text
stringlengths
4
267
ንጉሥ ሆይ፣ ትርጉሙ ይህ ነው፤ ልዑሉ አምላክ በጌታዬ በንጉሡ ላይ ይደርሳል ብሎ ያወጀው ነገር ይህ ነው።
ከሰዎች መካከል ትሰደዳለህ፤ ከዱር አራዊትም ጋር ትኖራለህ፤ እንደ በሬም ሣር ትበላለህ፤ በሰማያትም ጠል ትረሰርሳለህ፤ ልዑሉ አምላክ በሰው ልጆች መንግሥት ላይ እንደሚገዛና መንግሥቱንም ለወደደው እንደሚሰጥ እስክታውቅ ድረስ ሰባት ዘመናት ያልፉብሃል።
“‘ይሁንና የዛፉን ጉቶ ከነሥሩ እንዲተዉት ስለተነገራቸው፣ አምላክ በሰማያት እንደሚገዛ ካወቅክ በኋላ መንግሥትህ ይመለስልሃል።
ስለዚህ ንጉሥ ሆይ፣ ምክሬ በአንተ ዘንድ ተቀባይነት ያግኝ። ኃጢአት መሥራትህን ትተህ ትክክል የሆነውን አድርግ፤ ግፍ መፈጸምህን ትተህ ለድሆች ምሕረት አሳይ። ምናልባት የተደላደለ ሕይወት የምትኖርበት ዘመን ይራዘምልህ ይሆናል።’”
ይህ ሁሉ በንጉሥ ናቡከደነጾር ላይ ደረሰ።
ከ12 ወራት በኋላ በባቢሎን ቤተ መንግሥት ሰገነት ላይ እየተመላለሰ ነበር።
ንጉሡም “ይህች፣ ንጉሣዊ መኖሪያ እንድትሆን ለግርማዬ ክብር፣ በገዛ ብርታቴና ኃይሌ የገነባኋት ታላቂቱ ባቢሎን አይደለችም?” አለ።
ንጉሡ ንግግሩን ገና ከአፉ ሳይጨርስ እንዲህ የሚል ድምፅ ከሰማያት መጣ፦ “ንጉሥ ናቡከደነጾር ሆይ፣ የተላከልህ መልእክት ይህ ነው፦ ‘መንግሥትህ ከአንተ ተወስዷል፤
ከሰዎች መካከል ትሰደዳለህ። ከዱር አራዊት ጋር ትኖራለህ፤ እንደ በሬም ሣር ትበላለህ፤ ልዑሉ አምላክ በሰው ልጆች መንግሥት ላይ እንደሚገዛና መንግሥቱንም ለወደደው እንደሚሰጥ እስክታውቅ ድረስ ሰባት ዘመናት ያልፉብሃል።’”
ወዲያውኑ ይህ ቃል በናቡከደነጾር ላይ ተፈጸመ። ከሰው ልጆች መካከል ተሰደደ፤ እንደ በሬም ሣር መብላት ጀመረ፤ ፀጉሩ እንደ ንስር ላባ እስኪረዝም፣ ጥፍሮቹም እንደ ወፍ ጥፍሮች እስኪያድጉ ድረስ ሰውነቱ በሰማያት ጠል ረሰረሰ።
“ዘመኑ በተፈጸመ ጊዜ እኔ ናቡከደነጾር ወደ ሰማያት ተመለከትኩ፤ አእምሮዬም ተመለሰልኝ፤ ልዑሉንም አምላክ አመሰገንኩ፤ ለዘላለም የሚኖረውንም አወደስኩ፤ አከበርኩትም፤ ምክንያቱም የመግዛት ሥልጣኑ ዘላለማዊ ነው፤ መንግሥቱም ከትውልድ እስከ ትውልድ ይኖራል።
የምድር ነዋሪዎች ሁሉ እንደ ኢምንት ይቆጠራሉ፤ በሰማያት ሠራዊትና በምድር ነዋሪዎች ላይ እንደ ፈቃዱ ያደርጋል። ሊያግደው ወይም ‘ምን ማድረግህ ነው?’ ብሎ ሊጠይቀው የሚችል ማንም የለም።
“በዚህ ጊዜ አእምሮዬ ተመለሰልኝ፤ ደግሞም የመንግሥቴ ክብር፣ ግርማዊነቴና ሞገሴ ተመለሰልኝ። ከፍተኛ ባለሥልጣናቴና መኳንንቴ አጥብቀው ፈለጉኝ፤ እኔም ወደ መንግሥቴ ተመለስኩ፤ ከቀድሞውም የበለጠ ታላቅ ሆንኩ።
“አሁንም እኔ ናቡከደነጾር የሰማያትን ንጉሥ አወድሰዋለሁ፣ ከፍ ከፍ አደርገዋለሁ እንዲሁም አከብረዋለሁ፤ ምክንያቱም ሥራው ሁሉ እውነት፣ መንገዶቹም ትክክል ናቸው፤ በኩራት የሚመላለሱትንም ማዋረድ ይችላል።”
“በዚያ ዘመን ለሕዝብህ የሚቆመው ታላቁ አለቃ ሚካኤል ይነሳል። ብሔራት ከተቋቋሙበት ጊዜ አንስቶ እስከዚያ ጊዜ ድረስ ሆኖ የማያውቅ የጭንቀት ጊዜ ይመጣል። በዚያን ወቅት ሕዝብህ ይኸውም በመጽሐፍ ላይ ተጽፎ የተገኘ እያንዳንዱ ሰው ይተርፋል።
በምድር አፈር ውስጥ ካንቀላፉትም መካከል ብዙዎቹ ይነሳሉ፤ አንዳንዶቹ ለዘላለም ሕይወት፣ ሌሎቹ ደግሞ ለነቀፋና ለዘላለማዊ ውርደት ይነሳሉ።
“ደግሞም ጥልቅ ማስተዋል ያላቸው ሰዎች እንደ ሰማይ ጸዳል ያበራሉ፤ የጽድቅን ጎዳና እንዲከተሉ ብዙ ሰዎችን የሚረዱም ለዘላለም እንደ ከዋክብት ያበራሉ።
“አንተም ዳንኤል ሆይ፣ እስከ ፍጻሜው ዘመን ድረስ ቃሉን በሚስጥር ያዝ፤ መጽሐፉንም አትመው። ብዙዎች መጽሐፉን በሚገባ ይመረምራሉ፤ እውነተኛው እውቀትም ይበዛል።”
ከዚያም እኔ ዳንኤል ስመለከት ሌሎች ሁለት በዚያ ቆመው አየሁ፤ አንደኛው ከወንዙ በዚህኛው ዳር ቆሞ የነበረ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ ከወንዙ በዚያኛው ዳር ቆሞ ነበር።
ከዚያም አንዱ፣ ከወንዙ ውኃ በላይ ያለውንና በፍታ የለበሰውን ሰው “እነዚህ አስደናቂ ነገሮች ፍጻሜያቸውን የሚያገኙት ከምን ያህል ጊዜ በኋላ ነው?” አለው።
ከዚያም ከወንዙ ውኃ በላይ ያለውና በፍታ የለበሰው ሰው መልስ ሲሰጥ ሰማሁ። እሱም ቀኝ እጁንና ግራ እጁን ወደ ሰማያት ዘርግቶ ለዘላለም ሕያው በሆነው በመማል እንዲህ ሲል መልስ ሰጠ፦ “ከተወሰነ ዘመን፣ ዘመናትና የዘመን እኩሌታ በኋላ ነው። የቅዱሱ ሕዝብ ኃይል ተደምስሶ እንዳበቃ እነዚህ ሁሉ ነገሮች ፍጻሜያቸውን ያገኛሉ።”
እኔም ሰማሁ፤ ሆኖም ሊገባኝ አልቻለም፤ ስለዚህ “ጌታዬ ሆይ፣ የእነዚህ ነገሮች መጨረሻ ምን ይሆን?” አልኩት።
እሱም እንዲህ አለኝ፦ “ዳንኤል ሆይ፣ ሂድ፤ ምክንያቱም የፍጻሜው ዘመን እስኪመጣ ድረስ ቃሉ በሚስጥር የተያዘና የታተመ ይሆናል።
ብዙዎች ራሳቸውን ያጸዳሉ፣ ያነጻሉ እንዲሁም ይጠራሉ። ክፉዎች ደግሞ ክፉ ድርጊት ይፈጽማሉ፤ ከክፉዎች መካከል አንዳቸውም አይረዱትም፤ ጥልቅ ማስተዋል ያላቸው ግን ይረዱታል።
“የዘወትሩ መሥዋዕት ከተቋረጠበትና ጥፋት የሚያመጣው ርኩስ ነገር ከቆመበት ጊዜ አንስቶ 1,290 ቀን ይሆናል።
“ደግሞም 1,335ቱ ቀን እስከሚያልፍ ድረስ በትዕግሥት የሚጠባበቅ ሰው ደስተኛ ነው!
“አንተ ግን እስከ ፍጻሜው ድረስ ሂድ። ታርፋለህ፤ ሆኖም በዘመኑ ፍጻሜ ዕጣ ፋንታህን ለመቀበል ትነሳለህ።”
ዳርዮስ በመላው ንጉሣዊ ግዛቱ ላይ 120 የአውራጃ ገዢዎችን ለመሾም ወሰነ።
በእነሱ ላይ ሦስት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ሾመ፤ ከእነዚህም አንዱ ዳንኤል ነበር፤ ንጉሡ ለኪሳራ እንዳይዳረግ እነዚህ የአውራጃ ገዢዎች ተጠሪነታቸው ለባለሥልጣናቱ እንዲሆን ተደረገ።
ዳንኤልም በዓይነቱ ልዩ የሆነ መንፈስ ስለነበረው ከከፍተኛ ባለሥልጣናቱና ከአውራጃ ገዢዎቹ ይበልጥ ብቃት እንዳለው አስመሠከረ፤ ንጉሡም በመላው ንጉሣዊ ግዛቱ ላይ ከፍ ያለ ቦታ ሊሰጠው አሰበ።
በዚህ ጊዜ ከፍተኛ ባለሥልጣናቱና የአውራጃ ገዢዎቹ ከመንግሥት ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ዳንኤልን ለመክሰስ የሚያስችል ሰበብ ለማግኘት ይከታተሉት ነበር፤ ሆኖም ዳንኤል እምነት የሚጣልበት ስለነበርና ምንም ዓይነት እንከንና ጉድለት ስላልነበረበት በእሱ ላይ አንዳች ሰበብ ወይም ጉድለት ሊያገኙ አልቻሉም።
በመሆኑም “ከአምላኩ ሕግ ጋር በተያያዘ ካልሆነ በቀር ዳንኤልን ለመክሰስ ምንም ዓይነት ሰበብ ልናገኝ አንችልም” አሉ።
ስለዚህ ከፍተኛ ባለሥልጣናቱና የአውራጃ ገዢዎቹ ተሰብስበው ወደ ንጉሡ በመግባት እንዲህ አሉት፦ “ንጉሥ ዳርዮስ ሆይ፣ ለዘላለም ኑር።
ንጉሥ ሆይ፣ ለ30 ቀናት ያህል ለአንተ ካልሆነ በስተቀር ለአምላክም ሆነ ለሰው ልመና የሚያቀርብ ማንኛውም ግለሰብ ወደ አንበሶች ጉድጓድ እንዲወረወር የሚያዝዝ ንጉሣዊ ድንጋጌ እንዲወጣና እገዳ እንዲጣል የመንግሥት ባለሥልጣናቱ፣ አስተዳዳሪዎቹ፣ የአውራጃ ገዢዎቹ፣ የንጉሡ አማካሪዎችና አገረ ገዢዎቹ ሁሉ በአንድነት ተስማምተዋል።
አሁንም ንጉሥ ሆይ፣ ሊሻር በማይችለው የሜዶናውያንና የፋርሳውያን ሕግ መሠረት ድንጋጌው እንዳይለወጥ አጽናው፤ በጽሑፉም ላይ ፈርምበት።”
ስለዚህ ንጉሥ ዳርዮስ እገዳውን በያዘው ድንጋጌ ላይ ፈረመ።
ዳንኤል ግን ድንጋጌው በፊርማ መጽደቁን እንዳወቀ ወደ ቤቱ ገባ፤ በሰገነት ላይ ባለው ክፍሉ ውስጥ በኢየሩሳሌም አቅጣጫ ያሉት መስኮቶች ተከፍተው ነበር። ከዚህ በፊት አዘውትሮ ያደርግ እንደነበረውም በቀን ሦስት ጊዜ በጉልበቱ ተንበርክኮ ጸለየ፤ ለአምላኩም ውዳሴ አቀረበ።
ሰዎቹ በሩን በርግደው በገቡ ጊዜ ዳንኤል በአምላኩ ፊት ሞገስ ለማግኘት ልመና ሲያቀርብና ሲማጸን አገኙት።
በመሆኑም ወደ ንጉሡ ቀርበው “ንጉሥ ሆይ፣ ለ30 ቀናት ያህል ለአንተ ካልሆነ በስተቀር ለአምላክም ሆነ ለሰው ልመና የሚያቀርብ ማንኛውም ግለሰብ ወደ አንበሶች ጉድጓድ እንዲወረወር የሚደነግገውን እገዳ በፊርማህ አጽድቀህ አልነበረም?” በማለት ንጉሡ የጣለውን እገዳ አስታወሱት። ንጉሡም “ጉዳዩ ሊሻር በማይችለው በሜዶናውያንና በፋርሳውያን ሕግ መሠረት በሚገባ የጸና ነው” ሲል መለሰላቸው።
እነሱም ቀበል አድርገው ንጉሡን እንዲህ አሉት፦ “ንጉሥ ሆይ፣ ከይሁዳ ግዞተኞች አንዱ የሆነው ዳንኤል፣ ለአንተም ሆነ በፊርማህ ላጸደቅከው እገዳ አክብሮት የለውም፤ ይልቁንም በቀን ሦስት ጊዜ ይጸልያል።”
ንጉሡም ይህን በሰማ ጊዜ እጅግ ተጨነቀ፤ ዳንኤልንም መታደግ የሚችልበትን መንገድ ያወጣና ያወርድ ጀመር፤ ፀሐይ እስክትጠልቅም ድረስ እሱን ለማዳን የተቻለውን ሁሉ ጥረት ሲያደርግ ቆየ።
በመጨረሻም እነዚህ ሰዎች አንድ ላይ ሆነው ወደ ንጉሡ በመግባት ንጉሡን እንዲህ አሉት፦ “ንጉሥ ሆይ፣ በሜዶናውያንና በፋርሳውያን ሕግ መሠረት ንጉሡ ያጸናው ማንኛውም እገዳ ወይም ድንጋጌ ሊለወጥ እንደማይችል አትርሳ።”
ስለዚህ ንጉሡ ትእዛዝ አስተላለፈ፤ እነሱም ዳንኤልን አምጥተው አንበሶች ጉድጓድ ውስጥ ጣሉት። ንጉሡም ዳንኤልን “ሁልጊዜ የምታገለግለው አምላክህ ይታደግሃል” አለው።
ከዚያም ድንጋይ አምጥተው በጉድጓዱ አፍ ላይ ገጠሙት፤ ንጉሡም በዳንኤል ላይ የተወሰደው እርምጃ እንዳይለወጥ፣ በራሱ የማኅተም ቀለበትና በመኳንንቱ የማኅተም ቀለበት በድንጋዩ ላይ አተመበት።
ከዚያም ንጉሡ ወደ ቤተ መንግሥቱ ሄደ። ጾሙንም አደረ፤ በምንም ነገር መዝናናት አልፈለገም፤ እንቅልፍም በዓይኑ አልዞረም።
በመጨረሻም ንጉሡ ገና ጎህ ሲቀድ ተነስቶ እየተጣደፈ ወደ አንበሶቹ ጉድጓድ ሄደ።
ወደ ጉድጓዱ በቀረበ ጊዜ ሐዘን በተቀላቀለበት ድምፅ ጮክ ብሎ ዳንኤልን ተጣራ። ንጉሡም ዳንኤልን “የሕያው አምላክ አገልጋይ ዳንኤል ሆይ፣ ሁልጊዜ የምታገለግለው አምላክህ ከአንበሶቹ ሊታደግህ ችሏል?” አለው።
ዳንኤልም ንጉሡን እንዲህ አለው፦ “ንጉሥ ሆይ፣ ለዘላለም ኑር።
አምላኬ መልአኩን ልኮ የአንበሶቹን አፍ ዘጋ፤ እነሱም አልጎዱኝም፤ በፊቱ ንጹሕ ሆኜ ተገኝቻለሁና፤ ንጉሥ ሆይ፣ በአንተም ላይ የሠራሁት በደል የለም።”
ንጉሡ እጅግ ተደሰተ፤ ዳንኤልንም ከጉድጓዱ እንዲያወጡት አዘዘ። እነሱም ከጉድጓዱ አወጡት፤ ዳንኤል በአምላኩ ታምኖ ስለነበር ምንም ጉዳት አልደረሰበትም።
ከዚያም በንጉሡ ትእዛዝ መሠረት፣ የዳንኤልን ከሳሾች አምጥተው ከነልጆቻቸውና ከነሚስቶቻቸው ወደ አንበሶቹ ጉድጓድ ጣሏቸው። ገና ወደ ጉድጓዱ መጨረሻ ሳይደርሱ አንበሶቹ ተቀራመቷቸው፤ አጥንቶቻቸውንም ሁሉ አደቀቁ።
ከዚያም ንጉሥ ዳርዮስ በመላው ምድር ለሚኖሩ ከተለያዩ ብሔራትና ቋንቋዎች ለተውጣጡ ሕዝቦች ሁሉ እንዲህ ሲል ጻፈ፦ “ሰላም ይብዛላችሁ!
በየትኛውም የመንግሥቴ ግዛት የሚኖሩ ሰዎች የዳንኤልን አምላክ ፈርተው እንዲንቀጠቀጡ ትእዛዝ አስተላልፌአለሁ። እሱ ለዘላለም የሚኖር ሕያው አምላክ ነውና። መንግሥቱ ፈጽሞ አይጠፋም፤ የመግዛት ሥልጣኑም ዘላለማዊ ነው።
እሱ ይታደጋል፤ ደግሞም ያድናል፤ በሰማያትና በምድርም ተአምራዊ ምልክቶችንና ድንቅ ነገሮችን ያደርጋል፤ ዳንኤልን ከአንበሶች መዳፍ ታድጎታልና።”
ስለዚህ ዳንኤል በዳርዮስ መንግሥት እንዲሁም በፋርሳዊው በቂሮስ መንግሥት ሁሉ ነገር ተሳካለት።
ንጉሥ ቤልሻዛር በነገሠ በሦስተኛው ዓመት፣ ቀደም ሲል ከተገለጠልኝ ራእይ በኋላ ለእኔ፣ ለዳንኤል ሌላ ራእይ ተገለጠልኝ።
እኔም ራእዩን ተመለከትኩ፤ በራእዩም ላይ ራሴን፣ በኤላም አውራጃ በሚገኘው በሹሻን ግንብ አየሁት፤ ደግሞም ራእዩን ተመለከትኩ፤ እኔም በኡላይ የውኃ መውረጃ አጠገብ ነበርኩ።
ዓይኔን አንስቼ ስመለከት፣ እነሆ በውኃ መውረጃው አጠገብ ሁለት ቀንዶች ያሉት አንድ አውራ በግ ቆሞ ነበር። ሁለቱ ቀንዶች ረጃጅም ነበሩ፤ ይሁንና አንደኛው ከሌላው ይረዝማል፤ ይበልጥ ረጅም የሆነው ቀንድ የበቀለው በኋላ ነው።
አውራ በጉ ወደ ምዕራብ፣ ወደ ሰሜንና ወደ ደቡብ በቀንዱ ሲወጋ ተመለከትኩ፤ አንድም አውሬ ሊቋቋመው አልቻለም፤ ከእጁም መታደግ የሚችል ማንም አልነበረም። የፈለገውን ያደርግ ነበር፤ ራሱንም ከፍ ከፍ አደረገ።
እየተመለከትኩ ሳለ፣ እነሆ አንድ አውራ ፍየል ከምዕራብ ተነስቶ መሬት ሳይነካ መላዋን ምድር እያቋረጠ መጣ። አውራውም ፍየል በዓይኖቹ መካከል ጎልቶ የሚታይ ቀንድ ነበረው።
እሱም በውኃ መውረጃው አጠገብ ቆሞ ወዳየሁት ሁለት ቀንድ ወዳለው አውራ በግ አመራ፤ በታላቅ ቁጣም ተንደርድሮ መጣበት።
ወደ አውራው በግ ሲቀርብ አየሁት፤ በበጉም እጅግ ተመርሮ ነበር። በጉን መትቶ ሁለቱንም ቀንዶቹን ሰባበራቸው፤ አውራውም በግ ሊቋቋመው የሚችልበት አቅም አልነበረውም። በጉን መሬት ላይ ጥሎ ረጋገጠው፤ አውራ በጉንም ከእጁ የሚያስጥለው አልነበረም።
ከዚያም አውራው ፍየል እጅግ ታበየ፤ ሆኖም ኃያል በሆነ ጊዜ ትልቁ ቀንድ ተሰበረ፤ በምትኩም ጎልተው የሚታዩ አራት ቀንዶች ወደ አራቱ የሰማይ ነፋሳት በቀሉ።
ከእነሱ መካከል ከአንደኛው፣ አንድ ሌላ ትንሽ ቀንድ በቀለ፤ ወደ ደቡብ፣ ወደ ምሥራቅና ውብ ወደሆነችው ምድር በጣም እያደገ ሄደ።
ወደ ሰማይ ሠራዊት እስከሚደርስ ድረስ እያደገ ሄደ፤ ከሠራዊቱና ከከዋክብቱ መካከልም የተወሰኑትን ወደ ምድር ጣለ፤ ረጋገጣቸውም።
በሠራዊቱ አለቃ ላይ እንኳ ሳይቀር ራሱን ከፍ ከፍ አደረገ፤ የዘወትሩም መሥዋዕት ከአለቃው ተወሰደ፤ ጽኑ የሆነው የመቅደሱ ስፍራም ፈረሰ።
ከተፈጸመው በደል የተነሳ ሠራዊቱ ከዘወትሩ መሥዋዕት ጋር ለቀንዱ አልፎ ተሰጠ፤ እውነትን ወደ ምድር ጣለ፤ እንደ ፈቃዱ አደረገ፤ ደግሞም ተሳካለት።
ከቅዱሳኑም አንዱ ሲናገር ሰማሁ፤ ሌላውም ቅዱስ እየተናገረ ለነበረው ቅዱስ እንዲህ አለው፦ “ስለ ዘወትሩ መሥዋዕትና ጥፋት ስለሚያመጣው በደል እንዲሁም ቅዱሱ ስፍራና ሠራዊቱ እንዲረገጡ ስለመተዋቸው በሚገልጸው ራእይ ላይ የታየው ነገር የሚቆየው እስከ መቼ ነው?”
እሱም “2,300 ምሽቶችና ንጋቶች እስኪያልፉ ድረስ ነው፤ ቅዱሱም ስፍራ ወደ ትክክለኛው ሁኔታ በእርግጥ ይመለሳል” አለኝ።
እኔ ዳንኤል ራእዩን እየተመለከትኩና ለመረዳት እየጣርኩ ሳለ፣ ሰው የሚመስል ድንገት ከፊት ለፊቴ ቆሞ አየሁ።
ከዚያም ከኡላይ መካከል የሰው ድምፅ ሰማሁ፤ እሱም ጮክ ብሎ “ገብርኤል፣ ለዚህ ሰው ያየውን ነገር አስረዳው” አለ።
በመሆኑም እኔ ወደቆምኩበት ስፍራ ቀረበ፤ ሆኖም ወደ እኔ ሲመጣ፣ በጣም ከመደንገጤ የተነሳ በግንባሬ ተደፋሁ። እሱም “የሰው ልጅ ሆይ፣ ራእዩ የሚፈጸመው በዘመኑ ፍጻሜ መሆኑን ተረዳ” አለኝ።
እኔ ግን እያናገረኝ ሳለ መሬት ላይ በግንባሬ ተደፋሁ፤ ከባድ እንቅልፍም ወሰደኝ። ስለዚህ ዳሰሰኝና ቆሜበት በነበረው ቦታ እንድቆም አደረገኝ።
ከዚያም እንዲህ አለኝ፦ “እነሆ፣ በቁጣው ዘመን ማብቂያ ላይ የሚሆነውን ነገር አሳውቅሃለሁ፤ ምክንያቱም ራእዩ በተወሰነው የፍጻሜ ዘመን ይፈጸማል።
“ያየኸው ሁለት ቀንዶች ያሉት አውራ በግ የሜዶንንና የፋርስን ነገሥታት ያመለክታል።
ፀጉራሙ አውራ ፍየል የግሪክን ንጉሥ ያመለክታል፤ በዓይኖቹ መካከል ያለው ትልቁ ቀንድ የመጀመሪያውን ንጉሥ ያመለክታል።
ቀንዱ ተሰብሮ በምትኩ አራት ቀንዶች እንደወጡ ሁሉ ከእሱ ብሔር የሚነሱ አራት መንግሥታት ይኖራሉ፤ ሆኖም የእሱን ያህል ኃይል አይኖራቸውም።
“በዘመነ መንግሥታቸውም መገባደጃ ላይ በደለኞቹ እስከ መጨረሻ በደል ሲፈጽሙ፣ ግራ የሚያጋቡ አባባሎችን የሚረዳ አስፈሪ መልክ ያለው ንጉሥ ይነሳል።
ኃይሉ እጅግ ታላቅ ይሆናል፤ በገዛ ኃይሉ ግን አይደለም። ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ጥፋት ያደርሳል፤ የሚያደርገው ነገር ሁሉ ይሳካለታል። በኃያላን ሰዎችና በቅዱሳኑ ሕዝብ ላይ ጥፋት ያደርሳል።
መሠሪ ዘዴ ተጠቅሞ ብዙዎችን በማታለል ረገድ ይሳካለታል፤ በልቡም ራሱን ከፍ ከፍ ያደርጋል፤ ሰዎች ተረጋግተው በሚኖሩበት ጊዜም በብዙዎች ላይ ጥፋት ያደርሳል። አልፎ ተርፎም የልዑላን ልዑል በሆነው ላይ ይነሳል፤ ሆኖም የሰው እጅ ሳይነካው ይሰበራል።
“ምሽቶቹንና ንጋቶቹን በተመለከተ በራእይ የተነገረው ነገር እውነት ነው፤ አንተ ግን ራእዩን በሚስጥር ያዝ፤ ከብዙ ዘመን በኋላ የሚሆነውን ነገር የሚያመለክት ነውና።”
እኔም ዳንኤል ኃይሌ ተሟጠጠ፤ ለተወሰኑ ቀናትም ታመምኩ። ከዚያም ተነስቼ ለንጉሡ የማከናውነውን ሥራ መሥራት ጀመርኩ፤ ሆኖም ባየሁት ነገር የተነሳ ደንዝዤ ነበር፤ ራእዩንም ማንም ሰው ሊረዳው አልቻለም።
“እስራኤል ገና ልጅ ሳለ ወደድኩት፤ልጄንም ከግብፅ ጠራሁት።
እነሱ ደጋግመው በጠሯቸው መጠንበዚያው ልክ ከእነሱ ራቁ። ለባአል ምስሎች መሠዋታቸውን፣ለተቀረጹት ምስሎችም መሥዋዕት ማቅረባቸውን ቀጠሉ።
እኔ ግን ኤፍሬምን መራመድ አስተማርኩት፤ በክንዶቼም ተሸከምኳቸው፤የፈወስኳቸውም እኔ እንደሆንኩ አምነው አልተቀበሉም።
በሰዎች ገመድ፣ በፍቅርም ማሰሪያ ሳብኳቸው፤ደግሞም ከጫንቃቸው ላይ ቀንበር እንደሚያነሳ ሰው ሆንኩላቸው፤ለእያንዳንዳቸውም በደግነት ምግብ አቀረብኩላቸው።
እነሱ ወደ ግብፅ ምድር አይመለሱም፤ ሆኖም አሦር ንጉሣቸው ይሆናል፤ምክንያቱም ወደ እኔ ለመመለስ አሻፈረን ብለዋል።
በጠነሰሱት ሴራ የተነሳ በከተሞቹ ላይ ሰይፍ ያንዣብባል፤መቀርቀሪያዎቹንም ይሰባብራል፤ ይበላቸዋልም።
ሕዝቤ በእኔ ላይ ክህደት ከመፈጸም ወደኋላ አይሉም። ወደ ላይ ቢጠሯቸውም ማንም አይነሳም።
ኤፍሬም ሆይ፣ እንዴት ልተውህ እችላለሁ? እስራኤል ሆይ፣ እንዴት አሳልፌ ልሰጥህ እችላለሁ? እንዴትስ እንደ አድማህ አደርግሃለሁ? ደግሞስ እንዴት እንደ ጸቦይም ላደርግህ እችላለሁ? ስለ አንተ ያለኝ አመለካከት ተለወጠ፤የርኅራኄ ስሜቴም ተቀሰቀሰ።
የሚነድ ቁጣዬን አልገልጽም። ኤፍሬምን ዳግመኛ አላጠፋም፤እኔ አምላክ እንጂ ሰው አይደለሁምና፤በመካከልህ ያለሁ ቅዱስ አምላክ ነኝ፤በአንተም ላይ በቁጣ አልመጣም።
እነሱ ይሖዋን ተከትለው ይሄዳሉ፤ እሱም እንደ አንበሳ ያገሳል፤እሱ ሲያገሳ ልጆቹ ከምዕራብ እየተንቀጠቀጡ ይመጣሉ።
ከግብፅ ሲወጡ እንደ ወፍ፣ከአሦርም ምድር ሲወጡ እንደ ርግብ ይርገፈገፋሉ፤እኔም በየቤታቸው እንዲኖሩ አደርጋቸዋለሁ” ይላል ይሖዋ።
“ኤፍሬም በውሸት፣የእስራኤልም ቤት በማታለል ከበበኝ። ይሁዳ ግን አሁንም ከአምላክ ጋር ይሄዳል፤እጅግ ቅዱስ ለሆነውም አምላክ ታማኝ ነው።”
በይሁዳ ነገሥታት በዖዝያ፣ በኢዮዓታም፣ በአካዝና በሕዝቅያስ እንዲሁም በእስራኤል ንጉሥ በዮአስ ልጅ በኢዮርብዓም ዘመን ወደ ቤኤሪ ልጅ ወደ ሆሴዕ የመጣው የይሖዋ ቃል።
ይሖዋ በሆሴዕ አማካኝነት ቃሉን መናገር ሲጀምር ይሖዋ ሆሴዕን እንዲህ አለው፦ “ሄደህ ዝሙት አዳሪ ሴት አግባ፤ እሷ በምትፈጽመውም ምንዝር ልጆች ይወለዱልሃል፤ ምክንያቱም በምንዝር የተነሳ ምድሪቱ ይሖዋን ከመከተል ሙሉ በሙሉ ርቃለች።”
ስለዚህ ሄዶ የዲብላይምን ልጅ ጎሜርን አገባ፤ እሷም ፀነሰች፤ ወንድ ልጅም ወለደችለት።
ከዚያም ይሖዋ እንዲህ አለው፦ “ልጁን ኢይዝራኤል ብለህ ጥራው፤ በኢይዝራኤል ለፈሰሰው ደም የኢዩን ቤት በቅርቡ ተጠያቂ አደርጋለሁና፤ የእስራኤል ቤት ንጉሣዊ አገዛዝም እንዲያከትም አደርጋለሁ።
በዚያ ቀን የእስራኤልን ቀስት በኢይዝራኤል ሸለቆ እሰብራለሁ።”
እሷም ዳግመኛ ፀነሰች፤ ሴት ልጅም ወለደች። አምላክም እንዲህ አለው፦ “ልጅቷን ሎሩሃማ ብለህ ጥራት፤ ምክንያቱም ከእንግዲህ ለእስራኤል ቤት ምሕረት አላሳይም፤ በእርግጥ አስወግዳቸዋለሁ።