text stringlengths 4 267 |
|---|
ቅጥሮችሽን በግንብ መደርመሻ መሣሪያ ይደበድባል፤ ማማዎችሽንም በመጥረቢያ ያፈርሳል። |
ፈረሶቹ እጅግ ብዙ ከመሆናቸው የተነሳ አቧራ ያለብሱሻል፤ ሰዎች ቅጥሮቿ ወደፈረሱባት ከተማ እንደሚገቡ ሁሉ እሱም በበሮችሽ በሚገባበት ጊዜ የፈረሰኞቹ፣ የመንኮራኩሮቹና የሠረገሎቹ ድምፅ ቅጥሮችሽን ያናውጣል። |
የፈረሶቹ ኮቴዎች ጎዳናዎችሽን ሁሉ ይረግጣሉ፤ ሕዝብሽን በሰይፍ ይገድላል፤ ግዙፍ የሆኑት ዓምዶችሽ መሬት ላይ ይንኮታኮታሉ። |
ሀብትሽን ይበዘብዛሉ፤ ሸቀጥሽን ይዘርፋሉ፤ ቅጥሮችሽን ያፈርሳሉ፤ የሚያማምሩ ቤቶችሽንም ያወድማሉ፤ ከዚያም ድንጋዮችሽን፣ ሳንቃዎችሽንና አፈርሽን ወደ ባሕር ይጥላሉ።’ |
“‘የዘፈንሽ ጩኸት ጸጥ እንዲል አደርጋለሁ፤ የበገናሽም ድምፅ ከእንግዲህ አይሰማም። |
የሚያንጸባርቅ ገላጣ ዓለትም አደርግሻለሁ፤ የመረብ ማስጫ ቦታ ትሆኛለሽ። ዳግመኛ አትገነቢም፤ እኔ ይሖዋ ራሴ ተናግሬአለሁና’ ይላል ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ። |
“ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ ጢሮስን እንዲህ ይላል፦ ‘ሞት አፋፍ ላይ ያሉት ሲያቃስቱና በመካከልሽ ጭፍጨፋ ሲካሄድ፣ ከውድቀትሽ ድምፅ የተነሳ ደሴቶች አይናወጡም? |
የባሕርም ገዢዎች ሁሉ ከዙፋኖቻቸው ይወርዳሉ፤ ልብሳቸውንም ያወልቃሉ፤ የተጠለፉ ሸማዎቻቸውንም አውልቀው ይጥላሉ፤ ደግሞም በጣም ይንቀጠቀጣሉ። መሬት ላይ ተቀምጠው ያለማቋረጥ ይንቀጠቀጣሉ፤ በመገረምም አተኩረው ይመለከቱሻል። |
በአንቺም ላይ ሙሾ ያወርዳሉ፤ እንዲህም ይሉሻል፦ “ባሕር አቋርጠው የመጡ ሰዎች የሰፈሩብሽ፣ የተወደስሽ ከተማ ሆይ፣ እንዴት ጠፋሽ!አንቺም ሆንሽ ነዋሪዎችሽ በምድር ነዋሪዎች ሁሉ ላይሽብር የምትነዙ የባሕር ላይ ኃያላን ነበራችሁ። |
በምትወድቂበት ቀን ደሴቶች ይንቀጠቀጣሉ፤ጥፋት በሚደርስብሽ ጊዜ በባሕር ላይ ያሉ ደሴቶች ይሸበራሉ።”’ |
“ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላልና፦ ‘ሰው እንደማይኖርባቸው ከተሞች ባድማ ሳደርግሽ፣ የሚያጥለቀልቅ ውኃ ሳመጣብሽና ኃይለኛ ውኃ ሲሸፍንሽ፣ |
አንቺንም ሆነ ከአንቺ ጋር ወደ ጉድጓድ የሚወርዱትን፣ የጥንት ዘመን ሰዎች ወዳሉበት አወርዳችኋለሁ፤ ወደ ጉድጓድ ከሚወርዱት ጋር፣ ጥንት እንደወደሙት ቦታዎች እጅግ ዝቅተኛ በሆነ ምድር እንድትኖሪ አደርጋለሁ፤ ይህም የሚሆነው ሰው እንዳይኖርብሽ ነው። ከዚያ በኋላ የሕያዋንን ምድር ከፍ ከፍ አደርጋለሁ። |
“‘በአንቺ ላይ ድንገተኛ ሽብር አመጣለሁ፤ ከእንግዲህም አትኖሪም። ይፈልጉሻል ግን ፈጽሞ አትገኚም’ ይላል ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ።” |
በ30ኛው ዓመት፣ በአራተኛው ወር፣ ከወሩም በአምስተኛው ቀን፣ በኬባር ወንዝ አጠገብ በግዞት በተወሰደው ሕዝብ መካከል ሳለሁ ሰማያት ተከፍተው አምላክ የገለጠልኝን ራእዮች ማየት ጀመርኩ። |
ከወሩ በአምስተኛው ቀን ይኸውም ንጉሥ ዮአኪን በግዞት በተወሰደ በአምስተኛው ዓመት፣ |
በከለዳውያን ምድር በኬባር ወንዝ አጠገብ የይሖዋ ቃል የካህኑ የቡዚ ልጅ ወደሆነው ወደ ሕዝቅኤል መጣ። በዚያም የይሖዋ ኃይል በእሱ ላይ ወረደ። |
እኔም በማየት ላይ ሳለሁ ከሰሜን ኃይለኛ አውሎ ነፋስ ሲመጣ ተመለከትኩ፤ በዚያም ታላቅ ደመናና በደማቅ ብርሃን የተከበበ የእሳት ብልጭታ ነበር፤ ከእሳቱም መካከል የሚያብረቀርቅ ብረት የሚመስል ነገር ይወጣ ነበር። |
በመካከሉም የአራት ሕያዋን ፍጥረታት አምሳያ ነበር፤ የእያንዳንዳቸውም መልክ እንደ ሰው መልክ ነበር። |
እያንዳንዳቸው አራት አራት ፊትና አራት አራት ክንፍ ነበራቸው። |
እግሮቻቸው ቀጥ ያሉ ነበሩ፤ የእግራቸውም ኮቴ የጥጃ ኮቴ ይመስል ነበር፤ እግሮቻቸውም እንደተወለወለ መዳብ ያብረቀርቃሉ። |
በአራቱም ጎኖቻቸው ከክንፎቻቸው ሥር የሰው እጆች ነበሯቸው፤ አራቱም ፊቶችና ክንፎች ነበሯቸው። |
ክንፎቻቸውም እርስ በርሳቸው ይነካኩ ነበር። በሚሄዱበት ጊዜ አይዞሩም፤ እያንዳንዳቸውም ቀጥ ብለው ወደ ፊት ይሄዱ ነበር። |
የፊታቸው መልክ ይህን ይመስል ነበር፦ አራቱም የሰው ፊት ነበራቸው፤ በስተ ቀኝ የአንበሳ ፊት፣ በስተ ግራ የበሬ ፊት ነበራቸው፤ ደግሞም አራቱም የንስር ፊት ነበራቸው። |
ፊታቸው ይህን ይመስላል። ክንፎቻቸው ከእነሱ በላይ ተዘርግተዋል። እያንዳንዳቸው እርስ በርሳቸው የሚነካኩ ሁለት ክንፎች ነበሯቸው፤ ሁለቱ ክንፎቻቸው ደግሞ ሰውነታቸውን ይሸፍኑ ነበር። |
እያንዳንዳቸው መንፈሱ ወደመራቸው አቅጣጫ ሁሉ ቀጥ ብለው ወደ ፊት ይሄዱ ነበር። በሚሄዱበት ጊዜ አይዞሩም። |
የሕያዋን ፍጥረታቱ መልክ የሚነድ የከሰል ፍም ይመስላል፤ በሕያዋን ፍጥረታቱም መካከል እየነደደ ያለ ችቦ የሚመስል ነገር ወዲያና ወዲህ ይል ነበር፤ ከእሳቱም መካከል መብረቅ ይወጣ ነበር። |
ሕያዋን ፍጥረታቱም ወዲያና ወዲህ ሲሄዱ እንቅስቃሴያቸው የመብረቅ ብልጭታ ይመስል ነበር። |
እኔም ሕያዋን ፍጥረታቱን ስመለከት አራት ፊቶች ባሉት በእያንዳንዱ ሕያው ፍጡር አጠገብ በምድር ላይ አንድ አንድ መንኮራኩር አየሁ። |
መንኮራኩሮቹ በአጠቃላይ ሲታዩ እንደ ክርስቲሎቤ የሚያብረቀርቅ መልክ ነበራቸው፤ አራቱም ይመሳሰላሉ። መልካቸውና አሠራራቸው ሲታይ በአንድ መንኮራኩር ውስጥ በጎን በኩል ሌላ መንኮራኩር የተሰካ ይመስላል። |
በሚንቀሳቀሱበት ጊዜ መዞር ሳያስፈልጋቸው በአራቱም ጎን በፈለጉበት አቅጣጫ መሄድ ይችላሉ። |
የመንኮራኩሮቹም ጠርዝ እጅግ ረጅም ከመሆኑ የተነሳ የሚያስፈራ ነበር፤ የአራቱም መንኮራኩሮች ጠርዝ ዙሪያውን በዓይኖች የተሞላ ነበር። |
ሕያዋን ፍጥረታቱ በተንቀሳቀሱ ቁጥር፣ መንኮራኩሮቹም ከእነሱ ጋር አብረው ይንቀሳቀሳሉ፤ ሕያዋን ፍጥረታቱ ከምድር ከፍ ከፍ ሲሉ መንኮራኩሮቹም ከፍ ከፍ ይላሉ። |
መንፈሱ ወደመራቸው አቅጣጫ፣ መንፈሱ ወደሚሄድበት ቦታ ሁሉ ይሄዳሉ። መንኮራኩሮቹ ከእነሱ ጋር አብረው ከፍ ከፍ ይሉ ነበር፤ በሕያዋን ፍጥረታቱ ላይ የሚሠራው መንፈስ በመንኮራኩሮቹም ውስጥ ነበርና። |
ሕያዋን ፍጥረታቱ ሲንቀሳቀሱ እነሱም ይንቀሳቀሳሉ፤ ሕያዋን ፍጥረታቱ ሲቆሙ እነሱም ይቆማሉ፤ ከምድር ከፍ ከፍ ሲሉ መንኮራኩሮቹም ከእነሱ ጋር አብረው ከፍ ከፍ ይሉ ነበር፤ በሕያዋን ፍጥረታቱ ላይ የሚሠራው መንፈስ በመንኮራኩሮቹም ውስጥ ነበርና። |
ከሕያዋን ፍጥረታቱ ራስ በላይ እጅግ አስደናቂ እንደሆነ በረዶ የሚያብረቀርቅ ጠፈር የሚመስል ነገር ነበር፤ ይህም ከራሳቸው በላይ ተዘርግቶ ነበር። |
ከጠፈሩ በታች ክንፎቻቸው አንዳቸው ወደ ሌላው ቀጥ ብለው ነበር። እያንዳንዳቸውም በዚህ ጎንና በዚያኛው ጎን ሰውነታቸውን የሚሸፍኑባቸው ሁለት ሁለት ክንፎች ነበሯቸው። |
የክንፎቻቸውን ድምፅ ስሰማ እንደሚጎርፍ ውኃ ድምፅ፣ ደግሞም ሁሉን እንደሚችል አምላክ ድምፅ ነበር። በሚንቀሳቀሱበት ጊዜ ድምፁ እንደ ሠራዊት ድምፅ ነበር። በሚቆሙበት ጊዜ ክንፎቻቸውን ወደ ታች ያደርጋሉ። |
ከራሳቸው በላይ ካለው ጠፈር በላይ አንድ ድምፅ ይሰማ ነበር። (በሚቆሙበት ጊዜ ክንፎቻቸውን ወደ ታች ያደርጉ ነበር።) |
ከራሳቸው በላይ ካለው ጠፈር በላይ የሰንፔር ድንጋይ የመሰለ እንደ ዙፋን ያለ ነገር ነበር። ከላይ በኩል ባለው በዙፋኑ ላይ መልኩ የሰው መልክ የሚመስል ተቀምጦ ነበር። |
ወገቡ ከሚመስለው ነገር ጀምሮ ወደ ላይ፣ እሳት የሚመስል እንደ ብረት የሚያብረቀርቅ ነገር ሲወጣ አየሁ፤ ደግሞም ከወገቡ ጀምሮ ወደ ታች፣ እሳት የሚመስል ነገር አየሁ። በዙሪያውም ደማቅ ብርሃን ነበር፤ |
ይህም ዝናባማ በሆነ ቀን በደመና ውስጥ እንደሚታይ ቀስተ ደመና ነበር። በዙሪያው ያለው ደማቅ ብርሃን ይህን ይመስላል። ደግሞም የይሖዋን ክብር ይመስል ነበር። እኔም ባየሁት ጊዜ በግንባሬ ተደፋሁ፤ ከዚያም አንዱ ሲናገር ድምፅ ሰማሁ። |
“አንተም የሰው ልጅ ሆይ፣ ስለ እስራኤል ተራሮች ትንቢት ተናገር፤ እንዲህም በል፦ ‘የእስራኤል ተራሮች ሆይ፣ የይሖዋን ቃል ስሙ። |
ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “ጠላት ስለ እናንተ ‘እሰይ! የጥንቶቹ ከፍ ያሉ ቦታዎች ሳይቀሩ የእኛ ርስት ሆነዋል!’ ብሏል።”’ |
“ስለዚህ ትንቢት ተናገር፤ እንዲህም በል፦ ‘ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “ከብሔራት መካከል ለተረፉት ርስት እንድትሆኑ ባድማ ስላደረጓችሁና ከየአቅጣጫው ጥቃት ስለሰነዘሩባችሁ እንዲሁም ሰው አፍ ውስጥ ስለገባችሁና ሰዎች ስማችሁን ስላጠፉ፣ |
የእስራኤል ተራሮች ሆይ፣ ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ የተናገረውን ቃል ስሙ! ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ ለተራሮችና ለኮረብቶች፣ ለጅረቶችና ለሸለቆዎች፣ ፈራርሰው ባድማ ለሆኑት ቦታዎችና በዙሪያቸው ባሉት ከጥፋት የተረፉ ብሔራት ለተበዘበዙት እንዲሁም መሳለቂያ ለሆኑት የተተዉ ከተሞች ይህን ቃል ተናግሯል፤ |
ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ እነሱን በተመለከተ እንዲህ ይላል፦ ‘የግጦሽ ቦታዎቿን ለመውሰድና ምድሪቱን ለመበዝበዝ ሲሉ በታላቅ ደስታና በከፍተኛ ንቀት ምድሬን የገዛ ርስታቸው እንደሆነ አድርገው በተናገሩት፣ ከጥፋት በተረፉት ብሔራትና በመላዋ ኤዶም ላይ በቅንዓቴ እሳት እናገራለሁ።’”’ |
“ስለዚህ ስለ እስራኤል ምድር ትንቢት ተናገር፤ ለተራሮችና ለኮረብቶች፣ ለጅረቶችና ለሸለቆዎች እንዲህ በል፦ ‘ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “እነሆ፣ ብሔራት ያደረሱባችሁን ውርደት ስለተሸከማችሁ በቅንዓቴና በቁጣዬ እናገራለሁ።”’ |
“ስለዚህ ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘በዙሪያችሁ ያሉት ብሔራት የገዛ ራሳቸውን ኀፍረት ይሸከማሉ ብዬ እጄን አንስቼ ምያለሁ። |
የእስራኤል ተራሮች ሆይ፣ እናንተ ግን ለሕዝቤ ለእስራኤል ቅርንጫፍ ታወጣላችሁ፤ ፍሬም ታፈራላችሁ፤ እነሱ በቅርቡ ይመለሳሉና። |
እኔ ከእናንተ ጋር ነኝ፤ ፊቴንም ወደ እናንተ እመልሳለሁ፤ እናንተም ትታረሳላችሁ፤ ደግሞም ዘር ይዘራባችኋል። |
ሕዝባችሁን ይኸውም መላውን የእስራኤል ቤት አበዛለሁ፤ ከተሞቹም የሰው መኖሪያ ይሆናሉ፤ የፈራረሱትም ስፍራዎች ዳግመኛ ይገነባሉ። |
አዎ፣ ሕዝባችሁንና ከብቶቻችሁን አበዛለሁ፤ እነሱም ይበዛሉ፤ ፍሬያማም ይሆናሉ። እንደቀድሞው ዘመን ሰዎች እንዲኖሩባችሁ አደርጋለሁ፤ ደግሞም ከበፊቱ የበለጠ አበለጽጋችኋለሁ፤ እናንተም እኔ ይሖዋ እንደሆንኩ ታውቃላችሁ። |
በእናንተ ላይ ሰዎች ይኸውም ሕዝቤ እስራኤል እንዲመላለሱ አደርጋለሁ፤ እነሱም ይወርሷችኋል። የእነሱ ርስት ትሆናላችሁ፤ ከእንግዲህ ልጅ አልባ አታደርጓቸውም።’” |
“ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘“ሰዎችን የምትበላና በላይዋ ያሉትን ብሔራት የወላድ መሃን የምታደርግ ምድር ናችሁ” ስለሚሏችሁ፣’ |
‘ከእንግዲህ ሰው አትበሉም ወይም በምድሪቱ ላይ ያሉትን ብሔራት ልጅ አልባ አታደርጉም’ ይላል ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ። |
‘ከእንግዲህ ብሔራት እናንተን እንዲሰድቡ ወይም ሰዎች የሚሰነዝሩባችሁን ዘለፋ እንድትሸከሙ አልፈቅድም፤ ደግሞም በምድሪቱ ላይ ላሉት ብሔራት መሰናክል አትሆኑም’ ይላል ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ።” |
የይሖዋም ቃል ዳግመኛ እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፦ |
“የሰው ልጅ ሆይ፣ የእስራኤል ቤት ሰዎች በምድራቸው ላይ ይኖሩ በነበረበት ጊዜ በመንገዳቸውና በሥራቸው ምድሪቱን አረከሷት። መንገዳቸው በፊቴ እንደ ወር አበባ ርኩሰት ነበር። |
በምድሪቱ ላይ ደም ስላፈሰሱና ምድሪቱን አስጸያፊ በሆኑ ጣዖቶቻቸው ስላረከሱ ቁጣዬን አፈሰስኩባቸው። |
ደግሞም በብሔራት መካከል በተንኳቸው፤ በየአገሩም ዘራኋቸው። እንደ መንገዳቸውና እንደ ሥራቸው ፈረድኩባቸው። |
ሆኖም ወደ እነዚህ ብሔራት በመጡ ጊዜ ሰዎች ስለ እነሱ ‘እነዚህ የይሖዋ ሕዝብ ናቸው፤ ይሁን እንጂ ከእሱ ምድር ለመፈናቀል ተገደዱ’ እያሉ ቅዱስ ስሜን አረከሱ። |
በመሆኑም የእስራኤል ቤት በሄዱባቸው ብሔራት መካከል ያረከሱት ቅዱስ ስሜ ያሳስበኛል።” |
“ስለዚህ ለእስራኤል ቤት ሰዎች እንዲህ በል፦ ‘ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “የእስራኤል ቤት ሰዎች ሆይ፣ እርምጃ የምወስደው ለእናንተ ብዬ ሳይሆን በሄዳችሁባቸው ብሔራት መካከል ላረከሳችሁት ቅዱስ ስሜ ስል ነው።”’ |
‘በብሔራት መካከል የረከሰውን፣ ይኸውም በእነሱ መካከል ያረከሳችሁትን ታላቅ ስሜን በእርግጥ እቀድሰዋለሁ፤ ዓይኖቻቸው እያዩ በመካከላችሁ በምቀደስበት ጊዜ’ ይላል ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ፣ ‘ብሔራት እኔ ይሖዋ እንደሆንኩ ያውቃሉ። |
ከብሔራት መካከል አወጣችኋለሁ፤ ከየአገሩም ሁሉ ሰብስቤ ወደ ምድራችሁ አመጣችኋለሁ። |
ንጹሕ ውኃ እረጫችኋለሁ፤ እናንተም ንጹሕ ትሆናላችሁ፤ ከርኩሰታችሁ ሁሉና አስጸያፊ ከሆኑት ጣዖቶቻችሁ ሁሉ አነጻችኋለሁ። |
አዲስ ልብ እሰጣችኋለሁ፤ በውስጣችሁም አዲስ መንፈስ አሳድራለሁ። የድንጋይ ልባችሁን ከሰውነታችሁ አስወግጄ የሥጋ ልብ እሰጣችኋለሁ። |
መንፈሴን በውስጣችሁ አኖራለሁ፤ በሥርዓቴም እንድትመላለሱ አደርጋለሁ፤ ድንጋጌዎቼንም ትጠብቃላችሁ፣ በተግባርም ታውሏቸዋላችሁ። |
በዚያን ጊዜ ለአባቶቻችሁ በሰጠኋት ምድር ላይ ትኖራላችሁ፤ ሕዝቤም ትሆናላችሁ፤ እኔም አምላካችሁ እሆናለሁ።’ |
“‘ከርኩሰታችሁ ሁሉ አድናችኋለሁ፤ እህሉን እጠራዋለሁ፤ ደግሞም አበዛዋለሁ፤ ረሃብም አላመጣባችሁም። |
በረሃብ የተነሳ በብሔራት መካከል ዳግመኛ ውርደት እንዳይደርስባችሁ፣ የዛፉን ፍሬና የእርሻውን ምርት አበዛለሁ። |
በዚያን ጊዜ ክፉ መንገዳችሁንና መጥፎ ሥራችሁን ታስታውሳላችሁ፤ በበደላችሁና በምትፈጽሟቸው አስጸያፊ ልማዶች የተነሳ ራሳችሁን ትጸየፋላችሁ። |
ይሁንና ይህን እወቁ፦ ይህን የማደርገው ለእናንተ ብዬ አይደለም’ ይላል ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ። ‘ይልቁንም የእስራኤል ቤት ሰዎች ሆይ፣ ከመንገዳችሁ የተነሳ እፈሩ፤ ደግሞም ተሸማቀቁ።’ |
“ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘ከበደላችሁ ሁሉ በማነጻችሁ ቀን ከተሞቹ የሰው መኖሪያ እንዲሆኑ፣ የፈራረሱትም ቦታዎች እንደገና እንዲገነቡ አደርጋለሁ። |
አላፊ አግዳሚው ሁሉ ጠፍ ሆኖ ሲያየው የነበረው ባድማ መሬት ይታረሳል። |
ሰዎችም እንዲህ ይላሉ፦ “ባድማ የነበረው ምድር እንደ ኤደን የአትክልት ስፍራ ሆነ፤ ፈራርሰው ባድማና ወና ሆነው የነበሩት ከተሞችም አሁን የተመሸጉ ከተሞችና የሰው መኖሪያ ሆነዋል።” |
ደግሞም ከጥፋት የተረፉት በዙሪያችሁ ያሉት ብሔራት፣ የፈረሰውን የገነባሁትና ባድማ የሆነውን ምድር ያለማሁት እኔ ይሖዋ እንደሆንኩ ያውቃሉ። እኔ ይሖዋ ተናግሬአለሁ፤ ደግሞም አድርጌዋለሁ።’ |
“ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘የእስራኤል ቤት ሰዎችም ይህን እንዳደርግላቸው እንዲጠይቁኝ እፈቅድላቸዋለሁ፦ ሕዝባቸውን እንደ መንጋ አበዛዋለሁ። |
እንደ ቅዱሳን መንጋና በበዓል ወቅት በኢየሩሳሌም ውስጥ እንደሚገኘው መንጋ፣ ፈራርሰው የነበሩት ከተሞችም በሰው መንጋ ይሞላሉ፤ እነሱም እኔ ይሖዋ እንደሆንኩ ያውቃሉ።’” |
የይሖዋ ቃል ዳግመኛ እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፦ |
“አንተ የሰው ልጅ ሆይ፣ ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ ለእስራኤል ምድር እንዲህ ይላል፦ ‘ፍጻሜ! በአራቱ የምድሪቱ ማዕዘናት ላይ ፍጻሜ መጥቷል። |
አሁን ፍጻሜሽ ደርሷል፤ ቁጣዬንም በአንቺ ላይ አወርዳለሁ፤ እንደ መንገድሽም እፈርድብሻለሁ፤ ለፈጸምሻቸውም አስጸያፊ ድርጊቶች ሁሉ ተጠያቂ አደርግሻለሁ። |
ዓይኔ አያዝንልሽም፤ ደግሞም አልራራልሽም፤ የተከተልሽው መንገድ የሚያስከትለውን ውጤት አመጣብሻለሁና፤ የፈጸምሻቸው አስጸያፊ ድርጊቶች የሚያስከትሉትን መዘዝ ትቀምሻለሽ። እናንተም እኔ ይሖዋ እንደሆንኩ ታውቃላችሁ።’ |
“ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘እነሆ ጥፋት፣ በዓይነቱ ልዩ የሆነ ጥፋት እየመጣ ነው! |
ፍጻሜ እየመጣ ነው፤ ፍጻሜው ይመጣል፤ በአንቺ ላይ ይነሳል። እነሆ፣ ፍጻሜው እየመጣ ነው! |
አንቺ በምድሪቱ የምትኖሪ፣ ተራሽ ደርሷል። ጊዜው እየደረሰ ነው፤ ቀኑ ቀርቧል። በተራሮች ላይ የእልልታ ሳይሆን የሁከት ድምፅ ይሰማል። |
“‘በቅርብ ጊዜ ውስጥ ቁጣዬን በአንቺ ላይ አወርዳለሁ፤ ንዴቴንም ሁሉ በአንቺ ላይ እወጣለሁ፤ እንደ መንገድሽም እፈርድብሻለሁ፤ ለፈጸምሻቸውም አስጸያፊ ድርጊቶች ሁሉ ተጠያቂ አደርግሻለሁ። |
ዓይኔ አያዝንም፤ ደግሞም አልራራም። የተከተልሽው መንገድ የሚያስከትለውን ውጤት አመጣብሻለሁ፤ የፈጸምሻቸው አስጸያፊ ድርጊቶች የሚያስከትሉብሽን መዘዝ ትቀምሻለሽ። እናንተም የምመታችሁ እኔ ይሖዋ እንደሆንኩ ታውቃላችሁ። |
“‘እነሆ ቀኑ! እነሆ ቀኑ እየመጣ ነው! ተራሽ ደርሷል፤ በትሩ አብቧል፤ እብሪትም አቆጥቁጧል። |
ዓመፅ አድጎ የክፋት በትር ሆኗል። እነሱም ሆኑ ሀብታቸው ደግሞም ሕዝባቸውም ሆነ ታላቅነታቸው ይጠፋል። |
ጊዜው ይደርሳል፤ ቀኑም ይመጣል። የሚገዛ አይደሰት፤ የሚሸጥም አይዘን፤ በሕዝባቸው ሁሉ ላይ ቁጣ ነዷልና። |
ሻጩ በሕይወት ቢተርፍ እንኳ ወደተሸጠው ነገር አይመለስም፤ ራእዩ በሕዝቡ ሁሉ ላይ ነውና። ማንም አይመለስም፤ ከፈጸመውም በደል የተነሳ ማንም ሕይወቱን ማትረፍ አይችልም። |
“‘መለከት ነፍተዋል፤ ሁሉም ቢዘጋጁም ወደ ውጊያ የሚሄድ አንድም ሰው የለም፤ ምክንያቱም ቁጣዬ በሕዝቡ ሁሉ ላይ ነዷል። |
በውጭ ሰይፍ፣ በውስጥ ደግሞ ቸነፈርና ረሃብ አለ። በሜዳ ያለ ሁሉ በሰይፍ ይሞታል፤ በከተማዋ ውስጥ ያሉትን ደግሞ ረሃብና ቸነፈር ይፈጃቸዋል። |
አምልጠው መትረፍ የቻሉት ሁሉ ወደ ተራሮች ይሄዳሉ፤ እያንዳንዳቸውም በሸለቆ ውስጥ እንዳሉ ርግቦች በበደላቸው ይቃትታሉ። |
እጃቸው ሁሉ ይዝላል፤ ጉልበታቸውም ሁሉ በውኃ ይርሳል። |
ማቅ ለብሰዋል፤ ብርክም ይዟቸዋል። ሁሉም ኀፍረት ይከናነባሉ፤ ራስም ሁሉ ይመለጣል። |
“‘ብራቸውን በየጎዳናው ይጥላሉ፤ ወርቃቸውም አስጸያፊ ነገር ይሆንባቸዋል። በይሖዋ የቁጣ ቀን ብራቸውም ሆነ ወርቃቸው ሊያድናቸው አይችልም። በልተው አይጠግቡም፤ ሆዳቸውንም አይሞሉም፤ በኃጢአት እንዲወድቁ እንቅፋት ሆኖባቸዋልና። |
በጌጦቻቸው ውበት ታበዩ፤ በእነዚህም ጸያፍ የሆኑ ምስሎቻቸውን ይኸውም አስጸያፊ ጣዖቶቻቸውን ሠሩ። በዚህም ምክንያት ብሩንና ወርቁን ርኩስ ነገር አደርግባቸዋለሁ። |
ባዕዳን የሆኑ ሰዎች እንዲዘርፉት፣ በምድር ላይ የሚኖሩ ክፉ ሰዎችም እንዲበዘብዙት አሳልፌ እሰጣቸዋለሁ፤ እነሱም ያረክሱታል። |
Subsets and Splits
No community queries yet
The top public SQL queries from the community will appear here once available.