text
stringlengths
4
267
በቤቴ ውስጥ እህል እንዲኖር አሥራቱን ሁሉ ወደ ጎተራው አስገቡ” ይላል የሠራዊት ጌታ ይሖዋ፤ “የሰማያትን መስኮቶች ከፍቼ ማስቀመጫ እስክታጡ ድረስ የተትረፈረፈ በረከት ባላፈስላችሁ፣ እስቲ በዚህ ፈትኑኝ።”
“ለእናንተም ስል፣ በላተኛውን እገሥጻለሁ፤ የምድራችሁንም ፍሬ አያጠፋም፤ በእርሻችሁ ላይ ያለው የወይን ተክልም ፍሬ አልባ አይሆንም” ይላል የሠራዊት ጌታ ይሖዋ።
“እናንተ የደስታ ምድር ስለምትሆኑ ብሔራት ሁሉ ደስተኞች ብለው ይጠሯችኋል” ይላል የሠራዊት ጌታ ይሖዋ።
“በእኔ ላይ ኃይለ ቃል ተናግራችኋል” ይላል ይሖዋ። እናንተም “በአንተ ላይ የተናገርነው እንዴት ነው?” ትላላችሁ።
“እንዲህ ትላላችሁ፦ ‘አምላክን ማገልገል ዋጋ የለውም። ለእሱ ያለብንን ግዴታ በመጠበቃችንና በኃጢአታችን የተነሳ ማዘናችንን በሠራዊት ጌታ በይሖዋ ፊት በማሳየታችን ምን ተጠቀምን?
አሁን እብሪተኛ የሆኑ ሰዎችን ደስተኞች እንደሆኑ አድርገን እንመለከታቸዋለን። ደግሞም ክፉ አድራጊዎች ስኬታማ ሆነዋል። እነሱ በድፍረት አምላክን ይፈታተናሉ፤ ከቅጣትም ያመልጣሉ።’”
በዚያ ጊዜ ይሖዋን የሚፈሩ ሰዎች እርስ በርሳቸው፣ ከባልንጀሮቻቸው ጋር ተነጋገሩ፤ ይሖዋም በትኩረት አዳመጠ፤ ደግሞም ሰማ። ይሖዋንም ለሚፈሩና በስሙ ላይ ለሚያሰላስሉ በፊቱ የመታሰቢያ መጽሐፍ ተጻፈ።
“የእኔ ልዩ ንብረት በማደርጋቸውም ቀን እነሱ የእኔ ይሆናሉ” ይላል የሠራዊት ጌታ ይሖዋ። “አባት ለሚታዘዝለት ልጁ እንደሚራራ እኔም እራራላቸዋለሁ።
እናንተም በጻድቁና በክፉው እንዲሁም አምላክን በሚያገለግለውና በማያገለግለው ሰው መካከል ያለውን ልዩነት ዳግመኛ ታያላችሁ።”
“አሁንም ካህናት ሆይ፣ ይህ ትእዛዝ ለእናንተ ነው።
ለመስማት አሻፈረኝ ብትሉና ለስሜ ክብር ትሰጡ ዘንድ በልባችሁ ባታኖሩት” ይላል የሠራዊት ጌታ ይሖዋ፣ “በእናንተ ላይ እርግማን እሰዳለሁ፤ በረከታችሁንም ወደ እርግማን እለውጣለሁ። አዎ፣ በልባችሁ ስላላኖራችሁት እያንዳንዱን በረከት ወደ እርግማን ለውጫለሁ።”
“እነሆ፣ በእናንተ የተነሳ የዘራችሁትን ዘር አጠፋለሁ፤ ፈርሱንም ይኸውም በበዓሎቻችሁ ላይ የምትሠዉአቸውን እንስሳት ፈርስ ፊታችሁ ላይ እበትናለሁ፤ እናንተንም ወደዚያ ወስደው ይጥሏችኋል።
ይህን ትእዛዝ የሰጠኋችሁ ከሌዊ ጋር የገባሁት ቃል ኪዳን ጸንቶ እንዲኖር መሆኑን ታውቃላችሁ” ይላል የሠራዊት ጌታ ይሖዋ።
“ከእሱ ጋር የገባሁት ቃል ኪዳን የሕይወትና የሰላም ቃል ኪዳን ነው፤ እነዚህን በረከቶች በማግኘቱ እኔን ለመፍራት ተነሳሳ። አዎ፣ ለስሜ ታላቅ አክብሮት አሳየ።
የእውነት ሕግ በአፉ ውስጥ ነበር፤ በከንፈሮቹም ክፋት አልተገኘም። ከእኔ ጋር በሰላምና በቅንነት ሄደ፤ ብዙዎቹንም ከስህተት ጎዳና መለሰ።
ካህኑ ምንጊዜም በከንፈሮቹ ላይ እውቀት ሊኖረው ይገባል፤ ሰዎችም ሕጉን ከአፉ ሊሹ ይገባል፤ ምክንያቱም እሱ የሠራዊት ጌታ የይሖዋ መልእክተኛ ነው።
“እናንተ ግን ከመንገዱ ፈቀቅ ብላችኋል። ብዙዎች ከሕጉ ጋር በተያያዘ እንዲሰናከሉ አድርጋችኋል። የሌዊን ቃል ኪዳን አርክሳችኋል” ይላል የሠራዊት ጌታ ይሖዋ።
“ስለዚህ በሰዎች ሁሉ ፊት የተናቃችሁና የተዋረዳችሁ እንድትሆኑ አደርጋለሁ፤ ምክንያቱም መንገዶቼን አልጠበቃችሁም፤ ከዚህ ይልቅ ሕጉን ተግባራዊ ስታደርጉ አድልዎ ፈጽማችኋል።”
“የሁላችንም አባት አንድ አይደለም? የፈጠረንስ አምላክ አንድ አይደለም? ታዲያ የአባቶቻችንን ቃል ኪዳን በማርከስ አንዳችን በሌላው ላይ ክህደት የምንፈጽመው ለምንድን ነው?
ይሁዳ ክህደት ፈጽሟል፤ በእስራኤልና በኢየሩሳሌምም አስጸያፊ ነገር ተፈጽሟል፤ ይሁዳ፣ ይሖዋ የሚወደውን ቅድስናውን አርክሷልና፤ ደግሞም የባዕድ አምላክ ሴት ልጅን አግብቷል።
ይህን የሚያደርግ ማንኛውም ሰው ለሠራዊት ጌታ ለይሖዋ ስጦታ አድርጎ መባ ቢያቀርብም እንኳ ይሖዋ ከያዕቆብ ድንኳኖች ያስወግደዋል።”
“ሌላም የምታደርጉት ነገር አለ፤ ይህም የይሖዋ መሠዊያ በእንባ፣ በለቅሶና በሐዘን እንዲሞላ ምክንያት ሆኗል፤ በመሆኑም ስጦታ አድርጋችሁ የምታቀርቧቸውን መባዎች ከእንግዲህ አይቀበልም፤ የምታቀርቡትንም ነገር ሁሉ በሞገስ ዓይን አይመለከትም።
እናንተም ‘ይህ የሆነው ለምንድን ነው?’ ብላችኋል። ይህ የሆነው ይሖዋ በአንተ ላይ ስለመሠከረብህ ነው፤ ምክንያቱም እሷ አጋርህና የቃል ኪዳን ሚስትህ ሆና ሳለ በወጣትነት ሚስትህ ላይ ክህደት ፈጽመሃል።
ሆኖም እንዲህ ያላደረገ አለ፤ እሱ በተወሰነ መጠን የአምላክ መንፈስ ነበረው። ፍላጎቱስ ምን ነበር? የአምላክ ዘር ነበር። በመሆኑም መንፈሳችሁን ጠብቁ፤ በወጣትነት ሚስታችሁም ላይ ክህደት አትፈጽሙ።
እኔ ፍቺን እጠላለሁና” ይላል የእስራኤል አምላክ ይሖዋ፤ “ልብሱን በግፍ ድርጊት የሚሸፍነውንም እጠላለሁ” ይላል የሠራዊት ጌታ ይሖዋ። “መንፈሳችሁን ጠብቁ፤ ክህደትም አትፈጽሙ።
“ይሖዋን በቃላችሁ አታክታችሁታል። እናንተ ግን ‘ያታከትነው እንዴት ነው?’ ትላላችሁ። ‘ክፉ ድርጊት የሚፈጽም ሁሉ በይሖዋ ዓይን ጥሩ ነው፤ እሱ እንዲህ ባለ ሰው ደስ ይሰኛል’ ወይም ‘የፍትሕ አምላክ የት አለ?’ በማለታችሁ ነው።”
“እነሆ፣ ያ ቀን እንደ ምድጃ እየነደደ ይመጣል፤ በዚያ ጊዜ እብሪተኞች ሁሉና ክፉ አድራጊዎች በሙሉ እንደ ገለባ ይሆናሉ። የሚመጣው ቀን በእርግጥ ይበላቸዋል” ይላል የሠራዊት ጌታ ይሖዋ፤ “ሥርም ሆነ ቅርንጫፍ አይተውላቸውም።
ስሜን ለምታከብሩት ለእናንተ ግን የጽድቅ ፀሐይ በጨረሮቿ ፈውስ ይዛ ትወጣለች፤ እናንተም እንደሰቡ ጥጆች ትቦርቃላችሁ።”
“እኔም እርምጃ በምወስድበት ቀን ክፉዎችን ትረግጣላችሁ፤ ከእግራችሁ ሥር እንዳለ አቧራ ይሆናሉና” ይላል የሠራዊት ጌታ ይሖዋ።
“የአገልጋዬን የሙሴን ሕግ ይኸውም መላው እስራኤል እንዲያከብረው በኮሬብ ያዘዝኩትን ሥርዓትና ድንጋጌ አስታውሱ።
“እነሆ፣ ታላቁና የሚያስፈራው የይሖዋ ቀን ከመምጣቱ በፊት ነቢዩ ኤልያስን እልክላችኋለሁ።
እሱም መጥቼ ምድርን እንዳልመታና ፈጽሜ እንዳላጠፋ የአባቶችን ልብ እንደ ልጆች ልብ፣ የልጆችንም ልብ እንደ አባቶች ልብ ያደርጋል።”
ኢየሱስ ከስድስት ቀን በኋላ ጴጥሮስን፣ ያዕቆብንና ወንድሙን ዮሐንስን ብቻ ይዞ ወደ አንድ ረጅም ተራራ ወጣ።
በፊታቸውም ተለወጠ፤ ፊቱም እንደ ፀሐይ አበራ፤ ልብሱም እንደ ብርሃን አንጸባረቀ።
ከዚያም ሙሴና ኤልያስ ከእሱ ጋር ሲነጋገሩ ታዩአቸው።
በዚህ ጊዜ ጴጥሮስ ኢየሱስን “ጌታ ሆይ፣ እዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው። ከፈለግክ በዚህ ስፍራ አንድ ለአንተ፣ አንድ ለሙሴና አንድ ለኤልያስ ሦስት ድንኳኖች እተክላለሁ” አለው።
ገና እየተናገረ ሳለም ብሩህ ደመና ጋረዳቸው፤ ከደመናውም “በጣም የምደሰትበት፣ የምወደው ልጄ ይህ ነው። እሱን ስሙት” የሚል ድምፅ ተሰማ።
ደቀ መዛሙርቱ ይህን ሲሰሙ በፍርሃት ተውጠው በግንባራቸው ተደፉ።
በዚህ ጊዜ ኢየሱስ ወደ እነሱ ቀርቦ ዳሰሳቸውና “ተነሱ። አትፍሩ” አላቸው።
ቀና ብለው ሲመለከቱ ከኢየሱስ በቀር ሌላ ማንንም አላዩም።
ከተራራው እየወረዱ ሳሉ ኢየሱስ “የሰው ልጅ ከሞት እስኪነሳ ድረስ ራእዩን ለማንም እንዳትናገሩ” ሲል አዘዛቸው።
ይሁን እንጂ ደቀ መዛሙርቱ “ታዲያ ጸሐፍት ኤልያስ በመጀመሪያ መምጣት አለበት የሚሉት ለምንድን ነው?” ሲሉ ጠየቁት።
እሱም መልሶ እንዲህ አለ፦ “በእርግጥ ኤልያስ መጥቶ ሁሉንም ነገር ወደ ቀድሞ ሁኔታው ይመልሳል።
እኔ ግን እላችኋለሁ፣ ኤልያስ መምጣቱን መጥቷል፤ እነሱ ግን የፈለጉትን ነገር አደረጉበት እንጂ አላወቁትም። የሰው ልጅም እንደዚሁ በእነሱ እጅ ይሠቃያል።”
በዚህ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስ የነገራቸው ስለ መጥምቁ ዮሐንስ እንደሆነ ገባቸው።
ወደ ሕዝቡ በመጡ ጊዜ አንድ ሰው ወደ እሱ ቀረበና ተንበርክኮ እንዲህ አለው፦
“ጌታ ሆይ፣ ለልጄ ምሕረት አድርግለት፤ የሚጥል በሽታ ስላለበት በጠና ታሟል። አንዴ እሳት ውስጥ አንዴ ደግሞ ውኃ ውስጥ ይወድቃል።
ወደ ደቀ መዛሙርትህ አመጣሁት፤ እነሱ ግን ሊፈውሱት አልቻሉም።”
ኢየሱስም መልሶ “እምነት የለሽና ጠማማ ትውልድ ሆይ፣ ከእናንተ ጋር እስከ መቼ መቆየት ሊኖርብኝ ነው? እስከ መቼስ እናንተን መታገሥ ሊኖርብኝ ነው? ልጁን ወደ እኔ አምጡት” አለ።
ከዚያም ኢየሱስ ጋኔኑን ገሠጸው፤ ጋኔኑም ከልጁ ወጣ፤ ልጁም ከዚያች ሰዓት ጀምሮ ተፈወሰ።
ከዚህ በኋላ ደቀ መዛሙርቱ ብቻቸውን ወደ ኢየሱስ መጥተው “እኛ ልናስወጣው ያልቻልነው ለምንድን ነው?” አሉት።
እሱም “እምነታችሁ ስላነሰ ነው። እውነት እላችኋለሁ፣ የሰናፍጭ ቅንጣት የምታክል እምነት ካላችሁ ይህን ተራራ ‘ከዚህ ተነስተህ ወደዚያ ሂድ’ ብትሉት ይሄዳል፤ የሚሳናችሁም ነገር አይኖርም” አላቸው።
በገሊላ ተሰብስበው ሳሉ ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፦ “የሰውን ልጅ ለሰዎች አሳልፈው ይሰጡታል፤
እነሱም ይገድሉታል፤ እሱም በሦስተኛው ቀን ይነሳል።” ደቀ መዛሙርቱም በጣም አዘኑ።
ቅፍርናሆም ከደረሱ በኋላ የቤተ መቅደሱን ግብር የሚሰበስቡት ሰዎች ወደ ጴጥሮስ ቀርበው “መምህራችሁ የቤተ መቅደሱን ግብር አይከፍልም?” አሉት።
እሱም “ይከፍላል” አላቸው። ይሁን እንጂ ወደ ቤት በገባ ጊዜ ኢየሱስ በቅድሚያ እንዲህ አለው፦ “ስምዖን ምን ይመስልሃል? የምድር ነገሥታት ቀረጥ ወይም ግብር የሚቀበሉት ከማን ነው? ከልጆቻቸው ወይስ ከሌሎች?”
እሱም “ከሌሎች” ብሎ ሲመልስለት ኢየሱስ እንዲህ አለው፦ “እንግዲያው ልጆቹ ግብር ከመክፈል ነፃ ናቸው።
ሆኖም እንቅፋት እንዳንሆንባቸው ወደ ባሕሩ ሄደህ መንጠቆ ጣል፤ ከዚያም መጀመሪያ የምትይዘውን ዓሣ አፉን ስትከፍት አንድ የብር ሳንቲም ታገኛለህ። ሳንቲሙን ወስደህ ለእኔና ለአንተ ክፈል።”
ኢየሱስ ይህን ተናግሮ ከጨረሰ በኋላ ከገሊላ ወጥቶ ከዮርዳኖስ ማዶ ወዳሉት የይሁዳ ድንበሮች መጣ።
እጅግ ብዙ ሰዎችም ተከተሉት፤ እሱም በዚያ ፈወሳቸው።
ፈሪሳውያንም ወደ እሱ መጥተው ሊፈትኑት በማሰብ “አንድ ሰው በማንኛውም ምክንያት ሚስቱን እንዲፈታ ሕግ ይፈቅድለታል?” ሲሉ ጠየቁት።
እሱም መልሶ እንዲህ አለ፦ “ፈጣሪ ከመጀመሪያውም ወንድና ሴት አድርጎ እንደፈጠራቸው አላነበባችሁም?
‘ከዚህ የተነሳ ሰው ከአባቱና ከእናቱ ይለያል፤ ከሚስቱም ጋር ይጣበቃል፤ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ’ ብሎ እንደተናገረስ አላነበባችሁም?
በመሆኑም ከዚህ በኋላ አንድ ሥጋ ናቸው እንጂ ሁለት አይደሉም። ስለዚህ አምላክ ያጣመረውን ማንም ሰው አይለያየው።”
እነሱም “ታዲያ ሙሴ የፍቺ የምሥክር ወረቀት ሰጥቶ እንዲፈታት ያዘዘው ለምንድን ነው?” አሉት።
እሱም እንዲህ አላቸው፦ “ሙሴ የልባችሁን ደንዳናነት አይቶ ሚስቶቻችሁን እንድትፈቱ ፈቀደላችሁ እንጂ ከመጀመሪያው እንዲህ አልነበረም።
እኔ ግን እላችኋለሁ፣ በፆታ ብልግና ምክንያት ካልሆነ በስተቀር ሚስቱን ፈቶ ሌላ የሚያገባ ሁሉ ያመነዝራል።”
ደቀ መዛሙርቱም “በባልና በሚስት መካከል ያለው ሁኔታ እንዲህ ከሆነስ አለማግባት ይመረጣል” አሉት።
እሱም እንዲህ አላቸው፦ “ስጦታው ያላቸው ካልሆኑ በስተቀር ይህን ሁሉም ሰው ሊቀበለው አይችልም።
ምክንያቱም ጃንደረባ ሆነው የሚወለዱ አሉ፤ ሰው የሰለባቸው ጃንደረቦችም አሉ፤ እንዲሁም ለመንግሥተ ሰማያት ሲሉ ራሳቸውን ጃንደረባ ያደረጉ ጃንደረቦችም አሉ። ይህን ሊቀበለው የሚችል ይቀበለው።”
ከዚያም ኢየሱስ እጁን እንዲጭንባቸውና እንዲጸልይላቸው ትናንሽ ልጆችን ወደ እሱ አመጡ፤ ደቀ መዛሙርቱ ግን ገሠጿቸው።
ይሁን እንጂ ኢየሱስ “ልጆቹን ተዉአቸው፤ ወደ እኔ እንዳይመጡ አትከልክሏቸው፤ መንግሥተ ሰማያት እንደነዚህ ላሉት ነውና” አለ።
እጁንም ከጫነባቸው በኋላ ከዚያ ስፍራ ተነስቶ ሄደ።
ከዚያም አንድ ወጣት ወደ እሱ መጥቶ “መምህር፣ የዘላለም ሕይወት ለማግኘት ምን ጥሩ ነገር ማድረግ ይኖርብኛል?” አለው።
እሱም “ስለ ጥሩ ነገር ለምን ትጠይቀኛለህ? ጥሩ የሆነው አምላክ ብቻ ነው። ሆኖም ሕይወት ማግኘት የምትፈልግ ከሆነ ዘወትር ትእዛዛቱን ጠብቅ” አለው።
እሱም “የትኞቹን?” አለው። ኢየሱስም እንዲህ አለው፦ “አትግደል፣ አታመንዝር፣ አትስረቅ፣ በሐሰት አትመሥክር፣
አባትህንና እናትህን አክብር እንዲሁም ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ።”
ወጣቱም “እነዚህን ሁሉ ስጠብቅ ኖሬአለሁ፤ ታዲያ አሁን የሚጎድለኝ ነገር ምንድን ነው?” አለው።
ኢየሱስም “ፍጹም መሆን ከፈለግክ ሂድና ንብረትህን ሸጠህ ገንዘቡን ለድሆች ስጥ፤ በሰማይም ውድ ሀብት ታገኛለህ፤ ደግሞም መጥተህ ተከታዬ ሁን” አለው።
ወጣቱም ይህን ሲሰማ ብዙ ንብረት ስለነበረው እያዘነ ሄደ።
ከዚያም ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን እንዲህ አላቸው፦ “እውነት እላችኋለሁ፣ ሀብታም ሰው ወደ መንግሥተ ሰማያት መግባት እጅግ አስቸጋሪ ይሆንበታል።
ዳግመኛም እላችኋለሁ፣ ሀብታም ሰው ወደ አምላክ መንግሥት ከሚገባ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ቢሾልክ ይቀልላል።”
ደቀ መዛሙርቱ ይህን ሲሰሙ በጣም ተገርመው “በዚህ ዓይነትማ ማን ሊድን ይችላል?” አሉ።
ኢየሱስም ትኩር ብሎ እያያቸው “ይህ በሰዎች ዘንድ አይቻልም፤ በአምላክ ዘንድ ግን ሁሉ ነገር ይቻላል” አላቸው።
ከዚያም ጴጥሮስ መልሶ “እነሆ፣ እኛ ሁሉን ትተን ተከትለንሃል፤ ታዲያ የምናገኘው ምን ይሆን?” አለው።
ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ “እውነት እላችኋለሁ፣ ሁሉም ነገር አዲስ በሚሆንበት ጊዜ የሰው ልጅ፣ ክብራማ በሆነው ዙፋኑ ላይ ሲቀመጥ እኔን የተከተላችሁኝ እናንተ በ12 ዙፋኖች ላይ ተቀምጣችሁ በ12ቱ የእስራኤል ነገዶች ላይ ትፈርዳላችሁ።
እንዲሁም ስለ ስሜ ሲል ቤቶችን ወይም ወንድሞችን ወይም እህቶችን ወይም አባትን ወይም እናትን ወይም ልጆችን ወይም እርሻን የተወ ሁሉ መቶ እጥፍ ይቀበላል፤ የዘላለም ሕይወትም ይወርሳል።
“ሆኖም ፊተኞች የሆኑ ብዙዎች ኋለኞች፣ ኋለኞች የሆኑ ደግሞ ፊተኞች ይሆናሉ።
ኢየሱስ ለ12 ደቀ መዛሙርቱ መመሪያ ሰጥቶ ከጨረሰ በኋላ በሌሎች ከተሞች ለማስተማርና ለመስበክ ሄደ።
ዮሐንስ በእስር ቤት ሆኖ ክርስቶስ ስላከናወናቸው ሥራዎች ሲሰማ ደቀ መዛሙርቱን በመላክ
“ይመጣል የተባልከው አንተ ነህ ወይስ ሌላ እንጠብቅ?” ሲል ጠየቀው።
ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “ሄዳችሁ የምትሰሙትንና የምታዩትን ነገር ለዮሐንስ ንገሩት፤
ዓይነ ስውሮች እያዩ ነው፤ አንካሶች እየተራመዱ ነው፤ የሥጋ ደዌ የያዛቸው እየነጹ ነው፤ መስማት የተሳናቸው እየሰሙ ነው፤ ሙታን እየተነሱ ነው፤ ድሆችም ምሥራቹ እየተነገራቸው ነው።
በእኔ ምክንያት የማይሰናከል ደስተኛ ነው።”
መልእክተኞቹ ከሄዱ በኋላ ኢየሱስ ስለ ዮሐንስ እንዲህ ሲል ለሕዝቡ ይናገር ጀመር፦ “ወደ ምድረ በዳ የሄዳችሁት ምን ለማየት ነበር? ነፋስ የሚያወዛውዘውን ሸምበቆ?
ታዲያ ምን ለማየት ነበር የሄዳችሁት? ምርጥ ልብስ የለበሰ ሰው ለማየት? ምርጥ ልብስ የለበሱማ የሚገኙት በነገሥታት ቤት ነው።
ታዲያ ለምን ሄዳችሁ? ነቢይ ለማየት? አዎ፣ እላችኋለሁ፣ ከነቢይም የሚበልጥ ነው።
‘እነሆ፣ ከፊትህ እየሄደ መንገድህን እንዲያዘጋጅ መልእክተኛዬን ከአንተ አስቀድሜ እልካለሁ!’ ተብሎ የተጻፈው ስለ እሱ ነው።
እውነት እላችኋለሁ፣ ከሴት ከተወለዱት መካከል ከመጥምቁ ዮሐንስ የሚበልጥ አልተነሳም፤ ሆኖም በመንግሥተ ሰማያት ዝቅተኛ የሆነው እንኳ ይበልጠዋል።
መንግሥተ ሰማያት ከመጥምቁ ዮሐንስ ዘመን ጀምሮ እስካሁን ድረስ ሰዎች የሚጋደሉለት ግብ ሆኗል፤ በተጋድሏቸው የሚጸኑም ያገኙታል።