text
stringlengths
4
267
አባት በልጁ፣ ልጅ በአባቱ፣ እናት በልጇ፣ ልጅ በእናቷ፣ አማት በምራቷ፣ ምራት በአማቷ ላይ በመነሳት እርስ በርስ ይከፋፈላሉ።”
ከዚያም ለሕዝቡ ደግሞ እንዲህ አለ፦ “ከምዕራብ በኩል ደመና ሲመጣ ስታዩ ወዲያውኑ ‘ዶፍ ዝናብ ሊጥል ነው’ ትላላችሁ፤ እንዳላችሁትም ይሆናል።
የደቡብ ነፋስ ሲነፍስ ስታዩ ደግሞ ‘ኃይለኛ ሙቀት ይሆናል’ ትላላችሁ፤ በእርግጥም ይሆናል።
እናንተ ግብዞች፣ የምድሩንና የሰማዩን መልክ አይታችሁ መረዳት ትችላላችሁ፤ ታዲያ ይህን የአሁኑን ዘመን መርምራችሁ መረዳት እንዴት ተሳናችሁ?
ደግሞስ ጽድቅ የሆነውን ነገር ለራሳችሁ ለምን አትፈርዱም?
ለምሳሌ ከከሳሽህ ጋር ወደ አንድ ባለሥልጣን እየሄድክ ሳለ፣ ከእሱ ጋር ያለህን ቅራኔ እዚያው በመንገድ ላይ ለመፍታት ጥረት አድርግ፤ አለዚያ ዳኛ ፊት ያቀርብሃል፤ ዳኛውም ለፍርድ ቤቱ መኮንን አሳልፎ ይሰጥሃል፤ መኮንኑ ደግሞ እስር ቤት ያስገባሃል።
እልሃለሁ፣ የመጨረሻዋን ትንሽ ሳንቲም ከፍለህ እስክትጨርስ ድረስ ከዚያ ፈጽሞ አትወጣም።”
ከዚያም ምንጊዜም ተስፋ ሳይቆርጡ የመጸለይን አስፈላጊነት በተመለከተ ለደቀ መዛሙርቱ አንድ ምሳሌ ይነግራቸው ጀመር፤
እንዲህም አላቸው፦ “በአንዲት ከተማ አምላክን የማይፈራና ሰውን የማያከብር አንድ ዳኛ ነበር።
በዚያች ከተማ አንዲት መበለት ነበረች፤ በየጊዜው ወደ እሱ እየሄደች ‘ከባላጋራዬ ጋር ለምከራከርበት ጉዳይ ፍረድልኝ’ ትለው ነበር።
ይሁንና ዳኛው ለተወሰነ ጊዜ ፈቃደኛ ሳይሆን ቀረ፤ በኋላ ግን በልቡ እንዲህ ሲል አሰበ፦ ‘ምንም እንኳ አምላክን የማልፈራ፣ ሰውንም የማላከብር ብሆን
ይህች መበለት ሁልጊዜ እየመጣች ስለምታስቸግረኝ ፍትሕ እንድታገኝ አደርጋለሁ፤ አለዚያ በየጊዜው እየመጣች ትነዘንዘኛለች።’”
ከዚያም ጌታ እንዲህ አለ፦ “ምንም እንኳ ዳኛው ዓመፀኛ ቢሆንም ምን እንዳለ ልብ በሉ!
ታዲያ አምላክ በትዕግሥት የሚይዛቸውና ቀን ከሌት ወደ እሱ የሚጮኹት ምርጦቹ ፍትሕ እንዲያገኙ አያደርግም?
እላችኋለሁ፣ በቶሎ ፍትሕ እንዲያገኙ ያደርጋል። ሆኖም የሰው ልጅ በሚመጣበት ጊዜ በምድር ላይ በእርግጥ እምነት ያገኝ ይሆን?”
በራሳቸው ጽድቅ ለሚታመኑና ሌሎችን በንቀት ዓይን ለሚመለከቱ ደግሞ የሚከተለውን ምሳሌ ተናገረ፦
“ሁለት ሰዎች ለመጸለይ ወደ ቤተ መቅደስ ሄዱ፤ አንደኛው ፈሪሳዊ፣ ሌላኛው ደግሞ ቀረጥ ሰብሳቢ ነበር።
ፈሪሳዊው ቆሞ በልቡ እንዲህ ሲል ይጸልይ ጀመር፦ ‘አምላክ ሆይ፣ እንደ ሌላው ሰው ቀማኛ፣ ዓመፀኛ፣ አመንዝራ፣ በተለይ ደግሞ እንደዚህ ቀረጥ ሰብሳቢ ስላልሆንኩ አመሰግንሃለሁ።
በሳምንት ሁለቴ እጾማለሁ፤ ከማገኘውም ነገር ሁሉ አሥራት እሰጣለሁ።’
ቀረጥ ሰብሳቢው ግን ራቅ ብሎ ቆመ፤ ወደ ሰማይ ቀና ብሎ ለማየትም እንኳ አልደፈረም፤ እንዲያውም ‘አምላክ ሆይ፣ ኃጢአተኛ ለሆንኩት ለእኔ ቸርነት አድርግልኝ’ እያለ ደረቱን ይደቃ ነበር።
እላችኋለሁ፣ ከፈሪሳዊው ይልቅ ይሄኛው ሰው ይበልጥ ጻድቅ ሆኖ ወደ ቤቱ ተመለሰ። ምክንያቱም ራሱን ከፍ የሚያደርግ ሁሉ ይዋረዳል፤ ራሱን ዝቅ የሚያደርግ ሁሉ ግን ከፍ ይደረጋል።”
ሰዎችም ኢየሱስ እጁን እንዲጭንባቸው ሕፃናትን ወደ እሱ ያመጡ ጀመር፤ ደቀ መዛሙርቱ ግን ይህን ሲያዩ ገሠጿቸው።
ይሁን እንጂ ኢየሱስ ሕፃናቱን ወደ ራሱ ጠርቶ እንዲህ አለ፦ “ልጆቹ ወደ እኔ ይምጡ፤ አትከልክሏቸው፤ የአምላክ መንግሥት እንደነዚህ ላሉት ነውና።
እውነት እላችኋለሁ፣ የአምላክን መንግሥት እንደ አንድ ትንሽ ልጅ ሆኖ የማይቀበል ሁሉ ፈጽሞ ወደዚህ መንግሥት አይገባም።”
ከአይሁዳውያን አለቆችም አንዱ “ጥሩ መምህር ሆይ፣ የዘላለም ሕይወት ለመውረስ ምን ማድረግ ይኖርብኛል?” ሲል ጠየቀው።
ኢየሱስም እንዲህ አለው፦ “ለምን ጥሩ ብለህ ትጠራኛለህ? ከአንዱ ከአምላክ በቀር ጥሩ የለም።
‘አታመንዝር፣ አትግደል፣ አትስረቅ፣ በሐሰት አትመሥክር፣ አባትህንና እናትህን አክብር’ የሚሉትን ትእዛዛት ታውቃለህ።”
ሰውየውም “እነዚህን ሁሉ ከልጅነቴ ጀምሮ ስጠብቅ ኖሬአለሁ” አለ።
ኢየሱስ ይህን ከሰማ በኋላ “አሁንም አንድ የሚቀርህ ነገር አለ፤ ያለህን ነገር ሁሉ ሸጠህ ገንዘቡን ለድሆች አከፋፍል፤ በሰማያትም ውድ ሀብት ታገኛለህ፤ ደግሞም መጥተህ ተከታዬ ሁን” አለው።
ሰውየው በጣም ሀብታም ስለነበረ ይህን ሲሰማ እጅግ አዘነ።
ኢየሱስም ሰውየውን ተመልክቶ እንዲህ አለ፦ “ገንዘብ ላላቸው ሰዎች ወደ አምላክ መንግሥት መግባት ምንኛ አስቸጋሪ ነው!
እንዲያውም ሀብታም ሰው ወደ አምላክ መንግሥት ከሚገባ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ቢሾልክ ይቀልላል።”
ይህን የሰሙ ሰዎች “ታዲያ ማን ሊድን ይችላል?” አሉ።
እሱም “በሰዎች ዘንድ የማይቻል፣ በአምላክ ዘንድ ይቻላል” አለ።
ጴጥሮስ ግን “እነሆ፣ እኛ ያለንን ነገር ትተን ተከትለንሃል” አለ።
ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ “እውነት እላችኋለሁ፣ ለአምላክ መንግሥት ሲል ቤትን ወይም ሚስትን ወይም ወንድሞችን ወይም ወላጆችን ወይም ልጆችን የተወ ሁሉ፣
አሁን በዚህ ዘመን ብዙ እጥፍ፣ በሚመጣው ሥርዓት ደግሞ የዘላለም ሕይወት ያገኛል።”
ከዚያም አሥራ ሁለቱን ገለል አድርጎ በመውሰድ እንዲህ አላቸው፦ “እነሆ! ወደ ኢየሩሳሌም እየወጣን ነው፤ የሰውን ልጅ በተመለከተም በነቢያት የተጻፉት ነገሮች ሁሉ ይፈጸማሉ።
ለምሳሌ ለአሕዛብ አሳልፈው ይሰጡታል፤ ያፌዙበታል፤ ያንገላቱታል እንዲሁም ይተፉበታል።
ከገረፉትም በኋላ ይገድሉታል፤ በሦስተኛው ቀን ግን ይነሳል።”
ይሁን እንጂ ከዚህ ሁሉ መካከል አንዱንም አልተረዱም፤ የተናገረው ቃል ተሰውሮባቸው ነበርና፤ የተባለውም ነገር አልገባቸውም።
ኢየሱስ ወደ ኢያሪኮ እየተቃረበ ሳለ አንድ ዓይነ ስውር መንገድ ዳር ተቀምጦ ይለምን ነበር።
ዓይነ ስውሩም ብዙ ሕዝብ በዚያ ሲያልፍ ሰምቶ ስለ ሁኔታው ይጠይቅ ጀመር።
ሰዎቹም “የናዝሬቱ ኢየሱስ በዚህ እያለፈ ነው!” ብለው ነገሩት።
በዚህ ጊዜ “ኢየሱስ ሆይ፣ የዳዊት ልጅ፣ ምሕረት አድርግልኝ!” ሲል ጮኸ።
ከፊት ከፊት የሚሄዱትም ሰዎች ዝም እንዲል ገሠጹት፤ እሱ ግን “የዳዊት ልጅ ሆይ፣ ምሕረት አድርግልኝ!” እያለ ይበልጥ መጮኹን ቀጠለ።
ኢየሱስም ቆመና ሰውየውን ወደ እሱ እንዲያመጡት አዘዘ። ሰውየው ወደ እሱ በቀረበ ጊዜ ኢየሱስ እንዲህ ሲል ጠየቀው፦
“ምን እንዳደርግልህ ትፈልጋለህ?” እሱም “ጌታ ሆይ፣ የዓይኔን ብርሃን መልስልኝ” አለው።
ስለዚህ ኢየሱስ “የዓይንህ ብርሃን ይመለስልህ፤ እምነትህ አድኖሃል” አለው።
ወዲያውም የዓይኑ ብርሃን ተመለሰለት፤ አምላክን እያመሰገነም ይከተለው ጀመር። ሕዝቡም ሁሉ ይህን ሲያዩ አምላክን አወደሱ።
ስለዚህ በዚያ ተሰብስበው የነበሩት ሰዎች በሙሉ ተነስተው ወደ ጲላጦስ ወሰዱት።
ከዚያም እንዲህ እያሉ ይከሱት ጀመር፦ “ይህ ሰው ሕዝባችንን ሲያሳምፅ፣ ለቄሳር ግብር እንዳይከፈል ሲከለክልና ‘እኔ ክርስቶስ ንጉሥ ነኝ’ ሲል አግኝተነዋል።”
በዚህ ጊዜ ጲላጦስ “አንተ የአይሁዳውያን ንጉሥ ነህ?” ሲል ጠየቀው። እሱም መልሶ “አንተው ራስህ እኮ እየተናገርከው ነው” አለው።
ከዚያም ጲላጦስ ለካህናት አለቆቹና ለሕዝቡ “በዚህ ሰው ላይ ምንም ወንጀል አላገኘሁበትም” አለ።
እነሱ ግን “በመላው ይሁዳ፣ ከገሊላ አንስቶ እስከዚህ ድረስ እያስተማረ ሕዝቡን ይቀሰቅሳል” በማለት አጥብቀው ተናገሩ።
ጲላጦስ ይህን ሲሰማ ሰውየው የገሊላ ሰው መሆኑን ለማረጋገጥ ጠየቀ።
ከሄሮድስ ግዛት የመጣ መሆኑን ካረጋገጠ በኋላ በዚያን ጊዜ በኢየሩሳሌም ወደነበረው ወደ ሄሮድስ ላከው።
ሄሮድስ ኢየሱስን ሲያየው በጣም ደስ አለው። ስለ እሱ ብዙ ነገር ሰምቶ ስለነበር ለረጅም ጊዜ እሱን ለማየት ይፈልግ ነበር፤ አንዳንድ ተአምራት ሲፈጽም ለማየትም ተስፋ ያደርግ ነበር።
በመሆኑም ብዙ ጥያቄ ይጠይቀው ጀመር፤ እሱ ግን ምንም መልስ አልሰጠውም።
ይሁን እንጂ የካህናት አለቆቹና ጸሐፍት በተደጋጋሚ እየተነሱ አጥብቀው ይከሱት ነበር።
ከዚያም ሄሮድስ ከወታደሮቹ ጋር ሆኖ አቃለለው፤ እንዲሁም ያማረ ልብስ አልብሶ ካፌዘበት በኋላ መልሶ ወደ ጲላጦስ ላከው።
በዚያን ዕለት ሄሮድስና ጲላጦስ ወዳጆች ሆኑ፤ ከዚያ በፊት በመካከላቸው ጠላትነት ነበር።
ከዚያም ጲላጦስ የካህናት አለቆቹን፣ ገዢዎቹንና ሕዝቡን በአንድነት ጠርቶ
እንዲህ አላቸው፦ “ይህን ሰው ወደ እኔ ያመጣችሁት ሕዝቡን ለዓመፅ ያነሳሳል ብላችሁ ነበር። ይኸው በፊታችሁ መረመርኩት፤ ሆኖም በእሱ ላይ ያቀረባችሁትን ክስ የሚደግፍ ምንም ነገር አላገኘሁም።
ሄሮድስም ቢሆን ምንም ጥፋት ስላላገኘበት ወደ እኛ መልሶ ልኮታል፤ በመሆኑም ለሞት የሚያበቃ ምንም ነገር አልፈጸመም።
ስለዚህ ቀጥቼ እፈታዋለሁ።”
ሕዝቡ ሁሉ ግን “ይህን ሰው ግደለው፤ በርባንን ግን ፍታልን!” እያሉ ጮኹ።
(ይህ ሰው በከተማው ውስጥ በተከሰተ የሕዝብ ዓመፅና በነፍስ ግድያ የታሰረ ነበር።)
ጲላጦስ ኢየሱስን ሊፈታው ስለፈለገ ድምፁን ከፍ አድርጎ እንደገና ለሕዝቡ ተናገረ።
እነሱ ግን “ይሰቀል! ይሰቀል!” እያሉ ይጮኹ ጀመር።
እሱም ለሦስተኛ ጊዜ “ለምን? ይህ ሰው ምን ያጠፋው ነገር አለ? ለሞት የሚያበቃ ምንም ነገር አላገኘሁበትም፤ ስለዚህ ቀጥቼ እፈታዋለሁ” አላቸው።
በዚህ ጊዜ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ኢየሱስ እንዲገደል አጥብቀው ወተወቱት፤ ድምፃቸውም አየለ።
ስለዚህ ጲላጦስ የጠየቁት እንዲፈጸም ውሳኔ አስተላለፈ።
ሕዝብ በማሳመፅና በነፍስ ግድያ ታስሮ የነበረውንና እንዲፈታላቸው የጠየቁትን ሰው ለቀቀው፤ ኢየሱስን ግን የፈለጉትን እንዲያደርጉበት አሳልፎ ሰጣቸው።
ይዘውትም እየሄዱ ሳሉ ከገጠር እየመጣ የነበረውን ስምዖን የተባለ አንድ የቀሬና ሰው ያዙትና የመከራውን እንጨት አሸክመው ከኢየሱስ ኋላ እንዲሄድ አደረጉት።
ብዙ ሕዝብም ይከተለው ነበር፤ ከእነሱም መካከል በሐዘን ደረታቸውን እየደቁ የሚያለቅሱለት ሴቶች ነበሩ።
ኢየሱስም ወደ ሴቶቹ ዞር ብሎ እንዲህ አለ፦ “እናንተ የኢየሩሳሌም ልጆች፣ ለእኔ አታልቅሱ። ይልቁንስ ለራሳችሁና ለልጆቻችሁ አልቅሱ፤
ሰዎች ‘መሃን የሆኑ ሴቶች፣ ያልወለዱ ማህፀኖችና ያላጠቡ ጡቶች ደስተኞች ናቸው!’ የሚሉበት ቀን ይመጣልና።
በዚያን ጊዜ ተራሮችን ‘በላያችን ውደቁ!’ ኮረብቶችንም ‘ሸሽጉን!’ ይላሉ።
ዛፉ እርጥብ ሆኖ ሳለ እንዲህ ካደረጉ በደረቀ ጊዜማ ምን ይከሰት ይሆን?”
ወንጀለኞች የሆኑ ሌሎች ሁለት ሰዎችም ከእሱ ጋር ሊገደሉ እየተወሰዱ ነበር።
የራስ ቅል ወደተባለ ቦታ በደረሱ ጊዜ ኢየሱስን በዚያ ከወንጀለኞቹ ጋር በእንጨት ላይ ቸነከሩት፤ ወንጀለኞቹም አንዱ በቀኙ ሌላው ደግሞ በግራው ተሰቅለው ነበር።
ኢየሱስም “አባት ሆይ፣ የሚያደርጉትን ስለማያውቁ ይቅር በላቸው” ይል ነበር። ከዚህ በተጨማሪ ልብሶቹን ለመከፋፈል ዕጣ ተጣጣሉ።
ሕዝቡም ቆሞ ይመለከት ነበር። የሃይማኖት መሪዎቹ ግን “ሌሎችን አዳነ፤ የተመረጠው የአምላክ ክርስቶስ እሱ ከሆነ እስቲ ራሱን ያድን” እያሉ ያፌዙበት ነበር።
ወታደሮቹ እንኳ ሳይቀሩ ወደ እሱ ቀርበው የኮመጠጠ ወይን በመስጠት አፌዙበት፤
እንዲሁም “አንተ የአይሁዳውያን ንጉሥ ከሆንክ ራስህን አድን” ይሉት ነበር።
በተጨማሪም ከበላዩ “ይህ የአይሁዳውያን ንጉሥ ነው” የሚል ጽሑፍ ነበር።
ከዚያም በዚያ ከተሰቀሉት ወንጀለኞች አንዱ “አንተ ክርስቶስ አይደለህም እንዴ? እስቲ ራስህንም እኛንም አድን!” እያለ ይዘልፈው ጀመር።
ሌላኛው ግን መልሶ እንዲህ ሲል ገሠጸው፦ “አንተ ራስህ ተመሳሳይ ፍርድ ተቀብለህ እያለ ትንሽ እንኳ አምላክን አትፈራም?
እኛስ ላደረግነው ነገር የሚገባንን ቅጣት በሙሉ እየተቀበልን ስለሆነ በእኛ ላይ የተፈጸመው ፍርድ ተገቢ ነው፤ ይህ ሰው ግን ምንም የሠራው ጥፋት የለም።”
ቀጥሎም “ኢየሱስ ሆይ፣ ወደ መንግሥትህ ስትመጣ አስበኝ” አለው።
እሱም “እውነት እልሃለሁ ዛሬ፣ ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ” አለው።
ጊዜው ስድስት ሰዓት ገደማ የነበረ ቢሆንም ምድሪቱ በሙሉ እስከ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ በጨለማ ተሸፈነች፤
ይህም የሆነው የፀሐይ ብርሃን በመጥፋቱ ነው፤ ከዚያም የቤተ መቅደሱ መጋረጃ መሃል ለመሃል ተቀደደ።
ኢየሱስም በታላቅ ድምፅ ጮኾ “አባት ሆይ፣ መንፈሴን በእጅህ አደራ እሰጣለሁ” አለ። ይህን ካለ በኋላ ሞተ።
መኮንኑም የተፈጸመውን ነገር በማየቱ “ይህ ሰው በእርግጥ ጻድቅ ነበር” በማለት ለአምላክ ክብር ይሰጥ ጀመር።
ይህን ለማየት በቦታው ተሰብስበው የነበሩ ሰዎች ሁሉ የተከሰቱትን ነገሮች ሲመለከቱ በሐዘን ደረታቸውን እየደቁ ወደ ቤታቸው ተመለሱ።
በቅርብ የሚያውቁትም ሁሉ በርቀት ቆመው ነበር። እንዲሁም ከገሊላ አንስቶ አብረውት የተጓዙት ሴቶች በዚያ ተገኝተው እነዚህን ነገሮች ይመለከቱ ነበር።
እነሆም፣ የሸንጎ አባል የሆነ ዮሴፍ የሚባል አንድ ጥሩና ጻድቅ ሰው ነበረ።
(ይህ ሰው ሴራቸውንና ድርጊታቸውን በመደገፍ ድምፅ አልሰጠም ነበር።) እሱም የአይሁዳውያን ከተማ የሆነችው የአርማትያስ ሰው ሲሆን የአምላክን መንግሥት ይጠባበቅ ነበር።