text
stringlengths
4
267
“እግሮቻቸው ደም ለማፍሰስ ፈጣኖች ናቸው።”
“በመንገዳቸው ላይ ጥፋትና መከራ አለ፤
የሰላምንም መንገድ አያውቁም።”
“በዓይኖቻቸው ፊት አምላክን መፍራት የሚባል ነገር የለም።”
እንግዲህ አፍ ሁሉ እንዲዘጋና ዓለም በሙሉ በአምላክ ፊት ተጠያቂ እንዲሆን ሕግ የሚናገረው ሁሉ ከሕግ በታች ላሉት እንደሆነ እናውቃለን።
ስለዚህ ሕግን በመጠበቅ ማንም ሰው በፊቱ ጻድቅ ነህ ሊባል አይችልም፤ ምክንያቱም ስለ ኃጢአት ትክክለኛ ግንዛቤ የሚገኘው በሕጉ አማካኝነት ነው።
አሁን ግን ሕግ ሳያስፈልግ፣ በሕጉና በነቢያት የተመሠከረለት የአምላክ ጽድቅ ግልጽ ሆኗል፤
እምነት ያላቸው ሁሉ ደግሞ በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ባላቸው እምነት አማካኝነት የአምላክን ጽድቅ ያገኛሉ። ይህም የሆነው በሰዎች መካከል ምንም ልዩነት ስለሌለ ነው።
ምክንያቱም ሁሉም ኃጢአት ሠርተዋል፤ የአምላክንም ክብር ማንጸባረቅ ተስኗቸዋል፤
ይሁንና ክርስቶስ ኢየሱስ የከፈለው ቤዛ በሚያስገኘው ነፃነት አማካኝነት በጸጋው ጻድቃን ናችሁ መባላቸው እንዲሁ የተገኘ ነፃ ስጦታ ነው።
በኢየሱስ ደም የሚያምኑ ሁሉ ማስተሰረያ ያገኙ ዘንድ አምላክ እሱን መባ አድርጎ አቅርቦታል። አምላክ ይህን ያደረገው የራሱን ጽድቅ ለማሳየት ነው፤ ምክንያቱም አምላክ ቻይ በመሆን በቀደሙት ዘመናት የተፈጸሙትን ኃጢአቶች ይቅር ብሏል።
ይህን ያደረገው በዚህም ዘመን የራሱን ጽድቅ ለማሳየት ነው፤ ይህም በኢየሱስ የሚያምነውን ሰው ጻድቅ ነህ በማለት እሱ ራሱ ጻድቅ ይሆን ዘንድ ነው።
ታዲያ እንድንኮራ የሚያደርገን ነገር ይኖራል? ምንም ነገር የለም። እንዳንኮራ የሚያደርገን ሕግ የትኛው ነው? የሥራ ሕግ ነው? በፍጹም አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ እንዳንኮራ የሚያደርገን የእምነት ሕግ ነው።
ምክንያቱም አንድ ሰው ጻድቅ ነህ የሚባለው የሕግን ሥራ በመፈጸም ሳይሆን በእምነት እንደሆነ እንረዳለን።
ወይስ አምላክ የአይሁዳውያን አምላክ ብቻ ነው? የአሕዛብስ አምላክ አይደለም? አዎ፣ የአሕዛብም አምላክ ነው።
አምላክ አንድ ስለሆነ የተገረዙትን ከእምነት የተነሳ ጻድቃን ይላቸዋል፤ ያልተገረዙትንም በእምነታቸው አማካኝነት ጻድቃን ናችሁ ይላቸዋል።
ታዲያ በእምነታችን አማካኝነት ሕግን እንሽራለን ማለት ነው? በፍጹም! እንዲያውም ሕግን እንደግፋለን።
የክርስቶስ ተከታይ እንደመሆኔ መጠን የምናገረው እውነት ነው፤ ሕሊናዬ በመንፈስ ቅዱስ እየተመራ ከእኔ ጋር ሆኖ ስለሚመሠክር አልዋሽም፤
ታላቅ ሐዘንና የማያቋርጥ ሥቃይ በልቤ ውስጥ አለ።
የሥጋ ዘመዶቼ ስለሆኑት ስለ ወንድሞቼ ስል እኔ ራሴ የተረገምኩ ሆኜ ከክርስቶስ ብለይ በወደድኩ ነበርና።
እነሱ እስራኤላውያን ናቸው፤ አምላክ ልጆቹ አድርጎ የወሰዳቸው፣ ክብር ያገኙት፣ ቃል ኪዳን የተገባላቸው፣ ሕግ የተሰጣቸው፣ ቅዱስ አገልግሎት የማቅረብ መብት ያገኙትና ተስፋ የተሰጣቸው እነሱ ናቸው።
አባቶችም የእነሱ ናቸው፤ ክርስቶስም በሥጋ የተገኘው ከእነሱ ነው። የሁሉ የበላይ የሆነው አምላክ ለዘላለም ይወደስ። አሜን።
ይሁን እንጂ የአምላክ ቃል ከንቱ ሆኖ ቀርቷል ማለት አይደለም። ከእስራኤል የተወለደ ሁሉ በእርግጥ “እስራኤል” አይደለምና።
በተጨማሪም የአብርሃም ዘር ስለሆኑ ሁሉም ልጆቹ ናቸው ማለት አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ “ዘርህ የሚጠራልህ በይስሐቅ በኩል ይሆናል” ተብሎ ተጽፏል።
ይህም ሲባል በሥጋ ልጆች የሆኑ በእርግጥ የአምላክ ልጆች አይደሉም፤ በተስፋው ልጆች የሆኑት ግን ዘሩ እንደሆኑ ተደርገው ይቆጠራሉ።
የተስፋው ቃል “የዛሬ ዓመት በዚህ ጊዜ እመጣለሁ፤ ሣራም ወንድ ልጅ ትወልዳለች” ይላልና።
ተስፋው የተሰጠው በዚያን ጊዜ ብቻ ሳይሆን ርብቃ ከአባታችን ከይስሐቅ መንታ ልጆች በፀነሰች ጊዜ ጭምር ነው፤
ምርጫውን በተመለከተ የአምላክ ዓላማ በሥራ ሳይሆን በጠሪው ላይ የተመካ ሆኖ ይቀጥል ዘንድ ልጆቹ ከመወለዳቸውና ጥሩም ሆነ ክፉ ከማድረጋቸው በፊት
ርብቃ “ታላቁ የታናሹ ባሪያ ይሆናል” ተብሎ ተነግሯት ነበር።
ይህም “ያዕቆብን ወደድኩ፤ ኤሳውን ግን ጠላሁ” ተብሎ እንደተጻፈው ነው።
እንግዲህ ምን እንበል? አምላክ ፍትሕ ያዛባል ማለት ነው? በፍጹም!
ሙሴን “ልምረው የምፈልገውን እምረዋለሁ፤ ልራራለት የምፈልገውን ደግሞ እራራለታለሁ” ብሎታልና።
ስለዚህ ይህ የተመካው በአንድ ሰው ፍላጎት ወይም ጥረት ሳይሆን ምሕረት በሚያደርገው አምላክ ላይ ነው።
ቅዱስ መጽሐፉ ስለ ፈርዖን ሲናገር “በሕይወት ያቆየሁህ ኃይሌን በአንተ ለማሳየትና ስሜ በመላው ምድር እንዲታወጅ ለማድረግ ነው” ይላል።
ስለዚህ አምላክ የፈለገውን ይምራል፤ የፈለገውን ደግሞ ግትር እንዲሆን ይፈቅዳል።
በመሆኑም “እንደዚህ ከሆነ ታዲያ ሰዎችን ለምን ይወቅሳል? ደግሞስ ፈቃዱን ማን መቃወም ይችላል?” ትለኝ ይሆናል።
ለመሆኑ ለአምላክ የምትመልሰው አንተ ማን ነህ? አንድ ዕቃ ቅርጽ አውጥቶ የሠራውን ሰው “ለምን እንዲህ አድርገህ ሠራኸኝ?” ይለዋል?
ሸክላ ሠሪው ከዚያው ከአንዱ ጭቃ፣ አንዱን ዕቃ ክቡር ለሆነ አገልግሎት ሌላውን ዕቃ ደግሞ ክብር ለሌለው አገልግሎት ለመሥራት በጭቃው ላይ ሥልጣን እንዳለው አታውቅም?
አምላክ ቁጣውን ለማሳየትና ኃይሉ እንዲታወቅ ለማድረግ ቢፈልግም እንኳ ጥፋት የሚገባቸውን የቁጣ ዕቃዎች በብዙ ትዕግሥት ችሏቸው እንደሆነስ ምን ታውቃለህ?
ይህን ያደረገው ታላቅ ክብሩን አስቀድሞ ለክብር ባዘጋጃቸው የምሕረት ዕቃዎች ላይ ለመግለጥ
ይኸውም ከአይሁዳውያን ብቻ ሳይሆን ከአሕዛብም በጠራን በእኛ ላይ ታላቅ ክብሩን ለመግለጥ ቢሆንስ?
ይህም በሆሴዕ መጽሐፍ ላይ እንዲህ ብሎ እንደተናገረው ነው፦ “ሕዝቤ ያልሆኑትን ‘ሕዝቤ’ ብዬ፣ ያልተወደደችውንም ‘የተወደደች’ ብዬ እጠራለሁ፤
‘ሕዝቤ አይደላችሁም’ ተብሎ በተነገራቸው ስፍራም በዚያ ‘የሕያው አምላክ ልጆች’ ተብለው ይጠራሉ።”
ከዚህም በተጨማሪ ኢሳይያስ ስለ እስራኤል እንዲህ ሲል ድምፁን ከፍ አድርጎ ይናገራል፦ “የእስራኤል ልጆች ቁጥር እንደ ባሕር አሸዋ ቢሆንም እንኳ የሚድኑት ቀሪዎች ብቻ ናቸው።
ይሖዋ በምድር የሚኖሩትን ይፋረዳልና፤ ይህን ደግሞ ሳይዘገይ ይፈጽመዋል።”
ደግሞም ኢሳይያስ አስቀድሞ እንደተናገረው “የሠራዊት ጌታ ይሖዋ ዘር ባያስቀርልን ኖሮ እንደ ሰዶም በሆን፣ ገሞራንም በመሰልን ነበር።”
እንግዲህ ምን እንበል? አሕዛብ ጽድቅን ባይከታተሉም እንኳ ጽድቅን ይኸውም በእምነት አማካኝነት የሚገኘውን ጽድቅ አገኙ፤
ሆኖም እስራኤል የጽድቅን ሕግ ቢከታተልም ግቡ ላይ አልደረሰም፤ ይኸውም ሕጉን አልፈጸመም።
ይህ የሆነው ለምንድን ነው? በእምነት ሳይሆን በሥራ የሚገኝ እንደሆነ አድርገው ስለተከታተሉት ነው። ስለዚህ “በማሰናከያ ድንጋይ” ተሰናከሉ፤
ይህም “እነሆ፣ በጽዮን የሚያደናቅፍ ድንጋይና የሚያሰናክል ዓለት አኖራለሁ፤ በእሱ ላይ እምነት የሚጥል ግን አያፍርም” ተብሎ እንደተጻፈው ነው።
ስለዚህ አንተ ሰው፣ ማንም ሆንክ ማን በሌላው ላይ የምትፈርድ ከሆነ ምንም የምታመካኝበት ነገር የለህም፤ በሌላው ላይ ስትፈርድ ራስህንም ኮነንክ ማለት ነው፤ ምክንያቱም በሌላው ላይ የምትፈርድ አንተ ራስህ እነዚያኑ ነገሮች በተደጋጋሚ ታደርጋለህ።
አምላክ እንዲህ ያሉትን ነገሮች በሚፈጽሙ ሰዎች ላይ እንደሚፈርድ እናውቃለን፤ ፍርዱ ደግሞ ከእውነት ጋር የሚስማማ ነው።
ይሁን እንጂ አንተ ሰው፣ እንዲህ ያሉትን ነገሮች በሚፈጽሙ ሰዎች ላይ እየፈረድክ አንተ ግን እነዚያኑ ነገሮች የምታደርግ ከሆነ ከአምላክ ፍርድ አመልጣለሁ ብለህ ታስባለህ?
ወይስ አምላክ በደግነቱ ወደ ንስሐ ሊመራህ እየሞከረ እንዳለ ሳታውቅ የደግነቱን፣ የቻይነቱንና የትዕግሥቱን ብዛት ትንቃለህ?
እንግዲህ በግትርነትህና ንስሐ በማይገባው ልብህ የተነሳ በራስህ ላይ ቁጣ ታከማቻለህ። ይህ ቁጣ አምላክ የጽድቅ ፍርድ በሚፈርድበት ቀን ይገለጣል።
እሱም ለእያንዳንዱ እንደ ሥራው ይከፍለዋል፦
በመልካም ሥራ በመጽናት ክብርን፣ ሞገስንና ሊጠፋ የማይችል ሕይወትን ለሚፈልጉ የዘላለም ሕይወት ይሰጣቸዋል፤
ይሁን እንጂ ጠብ ወዳዶች በሆኑትና ለእውነት ከመታዘዝ ይልቅ ለዓመፅ በሚታዘዙት ላይ ቁጣና መዓት ይወርድባቸዋል።
ክፉ ሥራ በሚሠራ ሰው ሁሉ ላይ ይኸውም በመጀመሪያ በአይሁዳዊ ከዚያም በግሪካዊ ላይ መከራና ጭንቀት ይመጣል፤
ሆኖም መልካም ሥራ የሚሠራ ሁሉ ይኸውም በመጀመሪያ አይሁዳዊ ከዚያም ግሪካዊ ክብር፣ ሞገስና ሰላም ያገኛል።
በአምላክ ዘንድ አድልዎ የለምና።
ሕግ ሳይኖራቸው ኃጢአት የሠሩ ሁሉ ያለሕግ ይጠፋሉና፤ ሆኖም ሕግ እያላቸው ኃጢአት የሠሩ ሁሉ በሕግ ይፈረድባቸዋል።
ምክንያቱም በአምላክ ፊት ጻድቅ የሆኑት ሕግን የሚሰሙ አይደሉም፤ ከዚህ ይልቅ ጻድቃን ናችሁ የሚባሉት ሕግን የሚፈጽሙ ናቸው።
ሕግ የሌላቸው አሕዛብ በተፈጥሮ በሕጉ ውስጥ ያሉትን ነገሮች ሲያደርጉ እነዚህ ሰዎች ሕግ ባይኖራቸውም እንኳ እነሱ ለራሳቸው ሕግ ናቸውና።
የሕጉ መሠረታዊ ሐሳብ በልባቸው እንደተጻፈ የሚያሳዩት እነሱ ራሳቸው ናቸው፤ ሕሊናቸው ከእነሱ ጋር ሆኖ በሚመሠክርበት ጊዜ ሐሳባቸው በውስጣቸው እየተሟገተ አንዴ ይከሳቸዋል፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ጥፋተኛ አይደላችሁም ይላቸዋል።
ይህ የሚሆነው እኔ በማውጀው ምሥራች መሠረት አምላክ በክርስቶስ ኢየሱስ አማካኝነት ሰዎች በስውር በሚያስቧቸውና በሚያደርጓቸው ነገሮች ላይ በሚፈርድበት ቀን ነው።
አንተ አይሁዳዊ ተብለህ የምትጠራ፣ በሕጉ የምትመካ፣ ከአምላክ ጋር ባለህ ዝምድና የምትኩራራ፣
ፈቃዱን የምታውቅ፣ በሕጉ ውስጥ ያለውን ነገር የተማርክ በመሆንህ የላቀ ዋጋ ያላቸውን ነገሮች በሚገባ የምትገነዘብ፣
ለዕውር መሪ፣ በጨለማ ላሉት ብርሃን ነኝ ብለህ የምታምን፣
ማስተዋል የጎደላቸውን የማሠለጥንና ሕፃናትን የማስተምር ነኝ የምትል እንዲሁም በሕጉ ውስጥ ያሉትን የእውቀትና የእውነት መሠረታዊ ገጽታዎች የምታውቅ ከሆንክ፣
ታዲያ አንተ ሌላውን የምታስተምር ራስህን አታስተምርም? አንተ “አትስረቅ” ብለህ የምትሰብክ ትሰርቃለህ?
አንተ “አታመንዝር” የምትል ታመነዝራለህ? አንተ ጣዖትን የምትጸየፍ ቤተ መቅደስን ትዘርፋለህ?
አንተ በሕግ የምትኩራራ ሕጉን በመተላለፍ አምላክን ታዋርዳለህ?
ይህም “በእናንተ ምክንያት የአምላክ ስም በአሕዛብ መካከል ይሰደባል” ተብሎ እንደተጻፈው ነው።
መገረዝ ጥቅም የሚኖረው ሕጉን እስካከበርክ ድረስ ነው፤ ሕጉን የምትተላለፍ ከሆነ ግን መገረዝህ እንደ አለመገረዝ ይቆጠራል።
ያልተገረዘ ሰው በሕጉ ውስጥ ያሉትን የጽድቅ መሥፈርቶች የሚጠብቅ ከሆነ አለመገረዙ እንደ መገረዝ አይቆጠርም?
እንግዲህ አንተ የተጻፈ ሕግ ያለህና የተገረዝክ ሆነህ ሳለ ሕግን የምትጥስ ከሆነ በሥጋ ያልተገረዘ ሆኖ ሕግን የሚፈጽም ሰው ይፈርድብሃል።
ምክንያቱም እውነተኛ አይሁዳዊነት በውጫዊ ገጽታ የሚገለጽ አይደለም፤ ግርዘቱም ውጫዊና ሥጋዊ ግርዘት አይደለም።
ከዚህ ይልቅ በውስጡ አይሁዳዊ የሆነ እሱ አይሁዳዊ ነው፤ ግርዘቱም በተጻፈ ሕግ ሳይሆን በመንፈስ የሆነ የልብ ግርዘት ነው። እንዲህ ዓይነቱ ሰው ውዳሴ የሚያገኘው ከሰው ሳይሆን ከአምላክ ነው።
ወንድሞች፣ ለእስራኤላውያን ከልቤ የምመኘውና ስለ እነሱ ለአምላክ ምልጃ የማቀርበው እንዲድኑ ነው።
ለአምላክ ቅንዓት እንዳላቸው እመሠክርላቸዋለሁና፤ ሆኖም ቅንዓታቸው በትክክለኛ እውቀት ላይ የተመሠረተ አይደለም።
የአምላክን ጽድቅ ሳያውቁ የራሳቸውን ጽድቅ ለመመሥረት ስለፈለጉ ራሳቸውን ለአምላክ ጽድቅ አላስገዙም።
የሚያምን ሁሉ መጽደቅ ይችል ዘንድ ክርስቶስ የሕግ ፍጻሜ ነውና።
ሙሴ በሕጉ አማካኝነት ስለሚገኘው ጽድቅ ሲገልጽ “እነዚህን ነገሮች የሚያደርግ ሰው በእነሱ አማካኝነት በሕይወት ይኖራል” ሲል ጽፏል።
ሆኖም በእምነት የሚገኘውን ጽድቅ በተመለከተ እንዲህ ተብሏል፦ “በልብህ ‘ወደ ሰማይ ማን ይወጣል?’ አትበል፤ ይህም ክርስቶስን ለማውረድ ነው፤
ወይም ‘ወደ ጥልቁ ማን ይወርዳል?’ አትበል፤ ይህም ክርስቶስን ከሞት ለማስነሳት ነው።”
ይሁንና ቅዱስ መጽሐፉ ምን ይላል? “ቃሉ ለአንተ ቅርብ ነው፤ ደግሞም በአፍህና በልብህ ውስጥ ነው”፤ ይህም እኛ የምንሰብከው የእምነት “ቃል” ነው።
ኢየሱስ ጌታ እንደሆነ በአፍህ በይፋ ብትናገር እንዲሁም አምላክ ከሞት እንዳስነሳው በልብህ ብታምን ትድናለህና።
ሰው በልቡ አምኖ ይጸድቃልና፤ በአፉ ደግሞ እምነቱን በይፋ ተናግሮ ይድናል።
ቅዱስ መጽሐፉ “በእሱ ላይ እምነት የሚጥል ሁሉ አያፍርም” ይላል።
በአይሁዳዊና በግሪካዊ መካከል ምንም ልዩነት የለምና። የሁሉም ጌታ አንድ ነው፤ እሱም የሚለምኑትን ሁሉ አብዝቶ ይባርካል።
“የይሖዋን ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናልና።”
ይሁንና ካላመኑበት እንዴት አድርገው ይጠሩታል? ስለ እሱ ሳይሰሙስ እንዴት ያምኑበታል? ደግሞስ የሚሰብክላቸው ሳይኖር እንዴት ይሰማሉ?
ካልተላኩስ እንዴት ይሰብካሉ? ይህም “የተሻለ ነገር እንደሚመጣ ምሥራች የሚናገሩ ሰዎች እግሮቻቸው እንዴት ያማሩ ናቸው!” ተብሎ እንደተጻፈው ነው።
ሆኖም ምሥራቹን የታዘዙት ሁሉም አይደሉም። ኢሳይያስ “ይሖዋ ሆይ፣ ከእኛ የሰማውን ነገር ያመነ ማን ነው?” ብሏልና።
ስለዚህ እምነት የሚገኘው ቃሉን ከመስማት ነው። ቃሉን መስማት የሚቻለው ደግሞ ስለ ክርስቶስ የሚናገር ሰው ሲኖር ነው።
ይሁንና ‘ሳይሰሙ ቀርተው ይሆን?’ ብዬ እጠይቃለሁ። በእርግጥ ሰምተዋል፤ “ጩኸታቸው ወደ መላው ምድር ወጣ፤ መልእክታቸውም እስከ ዓለም ዳርቻዎች ተሰማ” ተብሏልና።
ይሁንና ‘እስራኤላውያን ሳያውቁ ቀርተው ይሆን?’ ብዬ እጠይቃለሁ። ሙሴ አስቀድሞ “እናንተን፣ ሕዝብ ባልሆኑት አስቀናችኋለሁ፤ ሞኝ በሆነ ብሔር አማካኝነትም ክፉኛ አስቆጣችኋለሁ” ብሏል።
ኢሳይያስም በድፍረት “ያልፈለጉኝ ሰዎች አገኙኝ፤ እኔን ለማግኘት ባልጠየቁ ሰዎችም ዘንድ የታወቅኩ ሆንኩ” ብሏል።
እስራኤልን በተመለከተ ግን “ወደማይታዘዝና ልበ ደንዳና ወደሆነ ሕዝብ ቀኑን ሙሉ እጆቼን ዘረጋሁ” ብሏል።