት።
ወደ አምላኬ ወደ ይሖዋ ጸለይኩ፤ ደግሞም ተናዘዝኩ፤ እንዲህም አልኩ፦ “እውነተኛው አምላክ ይሖዋ ሆይ፣ አንተ ለሚወዱህ፣ ትእዛዛትህንም ለሚያከብሩ ቃል ኪዳንህን የምትጠብቅና ታማኝ ፍቅር የምታሳይ ታላቅና የምትፈራ አምላክ ነህ፤
እኛ ኃጢአት ሠርተናል፤ በደል ፈጽመናል፤ ክፋት ሠርተናል እንዲሁም ዓምፀናል፤ ከትእዛዛትህና ከድንጋጌዎችህ ዞር ብለናል።
ለነገሥታታችን፣ ለመኳንንታችን፣ ለአባቶቻችንና ለምድሪቱ ሕዝብ ሁሉ በስምህ የተናገሩትን አገልጋዮችህን ነቢያትን አልሰማንም።
ይሖዋ ሆይ፣ ጽድቅ የአንተ ነው፤ እኛ ግን ይኸውም የይሁዳ ሰዎች፣ የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች እንዲሁም በቅርብም ይሁን በሩቅ ባሉ አገራት ሁሉ የበተንካቸው የእስራኤል ቤት ሰዎች በሙሉ ዛሬ እንደሆነው ሁሉ ኀፍረት ተከናንበናል፤ ምክንያቱም እነሱ ለአንተ ታማኝ ሳይሆኑ ቀርተዋል።
“ይሖዋ ሆይ፣ እኛ፣ ነገሥታታችን፣ መኳንንታችንና አባቶቻችን በአንተ ላይ ኃጢአት በመሥራታችን ኀፍረት ተከናንበናል።
ምሕረትና ይቅር ባይነት የአምላካችን የይሖዋ ነው፤ እኛ በእሱ ላይ ዓምፀናልና።
የአምላካችንን የይሖዋን ቃል አልታዘዝንም፤ አገልጋዮቹ በሆኑት በነቢያት አማካኝነት የሰጠንን ሕጎችም አላከበርንም።
የእስራኤል ቤት ሰዎች ሁሉ ሕግህን ተላልፈዋል፤ ቃልህን ባለመታዘዝም ለአንተ ጀርባቸውን ሰጥተዋል፤ በዚህም የተነሳ የእውነተኛው አምላክ አገልጋይ በሆነው በሙሴ ሕግ የተጻፈውን እርግማንና መሐላ በእኛ ላይ አወረድክ፤ በአንተ ላይ ኃጢአት ሠርተናልና።
በእኛ ላይ ታላቅ ጥፋት በማምጣት በእኛ ላይና እኛን በገዙት ገዢዎቻችን ላይ የተናገረውን ቃል ፈጸመብን፤ በኢየሩሳሌም ላይ እንደተፈጸመው ያለ ነገር ከሰማይ በታች ታይቶ አያውቅም።
በሙሴ ሕግ እንደተጻፈው ይህ ሁሉ ጥፋት ደረሰብን፤ ያም ሆኖ ከበደላችን በመመለስና ለእውነትህ ትኩረት በመስጠት የአምላካችንን የይሖዋን ሞገስ ለማግኘት አልተማጸንም።
“በመሆኑም ይሖዋ በትኩረት ሲከታተል ቆይቶ ጥፋት አመጣብን፤ አምላካችን ይሖዋ በሥራው ሁሉ ጻድቅ ነውና፤ እኛ ግን ቃሉን አልታዘዝንም።
“አሁንም ሕዝብህን ከግብፅ ምድር በኃያል እጅ ያወጣህና እስከዚህ ቀን ድረስ ስምህ እንዲታወቅ ያደረግክ አምላካችን ይሖዋ ሆይ፣ እኛ ኃጢአት ሠርተናል፤ ክፉ ድርጊትም ፈጽመናል።
ይሖዋ ሆይ፣ እንደ ጽድቅ ሥራህ መጠን፣ እባክህ ቁጣህንና ንዴትህን ከከተማህ ከኢየሩሳሌም ይኸውም ከቅዱስ ተራራህ መልስ፤ ምክንያቱም በኃጢአታችንና አባቶቻችን በፈጸሙት በደል የተነሳ ኢየሩሳሌምና ሕዝብህ በዙሪያችን ባሉት ሁሉ ዘንድ መሳለቂያ ሆነዋል።
አሁንም አምላካችን ሆይ፣ የአገልጋይህን ጸሎትና ልመና ስማ፤ ይሖዋ ሆይ፣ ለራስህ ስትል ለፈረሰው መቅደስህ ሞገስ አሳይ።
አምላኬ ሆይ፣ ጆሮህን አዘንብለህ ስማ! ዓይንህን ገልጠህ በስምህ በተጠራችው ከተማችን ላይ የደረሰውን ጥፋት ተመልከት፤ ልመናችንን በፊትህ የምናቀርበው ከእኛ ጽድቅ የተነሳ ሳይሆን ከታላቅ ምሕረትህ የተነሳ ነው።
ይሖዋ ሆይ፣ ስማ። ይሖዋ ሆይ፣ ይቅር በል። ይሖዋ ሆይ፣ ትኩረት ስጥ፤ እርምጃም ውሰድ! አምላኬ ሆይ፣ ለራስህ ስትል አትዘግይ፤ ስምህ በከተማህና በሕዝብህ ላይ ተጠርቷልና።”
እኔም ገና እየተናገርኩና እየጸለይኩ፣ የራሴንና የሕዝቤን የእስራኤልን ኃጢአት እየተናዘዝኩ እንዲሁም በአምላኬ ቅዱስ ተራራ ላይ ሞገሱን እንዲያደርግ አምላኬን ይሖዋን እየለመንኩ፣
አዎ፣ እየጸለይኩ ሳለ፣ ቀደም ሲል በራእዩ ላይ አይቼው የነበረው ሰው ገብርኤል፣ በጣም ተዳክሜ ሳለ የምሽቱ የስጦታ መባ በሚቀርብበት ጊዜ ወደ እኔ መጣ።
እሱም እንዲህ በማለት እንዳስተውል ረዳኝ፦ “ዳንኤል ሆይ፣ አሁን ጥልቅ ማስተዋልና የመረዳት ችሎታ ልሰጥህ መጥቻለሁ።
ልመናህን ገና ማቅረብ ስትጀምር ትእዛዝ ተሰጥቷል፤ እኔም ልነግርህ መጥቻለሁ፤ ምክንያቱም አንተ እጅግ የተወደድክ ነህ። ስለዚህ ለጉዳዩ ትኩረት ስጥ፤ ራእዩንም አስተውል።
“መተላለፍን ለማስቆም፣ ኃጢአትን ለመደምሰስ፣ በደልን ለማስተሰረይ፣ የዘላለም ጽድቅ ለማምጣት፣ ራእዩንና ትንቢቱን ለማተም እንዲሁም ቅድስተ ቅዱሳኑን ለመቀባት ለሕዝብህና ለቅድስቲቱ ከተማህ 70 ሳምንታት ተወስኗል።
ኢየሩሳሌምን ለማደስና መልሶ ለመገንባት ትእዛዝ ከሚወጣበት ጊዜ አንስቶ መሪ የሆነው መሲሕ እስከሚገለጥበት ጊዜ ድረስ 7 ሳምንታትና 62 ሳምንታት እንደሚሆን እወቅ፤ አስተውልም። ኢየሩሳሌም ትታደሳለች፤ ዳግመኛም ትገነባለች፤ አደባባይዋና የመከላከያ ቦይዋ እንደገና ይሠራል፤ ይህ የሚሆነው ግን በአስጨናቂ ወቅት ነው።
“ከ62ቱ ሳምንታት በኋላ መሲሑ ይቆረጣል፤ ትቶት የሚያልፈው ምንም ነገር አይኖርም። “የሚመጣውም መሪ ሠራዊት፣ ከተማዋንና ቅዱሱን ስፍራ ያጠፋል። ፍጻሜው በጎርፍ ይሆናል። እስከ ፍጻሜውም ድረስ ጦርነት ይሆናል፤ ጥፋትም ተወስኗል።
“እሱም ለብዙዎች ቃል ኪዳኑን ለአንድ ሳምንት ያጸናል፤ በሳምንቱም አጋማሽ ላይ መሥዋዕትንና የስጦታ መባን ያስቀራል። “ጥፋት የሚያመጣውም በአስጸያፊ ነገሮች ክንፍ ላይ ሆኖ ይመጣል፤ ጥፋት እስኪመጣም ድረስ የተወሰነው ነገር በወደመው ነገር ላይ ይፈስሳል።”
ናቡከደነጾር በነገሠ በሁለተኛው ዓመት ሕልሞችን አለመ፤ መንፈሱም እጅግ ከመታወኩ የተነሳ እንቅልፍ ሊወስደው አልቻለም።
ስለዚህ ንጉሡ ሕልሞቹን እንዲነግሩት አስማተኞቹ ካህናት፣ ጠንቋዮቹ፣ መተተኞቹና ከለዳውያኑ እንዲጠሩ አዘዘ። በዚህም መሠረት ገብተው በንጉሡ ፊት ቆሙ።
ከዚያም ንጉሡ “ሕልም አልሜ ነበር፤ ሕልሙ ምን እንደሆነ ማወቅ ስለፈለግኩ መንፈሴ ታውኳል” አላቸው።
ከለዳውያኑም በአረማይክ ቋንቋ ለንጉሡ እንዲህ ሲሉ መለሱ፦ “ንጉሥ ሆይ፣ ለዘላለም ኑር። ያየኸውን ሕልም ለአገልጋዮችህ ንገረን፤ እኛም ትርጉሙን እናሳውቅሃለን።”
ንጉሡም ለከለዳውያኑ እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “የመጨረሻ ውሳኔዬ ይህ ነው፦ ሕልሙን ከነትርጉሙ የማታሳውቁኝ ከሆነ ሰውነታችሁ ይቆራረጣል፤ ቤቶቻችሁም የሕዝብ መጸዳጃ ይሆናሉ።
ሕልሙንና ትርጉሙን ብታሳውቁኝ ግን ስጦታ፣ ሽልማትና ታላቅ ክብር እሰጣችኋለሁ። ስለዚህ ሕልሙንና ትርጉሙን አሳውቁኝ።”
እነሱም በድጋሚ መልሰው “ንጉሡ ሕልሙን ለአገልጋዮቹ ይንገረን፤ እኛም ትርጉሙን እንናገራለን” አሉት።
ንጉሡም እንዲህ ሲል መለሰ፦ “የመጨረሻ ውሳኔዬን ስላወቃችሁ ጊዜ ለማራዘም እየሞከራችሁ እንደሆነ በሚገባ ተረድቻለሁ።
ሕልሙን የማታሳውቁኝ ከሆነ ሁላችሁም የሚጠብቃችሁ ቅጣት አንድ ነው። እናንተ ግን ሁኔታው እስኪለወጥ ድረስ፣ የሆነ ውሸትና ማታለያ ልትነግሩኝ ተስማምታችኋል። ስለዚህ ሕልሙን ንገሩኝ፤ እኔም ትርጉሙን ልታብራሩ እንደምትችሉ በዚህ አውቃለሁ።”
ከለዳውያኑም ለንጉሡ እንዲህ ሲሉ መለሱ፦ “ንጉሡ የሚጠይቀውን ነገር መፈጸም የሚችል አንድም ሰው በምድር ላይ የለም፤ የትኛውም ታላቅ ንጉሥ ወይም ገዢ፣ ከማንኛውም አስማተኛ ካህን ወይም ጠንቋይ ወይም ከለዳዊ እንዲህ ዓይነት ነገር ጠይቆ አያውቅም።
ንጉሡ እየጠየቀ ያለው ነገር በጣም አስቸጋሪ ነው፤ በሰዎች መካከል ከማይኖሩት አማልክት በስተቀር ይህን ለንጉሡ ሊገልጽለት የሚችል የለም።”
በዚህ ጊዜ ንጉሡ በቁጣ ቱግ አለ፤ በባቢሎን ያሉት ጥበበኛ ሰዎች ሁሉ እንዲገደሉም አዘዘ።
ትእዛዙ ሲወጣና ጠቢባኑ ሊገደሉ ሲሉ ዳንኤልንና ጓደኞቹንም ለመግደል ይፈልጓቸው ጀመር።
በዚህ ጊዜ ዳንኤል በባቢሎን የሚገኙትን ጥበበኛ ሰዎች ለመግደል የወጣውን የንጉሡን የክብር ዘብ አለቃ አርዮክን በጥበብና በዘዴ አናገረው።
የንጉሡ ባለሥልጣን የሆነውን አርዮክን “ንጉሡ እንዲህ ያለ ከባድ ትእዛዝ ያወጣው ለምንድን ነው?” ሲል ጠየቀው። አርዮክም ጉዳዩን ለዳንኤል ገለጸለት።
ዳንኤልም ወደ ንጉሡ ገብቶ የሕልሙን ትርጉም ለእሱ የሚያስታውቅበት ጊዜ እንዲሰጠው ንጉሡን ጠየቀው።
ከዚያም ዳንኤል ወደ ቤቱ ሄደ፤ ጉዳዩንም ለጓደኞቹ ለሃናንያህ፣ ለሚሳኤልና ለአዛርያስ ነገራቸው።
ደግሞም ዳንኤልንና ጓደኞቹን ከቀሩት የባቢሎን ጠቢባን ጋር እንዳይገድሏቸው የሰማይ አምላክ ምሕረት እንዲያሳያቸውና ሚስጥሩን እንዲገልጥላቸው ይጸልዩ ዘንድ ነገራቸው።
ከዚያም ሚስጥሩ በሌሊት ለዳንኤል በራእይ ተገለጠለት። በመሆኑም ዳንኤል የሰማይን አምላክ አወደሰ።
ዳንኤልም እንዲህ አለ፦ “የአምላክ ስም ከዘላለም እስከ ዘላለም ይወደስ፤ጥበብና ኃይል የእሱ ብቻ ነውና።
እሱ ጊዜያትንና ወቅቶችን ይለውጣል፤ነገሥታትን ያስወግዳል፤ ደግሞም ያስቀምጣል፤ለጥበበኞች ጥበብን፣ ለአስተዋዮችም እውቀትን ይሰጣል።
ጥልቅ የሆኑትንና የተሰወሩትን ነገሮች ይገልጣል፤በጨለማ ውስጥ ያለውን ያውቃል፤ብርሃንም ከእሱ ጋር ይኖራል።
የአባቶቼ አምላክ ሆይ፣ ለአንተ ምስጋናና ውዳሴ አቀርባለሁ፤ምክንያቱም ጥበብንና ኃይልን ሰጥተኸኛል። አሁን ደግሞ ከአንተ የጠየቅነውን ነገር አሳውቀኸኛል፤ንጉሡ ያሳሰበውን ጉዳይ አሳውቀኸናል።”
ከዚያም ዳንኤል የባቢሎንን ጠቢባን እንዲያጠፋ ንጉሡ ወደ ሾመው ወደ አርዮክ ሄዶ “ከባቢሎን ጠቢባን መካከል አንዳቸውንም አትግደል። በንጉሡ ፊት አቅርበኝ፤ እኔም የሕልሙን ትርጉም ለንጉሡ አሳውቃለሁ” አለው።