text
stringlengths
4
267
አሳ ኢዮሳፍጥን ወለደ፤ኢዮሳፍጥ ኢዮራምን ወለደ፤ኢዮራም ዖዝያን ወለደ፤
ዖዝያ ኢዮዓታምን ወለደ፤ኢዮዓታም አካዝን ወለደ፤አካዝ ሕዝቅያስን ወለደ፤
ሕዝቅያስ ምናሴን ወለደ፤ምናሴ አምዖንን ወለደ፤አምዖን ኢዮስያስን ወለደ፤
ኢዮስያስ አይሁዳውያን ወደ ባቢሎን በተጋዙበት ዘመን ኢኮንያንን እና ወንድሞቹን ወለደ።
ወደ ባቢሎን ከተጋዙ በኋላ ኢኮንያን ሰላትያልን ወለደ፤ሰላትያል ዘሩባቤልን ወለደ፤
ዘሩባቤል አብዩድን ወለደ፤አብዩድ ኤልያቄምን ወለደ፤ኤልያቄም አዞርን ወለደ፤
አዞር ሳዶቅን ወለደ፤ሳዶቅ አኪምን ወለደ፤አኪም ኤልዩድን ወለደ፤
ኤልዩድ አልዓዛርን ወለደ፤አልዓዛር ማታንን ወለደ፤ማታን ያዕቆብን ወለደ፤
ያዕቆብ ዮሴፍን ወለደ፤ ዮሴፍም ክርስቶስ የተባለውን ኢየሱስን የወለደችው የማርያም ባል ነበር።
ስለዚህ ጠቅላላው ትውልድ፣ ከአብርሃም እስከ ዳዊት 14 ትውልድ፣ ከዳዊት አንስቶ አይሁዳውያን ወደ ባቢሎን እስከተጋዙበት ጊዜ ድረስ 14 ትውልድ እንዲሁም ወደ ባቢሎን ከተጋዙበት ዘመን እስከ ክርስቶስ ድረስ 14 ትውልድ ነው።
ይሁንና ኢየሱስ ክርስቶስ የተወለደበት ሁኔታ እንደሚከተለው ነው፦ እናቱ ማርያም ለዮሴፍ ታጭታ በነበረበት ጊዜ፣ አብረው መኖር ከመጀመራቸው በፊት በመንፈስ ቅዱስ ፀንሳ ተገኘች።
ይሁን እንጂ ባሏ ዮሴፍ ጻድቅ ስለሆነና በይፋ ሊያጋልጣት ስላልፈለገ በስውር ሊፈታት አሰበ።
ሆኖም ይህን ለማድረግ አስቦ ሳለ የይሖዋ መልአክ በሕልም ተገልጦለት እንዲህ አለው፦ “የዳዊት ልጅ ዮሴፍ ሆይ፣ ሚስትህ ማርያም የፀነሰችው በመንፈስ ቅዱስ ስለሆነ እሷን ወደ ቤት ለመውሰድ አትፍራ።
ወንድ ልጅ ትወልዳለች፤ እሱንም ኢየሱስ ብለህ ትጠራዋለህ፤ ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ያድናቸዋልና።”
ይህ ሁሉ የሆነው ይሖዋ በነቢዩ በኩል እንዲህ ሲል የተናገረው ይፈጸም ዘንድ ነው፦
“እነሆ! ድንግል ትፀንሳለች፤ ወንድ ልጅም ትወልዳለች፤ ስሙንም አማኑኤል ይሉታል”፤ ትርጉሙም “አምላክ ከእኛ ጋር ነው” ማለት ነው።
ከዚያም ዮሴፍ ከእንቅልፉ ነቃ፤ የይሖዋ መልአክ ባዘዘውም መሠረት ሚስቱን ወደ ቤቱ ወሰዳት።
ሆኖም ልጁን እስክትወልድ ድረስ ከእሷ ጋር የፆታ ግንኙነት አልፈጸመም፤ ልጁንም ኢየሱስ ብሎ ጠራው።
“እንዳይፈረድባችሁ በሌሎች ላይ አትፍረዱ፤
በምትፈርዱት ፍርድ ይፈረድባችኋል፤ በምትሰፍሩበት መስፈሪያም ይሰፍሩላችኋል።
ታዲያ በራስህ ዓይን ውስጥ ያለውን ግንድ ትተህ በወንድምህ ዓይን ውስጥ ያለውን ጉድፍ ለምን ታያለህ?
ወይም በራስህ ዓይን ውስጥ ግንድ እያለ ወንድምህን ‘ዓይንህ ውስጥ ያለውን ጉድፍ ላውጣልህ’ እንዴት ትለዋለህ?
አንተ ግብዝ! መጀመሪያ በራስህ ዓይን ውስጥ ያለውን ግንድ አውጣ፤ ከዚያም በወንድምህ ዓይን ውስጥ ያለውን ጉድፍ ለማውጣት አጥርተህ ማየት ትችላለህ።
“ቅዱስ የሆነውን ነገር ለውሾች አትስጡ፤ ዕንቁዎቻችሁንም በአሳማ ፊት አትጣሉ። አለዚያ ዕንቁዎቹን በእግራቸው ይረጋግጧቸዋል፤ ተመልሰውም ይጎዷችኋል።
“ደጋግማችሁ ለምኑ፣ ይሰጣችኋል፤ ሳታቋርጡ ፈልጉ፣ ታገኛላችሁ፤ ደጋግማችሁ አንኳኩ፣ ይከፈትላችኋል።
የሚለምን ሁሉ ይሰጠዋልና፤ የሚፈልግ ሁሉ ያገኛል፤ ለሚያንኳኳም ሁሉ ይከፈትለታል።
ደግሞስ ከእናንተ መካከል ልጁ ዳቦ ቢለምነው ድንጋይ የሚሰጠው አለ?
ወይስ ዓሣ ቢለምነው እባብ ይሰጠዋል?
ታዲያ እናንተ ክፉዎች ሆናችሁ ሳለ ለልጆቻችሁ መልካም ስጦታ መስጠት ካወቃችሁ በሰማያት ያለው አባታችሁማ ለሚለምኑት መልካም ነገር እንዴት አብልጦ አይሰጣቸው!
“እንግዲህ ሰዎች እንዲያደርጉላችሁ የምትፈልጉትን ነገር ሁሉ እናንተም አድርጉላቸው። ሕጉም ሆነ የነቢያት ቃል የሚሉት ይህንኑ ነው።
“በጠባቡ በር ግቡ፤ ምክንያቱም ወደ ጥፋት የሚወስደው በር ትልቅ፣ መንገዱም ሰፊ ነው፤ በዚያ የሚሄዱም ብዙዎች ናቸው፤
ወደ ሕይወት የሚወስደው በር ግን ጠባብ፣ መንገዱም ቀጭን ነው፤ የሚያገኙትም ጥቂቶች ናቸው።
“በውስጣቸው ነጣቂ ተኩላዎች ሆነው ሳሉ የበግ ለምድ ለብሰው ወደ እናንተ ከሚመጡ ሐሰተኛ ነቢያት ተጠንቀቁ።
ከፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ። ሰዎች ከእሾህ ወይን፣ ከአሜኬላስ በለስ ይለቅማሉ?
በተመሳሳይም ጥሩ ዛፍ ሁሉ መልካም ፍሬ ያፈራል፤ የበሰበሰ ዛፍ ሁሉ ግን መጥፎ ፍሬ ያፈራል።
ጥሩ ዛፍ መጥፎ ፍሬ ሊያፈራ አይችልም፤ የበሰበሰም ዛፍ መልካም ፍሬ ሊያፈራ አይችልም።
መልካም ፍሬ የማያፈራ ዛፍ ሁሉ ተቆርጦ ወደ እሳት ይጣላል።
በመሆኑም እነዚህን ሰዎች ከፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ።
“‘ጌታ ሆይ፣ ጌታ ሆይ’ የሚለኝ ሁሉ ወደ መንግሥተ ሰማያት አይገባም፤ ወደ መንግሥተ ሰማያት የሚገባው በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ ብቻ ነው።
በዚያ ቀን ብዙዎች እንዲህ ይሉኛል፦ ‘ጌታ ሆይ፣ ጌታ ሆይ፣ በስምህ ትንቢት አልተናገርንም? በስምህ አጋንንትን አላወጣንም? በስምህስ ብዙ ተአምራት አላደረግንም?’
እኔም በዚያ ጊዜ ‘ቀድሞውንም አላውቃችሁም! እናንተ ዓመፀኞች፣ ከእኔ ራቁ!’ እላቸዋለሁ።
“ስለዚህ ይህን ቃሌን ሰምቶ በተግባር የሚያውል ሁሉ ቤቱን በዓለት ላይ የሠራን አስተዋይ ሰው ይመስላል።
ዶፍ ወረደ፤ ጎርፍ ጎረፈ፤ ነፋስም ነፈሰ፤ ቤቱንም በኃይል መታው፤ ሆኖም ቤቱ በዓለት ላይ ስለተመሠረተ አልተደረመሰም።
ይህን ቃሌን ሰምቶ በተግባር የማያውል ሁሉ ግን ቤቱን በአሸዋ ላይ የሠራን ሞኝ ሰው ይመስላል።
ዶፍ ወረደ፤ ጎርፍ ጎረፈ፤ ነፋስም ነፈሰ፤ ቤቱንም በኃይል መታው፤ ቤቱም ተደረመሰ፤ እንዳልነበረም ሆነ።”
ኢየሱስ ንግግሩን በጨረሰ ጊዜ ሕዝቡ በትምህርት አሰጣጡ እጅግ ተደነቁ፤
የሚያስተምራቸው እንደ እነሱ ጸሐፍት ሳይሆን እንደ ባለሥልጣን ነበርና።
“በተጨማሪም መንግሥተ ሰማያት መብራታቸውን ይዘው ሙሽራውን ሊቀበሉ ከወጡ አሥር ደናግል ጋር ሊመሳሰል ይችላል።
አምስቱ ሞኞች፣ አምስቱ ደግሞ ልባሞች ነበሩ።
ሞኞቹ መብራታቸውን ቢይዙም መጠባበቂያ ዘይት አልያዙም ነበር፤
ልባሞቹ ግን ከመብራታቸው ጋር በዕቃ ዘይት ይዘው ነበር።
ሙሽራው በዘገየ ጊዜ ሁሉም እንቅልፍ ተጫጫናቸውና ተኙ።
እኩለ ሌሊት ላይ ‘ሙሽራው እየመጣ ነው፤ ወጥታችሁ ተቀበሉት!’ የሚል ጫጫታ ተሰማ።
በዚህ ጊዜ ደናግሉ ሁሉ ተነስተው መብራቶቻቸውን አዘጋጁ።
ሞኞቹ ደናግል ልባሞቹን ‘መብራታችን ሊጠፋብን ስለሆነ ከያዛችሁት ዘይት ላይ ስጡን’ አሏቸው።
ልባሞቹም ‘ለእናንተ ከሰጠናችሁ ለእኛም ለእናንተም ላይበቃን ስለሚችል ወደ ሻጮች ሄዳችሁ ለራሳችሁ የተወሰነ ዘይት ብትገዙ ይሻላል’ ብለው መለሱላቸው።
ሊገዙ ሄደው ሳሉም ሙሽራው ደረሰ። ተዘጋጅተው የነበሩት ደናግልም ወደ ሠርጉ ድግስ ገቡ፤ በሩም ተዘጋ።
በኋላም የቀሩት ደናግል መጥተው ‘ጌታ ሆይ፣ ጌታ ሆይ፣ ክፈትልን!’ አሉ።
እሱ ግን ‘እውነቴን ነው የምላችሁ፣ አላውቃችሁም’ አላቸው።
“እንግዲህ ቀኑንም ሆነ ሰዓቱን ስለማታውቁ ዘወትር ነቅታችሁ ጠብቁ።
“ደግሞም መንግሥተ ሰማያት ባሪያዎቹን ጠርቶ ንብረቱን ለእነሱ በአደራ በመስጠት ወደ ሌላ አገር ለመሄድ ከተነሳ ሰው ጋር ይመሳሰላል።
ለእያንዳንዱ እንደ ችሎታው፣ ለአንዱ አምስት ታላንት፣ ለሌላው ሁለት፣ ለሌላው ደግሞ አንድ በመስጠት ወደ ሌላ አገር ሄደ።
አምስት ታላንት የተቀበለው ሰው ወዲያው ሄዶ ነገደበትና ሌላ አምስት ታላንት አተረፈ።
በተመሳሳይም ሁለት ታላንት የተቀበለው ሌላ ሁለት አተረፈ።
አንድ ታላንት ብቻ የተቀበለው ባሪያ ግን ሄዶ መሬት ቆፈረና ጌታው የሰጠውን ገንዘብ ቀበረ።
“ከረጅም ጊዜ በኋላ የእነዚያ ባሪያዎች ጌታ መጥቶ ሒሳቡን ከባሪያዎቹ ጋር ተሳሰበ።
ስለዚህ አምስት ታላንት የተቀበለው ባሪያ ሌላ አምስት ተጨማሪ ታላንት ይዞ በመቅረብ ‘ጌታ ሆይ፣ አምስት ታላንት ሰጥተኸኝ ነበር፤ ይኸው ሌላ አምስት ታላንት አተረፍኩ’ አለ።
ጌታውም ‘ጎበዝ፣ አንተ ጥሩና ታማኝ ባሪያ! በጥቂት ነገሮች ታማኝ ሆነህ ተገኝተሃል። ስለዚህ በብዙ ነገሮች ላይ እሾምሃለሁ። ወደ ጌታህ ደስታ ግባ’ አለው።
ቀጥሎም ሁለት ታላንት የተቀበለው ባሪያ ቀርቦ ‘ጌታ ሆይ፣ ሁለት ታላንት ሰጥተኸኝ ነበር፤ ይኸው ሌላ ሁለት ታላንት አተረፍኩ’ አለ።
ጌታውም ‘ጎበዝ፣ አንተ ጥሩና ታማኝ ባሪያ! በጥቂት ነገሮች ታማኝ ሆነህ ተገኝተሃል። ስለዚህ በብዙ ነገሮች ላይ እሾምሃለሁ። ወደ ጌታህ ደስታ ግባ’ አለው።
“በመጨረሻም አንድ ታላንት የተቀበለው ባሪያ ቀርቦ እንዲህ አለው፦ ‘ጌታ ሆይ፣ አንተ ያልዘራኸውን የምታጭድ፣ ያልደከምክበትንም እህል የምትሰበስብ ኃይለኛ ሰው መሆንህን አውቃለሁ።
ስለዚህ ፈራሁ፤ ሄጄም ታላንትህን መሬት ውስጥ ቀበርኩት። ገንዘብህ ይኸውልህ።’
ጌታውም መልሶ እንዲህ አለው፦ ‘አንተ ክፉና ሰነፍ ባሪያ፣ ያልዘራሁትን የማጭድ፣ ያልደከምኩበትንም እህል የምሰበስብ መሆኔን ታውቅ ኖሯል?
ይህን ካወቅክ ገንዘቤን፣ ገንዘብ ለዋጮች ጋ ማስቀመጥ ነበረብህ፤ እኔም ስመጣ ገንዘቤን ከነወለዱ እወስደው ነበር።
“‘ስለዚህ ታላንቱን ውሰዱበትና አሥር ታላንት ላለው ስጡት።
ምክንያቱም ላለው ሁሉ ይጨመርለታል፤ ደግሞም ይትረፈረፍለታል። የሌለው ግን ያው ያለው እንኳ ይወሰድበታል።
ይህን የማይረባ ባሪያ ውጭ ወዳለው ጨለማ ጣሉት። በዚያም ያለቅሳል፤ ጥርሱንም ያፋጫል።’
“የሰው ልጅ ከመላእክቱ ሁሉ ጋር በክብሩ ሲመጣ በክብራማ ዙፋኑ ላይ ይቀመጣል።
ሕዝቦች ሁሉ በፊቱ ይሰበሰባሉ፤ እረኛ በጎቹን ከፍየሎቹ እንደሚለይ ሁሉ እሱም ሰዎችን አንዱን ከሌላው ይለያል።
በጎቹን በቀኙ፣ ፍየሎቹን ግን በግራው ያደርጋቸዋል።
“ከዚያም ንጉሡ በቀኙ ያሉትን እንዲህ ይላቸዋል፦ ‘እናንተ አባቴ የባረካችሁ ኑ፤ ዓለም ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ የተዘጋጀላችሁን መንግሥት ውረሱ።
ምክንያቱም ተርቤ አብልታችሁኛል፤ ተጠምቼ አጠጥታችሁኛል። እንግዳ ሆኜ አስተናግዳችሁኛል፤
ታርዤ አልብሳችሁኛል። ታምሜ አስታማችሁኛል። ታስሬ ጠይቃችሁኛል።’
ከዚያም ጻድቃኑ መልሰው እንዲህ ይሉታል፦ ‘ጌታ ሆይ፣ ተርበህ አይተን መቼ አበላንህ? ተጠምተህ አይተንስ መቼ አጠጣንህ?
እንግዳ ሆነህ አይተን መቼ አስተናገድንህ? ወይስ ታርዘህ አይተን መቼ አለበስንህ?
ታመህ ወይም ታስረህ አይተን መቼ ጠየቅንህ?’
ንጉሡም መልሶ ‘እውነት እላችኋለሁ፣ ከሁሉ ከሚያንሱት ከእነዚህ ወንድሞቼ ለአንዱ ያደረጋችሁት ሁሉ ለእኔ እንዳደረጋችሁት ይቆጠራል’ ይላቸዋል።
“ከዚያም በግራው ያሉትን እንዲህ ይላቸዋል፦ ‘እናንተ የተረገማችሁ፣ ከእኔ ራቁ፤ ለዲያብሎስና ለመላእክቱ ወደተዘጋጀው ዘላለማዊ እሳት ሂዱ።
ምክንያቱም ተርቤ አላበላችሁኝም፤ ተጠምቼ አላጠጣችሁኝም።
እንግዳ ሆኜ አላስተናገዳችሁኝም፤ ታርዤ አላለበሳችሁኝም፤ ታምሜና ታስሬ አልጠየቃችሁኝም።’
እነሱም መልሰው ‘ጌታ ሆይ፣ ተርበህ ወይስ ተጠምተህ ወይስ እንግዳ ሆነህ ወይስ ታርዘህ ወይስ ታመህ ወይስ ታስረህ መቼ አይተን ሳናገለግልህ ቀረን?’ ይሉታል።
እሱም መልሶ ‘እውነት እላችኋለሁ፣ ከሁሉ ከሚያንሱት ከእነዚህ ለአንዱ ይህን ሳታደርጉ መቅረታችሁ ለእኔ እንዳላደረጋችሁት ይቆጠራል’ ይላቸዋል።
እነዚህ ወደ ዘላለም ጥፋት ጻድቃን ግን ወደ ዘላለም ሕይወት ይሄዳሉ።”
በዚያን ቀን ኢየሱስ ከቤት ወጥቶ በባሕሩ ዳር ተቀመጠ።
እጅግ ብዙ ሰዎችም ወደ እሱ መጥተው ተሰበሰቡ፤ በመሆኑም ጀልባ ላይ ወጥቶ ተቀመጠ፤ ሕዝቡም ሁሉ በባሕሩ ዳር ቆመው ነበር።
ከዚያም ብዙ ነገሮችን እንዲህ እያለ በምሳሌ ይነግራቸው ጀመር፦ “እነሆ፣ አንድ ዘሪ ሊዘራ ወጣ።
በሚዘራበት ጊዜ አንዳንዶቹ ዘሮች መንገድ ዳር ወደቁ፤ ወፎችም መጥተው ለቀሟቸው።
ሌሎቹ ደግሞ ብዙ አፈር በሌለው ድንጋያማ መሬት ላይ ወደቁ፤ አፈሩም ጥልቀት ስላልነበረው ወዲያውኑ በቀሉ።
ፀሐይ በወጣ ጊዜ ግን ተቃጠሉ፤ ሥር ስላልነበራቸውም ደረቁ።
ሌሎቹ በእሾህ መካከል ወደቁ፤ እሾሁም አድጎ አነቃቸው።