text
stringlengths
4
267
ስለዚህ አምላክ ደግም ጥብቅም እንደሆነ ተመልከት። በወደቁት ላይ ጥብቅ ይሆናል፤ አንተ ግን የአምላክ ደግነት የሚገባህ ሆነህ እስከተገኘህ ድረስ ደግነቱን ያሳይሃል፤ አለዚያ ግን አንተም ተቆርጠህ ትጣላለህ።
እነሱም እምነት የለሽ ሆነው ካልቀጠሉ ይጣበቃሉ፤ አምላክ መልሶ ሊያጣብቃቸው ይችላልና።
አንተ በተፈጥሮ የዱር ከሆነው የወይራ ዛፍ ተቆርጠህ፣ ከተፈጥሮ ውጭ በሆነ መንገድ በጓሮ የወይራ ዛፍ ላይ መጣበቅ ከቻልክ እነዚህ ተፈጥሯዊ የሆኑት ቅርንጫፎችማ በራሳቸው የወይራ ዛፍ ላይ ተመልሰው መጣበቅ እንደሚችሉ የታወቀ ነው!
ወንድሞች፣ በራሳችሁ ዓይን ጥበበኞች የሆናችሁ እንዳይመስላችሁ ይህን ቅዱስ ሚስጥር እንድታውቁ እፈልጋለሁ፦ የአሕዛብ ቁጥር እስኪሞላ ድረስ የእስራኤል ሕዝብ በከፊል ስሜቱ ደንዝዟል፤
በዚህም መንገድ እስራኤል ሁሉ ይድናል። ይህም እንዲህ ተብሎ እንደተጻፈው ነው፦ “አዳኝ ከጽዮን ይወጣል፤ የያዕቆብም ዘሮች የክፋት ድርጊታቸውን እንዲተዉ ያደርጋል።
ኃጢአታቸውንም በማስወግድበት ጊዜ ከእነሱ ጋር የምገባው ቃል ኪዳን ይህ ነው።”
እርግጥ ከምሥራቹ ጋር በተያያዘ ለእናንተ ጥቅም ሲባል የአምላክ ጠላቶች ናቸው፤ በአምላክ ምርጫ መሠረት ግን ለአባቶቻቸው በተገባው የተስፋ ቃል የተነሳ በአምላክ ዘንድ የተወደዱ ናቸው።
አምላክ በስጦታውና በጠራቸው ሰዎች አይጸጸትምና።
በአንድ ወቅት እናንተ አምላክን የማትታዘዙ ነበራችሁ፤ አሁን ግን በእነሱ አለመታዘዝ ምክንያት ምሕረት አግኝታችኋል።
ስለዚህ አይሁዳውያን ሳይታዘዙ በመቅረታቸው አምላክ ለእናንተ ምሕረት አሳይቷችኋል፤ ከዚህም የተነሳ ለእነሱም ምሕረት ሊያሳያቸው ይችላል።
አምላክ ለሁሉም ምሕረት ያሳይ ዘንድ ሁሉም ያለመታዘዝ እስረኞች እንዲሆኑ ፈቅዷልና።
የአምላክ ብልጽግና፣ ጥበብና እውቀት እንዴት ጥልቅ ነው! ፍርዱም ፈጽሞ የማይመረመር ነው! መንገዱም የማይደረስበት ነው!
እንዲህ ተብሎ ተጽፏልና፦ “የይሖዋን ሐሳብ ማወቅ የቻለ ማን ነው? አማካሪውስ የሆነ ማን ነው?”
ወይስ “መልሶ ይከፍለው ዘንድ ለእሱ ያበደረ ማን ነው?”
ምክንያቱም ሁሉም ነገር የተገኘው ከእሱ፣ በእሱና ለእሱ ነው። ለእሱ ለዘላለም ክብር ይሁን። አሜን።
የክርስቶስ ኢየሱስ ባሪያ ከሆነው፣ ሐዋርያ እንዲሆን ከተጠራውና የአምላክን ምሥራች እንዲያውጅ ከተሾመው ከጳውሎስ፤
ይህ ምሥራች አምላክ በነቢያቱ አማካኝነት በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ አስቀድሞ የሰጠው የተስፋ ቃል ሲሆን
በሥጋ ከዳዊት ዘር ስለተወለደው ልጁ የሚገልጽ ነው፤
ይሁንና እሱ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል የአምላክ ልጅ መሆኑ እንዲታወቅ ተደርጓል። ይህም የሆነው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሞት በተነሳ ጊዜ ነው።
ለስሙ ክብር በብሔራት ሁሉ መካከል በእምነት የሚታዘዙ ሰዎች እንዲገኙ ሲባል በእሱ አማካኝነት ጸጋና ሐዋርያነት ተቀብለናል፤
የኢየሱስ ክርስቶስ እንዲሆኑ ከአሕዛብ ከተጠሩት መካከል እናንተም ትገኙበታላችሁ።
ቅዱሳን እንድትሆኑ ለተጠራችሁና በአምላክ ለተወደዳችሁ በሮም ለምትኖሩ ሁሉ፦ አባታችን ከሆነው አምላክና ከጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን።
ከሁሉ አስቀድሜ፣ ስለ እምነታችሁ በመላው ዓለም ስለሚወራ ስለ ሁላችሁም በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ለአምላኬ ምስጋና አቀርባለሁ።
ያለማቋረጥ ዘወትር በጸሎቴ እናንተን ሳልጠቅስ እንደማላልፍ፣ ስለ ልጁ የሚገልጸውን ምሥራች በማወጅ በሙሉ ልቤ ቅዱስ አገልግሎት የማቀርብለት አምላክ ምሥክሬ ነው፤
ደግሞም በአምላክ ፈቃድ አሁን በመጨረሻ እንደ ምንም ተሳክቶልኝ ወደ እናንተ መምጣት እንድችል ልመና እያቀረብኩ ነው።
ለመጽናት የሚያስችላችሁን መንፈሳዊ ስጦታ እንዳካፍላችሁ ላያችሁ እጓጓለሁና፤
ይህን ስል እኔ በእናንተ እምነት እናንተም በእኔ እምነት እርስ በርሳችን እንድንበረታታ ነው።
ይሁንና ወንድሞች፣ በሌሎች አሕዛብ መካከል ፍሬ እንዳፈራሁ ሁሉ በእናንተም መካከል ፍሬ አፈራ ዘንድ ወደ እናንተ ለመምጣት ብዙ ጊዜ አቅጄ እንደነበር እንድታውቁ እፈልጋለሁ። ሆኖም ለመምጣት ባሰብኩ ቁጥር የሆነ እንቅፋት ያጋጥመኛል።
ለግሪካውያንም ሆነ ግሪካውያን ላልሆኑ እንዲሁም ለጠቢባንም ሆነ ላልተማሩ ዕዳ አለብኝ፤
በመሆኑም በሮም ላላችሁት ለእናንተም ምሥራቹን ለማወጅ እጓጓለሁ።
እኔ በምሥራቹ አላፍርምና፤ እንዲያውም ለሚያምን ሁሉ ይኸውም በመጀመሪያ ለአይሁዳዊ ከዚያም ለግሪካዊ ምሥራቹ መዳን የሚያስገኝ የአምላክ ኃይል ነው።
ምክንያቱም “ጻድቅ ግን በእምነት ይኖራል” ተብሎ እንደተጻፈ ሁሉ እምነት ያላቸው ሰዎች፣ አምላክ በምሥራቹ አማካኝነት ጽድቁን እንደሚገልጥ ይረዳሉ፤ ይህ ደግሞ እምነታቸውን ያጠነክርላቸዋል።
እውነትን ለማፈን የተንኮል ዘዴ የሚጠቀሙ ሰዎች በሚፈጽሙት አምላክን የሚጻረር ድርጊትና ክፋት ሁሉ ላይ የአምላክ ቁጣ ከሰማይ እየተገለጠ ነው፤
ምክንያቱም ስለ አምላክ ሊታወቅ የሚችለው ነገር በእነሱ ዘንድ በግልጽ የታወቀ ነው፤ ይህም የሆነው አምላክ ይህን ግልጽ ስላደረገላቸው ነው።
የማይታዩት ባሕርያቱ ይኸውም ዘላለማዊ ኃይሉና አምላክነቱ ዓለም ከተፈጠረበት ጊዜ አንስቶ በግልጽ ይታያሉ፤ ምክንያቱም ባሕርያቱን ከተሠሩት ነገሮች ማስተዋል ይቻላል፤ ስለሆነም የሚያመካኙበት ነገር የላቸውም።
አምላክን የሚያውቁ ቢሆኑም እንኳ እንደ አምላክነቱ አላከበሩትም ብሎም አላመሰገኑትም፤ ከዚህ ይልቅ አስተሳሰባቸው ከንቱ ሆነ፤ የማያስተውለው ልባቸውም ጨለመ።
ጥበበኞች ነን ቢሉም ሞኞች ሆኑ፤
ሊጠፋ የማይችለውን አምላክ ክብር ጠፊ በሆነው ሰው፣ በወፎች፣ አራት እግር ባላቸው እንስሳትና በምድር ላይ በሚሳቡ ፍጥረታት ምስል ለወጡት።
ስለሆነም አምላክ እንደ ልባቸው ምኞት የገዛ ራሳቸውን አካል እንዲያስነውሩ ለርኩሰት አሳልፎ ሰጣቸው።
እነዚህ ሰዎች የአምላክን እውነት በሐሰት ለውጠዋል፤ በፈጣሪ ፋንታ ለፍጥረት ክብር ሰጥተዋል፤ ደግሞም ቅዱስ አገልግሎት አቅርበዋል፤ ይሁንና ለዘላለም ሊወደስ የሚገባው ፈጣሪ ብቻ ነው። አሜን።
አምላክ ልቅ ለሆነ የፆታ ምኞት አሳልፎ የሰጣቸው በዚህ ምክንያት ነው፤ ሴቶቻቸውም ተፈጥሯዊ የሆነውን ግንኙነት ከተፈጥሮ ውጭ በሆነ ግንኙነት ለወጡ፤
ወንዶቹም ተፈጥሯዊ በሆነ መንገድ ከሴቶች ጋር መገናኘት ትተው እርስ በርሳቸው ኃይለኛ በሆነ የፆታ ስሜት ተቃጠሉ፤ ወንዶች ከወንዶች ጋር አስነዋሪ ነገር ፈጸሙ፤ እነሱ ራሳቸውም ለጥፋታቸው የሚገባውን ቅጣት እየተቀበሉ ነው።
ለአምላክ እውቅና መስጠት ተገቢ መስሎ ስላልታያቸው መደረግ የማይገባውን ነገር እንዲያደርጉ አምላክ በእሱ ዘንድ ተቀባይነት ለሌለው አስተሳሰብ አሳልፎ ሰጣቸው።
ደግሞም እነዚህ ሰዎች በዓመፅ፣ በኃጢአተኝነት፣ በስግብግብነት፣ በክፋት፣ በቅናት፣ በነፍሰ ገዳይነት፣ በጥል፣ በማታለልና በተንኮል የተሞሉ ናቸው፤ እንዲሁም ስም አጥፊዎች፣
ሐሜተኞች፣ አምላክን የሚጠሉ፣ ተሳዳቢዎች፣ ትዕቢተኞች፣ ጉረኞች፣ ክፋት ጠንሳሾች፣ ለወላጆች የማይታዘዙ፣
የማያስተውሉ፣ ቃላቸውን የማይጠብቁ፣ ለሰው ፍቅር የሌላቸውና ምሕረት የለሾች ናቸው።
እነዚህ ሰዎች ‘እንዲህ ያሉ ነገሮችን የሚያደርጉ ሁሉ ሞት ይገባቸዋል’ የሚለውን የአምላክን የጽድቅ ሕግ በሚገባ የሚያውቁ ቢሆኑም በዚህ ድርጊታቸው መግፋት ብቻ ሳይሆን ይህን የሚያደርጉትንም ይደግፋሉ።
ወንድሞች፣ (እየተናገርኩ ያለሁት ሕግ ለሚያውቁ ሰዎች ነው፤) ሕጉ በአንድ ሰው ላይ ሥልጣን የሚኖረው በሕይወት እስከኖረ ድረስ ብቻ እንደሆነ አታውቁም?
ለምሳሌ ያህል፣ ያገባች ሴት ባሏ በሕይወት እስካለ ድረስ በሕግ ለእሱ የታሰረች ናት፤ ባሏ ከሞተ ግን ከባሏ ሕግ ነፃ ትወጣለች።
በመሆኑም ባሏ በሕይወት እያለ የሌላ ወንድ ብትሆን አመንዝራ ትባላለች። ባሏ ከሞተ ግን ከእሱ ሕግ ነፃ ስለምትሆን የሌላ ወንድ ብትሆን አመንዝራ አትባልም።
ስለዚህ ወንድሞቼ፣ እናንተም የሌላ ይኸውም ከሞት የተነሳው የክርስቶስ እንድትሆኑ በእሱ አካል አማካኝነት ለሕጉ ሞታችኋል፤ ይህም የሆነው ለአምላክ ፍሬ እንድናፈራ ነው።
ምክንያቱም እንደ ሥጋ ፍላጎት እንኖር በነበረበት ጊዜ ሕጉ ይፋ ያወጣቸው የኃጢአት ምኞቶች ለሞት ፍሬ እንድናፈራ በሰውነታችን ውስጥ ይሠሩ ነበር።
አሁን ግን አሮጌ በሆነው በተጻፈው ሕግ ሳይሆን በአዲስ መልክ በመንፈስ ባሪያዎች እንሆን ዘንድ አስሮ ይዞን ለነበረው ሕግ ስለሞትን ከሕጉ ነፃ ወጥተናል።
እንግዲህ ምን እንበል? ሕጉ ጉድለት አለበት ማለት ነው? በፍጹም! እንደ እውነቱ ከሆነ ሕጉ ባይኖር ኖሮ ኃጢአት ምን እንደሆነ ባላወቅኩ ነበር። ለምሳሌ ሕጉ “አትጎምጅ” ባይል ኖሮ መጎምጀት ምን እንደሆነ ባላወቅኩ ነበር።
ሆኖም ኃጢአት፣ ይህ ትእዛዝ ባስገኘው አጋጣሚ ተጠቅሞ ማንኛውንም ዓይነት ነገር የመጎምጀት ፍላጎት በውስጤ እንዲያድር አደረገ፤ ሕግ ባልነበረበት ጊዜ ኃጢአት የሞተ ነበርና።
በእርግጥ ሕግ ባልነበረበት ጊዜ ሕያው ነበርኩ። ትእዛዙ ሲመጣ ግን ኃጢአት ዳግመኛ ሕያው ሆነ፤ እኔ ግን ሞትኩ።
ወደ ሕይወት እንዲመራ የታሰበውም ትእዛዝ ሞት እንዳመጣ ተገነዘብኩ።
ምክንያቱም ኃጢአት ትእዛዙ ባስገኘው አጋጣሚ ተጠቅሞ አታሎኛል፤ እንዲሁም በትእዛዙ አማካኝነት ገድሎኛል።
ስለዚህ ሕጉ በራሱ ቅዱስ ነው፤ ትእዛዙም ቅዱስ፣ ጻድቅና ጥሩ ነው።
ታዲያ ይህ ጥሩ የሆነው ነገር ሞት አመጣብኝ ማለት ነው? በፍጹም! ከዚህ ይልቅ የገደለኝ ኃጢአት ነው። የኃጢአት ምንነት እንዲገለጥ ጥሩ በሆነው ነገር አማካኝነት ሞት ያመጣብኝ ኃጢአት ነው። ትእዛዙም ኃጢአት ምን ያህል ክፉ እንደሆነ አሳይቷል።
ሕጉ መንፈሳዊ እንደሆነ እናውቃለንና፤ እኔ ግን ለኃጢአት የተሸጥኩ ሥጋዊ ነኝ።
ለምን እንዲህ እንደማደርግ አላውቅም። ለማድረግ የምፈልገውን ነገር አላደርግምና፤ ከዚህ ይልቅ የማደርገው የምጠላውን ነገር ነው።
ይሁን እንጂ የማደርገው የማልፈልገውን ከሆነ ሕጉ መልካም ነው በሚለው እስማማለሁ።
ሆኖም አሁን ይህን የሚያደርገው በእኔ ውስጥ የሚኖረው ኃጢአት ነው እንጂ እኔ አይደለሁም።
ምክንያቱም በውስጤ ማለትም በሥጋዬ ውስጥ የሚኖር ምንም ጥሩ ነገር የለም፤ መልካም የሆነውን ነገር የማድረግ ፍላጎት እንጂ የመፈጸም ችሎታ የለኝም።
የምመኘውን መልካም ነገር አላደርግምና፤ የማልፈልገውን መጥፎ ነገር ግን አደርጋለሁ።
እንግዲህ የማደርገው የማልፈልገውን ነገር ከሆነ ይህን የማደርገው እኔ ሳልሆን በውስጤ የሚኖረው ኃጢአት ነው።
እንግዲያው ይህ ሕግ በራሴ ላይ ሲሠራ አያለሁ፦ ትክክል የሆነውን ነገር ማድረግ ስፈልግ ከእኔ ጋር ያለው ግን መጥፎ ነገር ነው።
በውስጤ በአምላክ ሕግ እጅግ ደስ ይለኛል፤
በሰውነቴ ውስጥ ግን ከአእምሮዬ ሕግ ጋር የሚዋጋውንና በሰውነቴ ውስጥ ላለው የኃጢአት ሕግ ምርኮኛ አድርጎ የሚሰጠኝን ሌላ ሕግ አያለሁ።
እኔ ምንኛ ጎስቋላ ሰው ነኝ! እንዲህ ወዳለው ሞት ከሚመራኝ ሰውነት ማን ይታደገኛል?
በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል የሚታደገኝ አምላክ የተመሰገነ ይሁን! ስለዚህ እኔ ራሴ በአእምሮዬ ለአምላክ ሕግ ባሪያ ስሆን በሥጋዬ ግን ለኃጢአት ሕግ ባሪያ ነኝ።
ሰው ሁሉ ለበላይ ባለሥልጣናት ይገዛ፤ ሥልጣን ሁሉ የሚገኘው ከአምላክ ነውና፤ ያሉት ባለሥልጣናት አንጻራዊ ቦታቸውን ያገኙት ከአምላክ ነው።
ስለዚህ ባለሥልጣንን የሚቃወም ሁሉ አምላክ ያደረገውን ዝግጅት ይቃወማል፤ ይህን ዝግጅት የሚቃወሙ በራሳቸው ላይ ፍርድ ያመጣሉ።
ገዢዎች የሚያስፈሩት ክፉ ለሚያደርጉ እንጂ መልካም ለሚያደርጉ አይደለምና። እንግዲያው ባለሥልጣንን መፍራት የማትፈልግ ከሆነ መልካም ማድረግህን ቀጥል፤ ከእሱም ምስጋና ታገኛለህ፤
ለአንተ ጥቅም ሲባል የተሾመ የአምላክ አገልጋይ ነውና። ክፉ የምታደርግ ከሆነ ግን ልትፈራ ይገባሃል፤ ምክንያቱም ሰይፍ የሚታጠቀው እንዲያው በከንቱ አይደለም። ክፉ የሚሠራን በመቅጣት የሚበቀል የአምላክ አገልጋይ ነው።
ስለዚህ ቁጣውን በመፍራት ብቻ ሳይሆን ስለ ሕሊናችሁ ስትሉም መገዛታችሁ አስፈላጊ ነው።
ቀረጥ የምትከፍሉትም ለዚሁ ነው፤ ምክንያቱም እነሱ ሕዝባዊ አገልግሎት የሚያከናውኑ የአምላክ አገልጋዮች ናቸው፤ የዘወትር ተግባራቸውም ይኸው ነው።
ለሁሉም የሚገባውን አስረክቡ፤ ቀረጥ ለሚጠይቅ ቀረጥ፣ ግብር ለሚጠይቅ ግብር ስጡ፤ መፈራት የሚፈልገውን ፍሩ፤ መከበር የሚፈልገውን አክብሩ።
እርስ በርስ ከመዋደድ በቀር በማንም ላይ ምንም ዕዳ አይኑርባችሁ፤ ሰውን የሚወድ ሁሉ ሕጉን ፈጽሟልና።
ምክንያቱም “አታመንዝር፣ አትግደል፣ አትስረቅ፣ አትጎምጅ” የሚሉት ሕጎችና ሌሎች ትእዛዛት በሙሉ “ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ” በሚለው በዚህ ቃል ተጠቃለዋል።
ፍቅር በባልንጀራው ላይ ክፉ አያደርግም፤ ስለዚህ ፍቅር የሕግ ፍጻሜ ነው።
ምን ዓይነት ዘመን ላይ እንደምንገኝ ስለምታውቁም ይህን አድርጉ፤ አማኞች ከሆንበት ጊዜ ይልቅ አሁን መዳናችን ይበልጥ ስለቀረበ ከእንቅልፍ የምትነቁበት ሰዓት አሁን ነው።
ሌሊቱ እየተገባደደ ነው፤ ቀኑም ቀርቧል። ስለዚህ ከጨለማ ጋር የተያያዙ ሥራዎችን አውልቀን የብርሃንን የጦር ዕቃዎች እንልበስ።
መረን በለቀቀ ፈንጠዝያና በስካር፣ ልቅ በሆነ የፆታ ግንኙነትና ዓይን ባወጣ ምግባር እንዲሁም በጠብና በቅናት ሳይሆን በቀን ብርሃን እንደምንመላለስ በጨዋነት እንመላለስ።
ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን ልበሱት፤ የሥጋ ፍላጎታችሁን ለማርካት ዕቅድ አታውጡ።
ታዲያ አይሁዳዊ መሆን ጥቅሙ ምኑ ላይ ነው? ግርዘትስ ፋይዳው ምንድን ነው?
በሁሉም መንገድ ትልቅ ጥቅም አለው። በመጀመሪያ ደረጃ የአምላክ ቅዱስ ቃል በአደራ ተሰጥቷቸዋል።
አንዳንድ አይሁዳውያን እምነት ቢጎድላቸውስ? የእነሱ እምነት ማጣት ሰዎች በአምላክ እንዳይታመኑ ሊያደርግ ይችላል?
በፍጹም! ከዚህ ይልቅ “በቃልህ ጻድቅ ሆነህ ትገኝ ዘንድ፣ በፍርድም ፊት ትረታ ዘንድ” ተብሎ እንደተጻፈ ሰው ሁሉ ሐሰተኛ ሆኖ ቢገኝ እንኳ የአምላክ እውነተኝነት የተረጋገጠ ነው።
ይሁን እንጂ የእኛ ክፋት የአምላክን ጽድቅ አጉልቶ የሚያሳይ ከሆነ ምን ማለት እንችላለን? አምላክ ቁጣውን መግለጹ ኢፍትሐዊ ያሰኘዋል እንዴ? (አንዳንድ ሰዎች እንደሚያስቡት ማለት ነው።)
በፍጹም! አለዚያ አምላክ በዓለም ላይ እንዴት ይፈርዳል?
ይሁንና በእኔ ውሸት የተነሳ የአምላክ እውነት ለእሱ ክብር በሚያመጣ መንገድ ይበልጥ ጎልቶ የሚወጣ ከሆነ ታዲያ እኔ ለምን ኃጢአተኛ ተብዬ ይፈረድብኛል?
እንዲህ ከሆነማ አንዳንድ ሰዎች “ጥሩ ነገር እንዲገኝ መጥፎ ነገር እንሥራ” ይላሉ በማለት በሐሰት እንደሚያስወሩብን ለምን አንልም? በእነዚህ ሰዎች ላይ የሚበየነው ፍርድ ፍትሐዊ ነው።
እንግዲህ ምን ማለት ይቻላል? እኛ የተሻልን ነን ማለት ነው? በፍጹም! ምክንያቱም አይሁዳውያንም ሆኑ ግሪካውያን ሁሉም የኃጢአት ተገዢዎች እንደሆኑ በመናገር አስቀድመን ከሰናቸዋል፤
ይህም እንዲህ ተብሎ እንደተጻፈው ነው፦ “ጻድቅ ሰው የለም፤ አንድም እንኳ የለም፤
ማስተዋል ያለው አንድም ሰው የለም፤ ደግሞም አምላክን የሚፈልግ አንድም ሰው የለም።
ሁሉም መንገድ ስተዋል፤ ሁሉም የማይረቡ ሆነዋል፤ ደግነት የሚያሳይ አንድም ሰው የለም፤ አንድም እንኳ አይገኝም።”
“ጉሮሯቸው የተከፈተ መቃብር ነው፤ በምላሳቸው ያታልላሉ።” “ከከንፈራቸው ሥር የእባብ መርዝ አለ።”
“አፋቸውም በእርግማንና በምሬት የተሞላ ነው።”