text
stringlengths
4
267
በዚህ ጊዜ ጸሐፍትና ፈሪሳውያን “አምላክን የሚዳፈረው ይሄ ማን ነው? ከአምላክ በቀር ኃጢአትን ማን ይቅር ሊል ይችላል?” ይባባሉ ጀመር።
ኢየሱስ ግን ሐሳባቸውን ተረድቶ እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “በልባችሁ የምታስቡት ምንድን ነው?
‘ኃጢአትህ ይቅር ተብሏል’ ከማለትና ‘ተነስተህ ሂድ’ ከማለት የቱ ይቀላል?
ይሁንና የሰው ልጅ በምድር ላይ ኃጢአትን ይቅር የማለት ሥልጣን እንዳለው ታውቁ ዘንድ . . .” አላቸውና ሽባውን “ተነስ፣ ቃሬዛህን ተሸከምና ወደ ቤትህ ሂድ” አለው።
በዚህ ጊዜ ሰውየው በፊታቸው ተነስቶ ተኝቶበት የነበረውን ቃሬዛ ተሸከመና አምላክን እያመሰገነ ወደ ቤቱ ሄደ።
ይህን ሲያዩ ሁሉም በአድናቆት ተውጠው አምላክን ማመስገን ጀመሩ፤ ታላቅ ፍርሃትም አድሮባቸው “ዛሬ የሚያስደንቅ ነገር አየን!” አሉ።
ይህ ከሆነም በኋላ ኢየሱስ ወጥቶ ሲሄድ ሌዊ የሚባል ቀረጥ ሰብሳቢ በቀረጥ መሰብሰቢያው ቦታ ተቀምጦ አየና “ተከታዬ ሁን” አለው።
እሱም ሁሉንም ነገር እርግፍ አድርጎ በመተው ተነስቶ ይከተለው ጀመር።
ከዚያም ሌዊ በቤቱ ለኢየሱስ ትልቅ ግብዣ አደረገ፤ በግብዣውም ላይ ብዙ ቀረጥ ሰብሳቢዎችና ሌሎች ሰዎች ከእነሱ ጋር ይበሉ ነበር።
ፈሪሳውያንና ከእነሱ ወገን የሆኑ ጸሐፍት ይህን ባዩ ጊዜ “ከቀረጥ ሰብሳቢዎችና ከኃጢአተኞች ጋር የምትበሉትና የምትጠጡት ለምንድን ነው?” በማለት በደቀ መዛሙርቱ ላይ ማጉረምረም ጀመሩ።
ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፦ “ሐኪም የሚያስፈልጋቸው ሕመምተኞች እንጂ ጤነኞች አይደሉም።
እኔ የመጣሁት ኃጢአተኞች ንስሐ እንዲገቡ ለመጥራት እንጂ ጻድቃንን ለመጥራት አይደለም።”
እነሱም “የዮሐንስ ደቀ መዛሙርት አዘውትረው ይጾማሉ፤ እንዲሁም ምልጃ ያቀርባሉ፤ የፈሪሳውያን ደቀ መዛሙርትም እንዲሁ ያደርጋሉ፤ የአንተ ደቀ መዛሙርት ግን ይበላሉ፣ ይጠጣሉ” አሉት።
ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ “ሙሽራው ከእነሱ ጋር እያለ የሙሽራው ጓደኞች እንዲጾሙ ልታደርጓቸው ትችላላችሁ?
ሆኖም ሙሽራው ከእነሱ የሚወሰድበት ጊዜ ይመጣል፤ በዚያን ጊዜ ይጾማሉ።”
በተጨማሪም እንዲህ ሲል አንድ ምሳሌ ነገራቸው፦ “ከአዲስ ልብስ ላይ ቁራጭ ጨርቅ ወስዶ በአሮጌ ልብስ ላይ የሚጥፍ ሰው የለም። እንዲህ ቢያደርግ ግን አዲሱ ቁራጭ ጨርቅ ተቦጭቆ ይነሳል፤ ከአዲሱ ልብስ የተቆረጠው ጨርቅ ከአሮጌው ልብስ ጋር አይስማማም።
ደግሞም ባረጀ አቁማዳ አዲስ የወይን ጠጅ የሚያስቀምጥ ሰው የለም። እንዲህ ቢያደርግ ግን አዲሱ የወይን ጠጅ አቁማዳውን ያፈነዳዋል፤ ወይኑ ይፈስሳል፤ አቁማዳውም ከጥቅም ውጭ ይሆናል።
ስለዚህ አዲስ የወይን ጠጅ በአዲስ አቁማዳ መቀመጥ አለበት።
አሮጌ የወይን ጠጅ ከጠጣ በኋላ አዲሱን የሚፈልግ የለም፤ ምክንያቱም ‘አሮጌው ግሩም ነው’ ይላል።”
በሌላ ወቅት ኢየሱስ በአንድ የሰንበት ቀን ከፈሪሳውያን መሪዎች ወደ አንዱ ቤት ምግብ ሊበላ በገባ ጊዜ በቤቱ ውስጥ ያሉት ሰዎች በትኩረት ይከታተሉት ነበር።
በዚያም ሰውነት የሚያሳብጥ በሽታ የያዘው አንድ ሰው ከፊት ለፊቱ ነበር።
ኢየሱስም ሕግ አዋቂዎችንና ፈሪሳውያንን “በሰንበት መፈወስ በሕግ ተፈቅዷል ወይስ አልተፈቀደም?” ሲል ጠየቃቸው።
እነሱ ግን ዝም አሉ። በዚህ ጊዜ በሰውየው ላይ እጁን ጭኖ ፈወሰውና አሰናበተው።
ከዚያም “ከእናንተ መካከል ልጁ ወይም በሬው በሰንበት ቀን የውኃ ጉድጓድ ውስጥ ቢወድቅ ወዲያውኑ ጎትቶ የማያወጣው ማን ነው?” አላቸው።
እነሱም ለዚህ መልስ ሊሰጡ አልቻሉም።
ኢየሱስ የተጋበዙት ሰዎች ለራሳቸው የክብር ቦታ ሲመርጡ ተመልክቶ እንዲህ ሲል አንድ ምሳሌ ነገራቸው፦
“አንድ ሰው ወደ ሠርግ ሲጠራህ በክብር ቦታ አትቀመጥ። ምናልባት ከአንተ የበለጠ የተከበረ ሰው ተጠርቶ ሊሆን ይችላል።
በመሆኑም ሁለታችሁንም የጋበዘው ሰው መጥቶ ‘ቦታውን ለዚህ ሰው ልቀቅለት’ ይልሃል። በዚህ ጊዜ እያፈርክ ወደ ዝቅተኛው ቦታ ትሄዳለህ።
አንተ ግን ስትጋበዝ ሄደህ በዝቅተኛው ስፍራ ተቀመጥ፤ የጋበዘህም ሰው ሲመጣ ‘ወዳጄ ሆይ፣ ወደ ላይ ከፍ በል’ ይልሃል። በዚህ ጊዜ አብረውህ በተጋበዙት ሰዎች ሁሉ ፊት ክብር ታገኛለህ።
ራሱን ከፍ ከፍ የሚያደርግ ሁሉ ዝቅ ይደረጋልና፤ ራሱን ዝቅ የሚያደርግ ሁሉ ደግሞ ከፍ ይደረጋል።”
ቀጥሎ ደግሞ የጋበዘውን ሰው እንዲህ አለው፦ “የምሳ ወይም የራት ግብዣ በምታደርግበት ጊዜ ጓደኞችህን ወይም ወንድሞችህን ወይም ዘመዶችህን ወይም ሀብታም ጎረቤቶችህን አትጥራ። አለዚያ እነሱም ሊጋብዙህና ብድር ሊመልሱልህ ይችላሉ።
ሆኖም ግብዣ በምታደርግበት ጊዜ ድሆችን፣ ሽባዎችን፣ አንካሶችንና ዓይነ ስውራንን ጥራ፤
ብድር ሊመልሱልህ ስለማይችሉ ደስተኛ ትሆናለህ። ምክንያቱም በጻድቃን ትንሣኤ ብድራት ይመለስልሃል።”
ከተጋበዙት መካከል አንዱ ይህን ሲሰማ “በአምላክ መንግሥት፣ ከማዕድ የሚበላ ደስተኛ ነው” አለው።
ኢየሱስም እንዲህ አለው፦ “አንድ ሰው ትልቅ የራት ግብዣ አዘጋጅቶ ብዙ ሰዎች ጠራ።
የራት ግብዣው ሰዓት በደረሰ ጊዜ የተጋበዙትን ሰዎች ‘አሁን ሁሉም ነገር ስለተዘጋጀ ኑ’ ብሎ እንዲጠራቸው ባሪያውን ላከ።
ይሁን እንጂ ሁሉም ሰበብ ያቀርቡ ጀመር። የመጀመሪያው ‘እርሻ ስለገዛሁ ሄጄ ማየት አለብኝ፤ ስለዚህ እባክህ ይቅርታ አድርግልኝ’ አለው።
ሌላውም ‘አምስት ጥማድ በሬዎች ገዝቻለሁ፤ ልፈትናቸው ስለሆነ እባክህ ይቅርታ አድርግልኝ’ አለ።
ሌላኛው ደግሞ ‘ገና ማግባቴ ስለሆነ መምጣት አልችልም’ አለ።
ባሪያውም መጥቶ ለጌታው ይህን ነገረው። በዚህ ጊዜ የቤቱ ጌታ ተቆጣ፤ ከዚያም ባሪያውን ‘ፈጥነህ ወደ ከተማው አውራ ጎዳናዎችና ስላች መንገዶች ሄደህ ድሆችን፣ ሽባዎችን፣ ዓይነ ስውራንንና አንካሶችን ወደዚህ አምጣቸው’ አለው።
በኋላም ባሪያው ‘ጌታዬ፣ ያዘዝከው ተፈጽሟል፤ ያም ሆኖ አሁንም ቦታ አለ’ አለው።
በመሆኑም ጌታው ባሪያውን እንዲህ አለው፦ ‘ቤቴ እንዲሞላ ወደ ጎዳናዎችና ወደ ስላች መንገዶች ሄደህ ያገኘሃቸውን ሰዎች በግድ አምጥተህ አስገባ።
እላችኋለሁ፣ ከእነዚያ ከተጋበዙት ሰዎች መካከል አንዳቸውም ያዘጋጀሁትን ራት አይቀምሱም።’”
ከዚያም እጅግ ብዙ ሕዝብ አብሮት እየተጓዘ ሳለ ወደ እነሱ ዞሮ እንዲህ አላቸው፦
“ወደ እኔ የሚመጣ ሁሉ አባቱን፣ እናቱን፣ ሚስቱን፣ ልጆቹን፣ ወንድሞቹንና እህቶቹን ሌላው ቀርቶ የገዛ ራሱን ሕይወት እንኳ የማይጠላ ከሆነ ደቀ መዝሙሬ ሊሆን አይችልም።
የራሱን የመከራ እንጨት ተሸክሞ የማይከተለኝ ሁሉ ደቀ መዝሙሬ ሊሆን አይችልም።
ለምሳሌ ከእናንተ መካከል፣ ግንብ ለመገንባት ፈልጎ ለመጨረስ የሚያስችል በቂ ገንዘብ እንዳለው ለማወቅ በመጀመሪያ ተቀምጦ ወጪውን የማያሰላ ማን ነው?
እንዲህ ካላደረገ ግን መሠረቱን ከጣለ በኋላ ፍጻሜ ላይ ማድረስ ሊያቅተውና የሚያዩት ሰዎች ሁሉ ሊያፌዙበት ይችላሉ፤
‘ይህ ሰው መገንባት ጀምሮ ነበር፤ መጨረስ ግን አቃተው’ ይሉታል።
ወይም ደግሞ አንድ ንጉሥ ሌላን ንጉሥ ጦርነት ለመግጠም በሚነሳበት ጊዜ 20,000 ሠራዊት አስከትቶ የመጣበትን ንጉሥ በ10,000 ሠራዊት ሊቋቋመው ይችል እንደሆነ ለማወቅ በቅድሚያ ተቀምጦ አይማከርም?
መቋቋም የማይችል ከሆነ ሊገጥመው የሚመጣው ንጉሥ ገና ሩቅ ሳለ አምባሳደሮች ልኮ እርቅ ለመፍጠር ይደራደራል።
እንደዚሁም ከእናንተ መካከል ያለውን ንብረት ሁሉ የማይሰናበት ፈጽሞ ደቀ መዝሙሬ ሊሆን አይችልም።
“ጨው ጥሩ ነገር እንደሆነ የታወቀ ነው። ሆኖም ጨው ራሱ የጨውነት ጣዕሙን ቢያጣ ጨውነቱን በምን መመለስ ይቻላል?
እንዲህ ያለ ጨው ለአፈር የሚሰጠው ጥቅም የለም፤ ማዳበሪያም ሊሆን አይችልም። በመሆኑም ሰዎች ወደ ውጭ ይጥሉታል። ስለዚህ የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ።”
ፋሲካ የሚባለው የቂጣ በዓል የሚከበርበት ጊዜ ተቃርቦ ነበር።
የካህናት አለቆችና ጸሐፍትም ሕዝቡን ይፈሩ ስለነበር እሱን የሚገድሉበትን ከሁሉ የተሻለ መንገድ እየፈለጉ ነበር።
ከዚያም ከአሥራ ሁለቱ አንዱ ሆኖ በተቆጠረውና አስቆሮቱ ተብሎ በሚጠራው በይሁዳ ሰይጣን ገባበት፤
ይሁዳም ወደ ካህናት አለቆችና ወደ ቤተ መቅደሱ ሹሞች ሄዶ ኢየሱስን ለእነሱ አሳልፎ መስጠት ስለሚችልበት መንገድ ተነጋገረ።
እነሱም በጉዳዩ ተደስተው የብር ገንዘብ ሊሰጡት ተስማሙ።
እሱም በዚህ ተስማምቶ ሕዝብ በሌለበት እሱን አሳልፎ መስጠት የሚችልበትን ምቹ አጋጣሚ ይፈልግ ጀመር።
የቂጣ በዓል የሚከበርበት ቀን ደረሰ፤ በዚህ ዕለት የፋሲካ መሥዋዕት ይቀርብ ነበር፤
ስለዚህ ኢየሱስ “ሄዳችሁ ፋሲካን እንድንበላ አዘጋጁልን” ብሎ ጴጥሮስንና ዮሐንስን ላካቸው።
እነሱም “የት እንድናዘጋጅ ትፈልጋለህ?” አሉት።
እሱም እንዲህ አላቸው፦ “ወደ ከተማው ስትገቡ የውኃ እንስራ የተሸከመ ሰው ታገኛላችሁ። እሱን ተከትላችሁ ወደሚገባበት ቤት ሂዱ።
የቤቱንም ባለቤት ‘መምህሩ “ከደቀ መዛሙርቴ ጋር ፋሲካን የምበላበት የእንግዳ ማረፊያ የት ነው?” ብሎሃል’ በሉት።
ሰውየውም የተሰናዳ ሰፊ ሰገነት ያሳያችኋል፤ በዚያ አዘጋጁ።”
እነሱም ሄዱ፤ እንዳላቸውም ሆኖ አገኙት፤ ለፋሲካ በዓሉም ዝግጅት አደረጉ።
ሰዓቱ በደረሰ ጊዜም ከሐዋርያቱ ጋር በማዕድ ተቀመጠ።
እንዲህም አላቸው፦ “መከራ ከመቀበሌ በፊት ይህን ፋሲካ አብሬያችሁ ለመብላት በጣም ስመኝ ነበር፤
እላችኋለሁና፣ የዚህ ፋሲካ ትርጉም በአምላክ መንግሥት ፍጻሜውን እስኪያገኝ ድረስ ፋሲካን ዳግመኛ አልበላም።”
ከዚያም ጽዋ ተቀብሎ አምላክን ካመሰገነ በኋላ እንዲህ አለ፦ “እንኩ፣ ይህን ጽዋ እየተቀባበላችሁ ጠጡ፤
እላችኋለሁና፣ ከአሁን ጀምሮ የአምላክ መንግሥት እስኪመጣ ድረስ ከዚህ ወይን ዳግመኛ አልጠጣም።”
በተጨማሪም ቂጣ አንስቶ አመሰገነ፣ ከቆረሰውም በኋላ ሰጣቸውና “ይህ ስለ እናንተ የሚሰጠውን ሥጋዬን ያመለክታል። ይህን ሁልጊዜ ለመታሰቢያዬ አድርጉት” አላቸው።
በተጨማሪም ራት ከበሉ በኋላ ጽዋውን አንስቶ ልክ እንደዚሁ አደረገ፤ እንዲህም አለ፦ “ይህ ጽዋ ስለ እናንተ በሚፈሰው ደሜ አማካኝነት የሚመሠረተውን አዲሱን ቃል ኪዳን ያመለክታል።
“ነገር ግን አሳልፎ የሚሰጠኝ ሰው እጅ ከእኔ ጋር በማዕድ ነው።
እርግጥ የሰው ልጅ አስቀድሞ በተወሰነው መሠረት ይሄዳል፤ አሳልፎ ለሚሰጠው ለዚያ ሰው ግን ወዮለት!”
ስለዚህ ከመካከላቸው በእርግጥ ይህን የሚያደርገው ማን ሊሆን እንደሚችል እርስ በርሳቸው ይነጋገሩ ጀመር።
ደግሞም ‘ከመካከላችን ታላቅ የሆነው ማን ነው?’ በሚል በመካከላቸው የጦፈ ክርክር ተነሳ።
እሱ ግን እንዲህ አላቸው፦ “የአሕዛብ ነገሥታት በእነሱ ላይ ሥልጣናቸውን ያሳያሉ፤ እንዲሁም በሕዝባቸው ላይ ሥልጣን ያላቸው ሰዎች በጎ አድራጊዎች ተብለው ይጠራሉ።
እናንተ ግን እንዲህ አትሁኑ። ከዚህ ይልቅ ከእናንተ መካከል ታላቅ የሆነ እንደ ታናሽ ይሁን፤ አመራር የሚሰጥም እንደ አገልጋይ ይሁን።
ለመሆኑ በማዕድ ከተቀመጠና ቆሞ ከሚያገለግል ማን ይበልጣል? በማዕድ የተቀመጠው አይደለም? እኔ ግን በመካከላችሁ ያለሁት እንደ አገልጋይ ሆኜ ነው።
“ይሁን እንጂ እናንተ በፈተናዎቼ ከጎኔ ሳትለዩ ቆይታችኋል፤
አባቴ ከእኔ ጋር ቃል ኪዳን እንዳደረገ ሁሉ እኔም ከእናንተ ጋር ለመንግሥት ቃል ኪዳን አደርጋለሁ፤
ይኸውም በመንግሥቴ ከማዕዴ እንድትበሉና እንድትጠጡ እንዲሁም በዙፋን ተቀምጣችሁ በ12ቱ የእስራኤል ነገዶች ላይ እንድትፈርዱ ነው።
“ስምዖን፣ ስምዖን፣ ሰይጣን ሁላችሁንም እንደ ስንዴ ያበጥራችሁ ዘንድ ጥያቄ አቅርቧል።
እኔ ግን እምነትህ እንዳይጠፋ ስለ አንተ ምልጃ አቀረብኩ፤ አንተም በተመለስክ ጊዜ ወንድሞችህን አበርታ።”
በዚህ ጊዜ ጴጥሮስ “ጌታ ሆይ፣ እኔ ከአንተ ጋር ወደ ወህኒ ለመውረድም ሆነ ለመሞት ዝግጁ ነኝ” አለው።
እሱ ግን “ጴጥሮስ ሆይ፣ እውነት እልሃለሁ፣ ዛሬ ዶሮ ከመጮኹ በፊት፣ አላውቀውም ብለህ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ” አለው።
በተጨማሪም እንዲህ አላቸው፦ “ያለገንዘብ ኮሮጆ፣ ያለምግብ ከረጢትና ያለትርፍ ጫማ በላክኋችሁ ጊዜ የጎደለባችሁ ነገር ነበር?” እነሱም “ምንም አልጎደለብንም” አሉ።
በዚህ ጊዜ እንዲህ አላቸው፦ “አሁን ግን የገንዘብ ኮሮጆ ያለው ኮሮጆውን ይያዝ፤ የምግብ ከረጢት ያለውም እንዲሁ፤ ሰይፍ የሌለው ደግሞ መደረቢያውን ሸጦ ሰይፍ ይግዛ።
ይህን የምላችሁ ‘ከዓመፀኞች ጋር ተቆጠረ’ ተብሎ የተጻፈው በእኔ ላይ መፈጸም ስላለበት ነው። ስለ እኔ የተነገረው ነገር ፍጻሜውን እያገኘ ነውና።”
እነሱም “ጌታ ሆይ፣ ይኸው ሁለት ሰይፎች አሉ” አሉት። እሱም “በቂ ነው” አላቸው።
ከዚያ ወጥቶም እንደ ልማዱ ወደ ደብረ ዘይት ተራራ ሄደ፤ ደቀ መዛሙርቱም ተከተሉት።
እዚያም በደረሱ ጊዜ “ወደ ፈተና እንዳትገቡ ተግታችሁ ጸልዩ” አላቸው።
እሱም የድንጋይ ውርወራ ያህል ከእነሱ በመራቅ ተንበርክኮ መጸለይ ጀመረ፤
እንዲህም አለ፦ “አባት ሆይ፣ ፈቃድህ ከሆነ ይህን ጽዋ ከእኔ አርቅ። ይሁንና የእኔ ሳይሆን የአንተ ፈቃድ ይፈጸም።”
ከዚያም አንድ መልአክ ከሰማይ ተገልጦለት አበረታታው።
ሆኖም በከፍተኛ ጭንቀት ተውጦ ከበፊቱ ይበልጥ አጥብቆ መጸለዩን ቀጠለ፤ ላቡም መሬት ላይ እንደሚንጠባጠብ ደም ሆኖ ነበር።
ከጸለየም በኋላ ወደ ደቀ መዛሙርቱ ሲሄድ ከሐዘን የተነሳ ደክሟቸው ስለነበር ሲያንቀላፉ አገኛቸው።
እሱም “ለምን ትተኛላችሁ? ተነሱ፤ ደግሞም ወደ ፈተና እንዳትገቡ ተግታችሁ ጸልዩ” አላቸው።