text
stringlengths
4
267
እርግጥ ኢየሱስ ያደረጋቸው ሌሎች ብዙ ነገሮችም አሉ፤ እነዚህ ሁሉ በዝርዝር ቢጻፉ ዓለም ራሱ የተጻፉትን ጥቅልሎች ለማስቀመጥ የሚበቃ ቦታ የሚኖረው አይመስለኝም።
ከፈሪሳውያን ወገን፣ የአይሁዳውያን ገዢ የሆነ ኒቆዲሞስ የሚባል ሰው ነበር።
ይህ ሰው በማታ ወደ ኢየሱስ መጥቶ እንዲህ አለው፦ “ረቢ፣ አንተ ከአምላክ ዘንድ የመጣህ አስተማሪ እንደሆንክ እናውቃለን፤ ምክንያቱም አምላክ ከእሱ ጋር ካልሆነ በቀር አንተ የምትፈጽማቸውን ተአምራዊ ምልክቶች መፈጸም የሚችል አንድም ሰው የለም።”
ኢየሱስም መልሶ “እውነት እውነት እልሃለሁ፣ አንድ ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር የአምላክን መንግሥት ሊያይ አይችልም” አለው።
ኒቆዲሞስም “ሰው ከሸመገለ በኋላ እንዴት ሊወለድ ይችላል? ዳግም ወደ እናቱ ማህፀን ገብቶ ሊወለድ ይችላል?” አለው።
ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰ፦ “እውነት እውነት እልሃለሁ፣ ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ አምላክ መንግሥት ሊገባ አይችልም።
ከሥጋ የተወለደ ሥጋ ነው፤ ከመንፈስ የተወለደ ደግሞ መንፈስ ነው።
‘ዳግመኛ መወለድ አለባችሁ’ ስላልኩህ አትገረም።
ነፋስ ወደፈለገው አቅጣጫ ይነፍሳል፤ ድምፁንም ትሰማለህ፤ ሆኖም ከየት እንደሚመጣና ወዴት እንደሚሄድ አታውቅም። ከመንፈስ የተወለደም ሁሉ እንደዚሁ ነው።”
ኒቆዲሞስም መልሶ “ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል?” አለው።
ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰለት፦ “አንተ የእስራኤል አስተማሪ ሆነህ ሳለህ እነዚህን ነገሮች አታውቅም?
እውነት እውነት እልሃለሁ፣ እኛ የምናውቀውን እንናገራለን፤ ያየነውንም እንመሠክራለን፤ እናንተ ግን እኛ የምንሰጠውን ምሥክርነት አትቀበሉም።
ስለ ምድራዊ ነገሮች ነግሬአችሁ የማታምኑ ከሆነ ስለ ሰማያዊ ነገሮች ብነግራችሁ እንዴት ታምናላችሁ?
ደግሞም ከሰማይ ከወረደው ከሰው ልጅ በቀር ወደ ሰማይ የወጣ የለም።
ሙሴ በምድረ በዳ እባቡን እንደሰቀለ፣ የሰው ልጅም እንዲሁ ሊሰቀል ይገባዋል፤
ይኸውም በእሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው ነው።
“አምላክ ዓለምን እጅግ ከመውደዱ የተነሳ በልጁ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ ሲል አንድያ ልጁን ሰጥቷል።
ምክንያቱም አምላክ ልጁን ወደ ዓለም የላከው በዓለም ላይ እንዲፈርድ ሳይሆን ዓለም በእሱ አማካኝነት እንዲድን ነው።
በእሱ የሚያምን ሁሉ አይፈረድበትም። በእሱ የማያምን ሁሉ ግን በአምላክ አንድያ ልጅ ስም ስለማያምን ቀድሞውኑም ተፈርዶበታል።
እንግዲህ የሚፈረድባቸው በዚህ መሠረት ነው፦ ብርሃን ወደ ዓለም መጣ፤ ሰዎች ግን ሥራቸው ክፉ ስለነበረ ከብርሃን ይልቅ ጨለማን ወደዱ።
መጥፎ ነገር የሚያደርግ ሁሉ ብርሃንን ይጠላልና፤ እንዲሁም ሥራው እንዳይጋለጥበት ወደ ብርሃን አይመጣም።
ትክክል የሆነውን የሚያደርግ ሁሉ ግን ያደረገው ነገር ከአምላክ ፈቃድ ጋር በሚስማማ መንገድ የተከናወነ መሆኑ እንዲታይ ወደ ብርሃን ይመጣል።”
ከዚህ በኋላ ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ወደ ይሁዳ ገጠራማ ክልል ሄዱ፤ በዚያም ከእነሱ ጋር ለተወሰነ ጊዜ ቆየ፤ ያጠምቅም ነበር።
ይሁንና ዮሐንስም በሳሊም አቅራቢያ በሄኖን ብዙ ውኃ በመኖሩ በዚያ እያጠመቀ ነበር፤ ሰዎችም እየመጡ ይጠመቁ ነበር፤
በዚህ ጊዜ ዮሐንስ ገና እስር ቤት አልገባም ነበር።
የዮሐንስ ደቀ መዛሙርት የመንጻት ሥርዓትን በተመለከተ ከአንድ አይሁዳዊ ጋር ተከራከሩ።
ከዚያ በኋላ ወደ ዮሐንስ መጥተው “ረቢ፣ በዮርዳኖስ ማዶ ከአንተ ጋር የነበረውና ስለ እሱ የመሠከርክለት ሰው እያጠመቀ ነው፤ ሰዉም ሁሉ ወደ እሱ እየሄደ ነው” አሉት።
ዮሐንስም መልሶ እንዲህ አለ፦ “አንድ ሰው ከሰማይ ካልተሰጠው በቀር አንዳች ነገር ሊያገኝ አይችልም።
‘እኔ ክርስቶስ አይደለሁም፤ ከዚህ ይልቅ ከእሱ በፊት የተላክሁ ነኝ’ እንዳልኩ እናንተ ራሳችሁ ትመሠክራላችሁ።
ሙሽራይቱ የሙሽራው ናት። ይሁን እንጂ የሙሽራው ጓደኛ በዚያ ቆሞ ሲሰማው በሙሽራው ድምፅ የተነሳ እጅግ ደስ ይለዋል። በመሆኑም የእኔ ደስታ ተፈጽሟል።
እሱ እየጨመረ መሄድ አለበት፤ እኔ ግን እየቀነስኩ መሄድ አለብኝ።”
ከላይ የሚመጣው ከሌሎች ሁሉ በላይ ነው። ከምድር የሆነው ምድራዊ ነው፤ የሚናገረውም ስለ ምድራዊ ነገሮች ነው። ከሰማይ የሚመጣው ከሌሎች ሁሉ በላይ ነው።
ስላየውና ስለሰማው ነገር ይመሠክራል፤ ነገር ግን ምሥክርነቱን የሚቀበል ሰው የለም።
ምሥክርነቱን የተቀበለ ሰው ሁሉ አምላክ እውነተኛ መሆኑን አረጋግጧል።
ምክንያቱም አምላክ የላከው የአምላክን ቃል ይናገራል፤ አምላክ መንፈሱን ቆጥቦ አይሰጥምና።
አብ ወልድን ይወዳል፤ ደግሞም ሁሉንም ነገር በእጁ ሰጥቶታል።
በወልድ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፤ ወልድን የማይታዘዝ ግን የአምላክ ቁጣ በላዩ ይኖራል እንጂ ሕይወትን አያይም።
በመንገድ እያለፈ ሳለም ሲወለድ ጀምሮ ዓይነ ስውር የሆነ አንድ ሰው አየ።
ደቀ መዛሙርቱም “ረቢ፣ ይህ ሰው ዓይነ ስውር ሆኖ የተወለደው ማን በሠራው ኃጢአት ነው? በራሱ ኃጢአት ነው ወይስ በወላጆቹ?” ሲሉ ጠየቁት።
ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰ፦ “እሱም ሆነ ወላጆቹ ኃጢአት አልሠሩም፤ ሆኖም ይህ የሆነው የአምላክ ሥራ በእሱ እንዲገለጥ ነው።
ቀን ሳለ፣ የላከኝን የእሱን ሥራ መሥራት አለብን፤ ማንም ሊሠራ የማይችልበት ሌሊት ይመጣል።
በዓለም እስካለሁ ድረስ የዓለም ብርሃን ነኝ።”
ይህን ካለ በኋላ መሬት ላይ እንትፍ በማለት በምራቁ ጭቃ ለወሰ፤ ጭቃውንም በሰውየው ዓይኖች ላይ ቀባ፤
ሰውየውንም “ሄደህ በሰሊሆም ገንዳ ታጠብ” አለው (ሰሊሆም ማለት “ተላከ” ማለት ነው)። ሰውየውም ሄዶ ታጠበ፤ ዓይኑም በርቶለት መጣ።
ከዚያም ጎረቤቶቹና ቀደም ሲል ሲለምን ያዩት የነበሩ ሰዎች “ይህ ሰው ተቀምጦ ይለምን የነበረው አይደለም እንዴ?” አሉ።
አንዳንዶች “አዎ፣ እሱ ነው” ሲሉ ሌሎች ደግሞ “አይ፣ እሱን ይመስላል እንጂ እሱ አይደለም” ይሉ ነበር። ሰውየው ግን “እኔው ነኝ” ይል ነበር።
በመሆኑም “ታዲያ ዓይኖችህ እንዴት ተከፈቱ?” ሲሉ ጠየቁት።
እሱም “ኢየሱስ የተባለው ሰው ጭቃ ለውሶ ዓይኖቼን ቀባና ‘ወደ ሰሊሆም ሄደህ ታጠብ’ አለኝ። እኔም ሄጄ ታጠብኩ፤ ዓይኔም በራልኝ” ሲል መለሰ።
በዚህ ጊዜ “ሰውየው የት አለ?” አሉት። እሱም “እኔ አላውቅም” አለ።
እነሱም ዓይነ ስውር የነበረውን ሰው ወደ ፈሪሳውያን ወሰዱት።
እንደ አጋጣሚ ሆኖ ኢየሱስ ጭቃውን የለወሰበትና የሰውየውን ዓይኖች ያበራበት ቀን ሰንበት ነበር።
በዚህ ጊዜ ፈሪሳውያኑም እንዴት ማየት እንደቻለ ጠየቁት። እሱም “ሰውየው ዓይኖቼን ጭቃ ቀባ፤ እኔም ታጠብኩ፤ ከዚያም ማየት ቻልኩ” አላቸው።
ከፈሪሳውያንም መካከል አንዳንዶቹ “ይህ ሰው ሰንበትን ስለማያከብር ከአምላክ የመጣ አይደለም” አሉ። ሌሎቹ ደግሞ “ኃጢአተኛ የሆነ ሰው እንዲህ ያሉ ተአምራዊ ምልክቶችን እንዴት ሊፈጽም ይችላል?” አሉ። በመሆኑም በመካከላቸው ክፍፍል ተፈጠረ።
በድጋሚም ዓይነ ስውሩን “ይህ ሰው ዓይኖችህን ስላበራልህ ስለ እሱ ምን ትላለህ?” አሉት። ሰውየውም “እሱ ነቢይ ነው” አለ።
ይሁን እንጂ አይሁዳውያኑ ማየት የቻለውን ሰው ወላጆች እስከጠሩበት ጊዜ ድረስ ሰውየው ዓይነ ስውር እንደነበረና በኋላ ዓይኑ እንደበራለት አላመኑም ነበር።
ወላጆቹንም “ዓይነ ስውር ሆኖ ተወልዷል የምትሉት ልጃችሁ ይህ ነው? ታዲያ አሁን እንዴት ሊያይ ቻለ?” ሲሉ ጠየቋቸው።
ወላጆቹም እንዲህ ሲሉ መለሱ፦ “ይህ ልጃችን እንደሆነና ዓይነ ስውር ሆኖ እንደተወለደ እናውቃለን።
አሁን ግን እንዴት ሊያይ እንደቻለ የምናውቀው ነገር የለም፤ ዓይኖቹን ማን እንዳበራለትም አናውቅም። እሱን ጠይቁት፤ ሙሉ ሰው ነው። ስለ ራሱ መናገር ያለበት እሱ ነው።”
ወላጆቹ ይህን ያሉት አይሁዳውያኑን ስለፈሩ ነው፤ ምክንያቱም አይሁዳውያን ኢየሱስን፣ ‘ክርስቶስ ነው’ ብሎ የተቀበለ ማንኛውም ሰው ከምኩራብ እንዲባረር አስቀድመው ወስነው ነበር።
ወላጆቹ “ሙሉ ሰው ነው። እሱን ጠይቁት” ያሉት ለዚህ ነበር።
ስለዚህ ዓይነ ስውር የነበረውን ሰው ለሁለተኛ ጊዜ ጠርተው “እውነቱን በመናገር ለአምላክ ክብር ስጥ፤ እኛ ይህ ሰው ኃጢአተኛ መሆኑን እናውቃለን” አሉት።
እሱም መልሶ “ኃጢአተኛ ይሁን አይሁን የማውቀው ነገር የለም። እኔ የማውቀው ዓይነ ስውር እንደነበርኩና አሁን ግን ማየት እንደቻልኩ ነው” አለ።
በዚህ ጊዜ “ምንድን ነው ያደረገልህ? ዓይንህን ያበራልህስ እንዴት ነው?” አሉት።
እሱም “ነገርኳችሁ እኮ፤ እናንተ ግን አትሰሙም። እንደገና መስማት የፈለጋችሁት ለምንድን ነው? እናንተም የእሱ ደቀ መዝሙር መሆን ፈለጋችሁ እንዴ?” ሲል መለሰላቸው።
እነሱም ሰውየውን በንቀት እንዲህ አሉት፦ “የዚያ ሰው ደቀ መዝሙር አንተ ነህ፤ እኛ ግን የሙሴ ደቀ መዛሙርት ነን።
አምላክ ሙሴን እንዳነጋገረው እናውቃለን፤ ይህ ሰው ግን ከየት እንደመጣ አናውቅም።”
ሰውየውም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “ከየት እንደመጣ አለማወቃችሁ በጣም የሚያስገርም ነገር ነው፤ ያም ሆነ ይህ ዓይኖቼን አብርቶልኛል።
አምላክ ኃጢአተኞችን እንደማይሰማ እናውቃለን፤ ፈሪሃ አምላክ ያለውንና ፈቃዱን የሚያደርገውን ሁሉ ግን ይሰማዋል።
ዓይነ ስውር ሆኖ የተወለደን ሰው ዓይኖች የከፈተ አለ ሲባል ከጥንት ዘመን ጀምሮ ተሰምቶ አይታወቅም።
ይህ ሰው ከአምላክ ባይሆን ኖሮ ምንም ነገር ሊያደርግ አይችልም ነበር።”
እነሱም መልሰው “አንተ ሁለመናህ በኃጢአት ተበክሎ የተወለድክ! እኛን ልታስተምር ትፈልጋለህ?” አሉት። ከዚያም አባረሩት!
ኢየሱስም ሰውየውን እንዳባረሩት ሰማ፤ ባገኘውም ጊዜ “በሰው ልጅ ላይ እምነት አለህ?” አለው።
ሰውየውም “ጌታዬ፣ አምንበት ዘንድ እሱ ማን ነው?” ሲል መለሰ።
ኢየሱስም “አይተኸዋል፤ ደግሞም እያነጋገረህ ያለው እሱ ነው” አለው።
እሱም “ጌታ ሆይ፣ በእሱ አምናለሁ” አለ። ከዚያም ሰገደለት።
ኢየሱስም “የማያዩ ማየት እንዲችሉ፣ የሚያዩም እንዲታወሩ፣ ለዚህ ፍርድ ወደዚህ ዓለም መጥቻለሁ” አለ።
በዚያ የነበሩ ፈሪሳውያንም ይህን ሰምተው “እናንተም ዕውሮች ናችሁ እያልከን ነው?” አሉት።
ኢየሱስም “ዕውሮች ብትሆኑማ ኖሮ ኃጢአት ባልሆነባችሁ ነበር። አሁን ግን ‘እናያለን’ ትላላችሁ። ስለዚህ ኃጢአታችሁ እንዳለ ይኖራል” አላቸው።
በሦስተኛውም ቀን በገሊላ በምትገኘው በቃና የሠርግ ድግስ ነበር፤ የኢየሱስ እናትም በዚያ ነበረች።
ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱም ወደ ሠርጉ ተጠርተው ነበር።
የወይን ጠጁ እያለቀ ሲሄድ የኢየሱስ እናት “የወይን ጠጅ አልቆባቸዋል” አለችው።
ኢየሱስ ግን “አንቺ ሴት፣ ይህ ጉዳይ እኔንና አንቺን ምን ይመለከተናል? ሰዓቴ ገና አልደረሰም” አላት።
እናቱም በዚያ የሚያገለግሉትን ሰዎች “የሚላችሁን ነገር ሁሉ አድርጉ” አለቻቸው።
የአይሁዳውያን የመንጻት ሥርዓት በሚያዘው መሠረት እያንዳንዳቸው ሁለት ወይም ሦስት የፈሳሽ መለኪያዎች የሚይዙ ከድንጋይ የተሠሩ ስድስት የውኃ ጋኖች በዚያ ተቀምጠው ነበር።
ኢየሱስም “ጋኖቹን ውኃ ሙሏቸው” አላቸው። እነሱም እስከ አፋቸው ድረስ ሞሏቸው።
ከዚያም “አሁን ቀድታችሁ ለድግሱ አሳዳሪ ስጡት” አላቸው። እነሱም ወስደው ሰጡት።
የድግሱ አሳዳሪም ወደ ወይን ጠጅ የተለወጠውን ውኃ ቀመሰ፤ ሆኖም ከየት እንደመጣ አላወቀም፤ ውኃውን የቀዱት አገልጋዮች ግን ያውቁ ነበር፤ አሳዳሪውም ሙሽራውን ጠርቶ
እንዲህ አለው፦ “ሰው ሁሉ በቅድሚያ ጥሩውን የወይን ጠጅ ያቀርብና ሰዎቹ ከሰከሩ በኋላ መናኛውን ያቀርባል። አንተ ግን ጥሩውን የወይን ጠጅ እስካሁን ድረስ አስቀምጠሃል።”
ኢየሱስ ከምልክቶቹ የመጀመሪያ የሆነውን ይህን ተአምር በገሊላ በምትገኘው በቃና ፈጸመ፤ ክብሩንም ገለጠ፤ ደቀ መዛሙርቱም በእሱ አመኑ።
ከዚህ በኋላ እሱና እናቱ እንዲሁም ወንድሞቹና ደቀ መዛሙርቱ ወደ ቅፍርናሆም ወረዱ፤ ሆኖም በዚያ ብዙ ቀን አልቆዩም።
በዚህ ጊዜ የአይሁዳውያን ፋሲካ ቀርቦ ነበር፤ ኢየሱስም ወደ ኢየሩሳሌም ወጣ።
በቤተ መቅደሱ ውስጥ ከብት፣ በግና ርግብ የሚሸጡ ሰዎችን እንዲሁም በዚያ የተቀመጡ ገንዘብ መንዛሪዎችን አገኘ።
በዚህ ጊዜ የገመድ ጅራፍ ሠርቶ ሁሉንም ከበጎቻቸውና ከከብቶቻቸው ጋር አስወጣ፤ የገንዘብ ለዋጮችንም ሳንቲሞች በተነ፤ ጠረጴዛዎቻቸውንም ገለባበጠ።
ርግብ ሻጮቹንም “እነዚህን ከዚህ አስወጡ! የአባቴን ቤት የንግድ ቤት ማድረጋችሁ ይብቃ!” አላቸው።
ደቀ መዛሙርቱም “ለቤትህ ያለኝ ቅንዓት ይበላኛል” ተብሎ የተጻፈው ትዝ አላቸው።
በዚህ ጊዜ አይሁዳውያን መልሰው “እነዚህን ነገሮች ለማድረግ ሥልጣን እንዳለህ የሚያረጋግጥ ምን ምልክት ታሳየናለህ?” አሉት።
ኢየሱስም መልሶ “ይህን ቤተ መቅደስ አፍርሱት፤ እኔም በሦስት ቀን ውስጥ አነሳዋለሁ” አላቸው።
አይሁዳውያኑም “ቤተ መቅደሱን ለመገንባት 46 ዓመት ፈጅቷል፤ ታዲያ አንተ በሦስት ቀን ታነሳዋለህ?” አሉት።
እሱ ግን ቤተ መቅደስ ሲል ስለ ራሱ ሰውነት መናገሩ ነበር።
ከሙታን በተነሳ ጊዜም፣ ደቀ መዛሙርቱ ይህን ደጋግሞ ይናገር እንደነበር አስታወሱ፤ ቅዱሳን መጻሕፍትንና ኢየሱስ የተናገረውንም ቃል አመኑ።