text stringlengths 4 267 |
|---|
ሴትየዋም ሳይታወቅባት መሄድ እንዳልቻለች በተረዳች ጊዜ እየተንቀጠቀጠች መጥታ በፊቱ ተደፋች፤ ከዚያም ለምን እንደነካችውና እንዴት ወዲያውኑ እንደተፈወሰች በሕዝቡ ሁሉ ፊት ተናገረች። |
እሱ ግን “ልጄ ሆይ፣ እምነትሽ አድኖሻል። በሰላም ሂጂ” አላት። |
ገና እየተናገረ ሳለ ከምኩራብ አለቃው ቤት የተላከ አንድ ሰው መጥቶ “ልጅህ ሞታለች፤ ከዚህ በኋላ መምህሩን አታስቸግረው” አለው። |
ኢየሱስ ይህን ሲሰማ “አትፍራ፤ ብቻ እመን፤ ልጅህ ትድናለች” አለው። |
ወደ ኢያኢሮስ ቤት በደረሰ ጊዜ ከጴጥሮስ፣ ከዮሐንስና ከያዕቆብ እንዲሁም ከልጅቷ አባትና እናት በስተቀር ማንም አብሮት ወደ ውስጥ እንዲገባ አልፈቀደም። |
በዚህ ጊዜ ሰዎቹ ሁሉ ለልጅቷ እያለቀሱና በሐዘን ደረታቸውን እየደቁ ነበር። ስለዚህ ኢየሱስ “በቃ አታልቅሱ፤ ልጅቷ ተኝታለች እንጂ አልሞተችም” አላቸው። |
ይህን ሲሰሙ ልጅቷ እንደሞተች ያውቁ ስለነበር በማፌዝ ይስቁበት ጀመር። |
እሱ ግን እጇን በመያዝ ድምፁን ከፍ አድርጎ “አንቺ ልጅ፣ ተነሽ!” አለ። |
የልጅቷም መንፈስ ተመለሰ፤ ወዲያውም ተነሳች፤ የምትበላውም ነገር እንዲሰጧት አዘዘ። |
ወላጆቿም የሚሆኑት ጠፋቸው፤ እሱ ግን የሆነውን ነገር ለማንም እንዳይናገሩ አዘዛቸው። |
ኢየሱስ እነዚህን ነገሮች ከተናገረ በኋላ ወደ ሰማይ ቀና ብሎ እንዲህ ሲል ጸለየ፦ “አባት ሆይ፣ ሰዓቱ ደርሷል። ልጅህ ያከብርህ ዘንድ ልጅህን አክብረው፤ |
ይህም በሥጋ ለባሽ ሁሉ ላይ ሥልጣን እንደሰጠኸው ሁሉ እሱም አንተ ለሰጠኸው ሰው ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲሰጥ ነው። |
የዘላለም ሕይወት ማግኘት እንዲችሉ ብቸኛው እውነተኛ አምላክ የሆንከውን አንተንና የላክኸውን ኢየሱስ ክርስቶስን ማወቅ አለባቸው። |
እንድሠራው የሰጠኸኝን ሥራ ፈጽሜ በምድር ላይ አከበርኩህ። |
ስለዚህ አባት ሆይ፣ ዓለም ከመመሥረቱ በፊት በጎንህ ሆኜ ክብር እንደነበረኝ ሁሉ አሁንም በጎንህ አድርገህ አክብረኝ። |
“ከዓለም ለሰጠኸኝ ሰዎች ስምህን ገልጬላቸዋለሁ። እነሱ የአንተ ነበሩ፤ አንተም ለእኔ ሰጠኸኝ፤ ደግሞም ቃልህን ጠብቀዋል። |
የሰጠኸኝ ነገር ሁሉ ከአንተ የተገኘ መሆኑን አሁን አውቀዋል፤ |
ምክንያቱም የሰጠኸኝን ቃል ሰጥቻቸዋለሁ፤ እነሱም ተቀብለውታል፤ እንዲሁም የአንተ ተወካይ ሆኜ መምጣቴን በእርግጥ አውቀዋል፤ አንተ እንደላክኸኝም አምነዋል። |
ስለ እነሱ እለምንሃለሁ፤ የምለምንህ ስለ ዓለም ሳይሆን አንተ ስለሰጠኸኝ ሰዎች ነው፤ ምክንያቱም እነሱ የአንተ ናቸው፤ |
ደግሞም የእኔ የሆነው ነገር ሁሉ የአንተ ነው፤ የአንተ የሆነውም ሁሉ የእኔ ነው፤ እኔም በእነሱ መካከል ከብሬአለሁ። |
“ከእንግዲህ እኔ በዓለም ውስጥ አልኖርም፤ እነሱ ግን በዓለም ውስጥ ናቸው፤ እኔ ወደ አንተ መምጣቴ ነው። ቅዱስ አባት ሆይ፣ እኛ አንድ እንደሆንን ሁሉ እነሱም አንድ እንዲሆኑ፣ ስለሰጠኸኝ ስለ ራስህ ስም ስትል ጠብቃቸው። |
እኔ ከእነሱ ጋር ሳለሁ፣ ስለሰጠኸኝ ስለ ራስህ ስም ስል ስጠብቃቸው ቆይቻለሁ፤ ደግሞም ጠብቄአቸዋለሁ፤ የቅዱስ መጽሐፉ ቃል ይፈጸም ዘንድ ከጥፋት ልጅ በቀር አንዳቸውም አልጠፉም። |
አሁን ግን ወደ አንተ መምጣቴ ነው፤ ደስታዬ በውስጣቸው ሙሉ እንዲሆን አሁን በዓለም ላይ እያለሁ እነዚህን ነገሮች እናገራለሁ። |
ቃልህን ሰጥቻቸዋለሁ፤ ሆኖም እኔ የዓለም ክፍል እንዳልሆንኩ ሁሉ እነሱም የዓለም ክፍል ስላልሆኑ ዓለም ጠላቸው። |
“የምለምንህ ከዓለም እንድታወጣቸው ሳይሆን ከክፉው እንድትጠብቃቸው ነው። |
እኔ የዓለም ክፍል እንዳልሆንኩ ሁሉ እነሱም የዓለም ክፍል አይደሉም። |
በእውነትህ ቀድሳቸው፤ ቃልህ እውነት ነው። |
አንተ ወደ ዓለም እንደላክኸኝ ሁሉ እኔም ወደ ዓለም ልኬአቸዋለሁ። |
እነሱም በእውነት እንዲቀደሱ እኔ ራሴም ስለ እነሱ ስል ቅድስናዬን እጠብቃለሁ። |
“የምለምንህ ስለ እነዚህ ብቻ ሳይሆን በእነሱ ቃል አማካኝነት በእኔ ለሚያምኑ ጭምር ነው፤ |
ይህን ልመና የማቀርበውም ሁሉም አንድ እንዲሆኑ ነው፤ ይኸውም ዓለም አንተ እንደላክኸኝ ያምን ዘንድ አባት ሆይ፣ አንተ ከእኔ ጋር አንድነት እንዳለህና እኔም ከአንተ ጋር አንድነት እንዳለኝ ሁሉ እነሱም ከእኛ ጋር አንድነት እንዲኖራቸው ነው። |
እኛ አንድ እንደሆንን ሁሉ እነሱም አንድ እንዲሆኑ ለእኔ የሰጠኸኝን ክብር ሰጥቻቸዋለሁ። |
እኔ ከእነሱ ጋር አንድነት አለኝ፤ አንተም ከእኔ ጋር አንድነት አለህ፤ ይህ ደግሞ እነሱም ፍጹም አንድ እንዲሆኑ ነው፤ በተጨማሪም ዓለም አንተ እንደላክኸኝ እንዲሁም እኔን እንደወደድከኝ ሁሉ እነሱንም እንደወደድካቸው ያውቅ ዘንድ ነው። |
አባት ሆይ፣ እነዚህ የሰጠኸኝ፣ እኔ ባለሁበት እነሱም ከእኔ ጋር እንዲሆኑ እፈልጋለሁ፤ ይህም ዓለም ከመመሥረቱ በፊት ስለወደድከኝ የሰጠኸኝን ክብር እንዲያዩ ነው። |
ጻድቅ አባት ሆይ፣ በእርግጥ ዓለም አላወቀህም፤ እኔ ግን አውቅሃለሁ፤ እነዚህ ደግሞ አንተ እንደላክኸኝ አውቀዋል። |
እኔን የወደድክበት ፍቅር እነሱም እንዲኖራቸው እንዲሁም እኔ ከእነሱ ጋር አንድነት እንዲኖረኝ ስምህን አሳውቄአቸዋለሁ፤ ደግሞም አሳውቃለሁ።” |
ከዚያም ጲላጦስ ኢየሱስን ወስዶ ገረፈው። |
ወታደሮቹም የእሾህ አክሊል ጎንጉነው በራሱ ላይ ደፉበት፤ እንዲሁም ሐምራዊ ልብስ አለበሱት፤ |
ወደ እሱ እየቀረቡም “የአይሁዳውያን ንጉሥ ሆይ፣ ሰላም ለአንተ ይሁን!” ይሉት ነበር። ደግሞም በጥፊ ይመቱት ነበር። |
ጲላጦስም ዳግመኛ ወደ ውጭ ወጥቶ “ምንም ጥፋት እንዳላገኘሁበት ታውቁ ዘንድ እነሆ ወደ ውጭ አወጣላችኋለሁ” አላቸው። |
በመሆኑም ኢየሱስ የእሾህ አክሊል እንደደፋና ሐምራዊ ልብስ እንደለበሰ ወደ ውጭ ወጣ። ጲላጦስም “እነሆ፣ ሰውየው!” አላቸው። |
ይሁን እንጂ የካህናት አለቆቹና የቤተ መቅደስ ጠባቂዎቹ ባዩት ጊዜ “ይሰቀል! ይሰቀል!” እያሉ ጮኹ። ጲላጦስም “እኔ ምንም ጥፋት ስላላገኘሁበት ራሳችሁ ወስዳችሁ ግደሉት” አላቸው። |
አይሁዳውያኑም “እኛ ሕግ አለን፤ ይህ ሰው ደግሞ ራሱን የአምላክ ልጅ ስላደረገ በሕጉ መሠረት መሞት አለበት” ሲሉ መለሱለት። |
ጲላጦስ ያሉትን ነገር ሲሰማ ይበልጥ ፍርሃት አደረበት፤ |
ዳግመኛም ወደ ገዢው መኖሪያ ገብቶ ኢየሱስን “ለመሆኑ ከየት ነው የመጣኸው?” አለው። ኢየሱስ ግን ምንም መልስ አልሰጠውም። |
ስለሆነም ጲላጦስ “መልስ አትሰጠኝም? ልፈታህም ሆነ ልገድልህ ሥልጣን እንዳለኝ አታውቅም?” አለው። |
ኢየሱስም “ከላይ ባይሰጥህ ኖሮ በእኔ ላይ ምንም ሥልጣን አይኖርህም ነበር። ለአንተ አሳልፎ የሰጠኝ ሰው የባሰ ኃጢአት ያለበት ለዚህ ነው” ሲል መለሰለት። |
ከዚህ የተነሳ ጲላጦስ ኢየሱስን መፍታት የሚችልበትን መንገድ ያስብ ጀመር፤ አይሁዳውያኑ ግን “ይህን ሰው ከፈታኸው አንተ የቄሳር ወዳጅ አይደለህም። ራሱን ንጉሥ የሚያደርግ ሰው ሁሉ የቄሳር ተቃዋሚ ነው” እያሉ ጮኹ። |
ጲላጦስ ይህን ከሰማ በኋላ ኢየሱስን ወደ ውጭ አውጥቶ የድንጋይ ንጣፍ በተባለ ቦታ በፍርድ ወንበር ተቀመጠ፤ ይህ ቦታ በዕብራይስጥ ጋባታ ይባላል። |
ጊዜው የፋሲካ የዝግጅት ቀን ነበር፤ ሰዓቱ ደግሞ ስድስት ሰዓት ገደማ ነበር። ጲላጦስም አይሁዳውያኑን “እነሆ፣ ንጉሣችሁ!” አላቸው። |
እነሱ ግን “አስወግደው! አስወግደው! ስቀለው!” እያሉ ጮኹ። ጲላጦስም “ንጉሣችሁን ልግደለው?” አላቸው። የካህናት አለቆቹም “ከቄሳር በቀር ሌላ ንጉሥ የለንም” ሲሉ መለሱ። |
በዚህ ጊዜ እንጨት ላይ እንዲሰቀል አሳልፎ ሰጣቸው። እነሱም ኢየሱስን ይዘው ወሰዱት። |
ኢየሱስም የመከራውን እንጨት ራሱ ተሸክሞ የራስ ቅል ቦታ ወደተባለ ስፍራ ወጣ፤ ይህ ቦታ በዕብራይስጥ ጎልጎታ ይባላል። |
በዚያም በእንጨት ላይ ቸነከሩት፤ ከእሱም ጋር ሁለት ሰዎችን የሰቀሉ ሲሆን ኢየሱስን በመካከል አድርገው አንዱን በዚህ ሌላውን በዚያ ጎን ሰቀሉ። |
በተጨማሪም ጲላጦስ ጽሑፍ ጽፎ በመከራው እንጨት ላይ አንጠለጠለው። ጽሑፉም “የአይሁዳውያን ንጉሥ፣ የናዝሬቱ ኢየሱስ” የሚል ነበር። |
ኢየሱስ በእንጨት ላይ የተቸነከረበት ቦታ በከተማዋ አቅራቢያ የሚገኝ በመሆኑ ብዙ አይሁዳውያን ይህን ጽሑፍ አነበቡት፤ ጽሑፉም የተጻፈው በዕብራይስጥ፣ በላቲንና በግሪክኛ ነበር። |
ይሁን እንጂ የአይሁድ የካህናት አለቆች ጲላጦስን “እሱ ‘የአይሁዳውያን ንጉሥ ነኝ’ እንዳለ ጻፍ እንጂ ‘የአይሁዳውያን ንጉሥ’ ብለህ አትጻፍ” አሉት። |
ጲላጦስም “እንግዲህ የጻፍኩትን ጽፌአለሁ” ሲል መለሰ። |
ወታደሮቹ ኢየሱስን በእንጨት ላይ ከቸነከሩት በኋላ መደረቢያዎቹን ወስደው እያንዳንዱ ወታደር አንድ አንድ ቁራጭ እንዲደርሰው አራት ቦታ ቆራረጧቸው፤ ከውስጥ ለብሶት የነበረውንም ልብስ ወሰዱ። ሆኖም ልብሱ ከላይ እስከ ታች አንድ ወጥ ሆኖ ያለስፌት የተሠራ ነበር። |
ስለዚህ እርስ በርሳቸው “ከምንቀደው ዕጣ ተጣጥለን ለማን እንደሚደርስ እንወስን” ተባባሉ። ይህም የሆነው “መደረቢያዎቼን እርስ በርሳቸው ተከፋፈሉ፤ በልብሴም ላይ ዕጣ ተጣጣሉ” የሚለው የቅዱስ መጽሐፉ ቃል ይፈጸም ዘንድ ነው። ወታደሮቹም ያደረጉት ይህንኑ ነበር። |
ይሁንና ኢየሱስ በተሰቀለበት የመከራ እንጨት አጠገብ እናቱ፣ የእናቱ እህት፣ የቀልዮጳ ሚስት ማርያምና መግደላዊቷ ማርያም ቆመው ነበር። |
ስለዚህ ኢየሱስ እናቱንና የሚወደውን ደቀ መዝሙር በአቅራቢያው ቆመው ሲያያቸው እናቱን “ልጅሽ ይኸውልሽ!” አላት። |
ከዚያም ደቀ መዝሙሩን “እናትህ ይህችውልህ!” አለው። ደቀ መዝሙሩም ከዚያ ሰዓት አንስቶ ወደ ራሱ ቤት ወሰዳት። |
ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ሁሉም ነገር እንደተፈጸመ አውቆ የቅዱስ መጽሐፉ ቃል እንዲፈጸም “ተጠማሁ” አለ። |
በዚያም የኮመጠጠ ወይን ጠጅ የሞላበት ዕቃ ተቀምጦ ነበር። በመሆኑም ወይን ጠጁ ውስጥ የተነከረ ሰፍነግ፣ በሂሶጵ አገዳ ላይ አድርገው ወደ አፉ አቀረቡለት። |
ኢየሱስ የኮመጠጠውን ወይን ጠጅ ከቀመሰ በኋላ “ተፈጸመ!” አለ፤ ራሱንም ዘንበል አድርጎ መንፈሱን ሰጠ። |
ዕለቱ የዝግጅት ቀን ስለነበር አይሁዳውያን በሰንበት (ያ ሰንበት ታላቅ ሰንበት ስለነበር) አስከሬኖቹ በመከራ እንጨቶቹ ላይ ተሰቅለው እንዳይቆዩ ሲሉ እግራቸው ተሰብሮ እንዲወርዱ ጲላጦስን ጠየቁት። |
ስለዚህ ወታደሮቹ መጥተው ከእሱ ጋር የተሰቀሉትን የመጀመሪያውን ሰውና የሌላኛውን ሰው እግሮች ሰበሩ። |
ወደ ኢየሱስ በመጡ ጊዜ ግን ቀደም ብሎ መሞቱን ስላዩ እግሮቹን አልሰበሩም። |
ሆኖም ከወታደሮቹ አንዱ ጎኑን በጦር ወጋው፤ ወዲያውም ደምና ውኃ ፈሰሰ። |
ይህን ያየው ሰውም ምሥክርነት ሰጥቷል፤ ምሥክርነቱም እውነት ነው፤ እናንተም እንድታምኑ ይህ ሰው የሚናገራቸው ነገሮች እውነት እንደሆኑ ያውቃል። |
ይህም የሆነው “ከእሱ አንድ አጥንት እንኳ አይሰበርም” የሚለው የቅዱስ መጽሐፉ ቃል እንዲፈጸም ነው። |
ደግሞም ሌላ የቅዱስ መጽሐፉ ቃል “የወጉትን ያዩታል” ይላል። |
ይህ ከሆነ በኋላ፣ የአርማትያሱ ዮሴፍ የኢየሱስን አስከሬን ለመውሰድ ጲላጦስን ጠየቀ፤ ዮሴፍ የኢየሱስ ደቀ መዝሙር ነበር። ሆኖም አይሁዳውያንን ይፈራ ስለነበር ይህን ለማንም አልተናገረም። ጲላጦስ ከፈቀደለት በኋላ መጥቶ የኢየሱስን አስከሬን ወሰደ። |
ቀደም ሲል በማታ ወደ ኢየሱስ መጥቶ የነበረው ኒቆዲሞስም 30 ኪሎ ግራም ገደማ የሚሆን የከርቤና የእሬት ድብልቅ ይዞ መጣ። |
የኢየሱስንም አስከሬን ወስደው በአይሁዳውያን የአገናነዝ ልማድ መሠረት ጥሩ መዓዛ ባላቸው በእነዚህ ቅመሞች ተጠቅመው በበፍታ ጨርቅ ገነዙት። |
እሱ በተገደለበት ቦታ አቅራቢያ አንድ የአትክልት ስፍራ ነበር፤ በአትክልት ስፍራው ውስጥ ደግሞ ገና ማንም ያልተቀበረበት አዲስ መቃብር ነበር። |
ዕለቱ አይሁዳውያን ለበዓሉ የሚዘጋጁበት ቀን ስለነበርና መቃብሩም በአቅራቢያው ይገኝ ስለነበር ኢየሱስን በዚያ አኖሩት። |
ማርያምና እህቷ ማርታ በሚኖሩበት መንደር በቢታንያ አልዓዛር የተባለ ሰው ታሞ ነበር። |
ማርያም በጌታ ላይ ጥሩ መዓዛ ያለው ዘይት ያፈሰሰችውና በፀጉሯ እግሩን ያበሰችው ሴት ስትሆን የታመመውም፣ ወንድሟ አልዓዛር ነበር። |
ስለዚህ እህቶቹ “ጌታ ሆይ፣ የምትወደው ሰው ታሟል” ሲሉ መልእክት ላኩበት። |
ኢየሱስ ግን ይህን በሰማ ጊዜ “ይህ ሕመም ለአምላክ ክብር የሚያመጣ ነው እንጂ በሞት የሚያበቃ አይደለም፤ ይህም የአምላክ ልጅ በዚህ አማካኝነት ክብር ይጎናጸፍ ዘንድ ነው” አለ። |
ኢየሱስ ማርታንና እህቷን እንዲሁም አልዓዛርን ይወዳቸው ነበር። |
ይሁን እንጂ አልዓዛር መታመሙን ከሰማ በኋላ በዚያው በነበረበት ቦታ ሁለት ቀን ቆየ። |
ከዚያም ደቀ መዛሙርቱን “ተመልሰን ወደ ይሁዳ እንሂድ” አላቸው። |
ደቀ መዛሙርቱ ግን “ረቢ፣ በቅርቡ እኮ የይሁዳ ሰዎች በድንጋይ ሊወግሩህ ፈልገው ነበር፤ ታዲያ ወደዚያ ተመልሰህ ልትሄድ ነው?” አሉት። |
ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “በቀን ውስጥ ብርሃን የሚሆንበት 12 ሰዓት አለ አይደል? ማንም ሰው በቀን ብርሃን የሚሄድ ከሆነ የዚህን ዓለም ብርሃን ስለሚያይ ምንም ነገር አያደናቅፈውም። |
ሆኖም በሌሊት የሚሄድ ሰው በእሱ ዘንድ ብርሃን ስለሌለ ይደናቀፋል።” |
ይህን ከነገራቸው በኋላም “ወዳጃችን አልዓዛር ተኝቷል፤ እኔም ልቀሰቅሰው ወደዚያ እሄዳለሁ” አላቸው። |
በዚህ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ “ጌታ ሆይ፣ ተኝቶ ከሆነ ይሻለዋል” አሉት። |
ይሁንና ኢየሱስ የተናገረው ስለመሞቱ ነበር። እነሱ ግን ለማረፍ ብሎ እንቅልፍ ስለመተኛቱ የተናገረ መሰላቸው። |
በዚህ ጊዜ ኢየሱስ በግልጽ እንዲህ አላቸው፦ “አልዓዛር ሞቷል፤ |
ታምኑ ዘንድ በዚያ ባለመኖሬ ስለ እናንተ ደስ ይለኛል። ያም ሆነ ይህ ወደ እሱ እንሂድ።” |
በዚህ ጊዜ ዲዲሞስ የሚባለው ቶማስ ለተቀሩት ደቀ መዛሙርት “ከእሱ ጋር እንድንሞት አብረነው እንሂድ” አላቸው። |
ኢየሱስ እዚያ በደረሰ ጊዜ አልዓዛር በመቃብር ውስጥ አራት ቀን እንደሆነው አወቀ። |
ቢታንያ ለኢየሩሳሌም ቅርብ የነበረች ሲሆን ሦስት ኪሎ ሜትር ያህል ርቀት ላይ ትገኝ ነበር። |
ወንድማቸውን በሞት ያጡትን ማርታንና ማርያምን ለማጽናናት ብዙ አይሁዳውያን መጥተው ነበር። |
ማርታ፣ ኢየሱስ እየመጣ መሆኑን ስትሰማ ልትቀበለው ወጣች፤ ማርያም ግን እዚያው ቤት ቀረች። |
ማርታም ኢየሱስን እንዲህ አለችው፦ “ጌታ ሆይ፣ አንተ እዚህ ብትሆን ኖሮ ወንድሜ ባልሞተ ነበር። |
አሁንም ቢሆን አምላክ የጠየቅከውን ነገር ሁሉ እንደሚሰጥህ አምናለሁ።” |
Subsets and Splits
No community queries yet
The top public SQL queries from the community will appear here once available.