text
stringlengths
4
267
ከዚህ ይልቅ በመጀመሪያ በደማስቆ ላሉ ቀጥሎም በኢየሩሳሌምና በመላው የይሁዳ አገር ሁሉ ለሚገኙ ከዚያም ለአሕዛብ ንስሐ እንዲገቡና ለንስሐ የሚገባ ሥራ በመሥራት ወደ አምላክ እንዲመለሱ የሚያሳስበውን መልእክት ማዳረሴን ቀጠልኩ።
አይሁዳውያኑ በቤተ መቅደሱ ውስጥ የያዙኝና ሊገድሉኝ የሞከሩት በዚህ የተነሳ ነው።
ይሁን እንጂ ከአምላክ እርዳታ በማግኘቴ እስከዚህ ቀን ድረስ ለትንሹም ሆነ ለትልቁ መመሥከሬን ቀጥያለሁ፤ ነቢያትና ሙሴ ይፈጸማል ብለው ከተናገሩት በስተቀር ምንም የተናገርኩት ነገር የለም፤
እነሱም የተናገሩት ክርስቶስ መከራ እንደሚቀበልና ከሙታን የመጀመሪያ ሆኖ በመነሳት ለዚህ ሕዝብም ሆነ ለአሕዛብ ስለ ብርሃን እንደሚያውጅ ነው።”
ጳውሎስ የመከላከያ መልሱን እየሰጠ ሳለ ፊስጦስ ጮክ ብሎ “ጳውሎስ አሁንስ አእምሮህን ልትስት ነው! ብዙ መማር አእምሮህን እያሳተህ ነው!” አለ።
ጳውሎስ ግን እንዲህ አለ፦ “ክቡር ፊስጦስ ሆይ፣ አእምሮዬን እየሳትኩ አይደለም፤ እኔ እየተናገርኩ ያለሁት እውነተኛ እንዲሁም ከጤናማ አእምሮ የሚመነጭ ቃል ነው።
እንደ እውነቱ ከሆነ በነፃነት እያናገርኩት ያለሁት ንጉሥ ስለ እነዚህ ነገሮች በሚገባ ያውቃል፤ እነዚህ ነገሮች በድብቅ የተፈጸሙ ባለመሆናቸው አንዳቸውም ቢሆኑ ከእሱ የተሰወሩ እንዳልሆኑ እርግጠኛ ነኝ።
ንጉሥ አግሪጳ ሆይ፣ በነቢያት ታምናለህ? እንደምታምን አውቃለሁ።”
አግሪጳም ጳውሎስን “በአጭር ጊዜ ውስጥ አሳምነህ ክርስቲያን ልታደርገኝ እኮ ምንም አልቀረህም” አለው።
በዚህ ጊዜ ጳውሎስ “በአጭርም ሆነ በረጅም ጊዜ አንተ ብቻ ሳትሆን ዛሬ እየሰሙኝ ያሉት ሁሉ ከእስራቴ በስተቀር እንደ እኔ እንዲሆኑ አምላክን እለምናለሁ” አለ።
ከዚያም ንጉሡ ተነሳ፤ አገረ ገዢው፣ በርኒቄና አብረዋቸው ተቀምጠው የነበሩት ሰዎችም ተነሱ።
እየወጡ ሳሉም እርስ በርሳቸው “ይህ ሰው ለሞት ወይም ለእስራት የሚያበቃ ምንም ነገር አላደረገም” ተባባሉ።
ከዚያም አግሪጳ ፊስጦስን “ይህ ሰው ወደ ቄሳር ይግባኝ ባይል ኖሮ ሊፈታ ይችል ነበር” አለው።
ቴዎፍሎስ ሆይ፣ ኢየሱስ ስላደረገውና ስላስተማረው ነገር ሁሉ በመጀመሪያው መጽሐፍ ላይ ጽፌልሃለሁ፤
ታሪኩም አምላክ እስከወሰደው ቀን ድረስ ያለውን ያካትታል። ለመረጣቸው ሐዋርያት በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት መመሪያዎች ከሰጣቸው በኋላ አረገ።
መከራ ከተቀበለ በኋላ ሕያው መሆኑን በብዙ አሳማኝ ማስረጃዎች አሳያቸው። እነሱም ለ40 ቀናት ያዩት ሲሆን እሱም ስለ አምላክ መንግሥት ይነግራቸው ነበር።
ከእነሱ ጋር ተሰብስቦ ሳለ እንዲህ ሲል አዘዛቸው፦ “ከኢየሩሳሌም አትውጡ፤ ከዚህ ይልቅ አብ ቃል የገባውንና እኔም ስለዚሁ ጉዳይ ስናገር የሰማችሁትን ቃል ፍጻሜ ተጠባበቁ፤
ዮሐንስ በውኃ አጥምቆ ነበርና፤ እናንተ ግን ከጥቂት ቀናት በኋላ በመንፈስ ቅዱስ ትጠመቃላችሁ።”
እንደገና ተሰብስበው ሳሉ “ጌታ ሆይ፣ ለእስራኤል መንግሥትን መልሰህ የምታቋቁመው በዚህ ጊዜ ነው?” ሲሉ ጠየቁት።
እሱም እንዲህ አላቸው፦ “ጊዜያትንና ወቅቶችን የመወሰን ሥልጣን ያለው አብ ብቻ ስለሆነ እናንተ ይህን ማወቅ አያስፈልጋችሁም።
ሆኖም መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በሚወርድበት ጊዜ ኃይል ትቀበላላችሁ፤ በኢየሩሳሌም፣ በመላው ይሁዳና በሰማርያ እንዲሁም እስከ ምድር ዳር ድረስ ምሥክሮቼ ትሆናላችሁ።”
ይህን ከተናገረ በኋላም እያዩት ወደ ላይ ወጣ፤ ደመናም ከዓይናቸው ሰወረው።
እሱ ወደ ላይ እየወጣ ሳለ ትኩር ብለው ወደ ሰማይ ሲመለከቱ ነጫጭ ልብስ የለበሱ ሁለት ሰዎች ድንገት አጠገባቸው ቆሙ፤
እንዲህም አሏቸው፦ “እናንተ የገሊላ ሰዎች፣ ወደ ሰማይ እየተመለከታችሁ የቆማችሁት ለምንድን ነው? ይህ ከእናንተ ወደ ሰማይ የተወሰደው ኢየሱስ ወደ ሰማይ ሲሄድ ባያችሁት በዚሁ ሁኔታ ይመጣል።”
ከዚያም ደብረ ዘይት ከተባለው ተራራ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ፤ ይህ ተራራ በኢየሩሳሌም አቅራቢያ የሚገኝ ሲሆን ርቀቱ የሰንበት መንገድ ያህል ብቻ ነበር።
እዚያ በደረሱ ጊዜ ያርፉበት ወደነበረው ደርብ ወጡ። እነሱም ጴጥሮስ፣ ዮሐንስ፣ ያዕቆብና እንድርያስ፣ ፊልጶስና ቶማስ፣ በርቶሎሜዎስና ማቴዎስ፣ የእልፍዮስ ልጅ ያዕቆብና ቀናተኛው ስምዖን እንዲሁም የያዕቆብ ልጅ ይሁዳ ነበሩ።
እነዚህ ሁሉ ከአንዳንድ ሴቶችና ከኢየሱስ እናት ከማርያም እንዲሁም ከወንድሞቹ ጋር በአንድ ልብ ተግተው ይጸልዩ ነበር።
በዚያው ሰሞን 120 የሚያህሉ ሰዎች አንድ ላይ ተሰብስበው ሳለ ጴጥሮስ በወንድሞች መካከል ቆሞ እንዲህ አለ፦
“ወንድሞች፣ ኢየሱስን የያዙትን ሰዎች እየመራ ስላመጣው ስለ ይሁዳ መንፈስ ቅዱስ በዳዊት በኩል በትንቢት የተናገረው የቅዱስ መጽሐፉ ቃል መፈጸሙ የግድ ነበር።
ምክንያቱም እሱ ከእኛ እንደ አንዱ ተቆጥሮ የነበረ ከመሆኑም በላይ በዚህ አገልግሎት የመካፈል አጋጣሚ አግኝቶ ነበር።
(ይኸው ሰው ለዓመፅ ሥራው በተከፈለው ደሞዝ መሬት ገዛ፤ በአናቱም ወድቆ ሰውነቱ ፈነዳ፤ ሆድ ዕቃውም ተዘረገፈ።
ይህም በኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ሁሉ ዘንድ ታወቀ፤ በመሆኑም መሬቱ በቋንቋቸው አኬልዳማ ተብሎ ተጠራ፤ ትርጉሙም “የደም መሬት” ማለት ነው።)
በመዝሙር መጽሐፍ ላይ ‘መኖሪያው ወና ይሁን፤ በውስጡም ማንም ሰው አይኑርበት’ እንዲሁም ‘የበላይ ተመልካችነት ሹመቱን ሌላ ሰው ይውሰደው’ ተብሎ ተጽፏልና።
ስለዚህ ጌታ ኢየሱስ በእኛ መካከል ሆኖ ሥራውን ያከናውን በነበረበት ጊዜ ሁሉ ከእኛ ጋር ከነበሩት ወንዶች መካከል በአንዱ እሱን መተካት ያስፈልጋል፤
የሚተካው ሰው ኢየሱስ በዮሐንስ ከተጠመቀበት ጊዜ አንስቶ ከእኛ እስከተወሰደበት ጊዜ ድረስ አብሮን የነበረ መሆን ይኖርበታል። በተጨማሪም ከእኛ ጋር የትንሣኤው ምሥክር መሆን ያስፈልገዋል።”
ስለዚህ ሁለት ሰዎችን ዕጩ አድርገው አቀረቡ፤ እነሱም በርስያን ተብሎ የሚጠራው ዮሴፍ (ኢዮስጦስ ተብሎም ይጠራል) እና ማትያስ ነበሩ።
ከዚያም እንዲህ ብለው ጸለዩ፦ “የሰውን ሁሉ ልብ የምታውቀው ይሖዋ ሆይ፣ ከእነዚህ ሁለት ሰዎች መካከል የመረጥከውን አመልክተን፤
ይሁዳ ወደ ገዛ ራሱ ስፍራ ለመሄድ ሲል የተወውን ይህን የአገልግሎትና የሐዋርያነት ቦታ የሚወስደውን ሰው ግለጥልን።”
ከዚያም በሁለቱ ሰዎች ላይ ዕጣ ጣሉ፤ ዕጣውም ለማትያስ ወጣና ከአሥራ አንዱ ሐዋርያት ጋር ተቆጠረ።
ሊቀ ካህናቱም “ይህ የተባለው ነገር ልክ ነው?” አለው።
እስጢፋኖስም እንዲህ ሲል መለሰ፦ “ወንድሞችና አባቶች ሆይ፣ ስሙ። አባታችን አብርሃም በካራን መኖር ከመጀመሩ በፊት በሜሶጶጣሚያ ሳለ የክብር አምላክ ተገለጠለት፤
እንዲህም አለው፦ ‘ከአገርህ ወጥተህ፣ ከዘመዶችህም ተለይተህ እኔ ወደማሳይህ ምድር ሂድ።’
እሱም ከከለዳውያን አገር ወጥቶ በካራን መኖር ጀመረ። አባቱ ከሞተ በኋላ ደግሞ አምላክ ከዚያ ተነስቶ አሁን እናንተ ወደምትኖሩበት ወደዚህ ምድር እንዲዛወር አደረገው።
ሆኖም በወቅቱ በዚህ ምድር ምንም ርስት፣ ሌላው ቀርቶ እግሩን ሊያሳርፍ የሚችልበት መሬት እንኳ አልሰጠውም፤ ይሁንና ገና ልጅ ሳይኖረው ለእሱም ሆነ ከእሱ በኋላ ለዘሮቹ ምድሪቱን ርስት አድርጎ እንደሚሰጣቸው ቃል ገባለት።
ከዚህም በላይ አምላክ፣ ዘሮቹ በሰው አገር ባዕዳን ሆነው እንደሚኖሩ እንዲሁም የአገሩ ሰዎች ለ400 ዓመት በባርነት እንደሚገዟቸውና እንደሚያጎሳቁሏቸው ነገረው።
ደግሞም አምላክ ‘በባርነት የሚገዛቸውን ብሔር እፈርድበታለሁ፤ ከዚያም በኋላ ከነበሩበት አገር ወጥተው በዚህ ስፍራ ቅዱስ አገልግሎት ያቀርቡልኛል’ ሲል ተናግሯል።
“በተጨማሪም አምላክ ከእሱ ጋር የግርዘት ቃል ኪዳን አደረገ፤ አብርሃምም ይስሐቅን ወለደ፤ በስምንተኛውም ቀን ገረዘው። ይስሐቅም ያዕቆብን ወለደ፤ ያዕቆብም 12ቱን የቤተሰብ ራሶች ወለደ።
የቤተሰብ ራሶቹም በዮሴፍ ቀንተው ወደ ግብፅ ሸጡት። ሆኖም አምላክ ከእሱ ጋር ነበር፤
ከመከራውም ሁሉ ታደገው፤ በግብፅ ንጉሥ በፈርዖንም ፊት ሞገስና ጥበብ አጎናጸፈው። ፈርዖንም በግብፅና በቤቱ ሁሉ ላይ ገዢ አድርጎ ሾመው።
ይሁንና በግብፅና በከነአን አገር ሁሉ ታላቅ መከራ ያስከተለ ረሃብ ተከሰተ፤ አባቶቻችንም የሚበሉት ነገር አጡ።
ሆኖም ያዕቆብ በግብፅ እህል መኖሩን ሲሰማ አባቶቻችንን ለመጀመሪያ ጊዜ ወደዚያ ላካቸው።
ለሁለተኛ ጊዜ ሲሄዱ ዮሴፍ ማንነቱን ለወንድሞቹ ነገራቸው፤ ፈርዖንም ስለ ዮሴፍ ቤተሰብ ሰማ።
ስለዚህ ዮሴፍ መልእክት ልኮ አባቱን ያዕቆብንና ዘመዶቹን ሁሉ ከዚያ አገር አስጠራ፤ እነሱም በአጠቃላይ 75 ሰዎች ነበሩ።
ያዕቆብም ወደ ግብፅ ወረደ፤ በዚያም ሞተ፤ አባቶቻችንም በዚያ ሞቱ።
አፅማቸውም ወደ ሴኬም ተወስዶ አብርሃም በሴኬም ከኤሞር ልጆች በብር ገንዘብ በገዛው መቃብር ውስጥ ተቀበረ።
“አምላክ ለአብርሃም የተናገረው የተስፋ ቃል የሚፈጸምበት ጊዜ ሲቃረብ ሕዝባችን በግብፅ እየበዛና እየተበራከተ ሄደ፤
ይህም የሆነው ዮሴፍን የማያውቅ ሌላ ንጉሥ በግብፅ እስከተነሳበት ጊዜ ድረስ ነው።
ይህ ንጉሥ በወገኖቻችን ላይ ተንኮል በመሸረብ ሕፃናት ልጆቻቸውን ለሞት አሳልፈው እንዲሰጡ አባቶቻችንን አስገደዳቸው።
በዚህ ወቅት በአምላክ ፊት እንኳ ሳይቀር እጅግ ውብ የነበረው ሙሴ ተወለደ። በአባቱም ቤት ሦስት ወር በእንክብካቤ ኖረ።
በተጣለ ጊዜ ግን የፈርዖን ልጅ ወስዳ እንደ ራሷ ልጅ አድርጋ አሳደገችው።
ሙሴም የግብፃውያንን ጥበብ ሁሉ ተማረ። በንግግሩና በተግባሩም ብርቱ ሆነ።
“ሙሴ 40 ዓመት በሞላው ጊዜ ወንድሞቹ የሆኑት የእስራኤል ልጆች ያሉበትን ሁኔታ ለማየት በልቡ አሰበ።
እሱም አንድ ግብፃዊ በአንድ እስራኤላዊ ላይ በደል ሲፈጽም አየ፤ ለእስራኤላዊውም አግዞ ግብፃዊውን በመግደል ተበቀለለት።
ወንድሞቹ አምላክ በእሱ አማካኝነት እንደሚያድናቸው የሚያስተውሉ መስሎት ነበር፤ እነሱ ግን ይህን አላስተዋሉም።
በማግስቱም እርስ በርሳቸው ሲጣሉ አገኛቸው፤ እሱም ‘ሰዎች፣ እናንተ እኮ ወንድማማቾች ናችሁ። ለምን እርስ በርሳችሁ ትጣላላችሁ?’ በማለት ሊያስታርቃቸው ሞከረ።
ይሁንና በባልንጀራው ላይ ጥቃት እየፈጸመ የነበረው ሰው ገፈተረውና እንዲህ አለው፦ ‘አንተን በእኛ ላይ ማን ገዢና ፈራጅ አደረገህ?
ትናንት ግብፃዊውን እንደገደልከው እኔንም ልትገድለኝ ትፈልጋለህ እንዴ?’
ሙሴ ይህን ሲሰማ ሸሽቶ በምድያም አገር ባዕድ ሆኖ ኖረ፤ በዚያም ሁለት ወንዶች ልጆች ወለደ።
“ከ40 ዓመትም በኋላ በሲና ተራራ አቅራቢያ በሚገኝ ምድረ በዳ፣ በሚነድ ቁጥቋጦ ነበልባል ውስጥ አንድ መልአክ ተገለጠለት።
ሙሴም ባየው ነገር ተደነቀ። ሆኖም ሁኔታውን ለማጣራት ወደዚያ ሲቀርብ የይሖዋ ድምፅ እንዲህ ሲል ሰማ፦
‘እኔ የአባቶችህ አምላክ፣ የአብርሃም፣ የይስሐቅና የያዕቆብ አምላክ ነኝ።’ በዚህ ጊዜ ሙሴ ይንቀጠቀጥ ጀመር፤ ሁኔታውን ይበልጥ ለማጣራትም አልደፈረም።
ይሖዋም እንዲህ አለው፦ ‘የቆምክበት ስፍራ ቅዱስ መሬት ስለሆነ ጫማህን አውልቅ።
በግብፅ ባለው ሕዝቤ ላይ እየደረሰ ያለውን ጭቆና በእርግጥ አይቻለሁ፤ የጭንቅ ጩኸታቸውንም ሰምቻለሁ፤ ልታደጋቸውም ወርጃለሁ። አሁንም ና፣ ወደ ግብፅ እልክሃለሁ።’
‘አንተን ማን ገዢና ፈራጅ አደረገህ?’ ብለው የተቃወሙትን ይህንኑ ሙሴን አምላክ በቁጥቋጦው ውስጥ በተገለጠለት መልአክ አማካኝነት ገዢና ነፃ አውጪ አድርጎ ላከው።
ይህ ሰው በግብፅ፣ በቀይ ባሕርና በምድረ በዳ ለ40 ዓመት ድንቅ ነገሮችንና ተአምራዊ ምልክቶችን በመፈጸም ከግብፅ እየመራ አወጣቸው።
“‘አምላክ ከወንድሞቻችሁ መካከል እንደ እኔ ያለ ነቢይ ያስነሳላችኋል’ ብሎ ለእስራኤል ልጆች የተናገረው ይኸው ሙሴ ነው።
በሲና ተራራ ካነጋገረው መልአክና ከአባቶቻችን ጋር በምድረ በዳ በጉባኤው መካከል የነበረው እሱ ነው፤ ደግሞም ለእኛ ይሰጠን ዘንድ ሕያው የሆነውን ቅዱስ ቃል ተቀበለ።
አባቶቻችን ለእሱ ለመታዘዝ ፈቃደኞች አልሆኑም፤ ከዚህ ይልቅ እሱን በመቃወም በልባቸው ወደ ግብፅ ተመለሱ፤
አሮንንም ‘ፊት ፊታችን የሚሄዱ አማልክት ሥራልን። ከግብፅ ምድር መርቶ ያወጣን ያ ሙሴ ምን እንደደረሰበት አናውቅምና’ አሉት።
ስለሆነም በዚያን ጊዜ ጥጃ ሠርተው ለጣዖቱ መሥዋዕት አቀረቡ፤ በእጃቸውም ሥራ ይደሰቱ ጀመር።
በዚህ ጊዜ አምላክ ፊቱን ከእነሱ አዞረ፤ በነቢያትም መጻሕፍት እንዲህ ተብሎ በተጻፈው መሠረት የሰማይ ሠራዊትን እንዲያመልኩ ተዋቸው፦ ‘የእስራኤል ቤት ሆይ፣ ለ40 ዓመት በምድረ በዳ መባና መሥዋዕት ያቀረባችሁት ለእኔ ነበር?
ይልቁንም ልታመልኳቸው የሠራችኋቸውን ምስሎች ይኸውም የሞሎክን ድንኳንና ሮምፋ የሚባለውን አምላክ ኮከብ ተሸክማችሁ ተጓዛችሁ። ስለዚህ ከባቢሎን ወዲያ እንድትሰደዱ አደርጋችኋለሁ።’
“አባቶቻችን በምድረ በዳ የምሥክሩ ድንኳን ነበራቸው፤ ይህ ድንኳን የተሠራው አምላክ ሙሴን ባነጋገረው ወቅት በሰጠው ትእዛዝና ባሳየው ንድፍ መሠረት ነበር።
አባቶቻችንም ይህን ድንኳን በመረከብ ከኢያሱ ጋር ሆነው አምላክ ከአባቶቻችን ፊት ያባረራቸው ብሔራት ይኖሩበት ወደነበረው ምድር ይዘውት ገቡ። እስከ ዳዊት ዘመን ድረስም በዚህ ምድር ቆየ።
ዳዊትም በአምላክ ፊት ሞገስ አገኘ፤ ለያዕቆብ አምላክም መኖሪያ ስፍራ የማዘጋጀት መብት እንዲሰጠው ጠየቀ።
ይሁን እንጂ ቤት የሠራለት ሰለሞን ነበር።
ሆኖም ልዑሉ አምላክ የሰው እጅ በሠራው ቤት አይኖርም፤ ይህም ነቢዩ እንዲህ ሲል በተናገረው መሠረት ነው፦
‘ሰማይ ዙፋኔ ነው፤ ምድር ደግሞ የእግሬ ማሳረፊያ ናት። ለእኔ የምትሠሩልኝ ምን ዓይነት ቤት ነው? ይላል ይሖዋ። ወይስ የማርፍበት ቦታ የት ነው?
እነዚህን ነገሮች ሁሉ የሠራው እጄ አይደለም?’
“እናንተ ግትሮች፣ ልባችሁና ጆሯችሁ ያልተገረዘ፣ ሁልጊዜ መንፈስ ቅዱስን እንደተቃወማችሁ ነው፤ አባቶቻችሁ እንዳደረጉት እናንተም እንዲሁ ታደርጋላችሁ።
ከነቢያት መካከል አባቶቻችሁ ስደት ያላደረሱበት ማን አለ? አዎ፣ እነሱ የጻድቁን መምጣት አስቀድመው የተናገሩትን ገድለዋቸዋል፤ እናንተም አሁን ይህን ጻድቁን አሳልፋችሁ ሰጣችሁት፤ ደግሞም ገደላችሁት፤
በመላእክት አማካኝነት የተላለፈውን ሕግ ተቀበላችሁ፤ ነገር ግን አልጠበቃችሁትም።”
እነሱም ይህን ሲሰሙ ልባቸው በንዴት በገነ፤ ጥርሳቸውንም ያፋጩበት ጀመር።
እሱ ግን በመንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ ትኩር ብሎ ወደ ሰማይ ሲመለከት የአምላክን ክብር እንዲሁም ኢየሱስ በአምላክ ቀኝ ቆሞ አየ፤
ከዚያም “እነሆ፣ ሰማያት ተከፍተው የሰው ልጅም በአምላክ ቀኝ ቆሞ አያለሁ” አለ።
በዚህ ጊዜ በኃይል እየጮኹ ጆሯቸውን በእጃቸው ደፍነው በአንድነት ወደ እሱ ሮጡ።
ይዘውት ከከተማው ውጭ ካስወጡት በኋላ በድንጋይ ይወግሩት ጀመር። ምሥክሮቹም መደረቢያቸውን ሳኦል በተባለ ወጣት እግር አጠገብ አስቀመጡ።
እስጢፋኖስም እየወገሩት ሳለ “ጌታ ኢየሱስ ሆይ፣ መንፈሴን ተቀበል” ብሎ ተማጸነ።
ከዚያም ተንበርክኮ በታላቅ ድምፅ “ይሖዋ ሆይ፣ ይህን ኃጢአት አትቁጠርባቸው” ብሎ ጮኸ። ይህን ከተናገረም በኋላ በሞት አንቀላፋ።
ፊስጦስም ወደ አውራጃው ከመጣና ኃላፊነቱን ከተረከበ ከሦስት ቀን በኋላ ከቂሳርያ ወደ ኢየሩሳሌም ወጣ።