text
stringlengths
4
267
ይሁንና በፋሲካ በዓል፣ በኢየሩሳሌም በነበረበት ጊዜ ብዙ ሰዎች የሚያከናውናቸውን ተአምራዊ ምልክቶች ሲያዩ በስሙ አመኑ።
ኢየሱስ ግን ሁሉንም ያውቃቸው ስለነበር አይተማመንባቸውም ነበር፤
እንዲሁም በሰው ውስጥ ያለውን ያውቅ ስለነበር ማንም ስለ ሰው እንዲመሠክርለት አላስፈለገውም።
“እውነት እውነት እላችኋለሁ፣ በበሩ ሳይሆን በሌላ በኩል ዘሎ ወደ በጎቹ ጉረኖ የሚገባ ሌባና ዘራፊ ነው።
በበሩ በኩል የሚገባ ግን የበጎቹ እረኛ ነው።
በር ጠባቂውም ለእሱ ይከፍትለታል፤ በጎቹም ድምፁን ይሰማሉ። የራሱን በጎች በየስማቸው ጠርቶ እየመራ ያወጣቸዋል።
የራሱ የሆኑትን ሁሉ ካወጣ በኋላ ከፊት ከፊታቸው ይሄዳል፤ በጎቹም ድምፁን ስለሚያውቁ ይከተሉታል።
እንግዳ የሆነውን ግን ይሸሹታል እንጂ በምንም ዓይነት አይከተሉትም፤ ምክንያቱም የእንግዳ ሰዎችን ድምፅ አያውቁም።”
ኢየሱስ ይህን ምሳሌ ነገራቸው፤ እነሱ ግን ምን እያላቸው እንዳለ አልገባቸውም።
ስለዚህ ኢየሱስ እንደገና እንዲህ አለ፦ “እውነት እውነት እላችኋለሁ፣ በጎቹ የሚገቡበት በር እኔ ነኝ።
አስመሳይ ሆነው በእኔ ስም የመጡ ሁሉ ሌቦችና ዘራፊዎች ናቸው፤ በጎቹ ግን አልሰሟቸውም።
በሩ እኔ ነኝ፤ በእኔ በኩል የሚገባ ሁሉ ይድናል፤ ይገባል፤ ይወጣል፤ መሰማሪያም ያገኛል።
ሌባው ለመስረቅ፣ ለመግደልና ለማጥፋት ካልሆነ በቀር ለሌላ አይመጣም። እኔ የመጣሁት ሕይወት እንዲኖራቸውና እንዲትረፈረፍላቸው ነው።
እኔ ጥሩ እረኛ ነኝ፤ ጥሩ እረኛ ሕይወቱን ለበጎቹ ሲል አሳልፎ ይሰጣል።
እረኛ ያልሆነና በጎቹ የራሱ ያልሆኑ ተቀጣሪ ሠራተኛ ተኩላ ሲመጣ ሲያይ በጎቹን ጥሎ ይሸሻል (ተኩላውም በጎቹን ይነጥቃል እንዲሁም ይበታትናል)፤
ሠራተኛው እንዲህ የሚያደርገው ተቀጣሪ ስለሆነና ለበጎቹ ደንታ ስለሌለው ነው።
እኔ ጥሩ እረኛ ነኝ። በጎቼን አውቃቸዋለሁ፤ በጎቼም ያውቁኛል፤
ይህም አብ እኔን እንደሚያውቀኝና እኔም አብን እንደማውቀው ነው፤ ሕይወቴንም ለበጎቹ ስል አሳልፌ እሰጣለሁ።
“ከዚህ ጉረኖ ያልሆኑ ሌሎች በጎች አሉኝ፤ እነሱንም ማምጣት አለብኝ፤ ድምፄንም ይሰማሉ፤ ሁሉም አንድ መንጋ ይሆናሉ፤ አንድ እረኛም ይኖራቸዋል።
ሕይወቴን መልሼ አገኛት ዘንድ አሳልፌ ስለምሰጣት አብ ይወደኛል።
በራሴ ተነሳስቼ አሳልፌ እሰጣታለሁ እንጂ ማንም ሰው ከእኔ አይወስዳትም። ሕይወቴን አሳልፌ ለመስጠት ሥልጣን አለኝ፤ መልሼ ለመቀበልም ሥልጣን አለኝ። ይህን ትእዛዝ የተቀበልኩት ከአባቴ ነው።”
ከዚህ ንግግር የተነሳ በአይሁዳውያኑ መካከል እንደገና ክፍፍል ተፈጠረ።
ብዙዎቹም “ይህ ሰው ጋኔን አለበት፤ አእምሮውን ስቷል። ለምን ትሰሙታላችሁ?” አሉ።
ሌሎቹ ደግሞ “ጋኔን የያዘው ሰው እንዲህ አይናገርም። ጋኔን የዓይነ ስውራንን ዓይን ሊከፍት ይችላል እንዴ?” አሉ።
በዚያ ጊዜ በኢየሩሳሌም የመታደስ በዓል ይከበር ነበር። ወቅቱም ክረምት ነበር፤
ኢየሱስም በቤተ መቅደሱ በሚገኘውና መጠለያ ባለው የሰለሞን መተላለፊያ ውስጥ እያለፈ ነበር።
በዚህ ጊዜ አይሁዳውያን ከበውት “እስከ መቼ ድረስ ልባችንን ታንጠለጥላለህ? አንተ ክርስቶስ ከሆንክ በግልጽ ንገረን” አሉት።
ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “እኔ ነግሬአችኋለሁ፤ እናንተ ግን አታምኑም። በአባቴ ስም እየሠራኋቸው ያሉት ሥራዎች ስለ እኔ ይመሠክራሉ።
ሆኖም እናንተ በጎቼ ስላልሆናችሁ አታምኑም።
በጎቼ ድምፄን ይሰማሉ፤ እኔም አውቃቸዋለሁ፤ እነሱም ይከተሉኛል።
የዘላለም ሕይወት እሰጣቸዋለሁ፤ መቼም ቢሆን ጥፋት አይደርስባቸውም፤ ከእጄ የሚነጥቃቸውም የለም።
አባቴ የሰጠኝ በጎች ከሌሎች ነገሮች ሁሉ ይበልጣሉ፤ እነሱንም ከአባቴ እጅ ሊነጥቃቸው የሚችል የለም።
እኔና አብ አንድ ነን።”
በዚህ ጊዜም አይሁዳውያኑ ሊወግሩት ድንጋይ አነሱ።
ኢየሱስም መልሶ “ከአብ ዘንድ ብዙ መልካም ሥራዎች አሳየኋችሁ። ታዲያ የምትወግሩኝ ከእነዚህ ሥራዎች መካከል በየትኛው የተነሳ ነው?” አላቸው።
አይሁዳውያኑም “እኛ የምንወግርህ ስለ መልካም ሥራህ ሳይሆን አንተ ሰው ሆነህ ሳለህ ራስህን አምላክ በማድረግ አምላክን ስለተዳፈርክ ነው” ሲሉ መለሱለት።
ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “በሕጋችሁ ላይ ‘“እናንተ አማልክት ናችሁ” አልኩ’ ተብሎ ተጽፎ የለም?
የአምላክ ቃል ያወገዛቸውን እሱ ‘አማልክት’ ብሎ ከጠራቸውና ቅዱስ መጽሐፉ ሊሻር የማይችል ከሆነ
አብ የቀደሰኝንና ወደ ዓለም የላከኝን እኔን፣ ‘የአምላክ ልጅ ነኝ’ ስላልኩ ‘አምላክን ትዳፈራለህ’ ትሉኛላችሁ?
እኔ የአባቴን ሥራ እየሠራሁ ካልሆነ አትመኑኝ።
የአባቴን ሥራ እየሠራሁ ከሆነ ግን እኔን ባታምኑኝ እንኳ ሥራዬን እመኑ፤ ይህም አብ ከእኔ ጋር አንድነት እንዳለው እንዲሁም እኔም ከአብ ጋር አንድነት እንዳለኝ እንድታውቁና ይህን ይበልጥ እያወቃችሁ እንድትሄዱ ነው።”
ስለዚህ እንደገና ሊይዙት ሞከሩ፤ እሱ ግን አመለጣቸው።
ከዚያም ዮሐንስ ቀደም ሲል ያጠምቅ ወደነበረበት ከዮርዳኖስ ማዶ ወዳለው ቦታ ዳግመኛ ሄደ፤ በዚያም ለተወሰነ ጊዜ ቆየ።
ብዙ ሰዎችም ወደ እሱ መጥተው እርስ በርሳቸው “ዮሐንስ አንድም ተአምራዊ ምልክት አላደረገም፤ ሆኖም ዮሐንስ ስለዚህ ሰው የተናገረው ነገር ሁሉ እውነት ነበር” ተባባሉ።
በዚያም ብዙዎች በእሱ አመኑ።
“ይህን ሁሉ የነገርኳችሁ እንዳትሰናከሉ ብዬ ነው።
ሰዎች ከምኩራብ ያባርሯችኋል። እንዲያውም እናንተን የሚገድል ሁሉ ለአምላክ ቅዱስ አገልግሎት እንዳቀረበ አድርጎ የሚያስብበት ሰዓት ይመጣል።
ሆኖም እነዚህን ነገሮች የሚያደርጉት አብንም ሆነ እኔን ስላላወቁ ነው።
ይሁንና እነዚህን ነገሮች የነገርኳችሁ የሚፈጸሙበት ሰዓት ሲደርስ አስቀድሜ ነግሬአችሁ እንደነበረ እንድታስታውሱ ነው። “ከእናንተ ጋር ስለነበርኩ እነዚህን ነገሮች በመጀመሪያ አልነገርኳችሁም።
አሁን ግን ወደ ላከኝ ልሄድ ነው፤ ሆኖም ከመካከላችሁ ‘ወዴት ነው የምትሄደው?’ ብሎ የጠየቀኝ የለም።
እነዚህን ነገሮች ስለነገርኳችሁ ልባችሁ በሐዘን ተሞልቷል።
ይሁንና እውነቱን ለመናገር እኔ የምሄደው ለእናንተው ጥቅም ነው። ምክንያቱም እኔ ካልሄድኩ ረዳቱ በምንም ዓይነት ወደ እናንተ አይመጣም፤ ከሄድኩ ግን እሱን ወደ እናንተ እልከዋለሁ።
እሱ ሲመጣ ስለ ኃጢአት፣ ስለ ጽድቅና ስለ ፍርድ ለዓለም አሳማኝ ማስረጃ ያቀርባል፦
በመጀመሪያ ደረጃ ስለ ኃጢአት የተባለው፣ ሰዎች በእኔ ስላላመኑ ነው፤
ከዚያም ስለ ጽድቅ የተባለው፣ እኔ ወደ አብ ስለምሄድና እናንተ ከእንግዲህ ስለማታዩኝ ነው፤
ስለ ፍርድ የተባለው ደግሞ የዚህ ዓለም ገዢ ስለተፈረደበት ነው።
“ገና ብዙ የምነግራችሁ ነገር አለኝ፤ አሁን ግን ልትሸከሙት አትችሉም።
ይሁን እንጂ እሱ ይኸውም የእውነት መንፈስ ሲመጣ ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል፤ ምክንያቱም የሚናገረው ከራሱ አመንጭቶ አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ የሰማውን ይናገራል፤ እንዲሁም ወደፊት የሚሆኑትን ነገሮች ያሳውቃችኋል።
የሚያሳውቃችሁ የእኔ ከሆነው ወስዶ ስለሆነ እሱ እኔን ያከብረኛል።
አብ ያለው ነገር ሁሉ የእኔ ነው። የእኔ ከሆነው ወስዶ ያሳውቃችኋል ያልኳችሁ ለዚህ ነው።
ከጥቂት ጊዜ በኋላ አታዩኝም፤ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ደግሞ ታዩኛላችሁ።”
በዚህ ጊዜ ከደቀ መዛሙርቱ አንዳንዶቹ እርስ በርሳቸው “‘ከጥቂት ጊዜ በኋላ አታዩኝም፤ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ደግሞ ታዩኛላችሁ’ እንዲሁም ‘ወደ አብ ልሄድ ነውና’ ሲለን ምን ማለቱ ነው?” ተባባሉ።
ስለዚህ “‘ከጥቂት ጊዜ በኋላ’ ሲል ምን ማለቱ ነው? ስለ ምን ነገር እየተናገረ እንደሆነ አልገባንም” አሉ።
ኢየሱስ ሊጠይቁት እንደፈለጉ ተረድቶ እንዲህ አላቸው፦ “እርስ በርሳችሁ ስለዚህ ጉዳይ የምትጠያየቁት ‘ከጥቂት ጊዜ በኋላ አታዩኝም፤ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ደግሞ ታዩኛላችሁ’ ስላልኩ ነው?
እውነት እውነት እላችኋለሁ፣ እናንተ ታለቅሳላችሁ እንዲሁም ዋይ ዋይ ትላላችሁ፤ ዓለም ግን ይደሰታል፤ እናንተ ታዝናላችሁ፤ ሆኖም ሐዘናችሁ ወደ ደስታ ይለወጣል።
አንዲት ሴት የመውለጃዋ ሰዓት ደርሶ ስታምጥ ትጨነቃለች፤ ሕፃኑን ከወለደች በኋላ ግን አንድ ሰው ወደ ዓለም በመምጣቱ ከደስታዋ የተነሳ ሥቃይዋን ሁሉ ትረሳለች።
ስለዚህ እናንተም አሁን አዝናችኋል፤ ሆኖም እንደገና ስለማያችሁ ልባችሁ በደስታ ይሞላል፤ ደስታችሁን ደግሞ ማንም አይነጥቃችሁም።
በዚያን ጊዜ እኔን ምንም ጥያቄ አትጠይቁኝም። እውነት እውነት እላችኋለሁ፣ አብን ማንኛውንም ነገር በስሜ ብትጠይቁት ይሰጣችኋል።
እስካሁን ድረስ በስሜ አንድም ነገር አልጠየቃችሁም። ደስታችሁ የተሟላ እንዲሆን ጠይቁ፤ ትቀበላላችሁ።
“እነዚህን ነገሮች የነገርኳችሁ በምሳሌ ነው። ይሁንና ለእናንተ በምሳሌ የማልናገርበት ሰዓት ይመጣል፤ ከዚህ ይልቅ ስለ አብ በግልጽ እነግራችኋለሁ።
በዚያ ቀን አብን በስሜ ትለምናላችሁ፤ ይህን ስል ስለ እናንተ አብን እጠይቃለሁ ማለቴ አይደለም።
ምክንያቱም እናንተ እኔን ስለወደዳችሁኝና የአምላክ ተወካይ ሆኜ እንደመጣሁ ስላመናችሁ አብ ራሱ ይወዳችኋል።
እኔ የአብ ተወካይ ሆኜ ወደ ዓለም መጥቻለሁ። አሁን ደግሞ ዓለምን ትቼ ወደ አብ ልሄድ ነው።”
ደቀ መዛሙርቱም እንዲህ አሉ፦ “አሁን እኮ በግልጽ እየተናገርክ ነው፤ በምሳሌም አልተናገርክም።
አሁን ሁሉን ነገር እንደምታውቅና ማንም ጥያቄ እስኪጠይቅህ ድረስ መጠበቅ እንደማያስፈልግህ ተረዳን። ስለሆነም ከአምላክ ዘንድ እንደመጣህ እናምናለን።”
ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “አሁን አመናችሁ?
እነሆ፣ ሁላችሁም ወደየቤታችሁ የምትበታተኑበትና እኔን ብቻዬን ትታችሁ የምትሄዱበት ሰዓት ቀርቧል፤ እንዲያውም ደርሷል። ይሁንና አብ ከእኔ ጋር ስላለ ብቻዬን አይደለሁም።
እነዚህን ነገሮች የነገርኳችሁ በእኔ አማካኝነት ሰላም እንዲኖራችሁ ነው። በዓለም ሳላችሁ መከራ ይደርስባችኋል፤ ነገር ግን አይዟችሁ! እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ።”
ከዚህ በኋላ የአይሁዳውያን በዓል ስለነበረ ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም ወጣ።
በኢየሩሳሌም በበጎች በር አጠገብ አምስት ባለ መጠለያ መተላለፊያዎች ያሉት በዕብራይስጥ ቤተዛታ ተብሎ የሚጠራ አንድ የውኃ ገንዳ ነበር።
በእነዚህ መተላለፊያዎች ውስጥ ብዙ ሕመምተኞች፣ ዓይነ ስውሮች፣ አንካሶችና ሽባዎች ይተኙ ነበር።
በዚያም ለ38 ዓመት ሕመምተኛ ሆኖ የኖረ አንድ ሰው ነበር።
ኢየሱስ ይህን ሰው በዚያ ተኝቶ አየውና ለረጅም ጊዜ ሕመምተኛ ሆኖ እንደኖረ አውቆ “መዳን ትፈልጋለህ?” አለው።
ሕመምተኛውም “ጌታዬ፣ ውኃው በሚናወጥበት ጊዜ ገንዳው ውስጥ የሚያስገባኝ ሰው የለኝም፤ ወደ ገንዳው ስሄድ ደግሞ ሌላው ቀድሞኝ ይገባል” ሲል መለሰለት።
ኢየሱስም “ተነስ! ምንጣፍህን ተሸክመህ ሂድ” አለው።
ሰውየውም ወዲያውኑ ተፈወሰ፤ ምንጣፉንም አንስቶ መሄድ ጀመረ። ቀኑም ሰንበት ነበር።
በመሆኑም አይሁዳውያን የተፈወሰውን ሰው “ሰንበት እኮ ነው፤ ምንጣፍህን እንድትሸከም ሕጉ አይፈቅድልህም” አሉት።
እሱ ግን “የፈወሰኝ ሰው ራሱ ‘ምንጣፍህን ተሸክመህ ሂድ’ ብሎኛል” ሲል መለሰላቸው።
እነሱም “‘ምንጣፍህን ተሸክመህ ሂድ’ ያለህ ሰው ማን ነው?” ሲሉ ጠየቁት።
ሆኖም ኢየሱስ ከቦታው ዞር ብሎ ከሕዝቡ ጋር ተቀላቅሎ ስለነበር ሰውየው የፈወሰውን ሰው ማንነት ማወቅ አልቻለም።
ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ሰውየውን በቤተ መቅደሱ ውስጥ አገኘውና “አሁን ደህና ሆነሃል። የባሰ ነገር እንዳይደርስብህ ከእንግዲህ ኃጢአት አትሥራ” አለው።
ሰውየውም ሄዶ የፈወሰው ኢየሱስ መሆኑን ለአይሁዳውያኑ ነገራቸው።
ከዚህም የተነሳ አይሁዳውያኑ በኢየሱስ ላይ ስደት ያደርሱበት ጀመር፤ ይህን ያደረጉት በሰንበት ቀን እነዚህን ነገሮች ይፈጽም ስለነበረ ነው።
እሱ ግን “አባቴ እስካሁን እየሠራ ነው፤ እኔም እሠራለሁ” ሲል መለሰላቸው።
ከዚህም የተነሳ አይሁዳውያኑ ሰንበትን ስለጣሰ ብቻ ሳይሆን አምላክን የገዛ አባቱ እንደሆነ አድርጎ በመጥራት ራሱን ከአምላክ ጋር እኩል ስላደረገ እሱን ለመግደል ይበልጥ ተነሳሱ።
ስለሆነም ኢየሱስ እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “እውነት እውነት እላችኋለሁ፣ ወልድ፣ አብ ሲያደርግ ያየውን ብቻ እንጂ በራሱ ተነሳስቶ አንድም ነገር ሊያደርግ አይችልም። አብ የሚያደርገውን ሁሉ ወልድም በተመሳሳይ መንገድ ያንኑ ያደርጋል።
ምክንያቱም አብ ወልድን ይወደዋል፤ እንዲሁም እሱ ራሱ የሚያደርገውን ነገር ሁሉ ያሳየዋል፤ እናንተም ትደነቁ ዘንድ ከእነዚህም የሚበልጥ ሥራ ያሳየዋል።
አብ ሙታንን እንደሚያስነሳቸውና ሕያው እንደሚያደርጋቸው ሁሉ ወልድም እንዲሁ የፈለገውን ሰው ሕያው ያደርጋል።
አብ በማንም ላይ አይፈርድምና፤ ከዚህ ይልቅ የመፍረዱን ሥልጣን ሁሉ ለወልድ ሰጥቶታል፤
ይህን ያደረገውም ሁሉም አብን እንደሚያከብሩ ሁሉ ወልድንም እንዲያከብሩ ነው። ወልድን የማያከብር ሁሉ እሱን የላከውን አብንም አያከብርም።