text
stringlengths
4
267
የላከኝ አብ ካልሳበው በቀር ወደ እኔ ሊመጣ የሚችል ሰው የለም፤ እኔም በመጨረሻው ቀን ከሞት አስነሳዋለሁ።
ነቢያት በጻፏቸው ጽሑፎች ላይ ‘ሁሉም ከይሖዋ የተማሩ ይሆናሉ’ ተብሎ ተጽፏል። ከአብ የሰማና የተማረ ሁሉ ወደ እኔ ይመጣል።
ከአምላክ ዘንድ ከመጣው በስተቀር አብን ያየ አንድም ሰው የለም፤ እሱ አብን አይቶታል።
እውነት እውነት እላችኋለሁ፣ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት አለው።
“ሕይወት የሚያስገኘው ምግብ እኔ ነኝ።
አባቶቻችሁ በምድረ በዳ መና በሉ፤ ይሁን እንጂ ሞቱ።
ከሰማይ የወረደውን ምግብ የሚበላ ሁሉ ግን አይሞትም።
ከሰማይ የወረደው ሕያው ምግብ እኔ ነኝ። ከዚህ ምግብ የሚበላ ሁሉ ለዘላለም ይኖራል፤ ምግቡ ደግሞ ለዓለም ሕይወት ስል የምሰጠው ሥጋዬ ነው።”
አይሁዳውያንም “ይህ ሰው እንዴት ሥጋውን እንድንበላ ሊሰጠን ይችላል?” በማለት እርስ በርሳቸው ይከራከሩ ጀመር።
በመሆኑም ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፦ “እውነት እውነት እላችኋለሁ፣ የሰውን ልጅ ሥጋ ካልበላችሁና ደሙን ካልጠጣችሁ በራሳችሁ ሕይወት የላችሁም።
ሥጋዬን የሚበላና ደሜን የሚጠጣ ሁሉ የዘላለም ሕይወት አለው፤ በመጨረሻውም ቀን ከሞት አስነሳዋለሁ፤
ሥጋዬ እውነተኛ ምግብ፣ ደሜም እውነተኛ መጠጥ ነውና።
ሥጋዬን የሚበላና ደሜን የሚጠጣ ሁሉ ከእኔ ጋር አንድነት ይኖረዋል፤ እኔም ከእሱ ጋር አንድነት ይኖረኛል።
ሕያው የሆነው አብ እንደላከኝና እኔም ከእሱ የተነሳ በሕይወት እንደምኖር ሁሉ የእኔን ሥጋ የሚበላም ከእኔ የተነሳ በሕይወት ይኖራል።
ከሰማይ የወረደው ምግብ ይህ ነው። ይህም አባቶቻችሁ በበሉበት ጊዜ እንደነበረው አይደለም፤ እነሱ ቢበሉም እንኳ ሞተዋል። ይህን ምግብ የሚበላ ሁሉ ግን ለዘላለም ይኖራል።”
ይህን የተናገረው በቅፍርናሆም በምኩራብ እያስተማረ ሳለ ነበር።
ከደቀ መዛሙርቱ ብዙዎቹ ይህን ሲሰሙ “ይህ የሚሰቀጥጥ ንግግር ነው፤ ማን ሊሰማው ይችላል?” አሉ።
ኢየሱስ ግን ደቀ መዛሙርቱ ስለዚህ ጉዳይ እያጉረመረሙ እንዳሉ ስለገባው እንዲህ አላቸው፦ “ይህ ያሰናክላችኋል?
ታዲያ የሰው ልጅ ቀድሞ ወደነበረበት ሲወጣ ብታዩ ምን ልትሉ ነው?
ሕይወትን የሚሰጠው መንፈስ ነው፤ ሥጋ ምንም አይጠቅምም። እኔ የነገርኳችሁ ቃል መንፈስም ሕይወትም ነው።
ነገር ግን ከእናንተ መካከል የማያምኑ አንዳንዶች አሉ።” ኢየሱስ ይህን ያለው የማያምኑት እነማን እንደሆኑና ማን አሳልፎ እንደሚሰጠው ከመጀመሪያው ያውቅ ስለነበረ ነው።
ከዚያም “አብ ካልፈቀደለት በቀር ወደ እኔ ሊመጣ የሚችል የለም ያልኳችሁ ለዚህ ነው” አላቸው።
ከዚህም የተነሳ ከደቀ መዛሙርቱ ብዙዎቹ ትተውት ወደነበረው ነገር ተመለሱ፤ ከዚያን ጊዜ ጀምሮም እሱን መከተላቸውን አቆሙ።
በዚህ ጊዜ ኢየሱስ አሥራ ሁለቱን “እናንተም መሄድ ትፈልጋላችሁ?” አላቸው።
ስምዖን ጴጥሮስም እንዲህ ሲል መለሰለት፦ “ጌታ ሆይ፣ ወደ ማን እንሄዳለን? አንተ የዘላለም ሕይወት ቃል አለህ።
አንተ የአምላክ ቅዱስ አገልጋይ እንደሆንክ አምነናል፤ ደግሞም አውቀናል።”
ኢየሱስም መልሶ “አሥራ ሁለታችሁንም የመረጥኳችሁ እኔ አይደለሁም? ይሁንና ከመካከላችሁ አንዱ ስም አጥፊ ነው” አላቸው።
ይህን ሲል የአስቆሮቱ ስምዖን ልጅ ስለሆነው ስለ ይሁዳ መናገሩ ነበር፤ ምክንያቱም ይሁዳ ከአሥራ ሁለቱ አንዱ ቢሆንም አሳልፎ የሚሰጠው እሱ ነበር።
12  ደግሞም ኢየሱስ ሰዎቹን እንዲህ አላቸው፦ “እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ። እኔን የሚከተል ሁሉ በምንም ዓይነት በጨለማ አይሄድም፤ ከዚህ ይልቅ የሕይወት ብርሃን ያገኛል።”
ፈሪሳውያንም “አንተ ስለ ራስህ ትመሠክራለህ፤ ምሥክርነትህም እውነት አይደለም” አሉት።
ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፦ “ስለ ራሴ ብመሠክር እንኳ ከየት እንደመጣሁና ወዴት እንደምሄድ ስለማውቅ ምሥክርነቴ እውነት ነው። እናንተ ግን ከየት እንደመጣሁና ወዴት እንደምሄድ አታውቁም።
እናንተ በሥጋዊ አስተሳሰብ ትፈርዳላችሁ፤ እኔ በማንም ላይ አልፈርድም።
እኔ ብፈርድ እንኳ ፍርዴ እውነተኛ ነው፤ ምክንያቱም የምፈርደው ብቻዬን አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ የላከኝ አብ ከእኔ ጋር ነው።
በሕጋችሁም ላይ ‘የሁለት ሰዎች ምሥክርነት እውነት ነው’ ተብሎ ተጽፏል።
ስለ ራሴ የምመሠክር አንዱ እኔ ነኝ፤ ደግሞም የላከኝ አብ ስለ እኔ ይመሠክራል።”
በዚህ ጊዜ “አባትህ የት ነው?” አሉት። ኢየሱስም “እናንተ እኔንም ሆነ አባቴን አታውቁም። እኔን ብታውቁኝ ኖሮ አባቴንም ባወቃችሁት ነበር” ሲል መለሰላቸው።
ኢየሱስ ይህን የተናገረው በቤተ መቅደስ፣ ግምጃ ቤቱ አካባቢ ሆኖ ሲያስተምር ነበር። ሆኖም ሰዓቱ ገና ስላልደረሰ ማንም አልያዘውም።
ኢየሱስም እንደገና “እኔ እሄዳለሁ፤ እናንተም ትፈልጉኛላችሁ፤ ይሁንና ኃጢአተኛ እንደሆናችሁ ትሞታላችሁ። እኔ ወደምሄድበት ልትመጡ አትችሉም” አላቸው።
አይሁዳውያኑም “‘እኔ ወደምሄድበት ልትመጡ አትችሉም’ የሚለው ራሱን ሊገድል አስቦ ይሆን እንዴ?” አሉ።
እሱም እንዲህ አላቸው፦ “እናንተ ከምድር ናችሁ፤ እኔ ከላይ ነኝ። እናንተ ከዚህ ዓለም ናችሁ፤ እኔ ከዚህ ዓለም አይደለሁም።
በኃጢአታችሁ ትሞታላችሁ ያልኳችሁ ለዚህ ነው። እኔ እሱ እንደሆንኩ ካላመናችሁ በኃጢአታችሁ ትሞታላችሁ።”
እነሱም “ለመሆኑ አንተ ማን ነህ?” አሉት። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “ድሮውንም እኔ ከእናንተ ጋር የምነጋገረው እንዲያው በከንቱ ነው።
ስለ እናንተ ብዙ የምናገረው ነገር አለኝ፤ ፍርድ የምሰጥበትም ብዙ ነገር አለኝ። በመሠረቱ የላከኝ እውነተኛ ነው፤ እኔም ከእሱ የሰማሁትን ያንኑ ነገር ለዓለም እየተናገርኩ ነው።”
እነሱ ግን ስለ አብ እየነገራቸው እንደሆነ አልተረዱም ነበር።
ከዚያም ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “የሰውን ልጅ ከሰቀላችሁት በኋላ እኔ እሱ እንደሆንኩና በራሴ ተነሳስቼ አንዳች ነገር እንደማላደርግ ከዚህ ይልቅ እነዚህን ነገሮች የምናገረው ልክ አብ እንዳስተማረኝ መሆኑን ታውቃላችሁ።
እኔን የላከኝ ከእኔ ጋር ነው፤ ሁልጊዜ እሱን ደስ የሚያሰኘውን ስለማደርግ ብቻዬን አልተወኝም።”
ይህን በተናገረ ጊዜ ብዙዎች በእሱ አመኑ።
ከዚያም ኢየሱስ በእሱ ላመኑት አይሁዳውያን እንዲህ አለ፦ “ቃሌን ጠብቃችሁ ብትኖሩ በእርግጥ ደቀ መዛሙርቴ ናችሁ፤
እውነትንም ታውቃላችሁ፤ እውነትም ነፃ ያወጣችኋል።”
እነሱም መልሰው “እኛ የአብርሃም ዘር ነን፤ ለማንም ባሪያዎች ሆነን አናውቅም። ታዲያ አንተ ‘ነፃ ትወጣላችሁ’ እንዴት ትለናለህ?” አሉት።
ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “እውነት እውነት እላችኋለሁ፣ ኃጢአት የሚያደርግ ሁሉ የኃጢአት ባሪያ ነው።
ደግሞም ባሪያ በጌታው ቤት ለዘለቄታው አይኖርም፤ ልጅ ከሆነ ግን ሁልጊዜ ይኖራል።
ስለዚህ ወልድ ነፃ ካወጣችሁ፣ በእርግጥ ነፃ ትሆናላችሁ።
የአብርሃም ዘር እንደሆናችሁ አውቃለሁ። ሆኖም ቃሌ በእናንተ ውስጥ ሥር ስለማይሰድ ልትገድሉኝ ትፈልጋላችሁ።
እኔ ከአባቴ ጋር ሳለሁ ያየሁትን ነገር እናገራለሁ፤ እናንተ ግን ከአባታችሁ የሰማችሁትን ነገር ታደርጋላችሁ።”
እነሱም መልሰው “አባታችን አብርሃም ነው” አሉት። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ “የአብርሃም ልጆች ብትሆኑ ኖሮ አብርሃም የሠራውን ትሠሩ ነበር።
እናንተ ግን ከአምላክ የሰማሁትን እውነት የነገርኳችሁን እኔን ልትገድሉኝ ትፈልጋላችሁ። አብርሃም እንዲህ አላደረገም።
እናንተ እየሠራችሁ ያላችሁት የአባታችሁን ሥራ ነው።” እነሱም “እኛስ በዝሙት የተወለድን አይደለንም፤ እኛ አንድ አባት አለን፤ እሱም አምላክ ነው” አሉት።
ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፦ “አምላክ አባታችሁ ቢሆን ኖሮ እኔ ወደዚህ የመጣሁት ከእሱ ዘንድ ስለሆነ በወደዳችሁኝ ነበር። እሱ ላከኝ እንጂ እኔ በራሴ ተነሳስቼ አልመጣሁም።
እየተናገርኩት ያለው ነገር የማይገባችሁ ለምንድን ነው? ቃሌን መስማት ስለማትችሉ ነው።
እናንተ ከአባታችሁ ከዲያብሎስ ናችሁ፤ የአባታችሁንም ፍላጎት መፈጸም ትሻላችሁ። እሱ በራሱ መንገድ መሄድ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ነፍሰ ገዳይ ነበር፤ በእሱ ዘንድ እውነት ስለሌለ በእውነት ውስጥ ጸንቶ አልቆመም። ውሸታምና የውሸት አባት ስለሆነ ውሸት ሲናገር ከራሱ አመንጭቶ ይናገራል።
በሌላ በኩል ግን እኔ እውነትን ስለምናገር አታምኑኝም።
ከመካከላችሁ እኔን ኃጢአት ሠርተሃል ብሎ በማስረጃ ሊወነጅለኝ የሚችል ማን ነው? የምናገረው እውነት ከሆነ ደግሞ የማታምኑኝ ለምንድን ነው?
ከአምላክ የሆነ የአምላክን ቃል ይሰማል። እናንተ ግን ከአምላክ ስላልሆናችሁ አትሰሙም።”
አይሁዳውያኑም መልሰው “‘አንተ ሳምራዊ ነህ፤ ደግሞም ጋኔን አድሮብሃል’ ማለታችን ትክክል አይደለም?” አሉት።
ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰ፦ “እኔ አባቴን አከብራለሁ እንጂ ጋኔን የለብኝም፤ እናንተ ግን ታቃልሉኛላችሁ።
እኔ ለራሴ ክብር እየፈለግኩ አይደለም፤ ይሁንና ይህን የሚፈልግና የሚፈርድ አለ።
እውነት እውነት እላችኋለሁ፣ ማንም ሰው ቃሌን የሚጠብቅ ከሆነ ፈጽሞ ሞትን አያይም።”
አይሁዳውያኑም እንዲህ አሉት፦ “አሁን በእርግጥ ጋኔን እንዳለብህ ተረዳን። አብርሃም ሞቷል፤ ነቢያትም ሞተዋል፤ አንተ ግን ‘ማንም ሰው ቃሌን የሚጠብቅ ከሆነ ፈጽሞ ሞትን አይቀምስም’ ትላለህ።
አንተ ከሞተው ከአባታችን ከአብርሃም ትበልጣለህ እንዴ? ነቢያትም ሞተዋል። ለመሆኑ አንተ ማን ነኝ ልትል ነው?”
ኢየሱስ እንዲህ ሲል መለሰ፦ “እኔ ራሴን የማከብር ከሆነ ክብሬ ከንቱ ነው። እኔን የሚያከብረኝ እናንተ አምላካችን ነው የምትሉት አባቴ ነው።
ሆኖም እናንተ አላወቃችሁትም፤ እኔ ግን አውቀዋለሁ። አላውቀውም ብል እንደ እናንተ ውሸታም መሆኔ ነው። ይሁንና እኔ አውቀዋለሁ፤ ቃሉንም እጠብቃለሁ።
አባታችሁ አብርሃም ቀኔን እንደሚያይ ተስፋ በማድረግ እጅግ ተደሰተ፤ አይቶትም ደስ ተሰኘ።”
አይሁዳውያኑም “አንተ ገና 50 ዓመት እንኳ ያልሞላህ፣ አብርሃምን አይቼዋለሁ ትላለህ?” አሉት።
ኢየሱስም “እውነት እውነት እላችኋለሁ፣ አብርሃም ከመወለዱ በፊት እኔ ነበርኩ” አላቸው።
በዚህ ጊዜ ሊወግሩት ድንጋይ አነሱ፤ ኢየሱስ ግን ተሰወረና ከቤተ መቅደሱ ወጥቶ ሄደ።
ከዚያም በአምፊጶሊስና በአጶሎንያ በኩል ተጉዘው የአይሁዳውያን ምኩራብ ወዳለበት ወደ ተሰሎንቄ መጡ።
ጳውሎስም እንደ ልማዱ ወደ ምኩራብ ገባ፤ ለሦስት ሰንበትም ከቅዱሳን መጻሕፍት እየጠቀሰ ከእነሱ ጋር ተወያየ፤
ክርስቶስ መከራ መቀበሉና ከሞት መነሳቱ አስፈላጊ እንደነበር ማስረጃ እየጠቀሰ በማብራራትና በማስረዳት “ይህ እኔ የማውጅላችሁ ኢየሱስ እሱ ክርስቶስ ነው” አላቸው።
ከዚህም የተነሳ ከእነሱ መካከል አንዳንዶቹ አማኞች በመሆን ከጳውሎስና ከሲላስ ጋር ተባበሩ፤ ከግሪካውያንም መካከል አምላክን የሚያመልኩ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች እንዲሁም ቁጥራቸው ጥቂት የማይባል የታወቁ ሴቶች እንዲሁ አደረጉ።
ሆኖም አይሁዳውያን ቅናት ስላደረባቸው በገበያ ስፍራ የሚያውደለድሉ አንዳንድ ክፉ ሰዎችን አሰባስበው አሳደሙ፤ ከተማዋንም በሁከት አመሷት። ጳውሎስንና ሲላስንም አምጥተው ለረብሻ የተሰበሰበው ሕዝብ ፊት ለማቅረብ የያሶንን ቤት ሰብረው ገቡ።
ባጧቸው ጊዜም ያሶንንና አንዳንድ ወንድሞችን እየጎተቱ ወስደው የከተማዋ ገዢዎች ፊት በማቅረብ እንዲህ እያሉ ጮኹ፦ “ዓለምን ሁሉ ያናወጡት እነዚያ ሰዎች እዚህም መጥተዋል፤
ያሶንም በእንግድነት ተቀብሏቸዋል። እነዚህ ሁሉ ሰዎች ኢየሱስ የሚባል ሌላ ንጉሥ አለ እያሉ የቄሳርን ሕግ የሚቃረን ነገር ያደርጋሉ።”
ሕዝቡና የከተማዋ ገዢዎች ይህን ሲሰሙ ተሸበሩ፤
ያሶንን እና ሌሎቹን የዋስትና ገንዘብ እንዲያስይዙ ካደረጓቸው በኋላ ለቀቋቸው።
ወንድሞችም እንደመሸ ጳውሎስንና ሲላስን ወደ ቤርያ ላኳቸው። እነሱም እዚያ እንደደረሱ ወደ አይሁዳውያን ምኩራብ ገቡ።
በቤርያ የነበሩት አይሁዳውያን በተሰሎንቄ ከነበሩት ይልቅ ቀና አስተሳሰብ ስለነበራቸው የሰሙት ነገር ትክክል መሆኑን ለማረጋገጥ በየዕለቱ ቅዱሳን መጻሕፍትን በሚገባ በመመርመር ቃሉን በታላቅ ጉጉት ተቀበሉ።
ስለዚህ ከእነሱ መካከል ብዙዎቹ እንዲሁም ቁጥራቸው ጥቂት የማይባል የተከበሩ ግሪካውያን ሴቶችና የተወሰኑ ወንዶች አማኞች ሆኑ።
ሆኖም በተሰሎንቄ ያሉት አይሁዳውያን ጳውሎስ የአምላክን ቃል በቤርያም እንዳወጀ ባወቁ ጊዜ ሕዝቡን ለማነሳሳትና ለማወክ ወደዚያ መጡ።
በዚህ ጊዜ ወንድሞች ወዲያውኑ ጳውሎስን ወደ ባሕሩ ዳርቻ ላኩት፤ ሲላስና ጢሞቴዎስ ግን እዚያው ቀሩ።
ጳውሎስን የሸኙት ሰዎችም እስከ አቴንስ አደረሱት፤ ከዚያም ጳውሎስ ‘ሲላስና ጢሞቴዎስ በተቻለ ፍጥነት ወደ እኔ እንዲመጡ ንገሯቸው’ የሚል መመሪያ ሰጣቸው፤ ሰዎቹም ተመልሰው ሄዱ።
ጳውሎስ በአቴንስ እየጠበቃቸው ሳለ ከተማዋ በጣዖት የተሞላች መሆኗን አይቶ መንፈሱ ተረበሸ።
ስለዚህ በምኩራብ ከአይሁዳውያንና አምላክን ከሚያመልኩ ሌሎች ሰዎች ጋር እንዲሁም በየዕለቱ በገበያ ስፍራ ከሚያገኛቸው ሰዎች ጋር ይወያይ ጀመር።
ሆኖም ከኤፊቆሮስና ከኢስጦይክ ፈላስፎች መካከል አንዳንዶቹ ይከራከሩት ጀመር፤ ሌሎቹ ደግሞ “ይህ ለፍላፊ ምን ሊያወራ ፈልጎ ነው?” ይሉ ነበር። “ስለ ባዕዳን አማልክት የሚያውጅ ይመስላል” የሚሉም ነበሩ። ይህን ያሉት ስለ ኢየሱስና ስለ ትንሣኤ የሚገልጸውን ምሥራች ያውጅ ስለነበር ነው።
ስለዚህ ይዘው ወደ አርዮስፋጎስ ከወሰዱት በኋላ እንዲህ አሉት፦ “ይህ የምትናገረው አዲስ ትምህርት ምን እንደሆነ ልታስረዳን ትችላለህ?
ምክንያቱም ለጆሯችን እንግዳ የሆነ ነገር እያሰማኸን ነው፤ ይህ ነገር ምን ማለት እንደሆነ ማወቅ እንፈልጋለን።”
የአቴንስ ሰዎችና በዚያ የሚገኙ የባዕድ አገር ሰዎች ትርፍ ጊዜያቸውን የሚያሳልፉት ስለ አዳዲስ ነገሮች በማውራትና በመስማት ብቻ ነበር።
በዚህ ጊዜ ጳውሎስ በአርዮስፋጎስ መካከል ቆሞ እንዲህ አለ፦ “የአቴንስ ሰዎች ሆይ፣ በሁሉም ነገር ከሌሎች ሰዎች ይበልጥ እናንተ አማልክትን እንደምትፈሩ ማየት ችያለሁ።
ለአብነት ያህል፣ እየተዘዋወርኩ ሳለሁ የምታመልኳቸውን ነገሮች በትኩረት ስመለከት ‘ለማይታወቅ አምላክ’ የሚል ጽሑፍ የተቀረጸበት አንድ መሠዊያ አይቻለሁ። ስለዚህ ይህን ሳታውቁ የምታመልኩትን እኔ አሳውቃችኋለሁ።
ዓለምንና በውስጡ ያለውን ነገር ሁሉ የፈጠረው አምላክ፣ እሱ የሰማይና የምድር ጌታ ስለሆነ በእጅ በተሠሩ ቤተ መቅደሶች ውስጥ አይኖርም፤