text
stringlengths
4
267
በተጨማሪም ሕይወትንና እስትንፋስንም ሆነ ማንኛውንም ነገር ለሰው ሁሉ የሚሰጠው እሱ ስለሆነ የሚጎድለው ነገር ያለ ይመስል በሰው እጅ አይገለገልም።
በምድር ሁሉ ላይ እንዲኖሩም የሰውን ወገኖች በሙሉ ከአንድ ሰው ፈጠረ፤ የተወሰኑትን ዘመናትና የሰው ልጆች የሚኖሩበትንም ድንበር ደነገገ፤
ይህን ያደረገው ሰዎች አምላክን እንዲፈልጉትና አጥብቀው በመሻት እንዲያገኙት ብሎ ነው፤ እንዲህ ሲባል ግን እሱ ከእያንዳንዳችን የራቀ ነው ማለት አይደለም።
ምክንያቱም ከእናንተ ባለቅኔዎች አንዳንዶቹ ‘እኛም የእሱ ልጆች ነንና’ ብለው እንደተናገሩት ሁሉ ሕይወት ያገኘነው፣ የምንንቀሳቀሰውና የምንኖረው በእሱ ነው።
“እንግዲህ እኛ የአምላክ ልጆች ከሆንን አምላክ በሰው ጥበብና ንድፍ ከወርቅ፣ ከብር ወይም ከድንጋይ የተቀረጸን ነገር ይመስላል ብለን ልናስብ አይገባም።
እርግጥ አምላክ ሰዎች ባለማወቅ የኖሩበትን ጊዜ ችላ ብሎ አልፎታል፤ አሁን ግን በየቦታው ያሉ ሰዎች ሁሉ ንስሐ እንዲገቡ እያሳሰበ ነው።
ምክንያቱም በሾመው ሰው አማካኝነት በዓለም ሁሉ ላይ በጽድቅ ለመፍረድ ዓላማ ያለው ሲሆን ይህን ለማድረግም ቀን ወስኗል፤ እሱንም ከሞት በማስነሳት ለሰዎች ሁሉ ዋስትና ሰጥቷል።”
እነሱም ስለ ሙታን ትንሣኤ በሰሙ ጊዜ አንዳንዶቹ ያሾፉበት ጀመር፤ ሌሎቹ ግን “ስለዚሁ ጉዳይ በድጋሚ መስማት እንፈልጋለን” አሉት።
በዚህ ጊዜ ጳውሎስ ትቷቸው ሄደ፤
አንዳንድ ሰዎች ግን ከእሱ ጋር በመተባበር አማኞች ሆኑ። ከእነሱም መካከል የአርዮስፋጎስ ፍርድ ቤት ዳኛ የሆነው ዲዮናስዮስና ደማሪስ የተባለች ሴት እንዲሁም ሌሎች ሰዎች ይገኙበታል።
ከጊዜ በኋላ፣ አጵሎስ በቆሮንቶስ በነበረበት ጊዜ ጳውሎስ በመሃል አገር አቋርጦ ወደ ኤፌሶን ወረደ። በዚያም አንዳንድ ደቀ መዛሙርትን አገኘ፤
እነሱንም “አማኞች በሆናችሁ ጊዜ መንፈስ ቅዱስ ተቀብላችሁ ነበር?” አላቸው። እነሱም “ኧረ እኛ ስለ መንፈስ ቅዱስ የሰማነው ነገር የለም” ሲሉ መለሱለት።
እሱም “ታዲያ ምን ዓይነት ጥምቀት ነው የተጠመቃችሁት?” አላቸው። እነሱም “የዮሐንስን ጥምቀት” አሉት።
ጳውሎስም እንዲህ አላቸው፦ “ዮሐንስ ያጠምቅ የነበረው የንስሐ ምልክት የሆነውን ጥምቀት ነበር፤ ሰዎች ከእሱ በኋላ በሚመጣው ይኸውም በኢየሱስ እንዲያምኑ ይነግራቸው ነበር።”
እነሱም ይህን ሲሰሙ በጌታ ኢየሱስ ስም ተጠመቁ።
ጳውሎስም እጁን በላያቸው በጫነ ጊዜ መንፈስ ቅዱስ ወረደባቸው፤ እነሱም በባዕድ ቋንቋዎች መናገርና መተንበይ ጀመሩ።
ሰዎቹም በአጠቃላይ 12 ገደማ ነበሩ።
ጳውሎስም ወደ ምኩራብ እየገባ ንግግር በመስጠትና ስለ አምላክ መንግሥት አሳማኝ በሆነ መንገድ በማስረዳት ለሦስት ወራት ያህል በድፍረት ሲናገር ቆየ።
ሆኖም አንዳንዶቹ ግትሮች ስለነበሩ ለማመን ፈቃደኞች አልሆኑም፤ የጌታን መንገድ በሕዝቡ ፊት ባጥላሉ ጊዜ ከእነሱ በመራቅ ደቀ መዛሙርቱን ለይቶ ወሰዳቸው፤ በጢራኖስ የትምህርት ቤት አዳራሽም በየዕለቱ ንግግር ይሰጥ ነበር።
ይህም ለሁለት ዓመት ያህል ቀጠለ፤ ከዚህም የተነሳ በእስያ አውራጃ የሚኖሩ አይሁዳውያንና ግሪካውያን ሁሉ የጌታን ቃል ሰሙ።
አምላክም በጳውሎስ እጅ በጣም አስደናቂ የሆኑ ነገሮችን መፈጸሙን ቀጠለ፤
ሰዎችም የጳውሎስን ሰውነት የነኩ ጨርቆችንና ሽርጦችን ወደታመሙት ሰዎች ሲወስዱ ሰዎቹ በሽታቸው ይለቃቸው ነበር፤ ርኩሳን መናፍስትም ይወጡ ነበር።
ይሁንና እየዞሩ አጋንንትን ያስወጡ ከነበሩት አይሁዳውያን አንዳንዶቹም “ጳውሎስ በሚሰብከው በኢየሱስ ስም እንድትወጣ አጥብቄ አዝሃለሁ” እያሉ ክፉ መናፍስት በያዟቸው ሰዎች ላይ የጌታ ኢየሱስን ስም ለመጥራት ሞከሩ።
አስቄዋ የተባለ የአንድ አይሁዳዊ የካህናት አለቃ ሰባት ወንዶች ልጆችም ይህን ያደርጉ ነበር።
ክፉው መንፈስ ግን መልሶ “ኢየሱስን አውቀዋለሁ፤ ጳውሎስንም አውቀዋለሁ፤ እናንተ ደግሞ ማን ናችሁ?” አላቸው።
ከዚያም ክፉው መንፈስ ያደረበት ሰው ዘሎ ጉብ አለባቸው፤ አሸነፋቸውም፤ ስለዚህ ራቁታቸውን ሆነውና ቆስለው ከዚያ ቤት ሸሹ።
በኤፌሶን የሚኖሩት አይሁዳውያንና ግሪካውያን ሁሉ ይህን ሰሙ፤ በመሆኑም ሁሉም ፍርሃት አደረባቸው፤ የጌታ ኢየሱስ ስምም ይበልጥ እየገነነ ሄደ።
አማኞች ከሆኑት መካከል ብዙዎቹም እየመጡ ያደረጉትን ይናዘዙና በግልጽ ይናገሩ ነበር።
ደግሞም አስማት ይሠሩ ከነበሩት መካከል ብዙዎች መጽሐፎቻቸውን አንድ ላይ ሰብስበው በማምጣት በሰው ሁሉ ፊት አቃጠሉ። የመጽሐፎቹንም ዋጋ ሲያሰሉ 50,000 የብር ሳንቲሞች ሆኖ አገኙት።
በዚህ መንገድ የይሖዋ ቃል በኃይል እየተስፋፋና እያሸነፈ ሄደ።
ይህ ሁሉ ከሆነ በኋላ ጳውሎስ በመቄዶንያና በአካይያ በኩል አልፎ ወደ ኢየሩሳሌም ለመሄድ ወሰነ። “እዚያ ከሄድኩ በኋላ ደግሞ ወደ ሮም ማቅናት አለብኝ” አለ።
ስለዚህ ከሚያገለግሉት መካከል ሁለቱን ማለትም ጢሞቴዎስንና ኤርስጦስን ወደ መቄዶንያ ላካቸው፤ እሱ ግን በእስያ አውራጃ ለተወሰነ ጊዜ ቆየ።
በዚህ ወቅት የጌታን መንገድ በተመለከተ ታላቅ ሁከት ተፈጠረ።
ምክንያቱም ድሜጥሮስ የተባለ አንድ የብር አንጥረኛ የአርጤምስን ቤተ መቅደስ የብር ምስሎች እየቀረጸ ለእጅ ጥበብ ባለሙያዎች ከፍተኛ ትርፍ ያስገኝ ነበር።
ድሜጥሮስ እነሱንና በተመሳሳይ ሙያ የተሰማሩ ሰዎችን ሰብስቦ እንዲህ አለ፦ “እናንተ ሰዎች፣ መቼም ብልጽግናችን የተመካው በዚህ ሥራ ላይ እንደሆነ ታውቃላችሁ።
አሁን ግን ይህ ጳውሎስ የተባለ ሰው በኤፌሶን ብቻ ሳይሆን በመላው የእስያ አውራጃ ማለት ይቻላል፣ በእጅ የተሠሩ አማልክት ሁሉ በፍጹም አማልክት አይደሉም እያለ ብዙ ሰዎችን አሳምኖ አመለካከታቸውን እንዳስለወጠ ያያችሁትና የሰማችሁት ጉዳይ ነው።
ከዚህም በላይ አሳሳቢ የሆነው ነገር የእኛ ሥራ መናቁ ብቻ ሳይሆን የታላቋ አምላክ የአርጤምስ ቤተ መቅደስ ዋጋ ቢስ ሆኖ ሊቀርና መላው የእስያ አውራጃም ሆነ ዓለም በሙሉ የሚያመልካት አርጤምስ ገናና ክብሯ ሊገፈፍ መሆኑ ጭምር ነው።”
ሰዎቹ ይህን ሲሰሙ በቁጣ ተሞልተው “የኤፌሶኗ አርጤምስ ታላቅ ናት!” እያሉ ይጮኹ ጀመር።
በመሆኑም ከተማዋ በረብሻ ታመሰች፤ ሕዝቡም የመቄዶንያ ሰዎች የሆኑትን የጳውሎስን የጉዞ ጓደኞች ይኸውም ጋይዮስንና አርስጥሮኮስን እየጎተቱ ግር ብለው ወደ ጨዋታ ማሳያው ስፍራ ገቡ።
ጳውሎስም ሕዝቡ ወዳለበት ሊገባ ፈልጎ ነበር፤ ደቀ መዛሙርቱ ግን ከለከሉት።
የጳውሎስ ወዳጆች የነበሩ አንዳንድ የበዓላትና የውድድር አዘጋጆች እንኳ ሳይቀሩ ወደ ጨዋታ ማሳያው ስፍራ በመግባት ራሱን ለአደጋ እንዳያጋልጥ መልእክት በመላክ ለመኑት።
በተሰበሰበው ሕዝብ መካከል ከፍተኛ ትርምስ ተፈጥሮ ስለነበር አንዳንዶቹ አንድ ነገር ሲናገሩ ሌሎቹ ደግሞ ሌላ ነገር እየተናገሩ ይጯጯኹ ነበር፤ አብዛኛው ሰው ለምን እዚያ እንደተገኘ እንኳ አያውቅም ነበር።
አንዳንዶች እስክንድርን ከሕዝቡ መካከል ባወጡት ጊዜ አይሁዳውያን ወደ ፊት ገፉት፤ እስክንድርም የመከላከያ ሐሳቡን ለሕዝቡ ሊያቀርብ ፈልጎ በእጁ ምልክት ሰጣቸው።
ሆኖም አይሁዳዊ መሆኑን ባወቁ ጊዜ ሁሉም በአንድ ድምፅ “የኤፌሶኗ አርጤምስ ታላቅ ናት!” እያሉ ለሁለት ሰዓት ያህል ጮኹ።
በመጨረሻ የከተማዋ ዋና ጸሐፊ ሕዝቡን ጸጥ አሰኝቶ እንዲህ አለ፦ “የኤፌሶን ሰዎች ሆይ፣ የታላቋ አርጤምስ ቤተ መቅደስና ከሰማይ የወረደው ምስሏ ጠባቂ የኤፌሶናውያን ከተማ እንደሆነች የማያውቅ ማን አለ?
ይህ ፈጽሞ የማይታበል ሐቅ ስለሆነ ልትረጋጉና የችኮላ እርምጃ ከመውሰድ ልትቆጠቡ ይገባል።
ምክንያቱም እነዚህ ያመጣችኋቸው ሰዎች ቤተ መቅደስ የዘረፉ ወይም የምናመልካትን አምላክ የሰደቡ አይደሉም።
ስለዚህ ድሜጥሮስና አብረውት ያሉት የእጅ ጥበብ ባለሙያዎች የሚከሱት ሰው ካለ ችሎት የሚሰየምባቸው ቀናት ያሉ ከመሆኑም ሌላ የሮም አገረ ገዢዎች አሉ፤ እዚያ መሟገት ይችላሉ።
ከዚህ ያለፈ ልታቀርቡት የምትፈልጉት ክስ ካለ ግን በመደበኛ ጉባኤ መዳኘት ይኖርበታል።
አለዚያ ዛሬ በተፈጸመው ነገር የተነሳ ሕዝብ አሳድማችኋል ተብለን እንዳንከሰስ ያሰጋል፤ ለዚህ ሁሉ ሁከት መንስኤው ምን እንደሆነ ብንጠየቅ የምንሰጠው አጥጋቢ መልስ የለም።”
ይህን ከተናገረ በኋላ የተሰበሰበው ሕዝብ እንዲበተን አደረገ።
በይሁዳ የነበሩት ሐዋርያትና ወንድሞች፣ አሕዛብም የአምላክን ቃል እንደተቀበሉ ሰሙ።
ስለዚህ ጴጥሮስ ወደ ኢየሩሳሌም በወጣ ጊዜ ግርዘትን የሚደግፉ ሰዎች ይተቹት ጀመር፤
“ወዳልተገረዙ ሰዎች ቤት ሄደህ ከእነሱ ጋር በልተሃል” አሉት።
በዚህ ጊዜ ጴጥሮስ እንዲህ ሲል ጉዳዩን በዝርዝር አብራራላቸው፦
“በኢዮጴ ከተማ እየጸለይኩ ሳለ ሰመመን ውስጥ ሆኜ ራእይ አየሁ፤ አንድ ትልቅ ጨርቅ የሚመስል ነገር በአራቱም ጫፍ ተይዞ ከሰማይ ወረደና ወደ እኔ መጣ።
ይህን ነገር ትኩር ብዬ ስመለከት አራት እግር ያላቸው የምድር እንስሳት፣ የዱር አራዊት፣ በምድር ላይ የሚሳቡ ፍጥረታትና የሰማይ ወፎች አየሁ።
በተጨማሪም አንድ ድምፅ ‘ጴጥሮስ፣ ተነሳና አርደህ ብላ!’ ሲለኝ ሰማሁ።
እኔ ግን ‘ጌታ ሆይ፣ በጭራሽ፤ ምክንያቱም ንጹሕ ያልሆነ ወይም የረከሰ ነገር ወደ አፌ ገብቶ አያውቅም’ አልኩ።
ለሁለተኛ ጊዜ ከሰማይ የመጣው ድምፅ ‘አምላክ ንጹሕ ያደረገውን ነገር ርኩስ ነው ማለትህን ተው’ ሲል መለሰልኝ።
ይህም ለሦስተኛ ጊዜ ተደገመ፤ ከዚያም ሁሉም ነገር እንደገና ወደ ሰማይ ተወሰደ።
ልክ በዚያው ሰዓት ደግሞ ከቂሳርያ ወደ እኔ የተላኩ ሦስት ሰዎች እኛ ወደነበርንበት ቤት ደረሱ።
በዚህ ጊዜ መንፈስ፣ ምንም ሳልጠራጠር አብሬያቸው እንድሄድ ነገረኝ። እነዚህ ስድስት ወንድሞችም አብረውኝ ሄዱ፤ ወደ ሰውየውም ቤት ገባን።
“እሱም በቤቱ ውስጥ መልአክ ቆሞ እንዳየና እንዲህ እንዳለው ነገረን፦ ‘ወደ ኢዮጴ ሰዎች ልከህ ጴጥሮስ ተብሎ የሚጠራውን ስምዖንን አስጠራ፤
እሱም አንተና መላው ቤተሰብህ መዳን ልታገኙ የምትችሉበትን ነገር ሁሉ ይነግርሃል።’
እኔም መናገር ስጀምር መንፈስ ቅዱስ በመጀመሪያ በእኛ ላይ እንደወረደው ሁሉ በእነሱም ላይ ወረደ።
በዚህ ጊዜ፣ ‘ዮሐንስ በውኃ አጠመቀ፤ እናንተ ግን በመንፈስ ቅዱስ ትጠመቃላችሁ’ እያለ ጌታ ይናገር የነበረውን ቃል አስታወስኩ።
እንግዲህ አምላክ በጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ላመንነው ለእኛ የሰጠውን ያንኑ ነፃ ስጦታ ለእነሱም ከሰጠ፣ ታዲያ አምላክን መከልከል የምችል እኔ ማን ነኝ?”
እነሱም ይህን በሰሙ ጊዜ መቃወማቸውን ተዉ፤ ደግሞም “እንዲህ ከሆነማ አምላክ አሕዛብም ሕይወት ማግኘት እንዲችሉ ንስሐ የሚገቡበት አጋጣሚ ሰጥቷቸዋል ማለት ነው” እያሉ አምላክን አከበሩ።
ከእስጢፋኖስ ሞት በኋላ በተቀሰቀሰው ስደት የተነሳ የተበተኑት ደቀ መዛሙርት እስከ ፊንቄ፣ ቆጵሮስና አንጾኪያ ድረስ ሄዱ፤ ቃሉን ይናገሩ የነበረው ግን ለአይሁዳውያን ብቻ ነበር።
ይሁን እንጂ ከእነሱ መካከል የቆጵሮስና የቀሬና ሰዎች የሆኑ አንዳንዶች ወደ አንጾኪያ መጥተው ግሪክኛ ተናጋሪ የሆኑ ሰዎችን በማነጋገር የጌታ ኢየሱስን ምሥራች ይሰብኩላቸው ጀመር።
የይሖዋም እጅ ከእነሱ ጋር ነበር፤ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎችም አማኝ በመሆን ጌታን መከተል ጀመሩ።
በኢየሩሳሌም የሚገኘው ጉባኤ ስለ እነሱ የሚገልጸው ወሬ ደረሰው፤ በዚህ ጊዜ በርናባስን ወደ አንጾኪያ ላኩት።
እሱም እዚያ ደርሶ አምላክ ለደቀ መዛሙርቱ ያሳየውን ጸጋ ባስተዋለ ጊዜ በጣም ተደሰተ፤ ሁሉም በጽኑ ልብ ለጌታ ታማኞች ሆነው እንዲቀጥሉም አበረታታቸው፤
በርናባስ መንፈስ ቅዱስ የሞላበትና ጠንካራ እምነት ያለው ጥሩ ሰው ነበር። ብዙ ቁጥር ያላቸው ሰዎችም በጌታ አመኑ።
በመሆኑም ሳኦልን ፈልጎ ለማግኘት ወደ ጠርሴስ ሄደ።
ካገኘውም በኋላ ወደ አንጾኪያ አመጣው። ከዚያም አንድ ዓመት ሙሉ ከእነሱ ጋር በጉባኤ አብረው እየተሰበሰቡ ብዙ ሕዝብ አስተማሩ፤ ደቀ መዛሙርቱም በመለኮታዊ አመራር ለመጀመሪያ ጊዜ ‘ክርስቲያኖች’ ተብለው የተጠሩት በአንጾኪያ ነበር።
በዚያን ጊዜ ነቢያት ከኢየሩሳሌም ወደ አንጾኪያ ወረዱ።
ከእነሱም መካከል አጋቦስ የተባለው ተነስቶ በምድሪቱ ሁሉ ታላቅ ረሃብ እንደሚከሰት መንፈስ አነሳስቶት ትንቢት ተናገረ፤ ይህም በቀላውዴዎስ ዘመን ተፈጸመ።
ስለዚህ ደቀ መዛሙርቱ እያንዳንዳቸው አቅማቸው በፈቀደ መጠን አዋጥተው በይሁዳ ለሚኖሩ ወንድሞች እርዳታ ለመላክ ወሰኑ፤
እርዳታውንም በበርናባስና በሳኦል እጅ ለሽማግሌዎቹ ላኩ።
አግሪጳ ጳውሎስን “ስለ ራስህ እንድትናገር ተፈቅዶልሃል” አለው። በዚህ ጊዜ ጳውሎስ እጁን ዘርግቶ እንዲህ ሲል የመከላከያ መልሱን ይሰጥ ጀመር፦
“ንጉሥ አግሪጳ ሆይ፣ አይሁዳውያን በእኔ ላይ ያቀረቡትን ክስ ሁሉ በተመለከተ ዛሬ በአንተ ፊት የመከላከያ መልስ መስጠት በመቻሌ እጅግ ደስተኛ ነኝ፤
በተለይ ደግሞ አንተ የአይሁዳውያንን ልማዶችና በመካከላቸው ያሉትን ክርክሮች ሁሉ ጠንቅቀህ ታውቃለህ። ስለዚህ በትዕግሥት እንድታዳምጠኝ እለምንሃለሁ።
“ገና ከልጅነቴ በሕዝቤ መካከልም ሆነ በኢየሩሳሌም እንዴት እንደኖርኩ አይሁዳውያን ሁሉ በሚገባ ያውቃሉ፤
ከድሮ ጀምሮ የሚያውቁኝ ሰዎች ሊመሠክሩ ፈቃደኞች ቢሆኑ ኖሮ በሃይማኖታችን ውስጥ ወግ አጥባቂ የሆነውን ቡድን በመከተል ፈሪሳዊ ሆኜ እንደኖርኩ ያውቃሉ።
አሁን ግን እዚህ ለፍርድ የቀረብኩት አምላክ ለአባቶቻችን የገባውን ቃል ተስፋ በማድረጌ ነው፤
ደግሞም 12ቱ ነገዶቻችን ለአምላክ ቀንና ሌሊት በትጋት ቅዱስ አገልግሎት በማቅረብ እየተጠባበቁ ያሉት የዚህኑ ተስፋ ፍጻሜ ነው። ንጉሥ ሆይ፣ አይሁዶች የከሰሱኝ በዚህ ተስፋ ምክንያት ነው።
“አምላክ ሙታንን የሚያስነሳ መሆኑ ሊታመን የማይችል ነገር እንደሆነ አድርጋችሁ የምታስቡት ለምንድን ነው?
እኔ ራሴ የናዝሬቱ ኢየሱስን ስም በተቻለኝ መጠን መቃወም እንዳለብኝ አምን ነበር።
ደግሞም በኢየሩሳሌም ያደረግኩት ይህንኑ ነው፤ ከካህናት አለቆችም ሥልጣን ተቀብዬ ብዙ ቅዱሳንን ወህኒ ቤት አስገብቻለሁ፤ እንዲገደሉም የድጋፍ ድምፅ ሰጥቻለሁ።
ብዙ ጊዜም በየምኩራቡ እነሱን እየቀጣሁ እምነታቸውን በይፋ እንዲክዱ ለማስገደድ ሞክሬአለሁ፤ በእነሱ ላይ እጅግ ተቆጥቼ በሌሎች ከተሞች ያሉትን እንኳ ሳይቀር እስከ ማሳደድ ደርሻለሁ።
“ይህን እያከናወንኩ በነበረበት ወቅት ከካህናት አለቆች ሥልጣንና ተልእኮ ተቀብዬ ወደ ደማስቆ እየተጓዝኩ ሳለ
ንጉሥ ሆይ፣ እኩለ ቀን ሲሆን በመንገድ ላይ ከፀሐይ ብርሃን የበለጠ ድምቀት ያለው ከሰማይ የመጣ ብርሃን በእኔና አብረውኝ በሚጓዙት ሰዎች ዙሪያ ሲያበራ አየሁ።
ሁላችንም መሬት ላይ በወደቅን ጊዜ አንድ ድምፅ በዕብራይስጥ ቋንቋ ‘ሳኦል፣ ሳኦል ለምን ታሳድደኛለህ? መውጊያውን መቃወምህን ከቀጠልክ ለአንተው የባሰ ይሆንብሃል’ ሲለኝ ሰማሁ።
እኔም ‘ጌታዬ፣ አንተ ማን ነህ?’ አልኩ። ጌታም እንዲህ አለኝ፦ ‘እኔ አንተ የምታሳድደኝ ኢየሱስ ነኝ።
ይሁንና አሁን ተነስተህ በእግርህ ቁም። የተገለጥኩልህ እኔን በተመለከተ ስላየኸው ነገርና ወደፊት ስለማሳይህ ነገር አገልጋይና ምሥክር እንድትሆን አንተን ለመምረጥ ነው።
ወደ እነሱ ከምልክህ ከዚህ ሕዝብና ከአሕዛብ እታደግሃለሁ፤
የምልክህም የኃጢአት ይቅርታ ያገኙና በእኔ ላይ ባላቸው እምነት አማካኝነት በተቀደሱት መካከል ርስት ይቀበሉ ዘንድ ዓይናቸውን እንድትገልጥ እንዲሁም ከጨለማ ወደ ብርሃን፣ ከሰይጣን ሥልጣንም ወደ አምላክ እንድትመልሳቸው ነው።’
“በመሆኑም ንጉሥ አግሪጳ ሆይ፣ ከሰማይ ለተገለጠልኝ ራእይ አልታዘዝም አላልኩም፤