text
stringlengths
4
267
ይህም ሰው ጲላጦስ ፊት ቀርቦ የኢየሱስ አስከሬን እንዲሰጠው ጠየቀ።
አስከሬኑንም አውርዶ በበፍታ ገነዘው፤ ከዚያም ማንም ሰው ተቀብሮበት በማያውቅ ከዓለት ተፈልፍሎ በተሠራ መቃብር ውስጥ አኖረው።
ዕለቱ የዝግጅት ቀን ነበር፤ ሰንበት የሚጀምርበት ጊዜም ተቃርቦ ነበር።
ከገሊላ ከኢየሱስ ጋር አብረው የመጡት ሴቶች ግን ተከትለው በመሄድ መቃብሩን አዩ፤ አስከሬኑም እንዴት እንዳረፈ ተመለከቱ።
ጥሩ መዓዛ ያላቸው ቅመሞችና ዘይቶች ለማዘጋጀትም ተመልሰው ሄዱ። ሆኖም ሕጉ በሚያዘው መሠረት በሰንበት አረፉ።
በአንድ የሰንበት ቀን ኢየሱስ በእህል እርሻ መካከል እያለፈ ሳለ ደቀ መዛሙርቱ እሸት ቀጥፈው በእጃቸው እያሹ ይበሉ ነበር።
በዚህ ጊዜ አንዳንድ ፈሪሳውያን “በሰንበት ቀን በሕግ የተከለከለ ነገር የምታደርጉት ለምንድን ነው?” አሏቸው።
ኢየሱስ ግን መልሶ እንዲህ አላቸው፦ “ዳዊት እሱና ከእሱ ጋር የነበሩት ሰዎች በተራቡ ጊዜ ያደረገውን ነገር ፈጽሞ አላነበባችሁም?
ወደ አምላክ ቤት ገብቶ ከካህናት በስተቀር ማንም እንዲበላው ያልተፈቀደውን በአምላክ ፊት የቀረበ ኅብስት ተቀብሎ እንደበላና ከእሱ ጋር ለነበሩት እንደሰጣቸው አላነበባችሁም?”
ከዚያም “የሰው ልጅ የሰንበት ጌታ ነው” አላቸው።
በሌላ የሰንበት ቀን ወደ ምኩራብ ገብቶ ያስተምር ጀመር። በዚያም ቀኝ እጁ የሰለለ አንድ ሰው ነበር።
ጸሐፍትና ፈሪሳውያንም ኢየሱስን የሚከሱበት ምክንያት ማግኘት ይፈልጉ ስለነበር በሰንበት ይፈውስ እንደሆነ ለማየት በትኩረት ይከታተሉት ነበር።
እሱ ግን ሐሳባቸውን አውቆ ስለነበር እጁ የሰለለበትን ሰው “ተነሳና መሃል ላይ ቁም” አለው። ሰውየውም ተነስቶ በዚያ ቆመ።
ከዚያም ኢየሱስ “እስቲ አንድ ነገር ልጠይቃችሁ፤ በሰንበት ቀን የተፈቀደው መልካም ማድረግ ነው ወይስ ክፉ? ሕይወት ማዳን ነው ወይስ ማጥፋት?” አላቸው።
በዙሪያው ያሉትን ሁሉ ከተመለከተ በኋላ ሰውየውን “እጅህን ዘርጋ” አለው። ሰውየውም እንደተባለው አደረገ፤ እጁም ዳነለት።
እነሱ ግን እጅግ ተቆጡ፤ በኢየሱስ ላይ ምን ሊያደርጉ እንደሚችሉም እርስ በርሳቸው ይነጋገሩ ጀመር።
በዚያው ሰሞን ኢየሱስ ሊጸልይ ወደ ተራራ ወጣ፤ ሌሊቱንም ሙሉ ወደ አምላክ ሲጸልይ አደረ።
በነጋ ጊዜም ደቀ መዛሙርቱን ወደ እሱ ጠርቶ ከመካከላቸው 12 ሰዎች መረጠ፤ ሐዋርያት ብሎም ሰየማቸው፤ እነሱም የሚከተሉት ናቸው፦
ጴጥሮስ ብሎ የሰየመው ስምዖን፣ ወንድሙ እንድርያስ፣ ያዕቆብ፣ ዮሐንስ፣ ፊልጶስ፣ በርቶሎሜዎስ፣
ማቴዎስ፣ ቶማስ፣ የእልፍዮስ ልጅ ያዕቆብ፣ “ቀናተኛው” የሚባለው ስምዖን፣
የያዕቆብ ልጅ ይሁዳና በኋላ ከሃዲ የሆነው የአስቆሮቱ ይሁዳ።
ከእነሱም ጋር ከተራራው ወርዶ ደልዳላ ቦታ ላይ ቆመ፤ ደቀ መዛሙርቱ የሆኑ እጅግ ብዙ ሰዎችም በዚያ ነበሩ፤ በተጨማሪም እሱን ለመስማትና ከበሽታቸው ለመፈወስ ከይሁዳ ሁሉና ከኢየሩሳሌም እንዲሁም በባሕር ጠረፍ አካባቢ ከሚገኙት ከጢሮስና ከሲዶና የመጡ በጣም ብዙ ሰዎች ነበሩ።
በርኩሳን መናፍስት ይሠቃዩ የነበሩ ሰዎችም እንኳ ተፈወሱ።
ኃይል ከእሱ እየወጣ ሁሉንም ይፈውስ ስለነበር ሕዝቡ ሁሉ ሊነካው ይፈልግ ነበር።
ኢየሱስ ወደ ደቀ መዛሙርቱ ቀና ብሎ በመመልከት እንዲህ ይል ጀመር፦ “እናንተ ድሆች የሆናችሁ ደስተኞች ናችሁ፤ የአምላክ መንግሥት የእናንተ ነውና።
“እናንተ አሁን የምትራቡ ደስተኞች ናችሁ፤ ኋላ ትጠግባላችሁና። “እናንተ አሁን የምታለቅሱ ደስተኞች ናችሁ፤ ኋላ ትስቃላችሁና።
“ሰዎች፣ በሰው ልጅ ምክንያት በሚጠሏችሁ፣ በሚያገሏችሁ፣ በሚነቅፏችሁና ክፉ እንደሆናችሁ አድርገው ያለስማችሁ ስም በሚሰጧችሁ ጊዜ ሁሉ ደስተኞች ናችሁ።
በሰማይ ታላቅ ሽልማት ስለሚጠብቃችሁ በዚያን ቀን ሐሴት አድርጉ፤ በደስታም ፈንጥዙ፤ አባቶቻቸው በነቢያት ላይ እንዲሁ ያደርጉ ነበርና።
“ነገር ግን እናንተ ሀብታሞች ወዮላችሁ፤ መጽናኛችሁን በሙሉ አግኝታችኋልና።
“እናንተ አሁን የጠገባችሁ ወዮላችሁ፤ ኋላ ትራባላችሁና። “እናንተ አሁን የምትስቁ ወዮላችሁ፤ ኋላ ታዝናላችሁና፤ እንዲሁም ታለቅሳላችሁ።
“ሰዎች ስለ እናንተ መልካም ነገር በሚናገሩበት ጊዜ ሁሉ ወዮላችሁ፤ አባቶቻቸው ለሐሰተኛ ነቢያት እንዲህ ያለ ነገር አድርገው ነበርና።
“ለእናንተ ለምትሰሙ ግን እላችኋለሁ፦ ጠላቶቻችሁን ውደዱ፤ ለሚጠሏችሁ መልካም አድርጉ፤
የሚረግሟችሁን መርቁ፤ እንዲሁም ለሚሰድቧችሁ ጸልዩ።
አንዱን ጉንጭህን ለሚመታህ ሌላውን ስጠው፤ መደረቢያህን ለሚወስድብህ እጀ ጠባብህንም አትከልክለው።
ለሚለምንህ ሁሉ ስጥ፤ ንብረትህን የሚወስድብህንም ሰው እንዲመልስ አትጠይቀው።
“በተጨማሪም ልክ ሰዎች እንዲያደርጉላችሁ እንደምትፈልጉት ሁሉ እናንተም እንዲሁ አድርጉላቸው።
“የሚወዷችሁን ብቻ ብትወዱ ምን የሚያስመሰግን ነገር አለው? ኃጢአተኞችም እንኳ የሚወዷቸውን ይወዳሉና።
መልካም ለሚያደርጉላችሁ መልካም ብታደርጉስ ምን ዋጋ አለው? ኃጢአተኞችም እንኳ እንዲሁ ያደርጋሉ።
እንዲሁም ይመልስልኛል ብላችሁ ለምታስቡት ሰው ብታበድሩ ምን ፋይዳ አለው? ኃጢአተኞችም እንኳ የሰጡትን ያህል መልሰው ለመቀበል ለኃጢአተኞች ያበድራሉ።
ከዚህ ይልቅ ጠላቶቻችሁን ውደዱ፤ መልካም አድርጉ፤ ደግሞም በምላሹ ምንም ሳትጠብቁ አበድሩ፤ ሽልማታችሁም ታላቅ ይሆናል፤ ደግሞም የልዑሉ አምላክ ልጆች ትሆናላችሁ፤ እሱ ለማያመሰግኑና ለክፉዎች ደግ ነውና።
አባታችሁ መሐሪ እንደሆነ ሁሉ እናንተም መሐሪዎች ሁኑ።
“በተጨማሪም በሌሎች ላይ አትፍረዱ፤ በእናንተም ላይ ፈጽሞ አይፈረድባችሁም፤ ሌሎችን አትኮንኑ፤ እናንተም ፈጽሞ አትኮነኑም። ምንጊዜም ሌሎችን ይቅር በሉ፤ እናንተም ይቅር ትባላላችሁ።
ለሰዎች ስጡ፤ እነሱም ይሰጧችኋል። ተትረፍርፎ እስኪፈስ ድረስ በተጠቀጠቀና በተነቀነቀ ጥሩ መስፈሪያ ሰፍረው በእቅፋችሁ ይሰጧችኋል። በምትሰፍሩበት መስፈሪያ መልሰው ይሰፍሩላችኋልና።”
ከዚያም እንዲህ ሲል አንድ ምሳሌ ነገራቸው፦ “ዕውር ዕውርን ሊመራ ይችላል? ሁለቱም ተያይዘው ጉድጓድ ውስጥ አይወድቁም?
ተማሪ ከአስተማሪው አይበልጥም፤ በሚገባ የተማረ ሁሉ ግን እንደ አስተማሪው ይሆናል።
ታዲያ በራስህ ዓይን ውስጥ ያለውን ግንድ ሳታይ በወንድምህ ዓይን ውስጥ ያለውን ጉድፍ ለምን ታያለህ?
በራስህ ዓይን ውስጥ ያለውን ግንድ ሳታይ ወንድምህን ‘ዓይንህ ውስጥ ያለውን ጉድፍ ላውጣልህ’ እንዴት ትለዋለህ? አንተ ግብዝ! መጀመሪያ በራስህ ዓይን ውስጥ ያለውን ግንድ አውጣ፤ ከዚያም በወንድምህ ዓይን ውስጥ ያለውን ጉድፍ ለማውጣት አጥርተህ ማየት ትችላለህ።
“መልካም ዛፍ ሆኖ ሳለ የበሰበሰ ፍሬ የሚያፈራ ዛፍ የለም፤ እንዲሁም የበሰበሰ ዛፍ ሆኖ መልካም ፍሬ የሚያፈራ ዛፍ የለም።
እያንዳንዱ ዛፍ በፍሬው ይታወቃል። ለምሳሌ ሰዎች ከእሾህ በለስ አይለቅሙም፤ ወይም ከእሾሃማ ቁጥቋጦ ወይን አይቆርጡም።
ጥሩ ሰው በልቡ ካከማቸው መልካም ነገር ጥሩ ነገር ያወጣል፤ ክፉ ሰው ግን ካከማቸው መጥፎ ነገር ክፉ ነገር ያወጣል፤ አንደበቱ የሚናገረው በልቡ ውስጥ የሞላውን ነውና።
“ታዲያ ‘ጌታ ሆይ! ጌታ ሆይ!’ የምትሉኝ፣ የምለውን ግን የማታደርጉት ለምንድን ነው?
ወደ እኔ የሚመጣ፣ ቃሌን የሚሰማና የሚያደርግ ሁሉ ከማን ጋር እንደሚመሳሰል ልንገራችሁ፦
ቤት ለመሥራት በጥልቀት ቆፍሮ በዓለት ላይ መሠረቱን ከጣለ ሰው ጋር ይመሳሰላል። በኋላም ጎርፍ በመጣ ጊዜ ወንዙ ቤቱን በኃይል መታው፤ ሆኖም ቤቱ በደንብ ስለተገነባ ሊያነቃንቀው አልቻለም።
በሌላ በኩል ደግሞ ቃሌን ሰምቶ የማይፈጽም ሰው ሁሉ መሠረት ሳይጥል፣ በአፈር ላይ ቤት ከሠራ ሰው ጋር ይመሳሰላል። ወንዙም ቤቱን በኃይል መታው፤ ወዲያውም ተደረመሰ፤ እንዳልነበረም ሆነ።”
ከዚያ በኋላ ብዙም ሳይቆይ የአምላክን መንግሥት ምሥራች እየሰበከና እያወጀ ከከተማ ወደ ከተማ እንዲሁም ከመንደር ወደ መንደር ተጓዘ። አሥራ ሁለቱም ከእሱ ጋር ነበሩ፤
በተጨማሪም ከክፉ መናፍስትና ከበሽታ የተፈወሱ አንዳንድ ሴቶች አብረውት ነበሩ፦ ሰባት አጋንንት የወጡላት መግደላዊት የተባለችው ማርያም፣
የሄሮድስ ቤት አዛዥ የኩዛ ሚስት ዮሐና፣ ሶስና እንዲሁም ሌሎች ብዙ ሴቶች የነበሩ ሲሆን በንብረታቸው ያገለግሏቸው ነበር።
ኢየሱስም የየከተማው ሕዝብ ተከትሎት በመጣ ጊዜና እጅግ ብዙ ሰዎች በተሰበሰቡበት ወቅት እንዲህ ሲል በምሳሌ ተናገረ፦
“አንድ ዘሪ ዘሩን ሊዘራ ወጣ። በሚዘራበት ጊዜ አንዳንዶቹ ዘሮች መንገድ ዳር ወድቀው ተረጋገጡ፤ የሰማይ ወፎችም መጥተው ለቀሟቸው።
አንዳንዶቹ ዓለት ላይ ወደቁ፤ ከበቀሉም በኋላ እርጥበት ስላላገኙ ደረቁ።
ሌሎቹ ደግሞ በእሾህ መካከል ወደቁ፤ አብሯቸው ያደገውም እሾህ አነቃቸው።
ሌሎቹ ግን ጥሩ አፈር ላይ ወደቁ፤ ከበቀሉም በኋላ 100 እጥፍ አፈሩ።” ይህን ከተናገረ በኋላ ድምፁን ከፍ አድርጎ “የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ” አለ።
ደቀ መዛሙርቱ ግን የዚህን ምሳሌ ትርጉም ጠየቁት።
እሱም እንዲህ አለ፦ “ለእናንተ የአምላክን መንግሥት ቅዱስ ሚስጥሮች የመረዳት ችሎታ ተሰጥቷችኋል፤ ለቀሩት ግን በምሳሌ እነግራቸዋለሁ፤ ይኸውም እያዩ እንዳያስተውሉ እንዲሁም እየሰሙ ትርጉሙን እንዳይረዱ ነው።
እንግዲህ የምሳሌው ትርጉም ይህ ነው፦ ዘሩ የአምላክ ቃል ነው።
በመንገድ ዳር የወደቁት ቃሉን የሰሙ ናቸው፤ ከዚያ በኋላ ግን አምነው እንዳይድኑ ዲያብሎስ መጥቶ ቃሉን ከልባቸው ይወስዳል።
በዓለት ላይ የወደቁት ቃሉን ሲሰሙ በደስታ የሚቀበሉ ናቸው፤ ነገር ግን ሥር የላቸውም። ለጊዜው አምነው ቢቀበሉም በፈተና ወቅት ይወድቃሉ።
በእሾህ መካከል የወደቁት ቃሉን የሰሙ ናቸው፤ ሆኖም በዚህ ዓለም የኑሮ ጭንቀት፣ ሀብትና ሥጋዊ ደስታ ትኩረታቸው ተከፋፍሎ ሙሉ በሙሉ ይታነቃሉ፤ ለፍሬም አይበቁም።
በጥሩ አፈር ላይ የወደቁት ደግሞ ቃሉን በመልካምና በጥሩ ልብ ሰምተው በውስጣቸው በማኖር በጽናት ፍሬ የሚያፈሩ ናቸው።
“መብራት አብርቶ ዕቃ የሚከድንበት ወይም አልጋ ሥር የሚያስቀምጥ ሰው የለም፤ ከዚህ ይልቅ ወደ ቤት የሚገቡ ሁሉ ብርሃን እንዲያገኙ በመቅረዝ ላይ ያስቀምጠዋል።
በመሆኑም ተሸሽጎ የማይገለጥ፣ በሚገባ ቢሰወርም የማይታወቅና ይፋ የማይወጣ ነገር የለም።
ስለዚህ እንዴት እንደምታዳምጡ በጥሞና አስቡ፤ ላለው ተጨማሪ ይሰጠዋልና፤ የሌለው ግን እንዳለው አድርጎ የሚያስበው ነገር እንኳ ይወሰድበታል።”
ከዚህ በኋላ እናቱና ወንድሞቹ እሱ ወዳለበት መጡ፤ ሆኖም ከሕዝቡ ብዛት የተነሳ ወደ እሱ ሊቀርቡ አልቻሉም።
ስለዚህ “እናትህና ወንድሞችህ ሊያገኙህ ፈልገው ውጭ ቆመዋል” ተብሎ ተነገረው።
እሱም መልሶ “እናቴና ወንድሞቼ የአምላክን ቃል ሰምተው የሚያደርጉት እነዚህ ናቸው” አላቸው።
አንድ ቀን ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ጀልባ ከተሳፈረ በኋላ “ወደ ሐይቁ ማዶ እንሻገር” አላቸው። በመሆኑም ጉዞ ጀመሩ።
እየተጓዙም ሳሉ ኢየሱስ እንቅልፍ ወሰደው። በዚህ ጊዜ ኃይለኛ አውሎ ነፋስ በሐይቁ ላይ ተነሳ፤ ጀልባቸውም በውኃ መሞላት ስለጀመረች አደጋ ላይ ወደቁ።
ስለዚህ ሄደው ቀሰቀሱትና “መምህር፣ መምህር ማለቃችን እኮ ነው!” አሉት። እሱም ከእንቅልፉ ነቅቶ ነፋሱንና የሚናወጠውን ውኃ ገሠጸ፤ በዚህ ጊዜ ነፋሱ ቆመ፤ ጸጥታም ሰፈነ።
ከዚያም “እምነታችሁ የት አለ?” አላቸው። እነሱ ግን በፍርሃት ተውጠውና በጣም ተደንቀው እርስ በርሳቸው “ለመሆኑ ይህ ማን ነው? ነፋስና ውኃ እንኳ ይታዘዙለታል” ተባባሉ።
ከዚያም በገሊላ ማዶ ወደሚገኘው ጌርጌሴኖን ወደተባለው ክልል የባሕር ዳርቻ ደረሱ።
ኢየሱስ ከጀልባዋ ወደ የብስ በወረደ ጊዜ አጋንንት ያደሩበት በአቅራቢያው በሚገኝ ከተማ የሚኖር አንድ ሰው አገኘው። ይህ ሰው ልብስ መልበስ ከተወ ብዙ ጊዜ ሆኖት ነበር፤ የሚኖረውም በቤት ውስጥ ሳይሆን በመቃብር ስፍራ ነበር።
ኢየሱስንም ባየው ጊዜ እየጮኸ በፊቱ ተደፋ፤ በታላቅ ድምፅም “የልዑል አምላክ ልጅ ኢየሱስ ሆይ፣ እኔ ከአንተ ጋር ምን ጉዳይ አለኝ? እንዳታሠቃየኝ እለምንሃለሁ” አለ።
(ይህን ያለውም ኢየሱስ ርኩሱ መንፈስ ከሰውየው እንዲወጣ እያዘዘው ስለነበረ ነው። ርኩሱ መንፈስ ሰውየውን ብዙ ጊዜ ይይዘው ነበር፤ ሰውየው በተደጋጋሚ በሰንሰለትና በእግር ብረት እየታሰረ ይጠበቅ የነበረ ቢሆንም የታሰረበትን ሰንሰለት ይበጣጥስ ነበር፤ ጋኔኑም ጭር ወዳሉ ቦታዎች ይነዳው ነበር።)
ኢየሱስ “ስምህ ማን ነው?” ሲል ጠየቀው። እሱም ብዙ አጋንንት ገብተውበት ስለነበር “ሌጌዎን” አለው።
አጋንንቱም ወደ ጥልቁ እንዲሄዱ እንዳያዛቸው ተማጸኑት።
በዚያም በተራራው ላይ ብዛት ያለው የአሳማ መንጋ ተሰማርቶ ነበር፤ ስለዚህ ወደ አሳማዎቹ ይገቡ ዘንድ እንዲፈቅድላቸው ተማጸኑት፤ እሱም ፈቀደላቸው።
በዚህ ጊዜ አጋንንቱ ከሰውየው ወጥተው አሳማዎቹ ውስጥ ገቡ፤ የአሳማውም መንጋ ከገደሉ አፋፍ እየተንደረደረ በመውረድ ሐይቁ ውስጥ ገብቶ ሰጠመ።
እረኞቹ ግን የሆነውን ነገር ሲያዩ ሸሽተው በመሄድ ወሬውን በከተማውና በገጠሩ አዳረሱ።
በዚህ ጊዜ ሕዝቡ የሆነውን ነገር ለማየት ወጡ። ወደ ኢየሱስ ሲመጡም አጋንንት የወጡለት ሰው ልብስ ለብሶና አእምሮው ተመልሶለት ኢየሱስ እግር ሥር ተቀምጦ አገኙት፤ በዚህ ጊዜ ፍርሃት አደረባቸው።
የተፈጸመውን ነገር ያዩ ሰዎች አጋንንት አድረውበት የነበረው ሰው እንዴት ጤናማ ሊሆን እንደቻለ አወሩላቸው።
በዚህ ጊዜ ከጌርጌሴኖን ክልል የመጡት ሰዎች በሙሉ ታላቅ ፍርሃት ስላደረባቸው ኢየሱስን ከዚያ እንዲሄድላቸው ለመኑት። እሱም ከዚያ ለመሄድ ጀልባዋ ላይ ተሳፈረ።
አጋንንት የወጡለት ሰው ግን አብሮት ይሆን ዘንድ ደጋግሞ ለመነው፤ ሆኖም ኢየሱስ ሰውየውን እንዲህ ሲል አሰናበተው፦
“ወደ ቤትህ ተመለስ፤ አምላክ ያደረገልህንም ነገር ተናገር።” ሰውየውም ኢየሱስ ያደረገለትን ነገር በከተማው ሁሉ እያወጀ ሄደ።
ሕዝቡ እየጠበቁት ስለነበር ኢየሱስ በተመለሰ ጊዜ ሁሉም በደስታ ተቀበሉት።
በዚህ ጊዜ ኢያኢሮስ የሚባል አንድ የምኩራብ አለቃ መጣ። ኢየሱስ እግር ላይም ወድቆ ወደ ቤቱ እንዲገባ ይማጸነው ጀመር፤
ይህን ያደረገው 12 ዓመት ገደማ የሆናት አንዲት ልጁ ልትሞት ተቃርባ ስለነበር ነው። ኢየሱስ እየተጓዘ ሳለ ሕዝቡ እየተጋፋ ያጨናንቀው ነበር።
በዚያም፣ ለ12 ዓመት ደም ሲፈስሳት የኖረች አንዲት ሴት የነበረች ሲሆን ይህችን ሴት ሊፈውሳት የቻለ አንድም ሰው አልነበረም።
ከኋላም መጥታ የልብሱን ዘርፍ ነካች፤ ይፈሳት የነበረውም ደም ወዲያውኑ ቆመ።
በዚህ ጊዜ ኢየሱስ “የነካኝ ማን ነው?” አለ። ሁሉም በካዱ ጊዜ፣ ጴጥሮስ “መምህር፣ ሕዝቡ ከቦህ እየተጋፋህ ነው የሚሄደው” አለው።
ኢየሱስ ግን “ኃይል ከእኔ እንደወጣ ስለታወቀኝ አንድ ሰው ነክቶኛል” አለ።